የአስተዳደግ ትርፍ ለአገር ሲተርፍ

ስለ አባታቸው እገዛ፣ ስለ አባታቸው ምክር፣ መመሪያ፣ ማስጠንቀቂያና እንክብካቤ ተናግረው የማይጠግቡት የዛሬዋ የሴቶች ገጽ እንግዳችን ወይዘሮ እታገኝ አሰፋ ይባላሉ። ትውልዳቸው ሰሜን ሸዋ ሲሆን፣ ትምህርታቸውንም ያጠናቀቁት በአቤቶ ነጋሲ ትምህርት ቤት ነው። ከአንደኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል የጨረሱት በዚሁ ትምህርት ቤት ነው። ከቤታቸው እስከ ትምህርት ቤታቸው ድረስ የሚያስኬደው የአምስት ደቂቃ መንገድ ብቻ ነበር። የቤተሰባቸው ብቸኛዋ ሴት ልጅ እርሳቸው ናቸው።

የአባታቸው ፍላጎት ልጃቸው ትምህርት እንዲማሩ ስለነበር፣ ከፍተኛ እገዛ ሲደረግላቸው ነበር። የዚሁ የአባታቸው ጥረት ከጀርባ በመኖሩ የተነሳ ትምህርታቸውን 12ኛ ክፍል እንዳገባደዱ ወደ መምህራን ኮሌጅ ገብተው በ1974 ዓ፣ም መመረቅ ችለዋል። በዚያን ጊዜ ተመራቂ መምህር የሚመደበው በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል ስለነበረ የደረሳቸው በጎንደር ክፍለ ሀገር ነበር።

ወይዘሮ እታገኝ ያሏቸው ሶስት ወንድሞች ሲሆኑ፣ እነርሱም ልክ እንደአባታቸው ሁሉ እንክብካቤ ያደርጉላቸው ነበር። ትምህርት ቤት የሚገኙት መምህራንም ሆነ ተማሪዎች ከአባታቸው በኩል ያለውን እገዛና ክትትል ያውቁ ስለነበር ለእርሳቸው የነበራቸው አመለካከት ቀና ነበር። የአባታቸው ሁኔታ ከነበሩበት አካባቢና ጊዜ በተለየና ወጣ ባለ መልኩ ነበር ድጋፉ።

እናታቸውን በተመለከተ ከእሳቸው አባት በፊት ሌላ ባል አግብተው አምስት ልጆች በሾተላይ አጥተዋል። አባታቸውም ሌላ አግብተው ልጅ አላገኙም ነበር፤ እናታቸውም እሳቸውን ሲወልዱ እታገኘሁ ያሉዋቸው ለዚሁ ነበር። በመሠረቱ ለእናታቸውም ለአባታቸውም “እህት ነበርኩ ማለት ይቻላል” ይላሉ ወይዘሮ እታገኝ። ቤተሰባቸው በኢኮኖሚም ችግር ያልነበረበት በመሆኑ አስተዳደጋቸው መልካም እንደሆነ እንግዳችን ይናገራሉ።

በአባታቸው ተፅዕኖ የተነሳም ከወንድሞቻቸውም በላይ ሆነው ነበር ያደጉት። በቤተሰብ ታቅፈውና ተደግፈው በማደጋቸው “ከሰው የምሻው ፍቅር ብቻ ይመስለኛል” ይላሉ፣ የሰው ሀብትና ገንዘብ ያለመፈለግ፣ በራስ ብቻ መቆም ስለሆነ የተነገራቸው፣ የተለማመዱትም ይህንኑ ብቻ ነበር።

እስከ 12ኛ ክፍል እርሳቸው በተማሩበት ቦታ ያሉት መምህራንና ሐኪሞች ብቻ ነበሩ። ከዚህም የተነሳ ብዙዎች የእርሳቸው እኩዮች የወደፊት ምርጫቸው ከሁለቱ አንዱ ነበር። የልጅነት ጊዜያቸውን ሲያጤኑ አድገው መማር እንጂ ትዳር የተመኙበትን ጊዜ አያስታውሱም።

እንግዳችን ትምህርታውን ካጠናቀቁ በኋላ መጀመሪያ ወደተመደቡበት ጎንደር ስማዳ ወረዳ ታገል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአስተማሪነት ሥራ ጀመሩ። በትውልድ ሥፍራቸው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቤታቸው ከትምህርት ቤቱ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ጉዞ የሚያደርጉት በእግራቸው ነበር። ይሁንና አስተማሪ ሆነው ከተመደቡ በኋላ በበቅሎ መሄድ ያልለመዱት መምህርት፣ ለሦስት ዓመታት ያህል የተመላለሱት በሰው ተደግፈው ነበር።

በመምህርነት ከሰለጠኑና ሥራ ከጀመሩ በኋላ ለ20 ዓመታት ያህል በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በገጠሪቷ ኢትዮጵያ አስተምረዋል። ከትዳራቸውም ሦስት ልጆች አፍርተዋል፤ ወደትዳር ከገቡ ሦስት ዓመት በኋላ አባታቸው በሞት ተለዩ። በትዳር 39 ዓመት ሆኖዋቸዋል።

በአጠቃላይ ከአርባ ዓመት በላይ ያገለገሉት እንግዳችን፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ ደግሞ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃ ሠርተዋል። መጀመሪያ ከትምህርት ሥራ አንደወጡ የወረዳ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሠርተዋል። ከዚያም ማዘጋጃ ቤት የጋብቻና ልደት መምሪያ ኃላፊ ነበሩ። ቀጥሎም በብሔራዊ ቲያትር የአንድ ክፍል ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል። በአሁኑ ወቅትም በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚኒስትሯ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

አሁን ወዳሉበት የኃላፊነት ስራ ከመምጣታቸው በፊት ከዚህ ቀደም በነበሩበት የወሳኝ ኩነት ሥራ ላይ ብዙ ተግዳሮቶች ገጥሟቸዋል። በተለይ በተለመደው የምልጃው አሠራር በጣም የተካነ ሠራተኛ ሰው እርሳቸው ዘንድ ነበር። ሥራው ደግሞ ውጭ ከመሄድ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ዞሮ ዞሮ የሚወስኑትና የሚያጸድቁት እርሳቸው በመሆናቸው ብዙ ያስቸግራቸው ነበር። ይህ ጉዳይ ሲብስባቸው ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ወሰዱት፤ በዚህ ጊዜ ሰውዬው በጨረቃ ከኢትዮጵያ ውጭ ወጣ። ሌብነትንም በዚህ መልኩ ለመከላከል ሞክረዋል።

የወሳኝ ኩነት አሠራርና አገልግሎትን በተለይ በክፍለ ከተማና በወረዳ እንዲመጣም መዋቅሩን የዘረጉት እርሳቸውና ባልደረቦቻቸው ነበሩ። ወረዳ ላይ ልደት ሞት፣ ያገባ ያላገባ ማስረጃ በሚል በዛ ደረጃ እንዲሰጥ አድርገዋል። በዚህም የህብረተሰቡን እንግልት መቀነስ ችለዋል።

ከመሬት ጋር በተያያዘ ወረዳ ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት ብዙ ተግዳሮቶች ነበሩ። በዚያን ጊዜ ሽጉጥ የተመዘዘባቸው ወቅት ነበር፤ ቦታው ኮልፌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ነበር፣ ጉዳዩ የተፈጠረው ቤት ለማፍረስ ሄደው ሳለ ነው። ቤት የሚፈርስበት ግለሰብ ሽጉጥ አውጥቶ እንዳስፈራራቸፈውና እሳቸውም ለዚህ ሳይበገሩ የገነባውን ህገወጥ ግንባታ እንዳስፈረሱት ይናገራሉ።

በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ ባለው አሠራር ከታች እርከን ወደ ላይ፣ ከአንዱ አገልግሎት ሰጪ ወደ ሌላው ኔትወርክ የሚባል ነገር አለ፤ እውነት ነው ኔትወርክ ለበጎም ለክፋትም ተግባራት ሲውል ይስተዋላል። ለምሳሌ አንዴ እርሳቸው የገጠማቸው ነገር አለ፣ በእርሳቸው ደረጃ ያሉ ሁለት ሠራተኞች ሰነድ አልባ የሆነ ይዞታ ላይ ይሠሩ ነበር፣ አንድ ባለጉዳይ ሲያስቸግራቸው ወደእርሳቸው ይልኩታል፣ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ጨርሰውለት ያው ውሰድ ሲሉት ማመን አቅቶት ደጋግሞ ጠይቋቸው አረጋገጡለት፣ በመጨረሻም “በቃ ጨረስኩ?” እያለ ተገረመ። በመጨረሻም ምን ያህል ተጉላልቶ እንደነበረ ነግሯቸው እግራቸውን ስሞ ሄደ።

በዚህ በጋብቻና በልደት ጉዳይ ላይም እንደሚታወቀው ልደት የሁሉም መነሻ ነው፣ ልደት ላይ ከተቆለፈ አንድ ሰው ማዘጋጃቤትም ሆነ የትም ጋብቻ ለማውጣት ይቸገራል። እንግዲህ ይህን አዙሪት ለመስበር በሚሞክሩበት ጊዜ ነው የኔትወርኩ ጥልፍልፍ አስቸጋሪ የሆነባቸው። ይህንን መተብተብ ለመፍታት የነበረው ፈተና በጣም ከባድ ነው ይላሉ። ይህንንም ለመበጠስ አገልግሎቱ በወረዳ ጭምር እንዲሰጥ ተደርጓል። ጋብቻ በክፍለ ከተማ እንዲሆን ሲታሰብ የተሰራው ከሕንፃው ዝግጅት ጀምሮ ነበር። የውጭ ሀገር ሰዎችም ጋብቻ ሊፈፅሙ ሊመጡ ስለሚችሉ ገጽታ ግንባታውም አብሮ ታስቦበታል።

የማዘጋጃ አሠራር በየዘመኑ ይለያያል። እርሳቸው በነበሩበትት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አርከበ ዕቁባይ ነበሩ፣ ከንቲባው፣ መንገድ ላይ ሆነ ከቢሮ ውጭም ማነጋገር የሚቻል ዓይነት ሰው ነበሩ። ‹‹አርከበ ዕቁባይ የሥራ ሰው ናቸው›› የሚሉት ወይዘሮዋ፣ ‹‹ፖለቲካ ሌላ ጉዳይ ነው፤ በሥራ ጉዳይ ግን በጣም ጠንካራ ሰው ነበሩ፤ ሥራ ተሰጥቶን ከወሰድን በኋላ ስለሥራው መሠራትና አለመሠራት የሚጠይቁበት አግባብ ማንም ሰው ሊማርበት የሚችል መልክ ነበረው›› ይሉናል።

ኔትወርክ በክፍለ ከተማም ሆነ በወረዳ በብዙ መልኩና ገፅታ አለው። ጠንካራ ሥራ የሚሠራ ሰውም ኔትወርክ አለው፣ ምንም ሥራ የማይሠራ ሰውም እንዲሁ ኔትወርክ አለው። ግን በየወቅቱ እየተገመገመ እርምጃ ይወሰድ ነበር፣ አሁንም እንደዚያ ይመስለኛል፣ ክፍያን በተመለከተ የዚያን ጊዜ ግን ለጋብቻ 50 ብር ነበር፤ ለልደትና ለመሳሰለው ደግሞ 20 ብር ነበር። ይህም መመሪያ ላይ ሰፍሮ ነበር፤ አሁን እንግዲህ ብዙ ለውጥ ስላለ ይቀየራል። የወረቀት ዋጋ ያን ጊዜ የነበረውና አሁን ያለው ይለያያል፤ ብዙ ጨምሯል። የኑሮ ውድነቱ ብዙውን ክፍል ነክቶታል፤ በጀት እንኳ በፊት የሚመደበውና የአሁኑ በእጅጉ ይለያያል።

ወይዘሮ እታገኝ፣ እንደሚሉት፤ በቀናነትና ከሕግ አገልጋይነት ወጥቶ በምልጃና በሙስና በመሳሰለው መሥመር መስራት የሚያመጣው ተሸናፊነትን ነው። ሌላው ደግሞ እራስን መሆን እንጂ ያልሆኑትን ለመሆን መሞከር አግባብ አይደለም። ለሰዎችም ያልተገባ ማንነትን ያለምንም ምክንያት መስጠት ትክክል አይሆንም።

አንዴ በማስተማር ዓለም እያሉ ያጋጠማቸውን ሲያወጉ፤ በአንድ አጋጣሚ በተለይ ተማሪዎችን ስድብ መሳደብ ያለውን መጥፎ ተፅዕኖ እንደተማሩበት ነገሩን። ትምህርት ላይ ፍላጎት የማያሳዩ ተማሪዎችን ‹‹ደደብ›› ብሎ መስደብ ሳይሆን ችግራቻውንና ምክንያታቸውን ተከታትሎ መረዳት ጠቃሚ ነው። በተለይ በፍቅርና በርህራሄ ቢያንስ ቢያንስ ተማሪዎችን ማየት፣ ራሳቸው ችግራቸውን ሊያካፍሉ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ ይናገራሉ።

እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ከራስ ጥቅም አልፎ ሕብረተሰብን ማሰብ ደግሞ አንድ ከፀብና ከጭቅጭቅ መታቀቢያ መፍትሄ ነው። ስልጣን ይመጣል፤ ይሄዳል፣ ይሁንና በሠራተኞች መካከል በሚነሳ ፀብና የሥራ መጓተት ሕብረተሰብ ይጎዳልና የቱ መቅደም እንዳለበት ማወቅ ይገባል።

አንዳንዴ ደግሞ ወሬ ከአንድ ወገን ተቀብሎ ከሰው ጋር የመጋጨት ጉዳይ አለ። ከታችኛው ሠራተኛ ወይም ከበላይ ካለው አመራር ወሬ ተቀብሎ ሳያጣሩና ሳይመዝኑ የመንቀሳቀስ ነገር ላለመግባባትና ለፍቅር መናድ አንዱ ምክንያት ነው፤ ስለዚህም መሪ ሁልጊዜ ጥበበኛ መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ።

አንድ ጊዜ በእርሳቸው ስር የነበረ ወንድ ሰራተኛ “ነገሮችን አጥብቀሽ ትይዣለሽ” አላቸው። ሌሎች መሥራት የሚገባቸውን ደግሞ እርሳቸው እንደሚሠሩ ሁለ በማንሳት ወቀሳቸው፤ እንግዲህ ወንዶችም አንዱ የአንዱ የበላይ ለመሆን ትግል ውስጥ ይገባሉ። ወንዶች በሥራ መወጠርን አይፈልጉም። ሴቷ ስትሠራና እነርሱን ዕረፍት ስትሰጣቸው እሱም ያስኮርፋቸዋል።

ልምድና ተሞክሯቸውን እግረመንገድ ሲነግሩን በተለይ አንዲት ሴት እችላለሁ የሚለውን ቃል መቀበል አለባት። እሱንም ለማረጋገጥ በትምህርትና በክህሎት ራስን ማብቃት ይገባል። ጎን ለጎን ደግሞ ነገሮችን በቅንነት ማየት፤ ሁሉም ሰው ሙሉ ባለመሆኑ ከሌላ ሰው ትምህርት መውሰድና አስፈላጊ መሆኑንም አብራሩልን። እንደ ምሳሌም እርሳቸው ከመማር ማስተማሩ ስራ ወደ ወረዳ ሲመጡ ደብዳቤዎችን መምራት የመሳሰሉትን ጉዳዮችን የተማሩት አንድ የመልዕክት ሠራተኛ የነበረን ሰው እየጠየቁ እንደነበረ ነገሩን።

ከፍርድ ቤትና ከመሳሰሉት አካባቢዎች የሚመጡት ደብዳቤዎች ውስብስብ ስለሚሉ ለእንግዳ ሰው ግር ይላል። በዚያን ጊዜ ዝቅ ብሎ መማር ይቻላል። ከፍ ብሎም መማር ይገባል። እኔ በቅቻለሁ፣ ከኔ በታች ያለው ሁሉ ታዛዥ ነው ብሎ ማሰብ ውድቀት ነው። ለሴትም የምመክረው ሁል ጊዜ ጠያቂ፣ አዳማጭ፣ ተማሪ መሆንን ነው። በተለይ አመራር ላይ ያለ ሰው ደግሞ አድማጭ መሆን ይገባዋል። ህብረተሰቡ ችግሬን ይፈታልኛል ብሎ የቀረበው ሰው አዳማጭ መሆን አለበት፣ ችግሩን ሊፈታለት ባይቻለው እንኳን ከማዳመጡ የተነሳ የመፍትሄ አቅጣጫ ቢያንስ ለመጠቆም ያስችለዋል።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን  መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You