አንዳንድ ጠንካራ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ የጀመሩት ነገር አገራዊ ይሆናል፤ ከዚያም አልፎ ዓለም አቀፋዊ ይሆናል፡፡ በብዙ ነገሮች ውስጥ ‹‹የመጀመሪያው›› እያልን የምንገልጸው አስጀማሪዎችን ለማመስገንና ለማስታወስ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ‹‹የፊደል ገበታ አባት›› ተብለው ይጠራሉ፡፡ የፊደል አባት የተባሉበት ምክንያት ‹‹ሀ ሁ ይስፋፋ፣ ድንቁርና ይጥፋ›› የሚል መሪ ቃል ይዘው የአማርኛ ሆሄያትን በእግራቸው እየዞሩ ስላስተዋወቁ ነው፡፡ በብራና እና በወቅቱ በነበሩ ሌሎች ልማዳዊ ነገሮች ላይ እየጻፉ የአማርኛ ሆሄያትን ለገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል አስተዋውቀዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የአማርኛ ቋንቋ ባለውለታ ሆነዋል፡፡
በዛሬው ባለውለታዎቻችን ዓምድ አንድ የአፋርኛ ቋንቋ ባለውለታ እናስተዋውቃችኋለን፡፡ ለአፋርኛ ቋንቋ፣ ታሪክና ባህል በዋሉት ውለታ በቅርቡ በስማቸው የባህልና አገር በቀል ዕውቀቶች የምርምር ማዕከል ተሰይሟል፡፡ ለመሆኑ እኝህ የአፋር ባለውለታ ማን ናቸው?
ጀማል አብዱልቃድር መሀመድ ሬዶ ይባላሉ፡፡ የተወለዱት በኤርትራ ምድር በተባለች ከተማ ቀይ ባህር ዳርቻ አካባቢ ሲሆን ዘመኑም በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ህዳር 18 ቀን 1948 ነው።
ዕድሜያቸው 7 ዓመት እንደደረሰ ሃይማኖታዊ ትምህርት ለመማር ቁርዓን ቤት ገብተው በስምንት ወር ውስጥ ሙሉ ቁርዓንን አጠናቀቁ (አኸተሙ)። ብልህ እና የትምህርት አቀባበላቸው ፈጣን ከመሆናቸው የተነሳ የቁርዓን አስተማሪያቸው በአፋርኛ ‹‹አስር መዖ›› (የመልካም እድል ባለቤት ማለት ነው) የሚል ቅፅል ስም አውጥተውላቸው እንደነበር በሕይወት ታሪካቸው ሰነዶች ላይ ይገኛል።
ዕድሜያቸው 9 ዓመት እንደደረሰ ደግሞ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር 1958 የአረብኛ ትምህርት ቤት በመግባት አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ ከተማቸው ተማሩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ከ1965 እስከ 1968 (በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር) በወቅቱ ከፍተኛ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ይማሩበት በነበረው አዲስ አበባ በሚገኘው ጀኔራል ዊንጌት እና ዘነበ ወርቅ ትምህርት ቤቶች ገብተው አጠናቀዋል።
በመቀጠል በአውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1969 የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በአስመራ ከተማ በመከታተል፣ በ1971 በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላ ወላጅ አባታቸውን በሞት አጡ። ቤተሰብ የማስተዳደር ኃላፊነት በእሳቸው ላይ በመውደቁ የሚወዱትን ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ መጻሕፍትን በማንበብ ራስን የማብቃት ዘዴን በመከተል በእውቀታቸው ከዩኒቨርሲቲ ምሩቃን መብለጥ እንደጀመሩ ታሪካቸው ያሳያል።
የክብር ዶክተር ጀማል አብዱልቃድር ሬዶ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ወደ ፖለቲካው ዓለም ተቀላቀሉ። ፖለቲካውን ብቻ አይደለም የተቀላቀሉት፤ ሽምቅ ተዋጊዎችን በመቀላቀል ወደ በረሃ አመሩ። በግብፅ ካይሮ ከተማ አዲስ የተጠነሰሰውን የአፋር አንድነት ንቅናቄ (በአፋርኛ ምሕጻረ ቃሉ QKA) አባል ሆኑ። ቀጥሎም በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር 1974 በጀርመን በርሊን ከተማ የተመሰረተውን ብሔራዊ የነፃነት ንቅናቄ (በእንግሊዘኛ ምሕጻረ ቃል NLM) የተሰኘ የፖለቲካ ድርጅት ከመሰረቱ ሰዎች አንዱ ነበሩ።
በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1974 በሶማሊያ ሞቃዲሾ ከተማ ለወታደራዊ ስልጠና በተጓዙበት ወቅት ከሞቃዲሾ ከተማ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ባርዌን በምትባል ከተማ የአፋርኛ ቋንቋ ጥናት ተጠነሰሰ። ለመጀመሪያ ጊዜ የአፋርኛ ቋንቋን ከስነ ቃል ቋንቋ ወደ ስነ ጽሑፍ ቋንቋ ለመቀየር ፊደላትን በማዘጋጀት ለመጀመሪያ ጊዜ የአፋርኛ ቋንቋ ፈደላት የተወለዱት ‹‹ባርዌን›› በምትባለው ከተማ ነው። የአፋርኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ፊደላት የተጠነሰሱበትን አዲሱን መጽሃፍ ‹‹ዲምስ እና ሬዶ›› በማለት ሰየሙት። በአያታቸው ስም ሬዶ እና ከእሳቸው ጋር በአፋርኛ ቋንቋ ውልደት ጥረት ሲያደርጉ በነበሩት የጓደኛቸው አያት ስም ዲምስ እንዲሆን ተወሰነ። የዲምስ እና ሬዶ ስያሜ በመላው አፋር ማህበረሰብ (በኢትዮጵያ፣ በጂቡቲ እና ኤርትራ) አፋሮች ዘንድ በአጠቃላይ ከፍተኛ እውቅና እና ተቀባይነት አገኘ።
ጀማል አብዱልቃድር ሬዶ የብሄራዊ ነፃነት ንቅናቄ (NLM) የተሰኘው ፖለቲካዊ ድርጅት የወታደራዊ ክንፍ አዛዥ ነበሩ። በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1976 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት (Ethiopian national Democratic revolution/NDRP) የብሔር ብሔረሰቦች መብት እንዲከበር በመጠየቅ እና ጥያቄያቸው መልስ በማግኘቱ ሰላማዊ ትግልን በመቀላቀል የአውሳ አውራጃ አስተዳዳሪ በመሆንም አገልግለዋል።
በዘመኑ በነበረው አጠራር እና አወቃቀር በወሎ ክፍለ ሀገር በተለያዩ የአመራርነት ኃላፊነቶች አገልግለዋል። የደርግ መንግስት ከወደቀ በኋላ የደርግ መንግስት ባለስልጣናት ተነጋግረው ከሀገር ሲያመልጡ እኝህ የአፋርኛ ባለውለታ የክብር ዶክተር ጀማል አብዱልቃድር ግን በቢሯቸው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደቆዩ ሁነቱን ያስተዋሉ የሥራ ጓዶቻቸው እና አብሮ አደጎቻቸው ከትበዋል፡፡ በሥራ ላይ እያሉ በኢህአዴግ መንግስት ቁጥጥር ስር ውለው 1983 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ለ4 ወራት ያህል ከታሰሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ አበባ ተወስደው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለ12 ዓመታት ታስረዋል፤ በመጨረሻ በዋስ ተፈትተዋል። የኢህአዴግ መንግስት ጀማል አብዱልቃድርን ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ክልከላ ጥሎባቸውም ነበር።
የክብር ዶክተር ጀማል አብዱልቃድር ሬዶ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ነው እንግዲህ ሙሉ ጊዜያቸውን የአፋርኛ ቋንቋን ስነ ጽሁፍ ለማሳደግ ሌት ተቀን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ መሥራት የጀመሩት።
ጀማል አብዱልቃድር ሬዶ አፋርኛ ቋንቋን በማበልጸግ ሂደት ውስጥ ቋንቋውን በዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንዲመራመሩበት አድርጎታል፡፡ ምክንያቱም በርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ቋንቋዎች እውቀት ነበራቸው። ለምሳሌ ከውጭ፤ አረብኛ ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ እና ከአገር ውስጥ አማርኛ፣ ሶማሊኛ፣ ኦሮምኛ ፣ ትግርኛ እና የአፍ መፍቻቸው የሆነውን አፋርኛ ጨምሮ 9 ቋንቋዎችን አቀላጥፈው ይናገሩ ነበር። ይህም ለቋንቋ ምርምር እና የተለያዩ ሕዝቦችን የስነ ጽሁፍ ዘይቤ እንዲያውቁ አድርጓቸዋል፡፡
የቋንቋ ሊቁ ጀማል አብዱልቃድር ሬዶ በአፋርኛ ቋንቋ እና ስነ ጽሁፍ ምርምር በተጨማሪ በርካታ መጻሕፍትን ለህዝባቸው አበርክተዋል። ከእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
‹‹አፋርኛ ማስተማሪያ ዲምስ እና ሬዶ መፅሐፍ፣ ‹‹ያለ አስማሪ መመሪያ መፅሐፍ››፣ ‹‹የአፋርኛ መዝገበ ቃላት (Dictionary)››፣ ‹‹አፋርኛ ቋንቋ የተማሪዎችና የመምህራን መጻሕፍት ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ክፍል››፣ ‹‹አይ ሲ ቲ (ICT) በአፋርኛ››፣ ‹‹የአፋር ሕግ (customer law)››፣ የአፋርኛ ልቦለድ (Fiction) መፅሐፍ፣ የመማሪያ መጻሕፍት ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ከፍል፣ ‹‹ኢትዮጵያ ምን አይነት አስተዳደር ይበጃታል?›› መፅሐፍ፣ ‹‹የሃማዲ ያዮ ታሪክ መፅሐፍ››፣ ‹‹የያሲን መሀሞዳ ታሪክ መፅሐፍ››፣ ‹‹አል ማንሃል›› የተሰኘ የአፋር ህዝብ ታሪክ ከአረብኛ ወደ አማርኛ ተርጉመዋል። ሌሎች ከ9 የሚበልጡ መጻሕፍትን ደግሞ በእንግሊዝኛ አሳትመዋል።
የቋንቋና ስነ ጽሑፍ ሊቁ የክብር ዶክተር ጀማል አብዱልቃድር ከ2005 ዓ.ም እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የአፋርኛ ትምህርት ክፍል መምህር ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። የዕድሜ ባለፀጋ የነበሩት እኝህ የቋንቋ ሊቅ የጡረታ ጊዜዬ ነው ልቀመጥ አላሉም። ጋዋን ለብሰው ክፍል ውስጥ ቆመው ያስተምሩም ነበር። በእርሳቸው ጥረት ዛሬ የአፋርኛ ቋንቋ በሁለተኛ ዲግሪ ጭምር ይሰጣል፣ በቅርቡ ሶስተኛ ድግሪ ለመክፈት እየተሰራ መሆኑን የሠመራ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት መረጃ ያመለክታል፡፡
በተለያዩ የዓለም አገራት በመሄድ ዓለምአቀፋዊ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ኮንፈረንሶችን በዋናነት በማዘጋጀት፣ ስራዎቻቸውን በማቅረብ ሽልማት አግኝተዋል፡፡ በእነዚህ ሁሉ አጋጣሚዎች ለአፋርኛ ቋንቋ ምርምር የሚሆናቸውን ተሞክሮዎች ቀስመዋል፤ የቀሰሙትንም ዕውቀት በተግባር አውለዋል፡፡
ለዚህ ሁሉ አብርክቷቸው የሠመራ ዩኒቨርሲቲ በ2005 ዓ.ም የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል፡፡ እኝህ የአፋር ባለውለታ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ሥራዎቻቸው ግን ከመቃብር በላይ ሆነው ዝንተ ዓለም ሲዘከሩ ይኖራሉ፡፡
የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ለዚህ ሁሉ ውለታቸው የክብር ዶክትሬት መስጠት ብቻውን በቂ ነው ብሎ አላመነም። የአፋርን ጠቅላላ ምንነት የሚገልጽ የጥናትና ምርምር ተቋም በስማቸው ሰይሞ በቅርቡ አስመርቋል። የምርምር ማዕከሉ የአፋር ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ እና የቱሪዝም መስህቦች የሚጠኑበት ነው፡፡ ይህ ትልቅ ተቋም ስያሜውን በእኝህ የአፋር ባለውለታ በማድረግ ‹‹ሬዶ የባህልና አገር በቀል ዕውቀቶች ማዕከል›› ተብሏል።
አፋርኛ ቋንቋ በአፍሪካ ቀንድ ከሚነገሩ ቋንቋዎች አንዱ እና ቀዳሚ እንደነበር እና አሁንም እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በጎረቤት አገራት በጅቡቲ፣ በኤርትራ፣ በሶማሊያ፣ በኬንያ እንዲሁም በግብፅ እና በሌሎች የዓለም አገራትም ጭምር በርካታ ተናጋሪ አለው፡፡ የአፋርኛ ቋንቋ እነሆ ዛሬ ላይ ከክልል የሥራ ቋንቋነት አልፎ የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ ለመሆን በመንግሥት እየተሰራበት ነው፡፡ ለአፋርኛ ቋንቋ እዚህ መድረስ የክብር ዶክተር ጀማል አብዱልቃድር መሀመድ ሬዶ ከላይ የገለጽናቸውን ውለታዎች ውለዋል፡፡
በየአካባቢው ያሉ ምሁራን ለአካባቢያቸውና አገራቸው እንዲህ አይነት ውለታ ሊውሉ ይገባል፡፡ ቋንቋ በውስጡ በያዘው ተረቶች ውስጥ የአንድን ማህበረሰብ ምንነት ይገልጻል፤ የማህበረሰቡ አገር በቀል ዕውቀቶች ይገኙበታል፡፡ የአንድ አካባቢ አገር በቀል ዕውቀት ደግሞ ለሌላው አካባቢም ዕውቀት ይሆናል፡፡ አፋር ውስጥ ያሉ ፍልስፍናዎች የኢትዮጵያ መገለጫ ናቸው። ስለዚህ የክብር ዶክተር ጀማል አብዱል ቃድር ሬዶ የኢትዮጵያም ባለውለታ ናቸው፡፡
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደግሞ ለእንዲህ አይነት አገር በቀል ዕውቀቶች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። የባህልና አገር በቀል ዕውቀቶች የምርምር ማዕከል በመገንባትና ለአፋርኛ ውለታ በዋሉት ሰው በመሰየም ለአካባቢውም ሆነ ለኢትዮጵያ ውለታ የዋለው የሠመራ ዩኒቨርሲቲም ምስጋና ይገባዋል፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 2016 ዓ.ም