የውሃ ማሞቂያን በተኪ ምርት

ወጣት አዲሱ ባዬ ይባላል። የጎንደር ከተማ ነዋሪ ነው። የውሃ መስመር ዝርጋታ ባለሙያ ሲሆን በሥራው ከውሃ ጋር ከሚገናኙ ማቴሪያል (ቁሳቁስ) ጋር የቀረበ ግንኙነት አለው። የውሃ መስመሮች ዝርጋታ ሲዘረጋ በአብዛኛው ከሚገጥሙት ችግሮች ውስጥ አንዱ ከውጭ ሀገር የሚመጣው የውሃ ማሞቂያ (ቦይለር) ብልሽት እንደነበር ያስታወሳል።

ታዲያ የተበላሸ የውሃ ማሞቂያ (ቦይለር) ሲፈለግ ቁሱን ፈታትቶ መልሶ ለመጠገን የሚያደርገው ጥረት አድካሚና ፈታኝ ሆኖበት ይቸገራል። ለጥገና የሚያስፈልጉት ቁሳቁስ በቅርበት አለመገኘታቸውና የውሃ ማሞቂያ ዋጋ ውድ መሆኑ በእጅጉ እያሳሰቡት ይመጣሉ። ከውጭ የሚገባውን የውሃ ማሞቂያ ፈትቶ መጠገኑ ቀላል የማይባል ፈተና የደቀነበት ወጣት አዲሱ፤ ለእዚህ ችግሮች መፍትሔ ፍለጋ ማሰላሰል ውስጥ ይገባል። ሁኔታው ‹‹ የውሃ ማሞቂያ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ቁሳቁስ መስራት ቢቻል ኖሮ ይህ ሁሉ ፈተና አይገጥመኝም ነበር›› ብሎ በጥልቀት እንዲያስብበት ምክንያት ሆነው።

ከውጭ የሚገባውን የውሃ ማሞቂያ በመፈታታት በውስጡ ያሉ ነገሮች ሲመለከት እነዚህን ቁሳቁስ በሀገር ውስጥ ባለው ቁሳቁስ የመተካት ፍላጎት አደረበት። ይህንን ፍላጎቱና ጉጉቱን ከግብ ለማድረስ ባደረገው ጥረትም ያሰበውን ማሳካት ቻለ። በሀገር ውስጥ የሚገኙ ቁሳቁስን በመጠቀም የውሃ ማሞቂያ (ቦይለር) መስራት ችሏል።

‹‹የፈጠራ ሥራው የሆነው የውሃ ማሞቂያ ቦይለሩ በኢትዮጵያ ጥራትና ደረጃዎች ኤጀንሲ የጥራት ደረጃው ተፈትሾ የጥራት ማረጋገጫ ተሰጥቶታል›› የሚለው አዲሱ፤ ይህ የፈጠራ ሥራ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ይጠቁማል። በተለይ ከውጭ ሀገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከሚገባው የውሃ ማሞቂያ ጋር ሲነጻጸር የሚሰጠው አገልግሎት ላቅ ያለ እንደሆነ ይናገራል።

አዲሱ እንደሚለው፤ ይህ የፈጠራ ሥራ ከውጭ ሀገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የውሃ ማሞቂያ/ ቦይለር/ የሚተካ ነው። ከውጭ ከሚገባው የውሃ ማሞቂያ የተሻለ የቆይታ ጊዜ አለው፤ በቀላሉ የሚበላሽ አይደለም። ዋጋውም በጣም ተመጣጣኝ ነው።

በሀገር ውስጥ የሚመረተው ይህ የውሃ ማሞቂያ ለመታጠቢያ ቤት የሚያገለግል ነው። በተለይ በየቀኑ በመታጠብ ንጽህናን የመጠበቅ ባህላችንን እንዲጨምር በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና አለው ይላል። አንዳንድ ሰዎች ገላቸውን ላለመታጠብ የውሃውን ቀዝቃዛ መሆን ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡ መሆኑን የሚጠቅሰው አዲሱ፤ ይህን የውሃ ማሞቂያ ቢጠቀሙ ግን ችግራቸውን መቅረፍ እንደሚቻል ይናገራል። በተለይም ደግሞ በቀዝቃዛማ አካባቢዎች፤ በተራራማ አካባቢዎች ላይ ተመራጭ መሆኑን ነው የሚገልጸው።

እሱ እንዳለው፤ ከውጭ የሚመጣው የውሃ ማሞቂያ /ቦይለር/ በየጊዜው ይበላሻል፤ አስቸኳይ ጥገና አግኝቶ አገልግሎት ለመስጠት የማይቻልባቸው ሁኔታዎችም አሉ። ለጥገና የሚያስፈልጉ ቁሳቁስን በቀላሉ ለማግኘት ያስቸግራል። ይህም ብዙ ሰዎች እንዳይጠቀሙት እያደረገ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም ዋጋው ውድ ስለሆነ ማንኛውም ሰው እንደፈለገው ማግኘት እንዳይችል ያደርገዋል።

ከውጭ ሀገር የሚገባ ማሞቂያ ዋጋው ሰባት ሺ ብር እና ከዚያ በላይ መሆኑንም ጠቅሶ፣ በሀገር ውስጥ የተመረተው ግን የሦስት ሺ አምስት መቶ እና የአምስት ሺ ብር የዋጋ ተመን የወጣለት ነው። የውሃ ማሞቂያዎቹ ዋጋ እንደአይነታቸው፣ ደረጃቸውና መጠናቸው ይለያያል። በሀገር ውስጥ የሚመረተው የውሃ ማሞቂያ የተለያየ አይነት ሲሆን፣ ለሆቴሎች፣ ለመኖሪያ ቤቶች (ለመታጠቢያና ለማዕድ ቤት) ተብለው ተለይተው የሚመረቱ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ከውጭ የሚገባ የውሃ ማሞቂያ ኤሌክትሪኩን አንድ ጊዜ ከተለኮሰ ሰው ኖረውም አልኖረውም ውሃውን ሁልጊዜ ያሞቃል። አዲሱ የፈጠራ ውጤት የሆነው የውሃ ማሞቂያ ግን ሰው እንዲለኩሰው ሳይፈልግ ውሃው በተፈለገ ጊዜ እንዲሞቅ በማድረግ ዝግጁ ያደርጋል። ውሃው ሲቀዘቅዝ ወዲያወኑ በራሱ /አውቶማቲካሊ/ በማሞቅ ያዘጋጃል።

በሥራ ላይ ከሚገጥሙት ችግሮች ተነስቶ ለችግሩ መፍትሄ የሚሆን የፈጠራ ሀሳብ እንደሚያመነጭ የሚገልፀው ወጣት አዲሱ፤ የውሃ ማሞቂያ (ቦይለር) የመስራት ሀሳቡን ካመነጨ በኋላ ከእህትና ከወንድሙ (ሰላማዊት ባዬ እና ዮሐንስ ባዬ) ጋር በመመካከር በማምረቱ ስራ በመሳተፍ በጋራ መስራታቸውን ይናገራል። የፈጠራ ሥራ ለመስራት ሙከራ ሲያደርግ እህትና ወንድሙ ከጎኑ ሆነው ሀሳቡን በመደገፍ፣ የራሳቸውን ሀሳብ በመጨመር የፈጠራ ሙያውን እንዲያዳብር እገዛ ሲያደርጉ እንደነበር ያስታውሳል። እህቱና ወንድሙ ለሥራው ውጤታማነት ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሶ፤ የፈጠራ ሥራው ዳብሮና አድጎ የውሃ ማሞቂያ ሊፈጥር መቻሉንና ሥራው የቤተሰብ የፈጠራ ሥራ ነው ማለት እንደሚቻል ይናገራል።

እነ አዲሱ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራውን የውሃ ማሞቂያ ከሰሩ በኋላ የፈጠራ ሀሳባቸውን ይዘው ሦስቱ (አዲሱ ባዬ፤ ሰላማዊት ባዬ እና ዮሐንስ ባዬ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባዘጋጀው የብሩህ ተስፋ የፈጠራ ውድድር ላይ ተወዳድረው የ2014 ዓ.ም አሸናፊም ሆነዋል።

ብሩህ ተስፋ ውድድር ላይ ተሳትፈው ካሸነፉ በኋላ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተጻፈላቸውን የድጋፍ ደብዳቤ ይዘው በጎንደር ከተማ የመስሪያ ቦታ ጠይቀው ማግኘት ችለዋል። በውድድሩ ላይ ባገኙት የገንዘብ ድጋፍ ላይ በመጨመር ሥራቸውን አሃዱ ብለው ጀምረዋል። አሁን ላይ ሥራቸውን አስፋፍተው ለመስራትና ምርቶቹን ለሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች በሚዳረስ መልኩ ለማምረት የሚያስችሏቸውን ሁኔታዎች እያመቻቹ ናቸው። ለዚህ የብድር አገልግሎት አግኝተው ሥራቸውን ለማስፋፋት የሚያስችላቸውን ድጋፍ የሚያገኙበትን አማራጭ ከልማት ባንክ እየተጠባበቁ መሆኑን ወጣት አዲሱ ይናገራል።

እነሱ የፈጠራ ሥራን መስራት ብቻ ሳይሆን እንዴት ማሻሻል ይቻላል በሚለው ላይ በጥልቀት አስበውና አተኩረው እንደሚሰሩ ወጣት አዲሱ ይናገራል። በዚህ የተነሳ በኤሌክትሪክ የሚሰራውን የውሃ ማሞቂያ ከሰሩ በኋላ ሌላ በሶላር የሚሰራ አዲስ የፈጠራ ሥራ መስራታቸውንም ይገልፃል።

እሱ እንዳለው፤ ይህ አዲሱ የፈጠራ ሥራም (በሶላር ብቻ የሚሰራ የውሃ ማሞቂያ) በአሁኑ ጊዜ ተመርቶ በገበያ ላይ ውሏል። ሥራው አዲስ ቢሆንም፣ በህብረሰተቡ ዘንድ ተፈላጊነቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። የህብረተሰቡን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግም ምርቱ ለህብረተሰቡ እንዲደርስ በስፋት ለማምረት ጥረት እየተደረ መሆኑን ይናገራል። በተለይ ለህብረተሰቡ የመታጠቢያ ቤት (ሻወር) አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች ማሞቂያውን ገዝተው እየተጠቀሙት ነው ብሏል።

‹‹ህብረተሰቡ የውሃ ማሞቂያውን ስለወደደው ገዝቶ እየተጠቀመበት ነው›› የሚለው አዲሱ፤ ‹‹ከውጭ ከሚመጣው ይልቅ የሀገር ውስጡ የሚመረጥበት የራሱ ምክንያት እንዳለውም ይናገራል፤ ‹‹ከውጭ የሚመጣው ለእኛ ሀገር የሚሆን አይደለም። የእኛ ሀገር ውሃ ኃይል የሌለው በመሆኑ ቦይለሩ ቶሎ ቶሎ ይቃጠላል፤ የውሃ ግፊት ይፈልጋል። በሀገር ውስጥ የተሰራው ግን ውሃው ግፊት ባይኖረውም እንኳ ማሞቂያው እንዳይቃጠል አድርገን ነው የሰራነው›› ይላል።

በአሁኑ ወቅት በኤሌክትሪክ የሚሰራና በሶላር የሚሰራ የውሃ ማሞቂያ ሰርተው እያመረቱ ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ። ለጥገና የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ እና የአጠቃቀም መመሪያም ጭምር ከማሞቂያው ጋር አብሮ ይሰጣል፤ ጥገና ሲያስፈልገውም የጥገና አገልግሎቱ በእነ ወጣት አዲሱ ድርጅት ባለሙያዎች እንደሚሰጥ የፈጠራ ባለሙያው ይናገራል።

ምርቶቹን አምርተው ገበያ ላይ ማዋል ከጀመሩ ሁለት ዓመት የሆናቸው ሲሆን ለ14 ሰዎችም የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል። በቀጣይም በኮንስትራክሽ ዘርፍ ብዙ ችግር ያለባቸውን ቁሳቁስ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል መፍትሔ ለማምጣት ጥረት እንደሚያደርጉና በስፋት እንደሚሰሩ ነው አዲሱ የሚናገረው።

የውሃ ማሞቂያውን ‹‹ማራኪ የኮንስትራክሽን ውጤቶች ማምረቻ ኃላ/የተ/የግ/ማ›› የተሰኘ ድርጅት ከፍተው እያመረቱ ሲሆን፣ ሁለቱም አይነት የውሃ ማሞቂያዎች በጎንደር ከተማና በዙሪያው በስፋት እየተሸጡ ናቸው። ምርቶቹ በአዲስ አበባ ከተማ እየተሸጡ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ምርቶቹን ወስደው የሚያከፋፍሉ ባለሱቆች መኖራቸውንም ነው የሚናገረው። ምርቶቹ በሌሎች አካባቢዎች እንዲዳረሱ ለማድረግ በማህበራዊ ሚዲያ በማስተዋወቅ ላይ እንደሆኑም አዲሱ ይናገራል።

‹‹በሀገሪቱ የፈጠራ ሥራ ገና ያልተነካ ሥራ ነው። አሁን ላይ እንደምናየው በአብዛኛው እየተሰሩ ያሉት ተመሳሳይ ናቸው፤ አንዱ የሚሰራውን ነው ሌሎች የሚሰሩት፤ ምንም የሚያሻሽሉት የለም። መሻሻል ያለበትን ማሻሻል ይገባል። በትኩረት ብናስብ በጣም ብዙ ነገሮችን መፍጠር እንችላለን። ›› ሲል ያስገነዝባል። ‹‹አብዛኞቻችን የማሰብ አቅማችንን እየተጠቀምንበት አይደለም። በጥልቀት በማሰብ የረዘመውን ማሳጠር፤ የተወደደውን በተመጣጠኝ ዋጋ እንዲገኝ ማድረግ፣ ገበያ ላይ የሌለውን እንዲኖር ማድረግ የሚያስችል ሰፊ እድል መፍጠር እንችላለን፤ ያለንን ብንጠቀምበትና አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር ልምድ ብናደርገው ብዙ መስራት እንችል ነበር›› ይላል።

ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ‹‹በውሃ መስመሮች ዝርጋታ ላይ ስሰራ በገጠመኝ ችግር የተነሳ ለችግሩ መፍትሔ ለማግኘት ያደረኩት ጥረት የመፍትሔ ሀሳብ አስገኝቶልኛል፤ ከችግሮች ጋር አብሮ መኖር አልወድም፤ ችግሮች ሲኖሩ ለምን መፍትሔ ማምጣት አንችልም በማለት መፍትሔ ላይ ትኩረት በማድረጌ ለውሃ ማሞቂያው ችግር መፍትሔ ለማምጣት ያደረግኩት ጥረት ተሳክቶልኛል›› ይላል።

የፈጠራ ባለሙያዎች የፈጠራ ሥራዎች ለመፍጠር ቢፈልጉ እንኳን ሙከራ የሚያደርጉበት የመሞከሪያ ቦታ የላቸውም የሚለው አዲሱ፤ በቀጣይ ኢንኩቤሽን ማዕከል በመክፈት የፈጠራ ባለሙያዎች ሥራዎችን የሚሞክሩበት ቦታ እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁሟል።

‹‹ሀገራችን ብዙ ችግሮች አሉባት፤ ለእነዚህ ችግሮቿ ደግሞ መፍትሔ ትሻለች። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሁሉም ያለው በእጃችን ነውና በተለይ ወጣቱ ትውልድ የፈጠራ ክህሎቱን ተጠቅሞ የመፍትሔ ሀሳብ ለማመንጨት መትጋት ይጠበቅበታል›› ሲልም ያስገነዝባል። ‹‹ለችግሮቻችን መፍትሔ ለማበጀት የሚችል ብዙ ወጣት ትውልድ አለን፤ ግን እየሰራን አይደለም። በአካባቢያችን ብዙ ችግሮችና ያልዘመኑ ነገሮች ስላሉ በርትተን ለመፍትሔ መትጋት ከሁላችንም ይጠበቃል›› ይላል።

ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ እንደሚለው፤ አሁን ላይ አብዛኛው ጥቅም ላይ የሚውሉ ነገሮች ኋላቀር በመሆናቸው ማዘመን ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በርትተን መስራት ይጠበቅበናል። በተለይ ወጣቶች ከተለያዩ የሥራ መስኮች ተመርቀው ሥራ በመፈለግ ጊዜያቸውን መጨረስ የለባቸውም። የፈጠራ ክህሎታቸውን ተጠቅመው ሀሳብ አመንጭተው ሥራ ፈጣሪ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

‹‹የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች፣ ለምሳሌ ዩቲዩብ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደምንችል በምንፈልገው ሀሳብ ይረዱናል፤ እነሱን ተጠቅመን ለሀገራችን ለአካባቢያችን ችግሮች የመፍትሔ ሀሳብ ማመንጨት እንችላለን›› ሲል ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ አዲሱ ባዬ ምክረ ሀሳቡን ይለግሳል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን  መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You