የአትክልት ዘርፍ ተወዳዳሪነት እና የውጭ ገበያን የማስፋት ጉዞ

መንግሥት የፍራፍሬ ልማት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እና የምግብ ሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተለይም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። በፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ትኩረት የተሰጠው የአቮካዶ ልማት መሆኑ ይታወቃል። በዚህ የልማት ሥራ ከውጭ በግዥ የሚገባውን በሀገር ውስጥ ለመተካት ብቻ ሳይሆን፣ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግም ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛል።

ይሁን እንጂ ልማቱና ለውጭ ገበያ ተልኮ የሚገኘው ገቢ ላይ ቅሬታዎች ይነሳሉ። ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ይልቅ የሀገር ውስጥ ሽያጭ የተሻለ እንደሆነም እንዲሁ በአንዳንድ አልሚዎች ሃሳብ ይሰጣል። ጉዳዩን አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡን በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብደላ ነጋሽ፤ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ የተለያዩ ክፍተቶችን ማሻሻል አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ። ሆኖም ግን ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው በሀገር ውስጥ የሚሸጠው በገቢ ያዋጣል የሚል ድምዳሜ ላይ መደረስ የለበትም ይላሉ።

እንደ አቶ አብደላ ማብራሪያ፤ ምርቱ በተመሳሳይ ጊዜ ስለሚደርስ አብዛኛው አምራችም ምርቱን የሚሰበስበው በተመሳሳይ ወቅት ነው። ገበያው ላይ ምርት በስፋት ሲኖር ዋጋ ይወርዳል። የተትረፈረፈ ምርት ይቀርባል። የተትረፈረፈ ምርት በሚቀርብበት ጊዜ ደግሞ ተወዳዳሪነትን የሚጨምር ሥራ መሥራት ይጠበቃል። እዚህ ላይ ለጥራት ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ በዚህ ወቅት ምርት ይጨምራል። ኢትዮጵያ የምትወዳደረው ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመሆኑ ጥሩ እድሎች አሉ።

ከገበያ አንጻርም አቶ አብደላ እንደገለጹት፤ ሁሉም አይነት ፍራፍሬ ገበያ ያለው ቢሆንም ሙዝና አቮካዶ ተፈላጊነታቸው ከፍተኛ በመሆኑ ያላቸው ድርሻም ከፍተኛ ነው። ልማቱም የውጭ ገበያውን ፍላጎት ታሳቢ ተደርጎ በስፋት እየለማ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ ወደ 162ሺ ሄክታር መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬ እየለማ ሲሆን፤ ከ19 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ይመረታል። ከልማቱ በመሬት ስፋትም ሆነ በምርት መጠን ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ደግሞ የሙዝ ልማት ነው።

ከዚህ ቀደም በነበረው ማንጎ በመሬት ስፋት መጠን ሁለተኛ ደረጃ ነበር። ሆኖም ማንጎን የሚያጠቃ ተባይ በመከሰቱ ምክንያት የመሬት ስፋት መጠኑ እየቀነሰና በምርት ላይም በተመሳሳይ መቀዛቀዝ በማጋጠሙ በምትኩ በሁለተኛ ደረጃ ድርሻ የያዘው የአቮካዶ አትክልት ነው። እየተመረተ ያለው አትክልትም የተሻለ ገበያ ያላቸው የተመረጡ ዝርያዎች ናቸው። በዚህ መንገድ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራቱ እንደሀገር ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል።

የልማት ሥራው በዚህ መልኩ እየተከናወነ ቢሆንም፤ ገበያው በሚፈልገው ልክ ማቅረብ ላይ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙ አቶ አብደላ አንስተዋል። ከሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች አንዱ በልማቱ ሥፍራ ላይ ምርቱን በቅዝቃዜ ሰንሰለት ሊያቆዩ የሚችሉ የማቀዝቀዣ መጋዘኖች፣ በምርት መሰብሰብ ወቅት ምርቱ እንዲባክንና ከጥቅም ውጭ እንዳይሆን የሚያስችል የምርት መሰብሰቢያ ዘዴ አለመጠቀም፣ በማጓጓዝ ሂደትም ከተለያዩ ነገሮች ጋር በመጫን፣ የሚፈለገውን የሙቀትና የቅዝቃዜ መጠን ጠብቆ ጥንቃቄ አለማድረግና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው። እነዚህ ደግሞ ለምርት ጥራት መቀነስ ምክንያት ይሆናሉ። ጥራት ሲቀንስ ገበያ ላይ ያለው ተፈላጊነትም ይቀንሳል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ልማቱ ላይ የተሰጠው ትኩረት በምርት መሰብሰብና ከተመረተ በኋላም የሚያስፈልጉ ነገሮች እንዲሟሉ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ የገለጹት አቶ አብደላ፤ ገበያው የሚፈልገውን በማሟላት ረገድ ከምርታማነት ጎን ለጎን ማስኬድ ካልተቻለ ተጽእኖው እየጨመረ እንደሚሄድ ነው ያመለከቱት። የመልካም እርሻ አተገባበር ሥራዎችን መሥራት ለገበያው ወሳኝነት እንዳለው አስታውቀዋል።

እንደ አቶ አብደላ ማብራሪያ፤ ለጥራት መቀነስ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ባለመሠራታቸው ምክንያት የመሸጫ ዋጋ መተመን አልተቻለም። ምርቱ ጥራት የለውም በሚል መከራከሪያ ገበያው በሚፈልገው ዋጋ ማቅረብ ግድ እየሆነ ነው። በዚህም የአውሮፓ ገበያን ሰብሮ ለመግባት ያለው ጥረት ውስን ነው። መካከለኛው ምሥራቅ እና ሩቅ ምሥራቅ ሀገራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ ይታወቃል ግን በሚያነሱት የጥራት መጓደል ምክንያት በሚፈለገው ልክ እየቀረበ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ ከ80 እስከ 90 በመቶ የገበያ መዳረሻዎች ጅቡቲ፣ ሶማሌና ሌሎች አጎራባች ሀገሮች ናቸው። የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ያለውም ወደነዚህ ሀገራት በመላክ ነው።

የሚሠሩ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው ያልተጠበቁ ነገሮችም ለዘርፉ ተግዳሮት እንደሆኑ አቶ አብደላ አንስተዋል። እርሳቸው እንዳሉት፤ ሀገሪቱን ከገጠማት የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በተለይም በአማራ ክልል የተመረተ የአቮካዶ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ተግዳሮት አጋጥሟል። የፀጥታ ስጋቱን መቅረፍ ካልተቻለ አምራቹ በድጋሚ ምርት ለማምረት አይነሳሳም። ምርቶቹም በባህሪያቸው ቶሎ ለብልሽት የሚጋለጡ በመሆናቸው ፈጥኖ ገበያ ላይ ማዋል ካልተቻለ ለኪሳራ ይዳርጋሉ። ይህም ሌላው ለአምራቹ ስጋት በመሆኑ ለማምረት አይበረታታም። እንዲህ አይነት ስጋቶችን መቅረፍ የሚቻለው ከአምራቹ ጋር ትስስር የሚፈጥሩ የዘርፉ ባለሙያዎንና በዚህ ላይ የሚሠሩትን በማሳተፍ ነው። ሀገራዊ መረጋጋትም ላይ እንዲሁ ከመንግሥት ጋር መቆም ይጠይቃል።

ሌላው የማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ከመያዝ ጀምሮ ፣ የማጓጓዣና የተለያዩ አስፈላጊ ነገሮች የማሟላት፣ ገዥዎችን መፈለግ፣ ሂደቶችን ማለፍ ይጠይቃል። ይህን ተከትሎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚጠይቀውን ዋጋ አለመክፈል ክፍተት ይስተዋላል። በጥራት የራስን መለያ ይዞ ለማምረት ጥረት ቢደረግ፣ የኢትዮጵያ ፍራፍሬ የተፈጥሮ (ኦርጋኒክ) በመሆኑ በውጭ ገበያ ተፈላጊ ነው። ጠንክሮ መሥራት ከተቻለ የመሸጫ ዋጋ ወጥቶላቸው ገበያ ላይ እንዲቀርቡ ማድረግ ይቻላል። አሁን ያለው የውጭ ገበያ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም። ያለውን በማጠናከር ክፍተቶችንም በማረትም መሥራት ነው የሚያዋጣው። አማራጩም ይኸው ነው። በኢትዮጵያ አቮካዶ ልማት ላይ የውጭ ባለሀብቶችም ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውንና ተስፋ ሰጪ ነገር መኖሩን አቶ አብደላ አመልክተዋል።

ሌላው መሠራት አለበት ያሉት የማስተዋወቅ ሥራ ነው። ምርቱን በተለያዩ ሀገራት ማስተዋወቅ እንደሚጠበቅና በዚህ ረገድም መሥራት ያለባቸው አካላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ነው የገለጹት። አምራቹ እንዲበረታታም በተሻለ ዋጋ የሚያቀርብበት ሁኔታ ላይም መታሰብ አለበት ብለዋል። መካከል ላይ ሆኖ የድለላ ሥራ የሚሠራውም ለዘርፉ እንቅፋት ነው። ዋጋ ከፍ በማድረግና ዝቅ በማድረግ በሚጫወቱት ሚና አምራቹንም ላኪውንም በማሳሳት ችግር ይፈጥራሉ። በዚህ ረገድም ቢሆን የጋራ ሥራ ይጠይቃል። ከዘርፉ የሚጠበቀውን ለማግኘት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን ሲወጡና በጋራ ሆነው ሲንቀሳቀሱ እንደሆነም አመልክተዋል። ግብርና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በዘርፉ ላይ በሚስተዋሉ ማነቆዎች ላይ በምክክር መድረክ ላይ በማንሳት መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ከውይይት በኋላም ቢሆን ማን ምን ሠራ የሚለውንም በመገምገም ሥራውን ለማስቀጠል ነው ጥረት እያደረገ የሚገኘው።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ በማብራሪያቸው፤ የአቮካዶ አትክልት በስፋት እያመረቱ ለገበያ የሚያቀርቡ ሀገሮች በርካታ ናቸው። ኢትዮጵያም የምትወዳደረው ከነዚህ አምራች ሀገራት ጋር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አቮካዶን ጨምሮ የተለያዩ ፍራፍሬዎች ባይመረቱ ኖሮ ከውጭ በግዥ ማስገባት ግድ ይሆን ነበር። በመሆኑም ምርት መጨመር ላይ ሥራ መሠራቱ ተገቢ ነው። ምርት በስፋት ሲመረት የሀገር ውስጥ ሸማችም በአነስተኛ ዋጋ የሚገዛበት እድል ይፈጠራል።

እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ማብራሪያ፤ አሁን ላይ የሀገር ውስጥ ፍላጎት እያደገ መጥቷል። ፍላጎት ሲያድግ በትንሽ ነገር ላይ የሚሻማው ሰው ይጨምራል። የብር መዋዠቅና የዋጋ ግሽበት ሲያጋጥም ደግሞ አምራቹ ወይንም ገበሬው የጉልበቱን ዋጋ ብቻ ሳይሆን የኑሮውንም ሁኔታ በማሰብ በከፍተኛ ዋጋ መሸጥ ይፈልጋል። ምርቱን ከገበሬው ተቀብሎ የሚሸጠውና በመካከል ላይ ያለው ደላላ ደግሞ ገበያውን ያንሩታል። ምርቱ ሸማቹ ጋር የሚደርሰው ከማምረቻው ስፍራ ብዙ ሰንሰለቶችን አልፎ ነው። እነዚህን ክፍተቶች ለማለፍ አማራጭ መፍትሄ የሚሆነው ምርት በስፋት በማምረት ነው።

የኢትዮጵያ የህዝብ ብዛት ከአንድ መቶ ሰማኒያ ሚሊዮን በላይ መድረሱንና በዚያው ልክም የተጠቃሚው ቁጥር ማደጉን የጠቆሙት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤የሀገር ውስጥ ገበያ እየተሻማ ያለው ከውጭው ገበያ ጋር እንደሆነ አመልክተዋል። እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ አንዳንድ አትክልት አምራች ሀገሮች የሚያመርቱት አቮካዶም ሆነ ሌሎች አትክልቶችን በሰፋፊ የእርሻ መሬት ላይ በኢንዱስትሪ ደረጃ ነው። በስፋት በማምረታቸው የመሸጫ ዋጋቸውም አነስተኛ ነው። በማምረት ሂደትም ቢሆን ያላቸው ተሞከሮ በመልካም የሚገለጽ ነው። እያንዳንዱ ገበሬ በተለያየ የግብርና ሥራና ውጤት ለመታወቅ ጥረት ያደርጋል። ለአብነት ከአትክልትና ፍራፍሬ በአቮካዶ ልማት ብቻ ፤ በማር፣ በቅቤ፣ በከብት ሀብት ልማት እና በሌሎችም እራሱን በሚያሳውቅ መልኩ ይንቀሳቀሳል።

እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ተሰብስቦ ለውጭ ገበያ እየቀረበ ያለው እያንዳንዱ ገበሬ ለእለት ጉርሱ ከሚያምርተው ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ በመጀመሪያ በማምረት ላይ ትኩረት መደረግ አለበት። እንደመንግሥት በስንዴ ልማት ላይ እንደተያዘው አቅጣጫ በሁሉም የግብርና ሥራዎች ላይ በተመሳሳይ መተግበር ይኖርበታል። ምርት እንዲያድግ ባለሀብቱንም ማሳተፍ ይገባል። ምርት ሲትረፈረፍ ገበያው ላይም ተጠቃሚ መሆን ይቻላል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ስኳር ለውጭ ገበያ ይቀርብ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ አሁን ላይ ያሉት ስኳር ፋብሪካዎች ቀድሞ የተቋቋሙ በመሆናቸው እንኳን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሀገር ውስጥን ፍላጎትንም ለማሟላት አዳጋች ሆኖ በግዥ ከውጭ እየመጣ እንደሆነ ይገልፃሉ። እንዲህ ያሉ ችግሮችን ማስቀረት የሚቻለው በሀገር ውስጥ ልማቱ ላይ ጠንክሮ በመሥራት እንደሆነ ምክረሃሳብ ሰጥተዋል።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንዳሉት፤ አሁን ባለው መረጃ አጠቃላይ የኢትዮጵያ የወጭ ንግድ ከአራት ቢሊዮን ብር በታች ነው። ይህ የሚያሳየው ሰፊ ሥራ እንደሚጠበቅ ነው። እየተመረተ ያለው የምርት መጠንና የህዝቡ ብዛት፣ ከፍላጎት ጋር ይጣጣማል ወይ የሚለውንም ማየት ያስፈልጋል። ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ጥረት መደረግ ያለበት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት ሳይቻል ነው።

የውጭ ባንኮችን በሀገር ውስጥ እንዲሠሩ ማድረግም ሌላው አማራጭ ነው። ባንኮቹ ካፒታል ይዘው ስለሚገቡ የሚስተዋለውን የውጭ ምንዛሪ ጫና ለመቀነስ ያግዛል። በአሁኑ ጊዜ በመቋቋም ላይ ያለው የካፒታል ሥርዓት ገበያም ሥራ ሲጀምር ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ በምትልከው ላይ ተጽእኖ ስለሚኖረው አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲን በመፈተሽ መተግበር ያስፈልጋል።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ሌላው ያነሱት፤ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ፍላጎቱ እስካለ ድረስ ከዓለም ኢኮኖሚ ውጭ መሆን እንደማይቻል ነው። ቀድመው መሠራት ያላባቸው ሥራዎች እንዳሉም አመልክተዋል። እርሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ላይ በውጭ ምንዛሪ በኩል ተግዳሮት እየሆነ ያለው ገበያውን መቆጣጠር አለመቻል ነው። በዚህ ወቅት የውጭ ምንዛሪውን እየመራው ያለው የጥቁር ገበያው ነው። ይህን ችግር መንግሥት ብቻውን እንዲፈታው መጠበቅ የለበትም። ከአምራቾች፣ ከላኪዎችና ከሸማቾች እንዲሁም ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማህበራት፣ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ያስፈልጋል።

ዓለም አንድ መንደር እየሆነ በመጣበት በዚህ ወቅት፤ የፋይናንስ ፖሊሲን መከተልም ችግር እየሆነ ነው። የሌላው ዓለም የፋይናንስ ፖሊሲ ችግር ሲገጥመው ኢትዮጵያ ላይም ጫና ያሳድራል። ችግሩን ለመፍታት ሁሉም የየድርሻውን እስካልተወጣ ድረስ ጥቁር ገበያው እየመራ መሄዱ አይቀሬ ነው። ሀገር ሕጋዊ የሆነ ገንዘብ እንድታገኝ፣ የልማት እቅዶችንም ለማሳካት በተግዳሮቶች ላይ ተወያይቶ የጋራ መፍትሄ ይጠበቃል ሲሉም ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አሳይተዋል።

አቶ አብዳለም ሆኑ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላትም ሆነ በውጭ ገበያው ተወዳዳሪ ለመሆን ቀድመው መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን  መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You