አዲሱ ዓመት በባተ በሶስተኛው ቀን ማለዳ በሰፈሩ አስደንጋጭ ወሬ ተሰማ።ወሬውን ተከትሎ አብዛኞቹ ተሯሩጠው ከቦታው ደረሱ። ሁኔታውን ያዩ ደግሞ ላልሰሙት ፈጥነው አሰሙ።ዓይናቸው እውነቱን ያረጋገጠ በርካቶች በሆነው ሁሉ አዘኑ።እግራቸው በስፍራው የረገጠ እናቶችም ደረታቸውን ደቅተው አነቡ።
ገርጂ «ካዛንቺስ» ከተባለው ሰፈር እልፍ ብሎ የሚገኘው ወንዝ ሌሊቱን ብቻውን አላደረም።ለወትሮው ከመስኩ በርቀት የሚለየው ወራጅ ዕለቱን ከበድ ያለው ይመስላል። አንገቱን ዘንበል አድርጎ በዝምታ ያሸለበውን ወጣት እንዳጋደመ ባሻገር ይታያል።ሁኔታው ደግሞ እንደክረምቱ ማየል አልሆነም።ከላዩ ያረፈውን እንግዳ ቁልቁል ሳይሰድ የጎንዮሽ ተረጋግቶ እየተጓዘ ነው።
የ2003 ዓም የአዲስ ዘመን ፀሀይ በማለዳው መፈንጠቅ ስትጀምር በድንገት እግር የጣላቸው መንገደኞችም በወንዙ አጠገብ እያለፉ ነው ።በርቀት ያዩትን ቀርበው እስኪያውቁት ከዳርቻው የወደቀው ፍጡር ትንፋሽ አልባ በድን መሆኑን አልገመቱም።ወጣቱ በግራ ሆዱ አራት ቦታ ላይ በስለት ተወግቷል። ዝቅ ብሎ ያለው ብሽሽቱም ተመሳሳይ ጉዳት ይታይበታል። ከሆዱ ላይ በግልጽ የሚስተዋለው በደም የተበከለ ክፍተት የትንሹን አንጀት ጫፍ ያሳያል።
የወደቀውን ሰው ገጽታ ያስተዋሉ አንዳንዶች ስለማንነቱ መለየት አላዳገታቸውም።በዚሁ አካባቢ ተከራይቶ የሚኖርና ብዙዎቹ በአይንም በመግባባትም የሚያውቁት ነዋሪ ነው። ዳር ሆነው ከሚያዩት መሀል የደፈሩት ወደወንዙ ዘልቀው ትንፋሹን አዳመጡ። የሌቱ ቅዝቃዜ ያደነዘዘው ወጣት ልብ እየመታች መሆኗን ሲያወቁ ህይወቱን ለማትረፍ ተረባረቡ።
በስፍራው ፈጥኖ የደረሰው የፖሊስ አምቡላንስ ድምጽ እያሰማ ቀረበ ።ወዲያው ዙሪያውን የከበቡ ሰዎች ከፖሊስ ጋር ተረባርበው ክፉኛ የተጎዳውን ወጣት ወደ አምቡላንሱ አስገቡት።የፖሊስ የምርመራ ቡድንም በስፍራው ተገኝቶ አስፈላጊውን ቴክኒካዊ ምርመራ ወሰደ ።እግረ መንገዱንም የወጣቱን ማንነትና ውሎ አዳሩን አጣርቶ መረጃዎችን ሰበሰበ።
የአካባቢው ነዋሪዎች ስለወጣቱ «እናውቃለን» ያሉትን ሁሉ ተናገሩ።የፖሊስ አምቡላንስ በሞትና ህይወት መካከል ያለውን ተጎጂ ይዞ ወደ ሆስፒታል ገሰገሰ።ይህ በሆነ አፍታ ደቂቃ ውስጥ ግን የተጎጂው ትንፋሽ ድንገት ተቋረጠ። መሞቱ በፖሊስ እንደተረጋገጠ ለቀጣዩ ምርመራ አስፈላጊው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ አስከሬኑ ወደ ዳግማዊ ሚኒልክ ሆስፒታል ተላከ ።
የወጣቱን ህይወት ማለፍ የሰሙ የአካባቢው ነዋሪዎች ሀዘን ዳግመኛ በረታ።ከጉዳቱ ባለፈ ለሊቱን በወንዝ ውስጥ ማደሩ እርዳታ እንዳያገኝ ምክንያት ሆኗልና ብዘዎችን ከቁጭት ላይ ጣለ።መሞቱን ተከትሎ ገንዘብ ማሰባሰብ የጀመረው ነዋሪ አስከሬኑን ወደትውልድ ሀገሩ ለመሸኘት የአቅሙን አዋጥቶ፣ አልቅሶና ተላቅሶ የደንቡን ፈጸመ ።ከዚህ ሁሉ መልካምነት ጀርባ ግን ይህን የጭካኔ ድርጊት በማን ተፈጸመ? የሚለው ጥያቄ የፖሊስ ብቻ አልነበረም።
ከዓመታት በፊት
ገመቹ ዱቢሳ በልጅነቱ ሲቦርቅበት ያደገውን የጀልዱ ጫካ ከልቡ ይወደዋል።ለእሱ ግብርና ህይወቱ ነው። ከማለዳ እስከምሽት በሬዎቹን ጠምዶ የአገሩን መሬት ሲያርስና ሲጎለጉል ኖሯል። ገመቹ በዕድሜው ከፍ ሲል ከእርሻው ሌላ ለትምህርት አልታደለም። ቤተሰቦቹ ከአጠገባቸው ሆኖ እንዲያግዙት መሻታቸው የፊደልን ሀሁ እንዳያውቅ ምክንያት ሆኗል።
ልጅነቱን አጋምሶ ወጣትነት ላይ ሲደርስ ግን ልቡ ይሸፍት ያዘ ።በስም እንደሚያውቃቸው ያገሩ ልጆች መሀል አገር ዘልቆ ከተሜ መሆንን ፈለገ።እስከዛሬ ወላጆቹን በጉልበቱ ሲያግዝ ኖሯልና በውሳኔው አልዋለለም።አዲስ አበባ ገብቶ ራሱን ቀይሮና ህይወቱን ለውጦ መኖርን ምርጫው አደረገ ። ገመቹ የትውልድ ሀገሩን ጀልዱን ትቶ አዲስ አበባ ሲገባ ለእንግድነቱ ተቀባይ አላጣም።
ገመቹና ሸገር ይበልጥ የተዋወቁት ቦሌ አየር ማረፊያ አካባቢ ባገኘው የሳር አጨዳ ስራ ነበር። ለእሱ ይህ አይነቱ ሙያ ከባድ አልነበረም። ሲያርስና ሲከምር የኖረው ክንዱ አጨዳውን ለማቀላጠፍ የቀለለ ሆነለት ።በዚህ ውሎ እጁን ያሟሸው ስራ ፈላጊ እያደር ሌሎች አማራጮችን ፈለገ። ውሎ አድሮ ካገሩ ልጆች መገናኘቱ ደግሞ ከተማዋን በቀላሉ እንዲያውቅና ራሱን ችሎ እንዲኖር ዕድል ሰጠው።
አሁን ገመቹ የአዲስ አበባ ህይወትን በአግባቡ ለምዷል።ካገሩ ልጆች መዋሉና ቤት ተከራይቶ መኖሩም ይበልጥ አረጋግቶታል። ከተማውን ጠልቆ ሲያውቀው የተሰማራበት የቀን ስራ ከብዙዎች አወዳጅቶታል። በሚኖርበት ገርጂ አካባቢ እንደሱ ካገራቸው የወጡ እኩዮቹ በርካታ ናቸው።በስራ ቀኑን ሲደክሙ ቆይተው በእረፍታቸው ጊዜ ዘና የሚሉት ደግሞ ጥቂቶች አይደሉም።
ገመቹ በዚህ ስፍራ እነ ቢቂላን ካገኘ ወዲህ መተማመኑ ይበልጥ ጨምሯል።እነሱ ዘወትር ከሚያወጉት የቤተሰብ ጨዋታ የዘለለ የብርጭቆ ወገብ ይዘው የሚዝናኑበት ጊዜ ይበልጣል።ከጠጅና አረቄው፣ ከቢራና ድራፍቱ እየቀላቀሉ በጭፈራና ሆታ የሚያመሹበትን ጊዜ ከልብ ይወዱታል። እንዲሀ በሆነ ጊዜም ጋባዥና ተጋባዡ ይበረክታል።«እኔ እልቅ ፣እኔ እበልጥ» ፉክክሩ ያይላል።
ቢቂላ የገመቹ ያገር ልጅ ነው።ከቀዬው ርቆ ለመውጣቱ ዋና ምክንያት እንደሌሎቹ የከተማን እንጀራ መሻቱ ነበር።እሱ ከባልንጀሮቹ በተሻለ ከዕውቀት ጋር ተዋውቋል።አንደኛ ደረጃን ጨርሶ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ተምሯል።ቀጣዩን ለመማር ግን ልቡ የተረጋጋ አልሆነም። የአገሩ ልጆች ከተማ የመግባት ጉዳይ ሰላም አልሰጠውም።እሱም እንደ እነሱ ዘመናይ ተብሎ ብር መቁጠርን ፈለገ ።ከገጠር ኩራዝ ይልቅ የከተማው መብራትና ብርሀን ናፈቀው።
ቢቂላ አዲስ አበባ እንደገባ የመጀመሪያ መገኛው ቀን ስራ ላይ ሆነ። የገጠር እንጀራን የለመደው ወጣት ለጊዜው ህይወት ከብዶ ታየው።እያደር ኑሮን ሲረዳና ካገሩ ልጆች ሲገናኝ ግን ደስተኛ መሆን ጀመረ።በዙሪያው አንዳሉት ሁሉ ከሆዱ ቆጥቦ ለኪሱ ማስቀመጥ ያዘ ።ጠግቦ መብላትን ረስቶም በልኩ መኖርን ለመደ ።ቀናት ሲቆጠሩ ደግሞ ለተጨማሪ ገቢው እንደ አማራጭ ከሌላው ጥግ ተገኘ።አዋጭነቱ ሲገባው በሙከራው ቀጥሎ በመንገዱ ገፋበት።
እነ ቢቂላ አሁን ባገር ልጅነት ሰበብ መፈላለግ ጀምረዋል።ለዚህ ደግሞ የገርጂው ካሳንቺስ ሰፈር መናሀሪያቸው ነው ። በእረፍት ቀናቸው ሲገናኙ «ፉት…» እያሉ የሚያደምቁት ጨዋታ አንዳንዴ አውሎ ያስመሻቸዋል። ብዙ ጊዜ ግን ሁኔታው እንዳጀማመሩ አይዘልቅም።ቆይታቸው በጭቅጭቅ ተዋዝቶ በጠብ ጭምር ሊቋጭ ይችላል።
ሁሌም ከጎናቸው ሻጥ የሚያደርጉት ጩቤ እርስ በእርሳቸው እንዳይተማመኑ አድርጓል።በዚህ ስለት አንዳንዴ ጨለማን ተግነው ዝርፊያ ይፈጽሙበታል።ያገኙትን ይዘው ለመሮጥ ፣ያዩትን ተቀብለው ለማምለጥ ስለታማው ጩቤያቸው አጋዣቸው ሆኖ ቆይቷል።ይህ የዝርፊያ ጥቅም እያደር ሲጥማቸው ደግሞ በቀላሉ ሊተውት አልፈለጉም።
ከነቢቂላ ያገር ልጆች አንዱ አመንሲሳ ቦሩ ሁሌም ካጠገባቸው አይርቅም።ከበሉት ቀምሶ ከጠጡትም ተጎንጭቶ አብሯቸው ያሳልፋል።አመንሲሳ ሁሌም ቢሆን ጥቂት ሲቀምስ ሞቅ ይለዋል።ሞቅታው እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ ደጋግሞ ከመጠጣት አይመለስም።እንዲህ በሆነ ግዜ ከሰዎች የማያግባባው ባህሪይው ከብዙዎች ጋር ሲያጋጨው ቆይቷል።
አመንሲሳ በገርጂው የካሳንቺስ ሰፈር ከሌላ ጓደኛው ጋር ተከራይቶ የሚኖር ነው። በቀን ስራው ውሎ ሲደክም የሚውለው አካሉ ለመዝናናት ሲሉት ሁሌም ይበረታል።ይህን ጊዜ ካገሩ ልጆች ጋር ማሳለፍ የሚፈልግው ወጣት ሲሰክር በሚያሳየው ባህርይ ከማንም ጋር አይስማም።ባልንጀሮቹም ቢሆኑ «ወቀሳና ምክሩ ሰልችቶናል» ሲሉ ከእሱ መራቅን ይመርጣሉ።
መስከረም 02 ቀን 2003 ዓም
የአውደ ዓመት ማግስት ግርግር ዛሬም እንደትናንቱ አልቀዘቀዘም።በመንገዱ በአገር ልብስ አጊጠው ወዲያ ወዲህ የሚሉት በርክተዋል።በየስፍራው ደምቆ የሚሰማው ሙዚቃም ለቀኑ ይበልጥ ትርጉም ሰጥቷል።ዕለቱን በጓደኛቸው የክርስትና ጥሪ ላይ የቆዩት ጓደኛሞች መሸትሸት ሲል ለመዝናናት ወጥተዋል።ቀኑ የአውደ ዓመት ማግስት መሆኑ ደግሞ እንዲህ ለማድረጉ ሰበብ ነበር። ከሰፈራቸው እምብዛም ሳይርቁ ጎራ ያሉበት ግሮሰሪ ሙዚቃ ከሌላው ቀን በተለየ ልቆ ይሰማል።ለመስተንግዶ ፈጥነው የደረሱት አስተናጋጆች የታዘዙትን አስተናግደው ዞር ከማለታቸው እነ ቢቂላ ከጓደኛቸው አመንሲሳ ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጩ።
አመንሲሳ እንደተለመደው በሞቅታ ውስጥ ሆኖ ይታያል።ከያዘው መጠጥ በላይ በላዩ እያስቀዳም በሙዚቃው ይወዛወዛል።ድንገት ጓደኞቹን ሲያይ ግን ከነበረበት ለቆ ወደ እነሱ ተጠጋ ።ድንገት ያገሩን ልጆች ማግኘቱ አስደስቶታል።ይህ ስሜቱ ደግሞ ግብዣውን እንዲሸፍን ምክንያት ሆኖ አቀራርቦታል።ጥቂት ቆይቶ የሞቅታው ጨዋታ ቀጠለ ።ይህኔ አመንሲሳ ከወትሮው በተለየ ግንባሩን የሸፈነበት ኮፍያ በግልጽ ሊታይ ግድ ሆነ ።
አመንሲሳ ጓደኞቹ ፊቱ ቀርበው ገጽታውን ማስተዋላቸው አልተመቸውም።ከዚህ ቀጥሎ ምን እንደሚሉት አልጠፋውም ።ሁሌም በስካሩ ሰበብ የሚነገረው ምክርና ተግሳጽ እንዳበሳጨው ነው። በእሱ ወድቆ መነሳት የእነሱን «ያገባናል» ይሉትን ቁጭት ተረድቶት አያውቅም ።ይህ አቋሙም ከብዙዎቹ ጋር እንዳጋጨው፣እንዳጨቃጨቀው ዘልቋል።
የፊቱን መላላጥና ጉዳት የተመለከቱ ቢቂላና ገመቹ እንደተለመደው ወቀሳቸውን ቀጠሉ።የእሱ እንደዚህ መሆን የእነሱን ማንነት ጭምር እንደሚያስወቅስ እያነሱም በሀይለ ቃል ተናገሩት ።ይህን ሲሰማ አመንሲሳ በንዴት ጦፈ ።የእሱ መጠጣትና መስከር ከእነሱ ክብር ጋር እንደማይገናኝ ለማስረዳትም በጨኸት አምባረቀ።የመጠጥ ግሮሰሪው ከሙዚቃው ድምጽ ጋር ተዳምሮ የባልንጀራሞቹን ጠብ ሲያስተናግድ አመሸ።
ምሽቱ እየገፋ ነው።አምስት ሰዓት አለፍ እንዳለ ግን አመንሲሳና ያገሩ ልጆች ወደቤታቸው ለመሄድ ተነሱ። የሁሉም መኖሪያ በአንድ አቅጣጫ በመሆኑ መነጣጠል አልተቻላቸውም።ሁለቱ በአንድነት አመንሲሳ ደግሞ ለብቻው ሙግታቸውን ቀጥለዋል።ወቀሳው የበዛበት አመንሲሳ ትዕግስቱ እንደተሟጠጠ ያስታውቃል።እነሱ መካሪዎች እሱ ደግሞ ተመካሪ መሆኑ ከልብ እያበሳጨው ነው።በድንገት ግን በገመቹ ላይ አመረረ።እየተንገዳደደ ተጠግቶም ከበድ ያለ ቡጢ ፊቱ ላይ አሳረፈበት።
በሁለቱ መሀል ግርግር ሲነሳ ቢቂላ ለመገላገል ከመሀል ገባ።ይህኔ አመንሲሳ ጎኑን ዳበሰ።እጁ ከጩቤው ሲገናኝም ገላጋዩ ላይ ሰነዘረ ።ስለቱ አፍንጫው አካባቢ ያረፈው ቢቂላ ከአመንሲሳ ስለቱን ተቀብሎ ደጋግሞ ወጋው። ጓደኛውም ለድርጊቱ አጋር ሆኖ ተባበረው።የተወጋው ሲወድቅ አቅሙ ተዳከመ ።መላው አካሉ በደም ሲርስ ተሸክመው ወደ ወንዙ ጎተቱት።ድንገት ግን ኮሽታ ሰምተው ቀና ሲሉ። ከአንድ መንገደኛ ጋር ተጋጠሙ።
መንገደኛው ድርጊታቸው የዝርፊያ መሆኑን ጠርጥሮ እያስተዋላቸው ነበር።ሰውዬው ማንነታቸውን ለይቷል።ለምን? ብሎ ከመጠየቁ በፊት ግን እያዋከቡ ከስፍራው አባረሩት ።ሌላ ሰው እንዳላያቸው ሲያውቁም አመንሲሳን ወደ ወንዙ ጥግ ወስደው ወረወሩት።
አመንሲሳ ከተለመደው በላይ መቆየቱን ያወቀው አብሮ ኗሪ ጓደኛው ደጅ ደጁን ሲያይ ለሊቱን አጋመሰ።አብሮት የሚኖር በመሆኑ የባልንጀራውን ባህርይ ጠንቅቆ ይረዳል።የማምሸት እንጂ የማደር ልምድ እንደሌለው ያውቃልና የዛሬ ቆይታውን በስጋት አሳልፎ ከንጋቱ ደርሷል።
የፖሊስ ምርመራ
ድርጊቱ ተፈጽሞ ቀናት እንደተቆጠሩ የፖሊስ የምርመራ ቡድን ከአካባቢው ደርሶ የክትትል ስራውን ጀመረ።በወቅቱ ሟቹን የገደሉት እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ጊዜ የፈጀ ምርመራ የሚያሻ አልሆነም።የተጠርጣሪዎችን ማንነት ለማወቅ በስፍራው ያሉ ያገራቸው ልጆችና በጨለማው ውስጥ ድርጊታቸውን ያስተዋለው መንገደኛ እማኝነት በቂ ነበር።
ገመቹና ቢቂላ ጓደኛቸው ሲሰቃይ አድሮ ሲነጋ ህይወቱ ስለማለፉ መረጃው ደርሷቸዋል።ይህን እንዳወቁ ለራሳቸው መላ መፈለግ እንዳለባቸው ሲመክሩ ቆዩ።ጥቂት ቆይተውም አድራሻቸውን ነጣጥለው ወደ ተለያዩ ስፍራዎች ተጓዙ።ሁለቱም የሰሙትን ወሬ ሁሉ ሊለዋወጡ ቃል ገብተዋል።አንዳቸው የሌላቸውን መገኛ ላለማሳወቅም ተማምለዋል።
ፖሊስ የተጠርጣሪዎችን መሰወር እንዳወቀ ክትትሉን አጠናከረ።የመጀመሪያው ጥቆማ የገመቹ መገኛ ምስራቅ ሸዋ ዞን ወለንጪቲ ከተማ ስለመሆኑ አመላከተ።ፖሊስ የመያዣ ፈቃድ አውጥቶ ለጉዞ ተዘጋጀ ። ባገኘው መረጃ ተመስርቶም ከዞኑ ፖሊስ ጋር በቅንጅት ተንቀሳቀሰ ።ይህ ሰንሰለታዊ የክትትል ስራ ውጤታማ ነበር።የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ ተፈላጊውን ተጠርጣሪ ካለበት ቦታ ተከታትሎ በቁጥጥር ስር እንዳዋለው ታወቀ።
የገመቹ መገኘት ሁለተኛውን ተፈላጊ ለመያዝ በር የከፈተ ሆነ ።ተጠርጣሪው በተደረገለት ፖሊሳዊ ምርመራ የጓደኛውን መገኛ ያለአንዳች ስህተት በምልክት ተናገረ።ቢቂላ አዳማ ዙሪያ ቂሊምጦ ቀበሌ ከአንድ ግለሰብ ቤት በግብርና ተቀጥሮ እያገለገለ ሳለ በቁጥጥር ስር ዋለ።ፖሊስ ተፈላጊዎቹን እጁ ካስገባ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ይዟቸው ተመለሰ።በበቂ መረጃዎች የተደራጀውን መዝገብ አጠናክሮም ለክስ በሚያመች ሁኔታ ለፍርድ ሂደቱ አመቻቸ።
በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 196/06 የተዋቀረው መረጃ በመርማሪ ዋና ሳጂን ታሪኩ ኢርኮ መሪነት ተጠናቆ ለዓቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ዝግጁ ሆኗል።በበቂ የሰውና የሰነድ ማስረጃ፣ በህክምና ምርመራዎችና በቴክኒክ ማሳያዎች የተደራጀው የክስ ሂደት ከፍጻሜው ደርሶም ለፍርድ ቤት ውሳኔ ቀርቧል።
ውሳኔ በከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ህግና በተከሳሾች መካከል ያለውን የፍርድ ሂደት ሲከታተል የቆየው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባልንጀራሞቹ በባልንጀራቸው ላይ በፈጸሙት የሰው መግደል ወንጀል ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋግጧል።
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ለሀምሌ 11 ቀን 2005 ዓም በአንደኛው ተከሳሽ ቢቂላ ሆርዶፋ ላይ ባስተላለፈው ቅጣት ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።የሁለተኛው ተከሳሽ የፍርድ ሂደትም እንዲሁ ወደፊት ተፈጻሚ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011
መልካምስራ አፈወርቅ