የበርሊን ማራቶን አሸናፊዎች ዘንድሮም ለድል ይጠበቃሉ

በማራቶን ውድድር በርካታ ታሪክ በማስመዝገብ በርሊንን የሚያክል የለም፡፡ በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ከተሰጣቸው ስድስት የማራቶን ውድድሮች አንዱ የሆነው የበርሊን ማራቶን፤ የዓለም ክብረወሰን በተደጋጋሚ የተሰበረበት ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ በስፖርቱ ድንቅ አቋም ላይ የሚገኙ አትሌቶች መዳረሻቸው አድርገው ይመርጡታል፡፡

ዘንድሮ ለ49ኛ ጊዜ በመጪው እሁድ ታላላቅ አትሌቶችን የሚያፋልመው የበርሊን ማራቶን 45ሺ ተሳታፊዎች ይደምቃል ተብሎ ይጠበቃል። በኢትዮጵያውያንና የኬንያ አትሌቶች የበላይነት በመጠናቀቅ ረጅም ዓመታትን ባስቆጠረው በዚህ ውድድር ዘንድሮም ከእነዚሁ ሃገራት አትሌቶች አሸናፊነት ይፈፀማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አምና በዚህ ውድድር በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ የነበሩት አትሌቶች ዘንድሮም ወደ ውድድሩ እንደሚመለሱ ማሳወቃቸው ደግሞ ቅድመ ግምቱን ‹‹ታሪክ ራሱን ይደግም ይሆን?›› በሚል ፉክክሩን አጓጊ አድርጎታል፡፡ አምና የርቀቱ የወንዶች የዓለም ክብረወሰን በኬንያዊው አትሌት ሲሰበር፤ በሴቶቹ ውድድር የውድድሩ ክብረወሰን በኢትዮጵያዊቷ አትሌት መሻሻሉ ይታወቃል፡፡ 2:15:37 የሆነ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ውድድሩን ያሸነፈችው አትሌት ትዕግስት አሰፋ ስትሆን፤ ዘንድሮም በርሊን ላይ ተመሳሳይ ታሪክ ለማስመዝገብ እንደምትሮጥ አረጋግጣለች፡፡ በ800 ሜትር የምትታወቀውና ሃገሯን እስከ 2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ ድረስ የወከለችው አትሌቷ ወደ ማራቶን ያደረገችው ሽግግር በአስደናቂ ብቃት የታጀበ ሊሆንላት ችሏል። በበርሊን ያስመዘገበችው ይህ ፈጣን ሰዓትም በድጋሚ የውድድሩ አሸናፊ ሊያደርጋት ይችላል በሚል እንድትጠበቅ አድርጓታል፡፡

በውድድሩ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚካፈሉ ቢሆንም፤ ከሌሎች አትሌቶች ለትዕግስት የተጠጋ ሰዓት ያላትና ብርቱ ተፎካካሪም ልትሆን ትችላለች በሚል የምትጠበቀው ኬንያዊቷ ሺላ ቼፕኪሩይ ናት፡፡ በቅርቡ ወደ ማራቶን የገባችው አትሌቷ አምና ቫሌንሺያ ማራቶን ላይ ያስመዘገበችው 2:17:29 የሆነ ፈጣን ሰዓት አላት፡፡ ይህም ለውድድሩ የአሸናፊነት ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል አንዷ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ይሁንና በርቀቱ የካበተ ልምድ ያላቸውና ለአሸናፊነትም ጠንካራ ፉክክር ለማድረግ የሚችሉ ብርቱ አትሌቶች አሉ፡፡ ትዕግስት አባያቸው፣ ወርቅነሽ ኢዴሳ፣ ዘይነባ ይመር፣ ድሬ ዲዳ፣ ሰንበሬ ተፈሪ፣… የመሳሰሉ አትሌቶችም ለአሸናፊነት የሚያደርጉት የእርስ በእርስ ፍጥጫ እጅግ ተጠባቂ ሆኗል፡፡ አትሌቶቹ የሚያስመዘግቡት ውጤት ለመጪው የፓሪስ ኦሊምፒክ ሃገራቸውን ለመወከል ከሚያስችላቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ እንደበርሊን ባሉት ስድስቱ ውድድሮች የተሻለ ሆኖ መገኘት በመሆኑ ትርጉሙ ከውድድርም በላይ ነው፡፡

በበርሊን ማራቶን የሴቶች ሩጫ የሁለት ጊዜ አሸናፊዋ ጌጤ ዋሚ፤ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ስትሆን እሷን ተከትለው በርካታ አትሌቶች የመድረኩን ክብር ሊቀዳጁ ችለዋል፡፡ እነዚህም አጸደ ሃብታሙ፣ አበሩ ከበደ፣ ትርፌ ጸጋዬ፣ አሸቴ በከሪ ናቸው፡፡ በአንጻሩ በወንዶች በኩል ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ እአአ ከ2006-2009 ባሉት አራት ዓመታት በተከታታይ አሸናፊ ሲሆን፤ በሁለቱ የዓለምን ክብረወሰን በመስበር ታሪካዊ አትሌት ነው፡፡ ቀነኒሳ በቀለ ለሁለት ጊዜ በመድረኩ ሲያሸንፍ፤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት ማግስት ጉዬ አዶላ የበርሊን ቻምፒዮን መሆን ችሏል። ከኢትዮጵያዊው አትሌት ባሻገር ለአራት ጊዜያት በበርሊን አሸናፊ በመሆን የታሪክ አካል የሆነው ደግሞ ኬንያዊው አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ ነው። ይህ አትሌት ለሁለት ጊዜ ክብረወሰንን በዚህ ውድድር ሲሰብር፤ አምና ያስመዘገበው 2:01:09 የሆነ ሰዓት የሰው ልጅ ማራቶንን ከ2ሰዓት በታች መሮጥ እንደሚችል ማሳያ ሊሆን ችሏል፡፡

ከቀናት በኋላ በድጋሚ በርሊን ላይ ለሚያደርገው ሩጫ የረጅም ጊዜ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየው አትሌቱ ምናልባትም ሌላኛውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ የርቀቱን ንግስና በድጋሚ ሊቆጣጠር ይችላል በሚልም ይጠበቃል። በወንዶቹ ምድብ በርካታ ኬንያውያን አትሌቶች በሩጫው የሚካፈሉ ሲሆን፤ ለዓለም ክብረወሰኑ የተቀራረበ ፈጣን ሰዓትም አላቸው። በአንጻሩ በኢትዮጵያ በኩል ታዱ አባቴ፣ አንዷለም ሽፈራው እና ሃፍቱ ተክሉ ተሳታፊነታቸው የተረጋገጠ አትሌቶች ሆነዋል። አትሌቶቹ 2ሰዓት ከ05 ደቂቃ የሆነ ሰዓት ያላቸው ሲሆኑ ከኬንያውያኑ ጋር ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉም ይጠበቃል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  መስከረም 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You