ዛሬን እያሳጡን ያሉ የፖለቲካ ስንክሳሮቻችን

ሀገራችን ኢትዮጵያ በበርካታ ፈተና በተሞላበት ታሪካዊ ሂደት ያለፈች ሀገር ናት። ችግሮቿም መጠነ ሰፊና አድማስ ተሻጋሪ ናቸው። ሀገሪቱ ረጅም የመንግሥትነት ታሪክ ባለቤት ብትሆንም በየዘመናቱ በውስጥና በውጭ ጠላቶቿ ያልተፈተነችበት ጊዜ የለም። ዘመናዊ ፖለቲካን ጀምረናል ከሚባልበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ፖለቲካው ጤናማ ሆኖ አያውቅም። ያለን ታሪክ በአብዛኛው የሥልጣን ሽኩቻ ታሪክ ነው። ያለን ታሪክ የጦርነትና የግጭት ታሪክ ነው።

በተለያዩ ጊዜያቶች ሥልጣን ላይ ሲወጡ የነበሩ መሪዎች ሥልጣንን ማህበረሰብን ወደተሻለ ቦታ ማድረሻ መሣሪያ አድርጎ ከማሰብ ይልቅ ጤናማ ባልሆነ መንገድ ማዋላቸውና በአፈሙዝ ማመናቸው በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ እንዲያገነግን ምክንያት ሆኖ በተደጋጋሚ ታይቷል። ይህ ደግሞ በተለያዩ ጎራዎች በተሰለፉ ዜጎች መካከል ሲፈጠሩ ለነበሩና እስካሁንም ድረስ ለዘለቁ ግጭቶችና አለመግባባቶች አንዱ መነሻ ሆኖ ሕዝባችንን ትልቅ ዋጋ አስከፍለውታል።

በዚህ ላይ ደግሞ አግባብነት ባለው መልኩ ሳይፈቱ ከዘመን ዘመን እየተንከባለሉ የመጡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ስንክሳሮቻችን ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲያገኙ ባለመደረጉ ሀገሪቷ የቀደመ አኩሪ ታሪኳን የሚመጥን እድገት ሳይኖራት፣ ሕዝቡም የረባ እፎይታ ሳያገኝ አሁን የምንገኝበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።

በትውልድ ሽግግሮች የተፈጠሩት የፖለቲካ ቀውሶችና ውጥንቅጦች ረግበው ሕዝቡን በላዩ ላይ ከተጫነው መከራና ስቃይ እፎይ ከማሰኘት ይልቅ ቀን በገፋ ቁጥር ችግሮቹ በይበልጥ ገዝፈውና ተወሳስበው ወደ ግጭትና መጠፋፋት እየወሰዱ የኢትዮጵያ ልጆች ደም በከንቱ እንዲፈስ፣ የወጣቶች ውድ ሕይወት እንዲቀጠፍ፣ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች ያለ ልጅ፣ ያለጧሪና ቀባሪ እንዲቀሩ፤ የእናቶች እንባ እንዲረግፍ ማድረጋቸው ጥሬ ሀቅ ነው። በዚህ መልኩ ሕዝቡ ተነግሮ የማያልቅ በርካታ ፍዳ አይቷል።

በማኅበረሰቡ ዘንድ ግጭት ያስከትላሉ ለሚባሉት የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የልማት፣ የሰብአዊ መብት፣ የመልካም አስተዳደር…ጥያቄዎች አፋጣኝና ፍትሀዊ ምላሽ ሳያገኙ መቅረት ወደ ብሶት አድጎ ሲከሰቱ የነበሩት ግጭቶች፣ ንትርኮችና አለመተማመኖች፣ መሳደድ፣ መገዳደል፣… የየወቅቱ ፖለቲካ ዋና መገለጫ ሆኖ የሀገሪቱ እድገት ወደ ኋላ እንዲጎተት ምክንያት ሆኗል። የዚህ ሁሉ መንስኤው ኋላቀር የፖለቲካ ባህላችን የወለደው ከሕግ በላይ የመሆን ክፉ ልማድና በአፈሙዝ የማመን አባዜ ነው።

ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ሁላችንም የኖርንበት ሕይወትና የመጣንበት መንገድ የሚያሳየን ነገር ፖለቲካው ‹‹የሰጡህን ብቻ ተቀበል›› በሚለው አምባገነናዊ የአስተዳደር ዘይቤ የተቃኘ መሆኑን ነው። በተጨማሪም ፖለቲካችን የጥቂቶችን ፍላጎት ብቻ ይዞ የመሮጡ ነገር ያለና ዛሬም ድረስ ሊቆም ያልቻለ እውነት ነው። ፖለቲካችንን የወል ማድረግ ተስኖናል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሴራ፣ መጠላለፍና መገፋፋት፣ አለመተማመን፣ አለመደማመጥ፣ ከትብብር ይልቅ ሽኩቻ፣ መበቃቀል፣ «እኔ እበልጥ»፣ «እኔ እበልጥ» ፉክክር፣ መሸናነፍ፣ መገዳደል፣ ሁሉን ነገር መቆጣጠር፣ ቃልአባይነት…ወዘተ ዋና ዋና መገለጫዎቹ ናቸው ማለት ይቻላል።

መቻቻልና መደማመጥ ባልተለመደበት በዘመነ ደርግ ፖለቲካ «የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ኀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ» እንዲል ብሂሉ ወንድም ወንድሙን ገድሎ ግዳይ እንደጣለ ጀግና በ «ፍየል ወጠጤ…» ዜማ ፉከራ የተፎከረበትን ጊዜ እንደዋዛ አልፈናል።

በተለያዩ ጊዜያቶች የነበረው የፖለቲካ ሂደት በፈጠረው የአመለካከት (የርዕዮት ትርክት) ልዩነት ሰበብ በርካታ ዜጎች እንደ ጠላት ተፈርጀው ለእስር፣ ለእንግልት እና ለግድያ ተዳርገዋል። የአንድ ቤተሰብ አባላት በአመለካከት ልዩነት ምክንያት ብቻ በጠላትነት ተፈራርጀው በነፍስ እስከመፈላልግ ደርሰዋል። ሀገር የምትመካባቸው በርካታ ምሁራን በየአደባባዩ በጥይት ተቆልተው ሀገሪቱን እንደ ትውልድ ወደኋላ የጐተተ ምሁር አልባ እንድትሆን አድርጓታል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ከስክነት የራቀው ፖለቲካ የሚያመጣው ጣጣና መዘዝ አስግቷቸው «ፖለቲካና ኮረኒቲ በሩቁ» በሚል ብሂል ለሀገራቸው ፖለቲካ ባይተዋር ወይም የበዪ ተመልካች ሆነው እንዲቆዩ ተገደዋል። ይህ በማኅበረሰቡ ፖለቲካ ባህል ላይ እስካሁን ድረስ ያልሻረ መጥፎ ጠበሳ ጥሎ አልፏል። ይህንን ሁላችንም ማስቀረት እንችልና ይገባንም ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ግን ፖለቲካውን ጨከን ብለን የጋራ ማድረግ አልቻልንም።

እንደምናውቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ፤ አኩሪ ባህል፤ ታሪክ እና እሴቶች ባለቤት ናት። ሕዝቦቿ ከነጉድለታቸው ተሳስበው፣ ተከባብረው፣ ተቻችለውና ተፈቃቅረው ለዘመናት ሕይወትን በጋራ ኖረዋል። የወግ፣ የትውፊት እና የባህል ትስስራችንም ላይለያይ አንድ ሆኗል። አንዳችን ካንዳችን ተዛምደን ተጋምደናል።

ከዚህ ጎን ለጎን ለዘመናት የተነሱነብንን የውጭ ጠላቶች ዘር ጎሳ ሳይለያየን በጋራ ወኔ ድል አድርገን መልሰናቸዋል። ወርቃማው የዓድዋ ድልን ጨምሮ ፣ የኦጋዴን፣ የካራማራ…የጦር ሜዳ ገድሎች በዘር ጎሳ ሳንለያይ ድል ያስመዘገብንባቸው የጋራ እሴቶቻችን ማሳያ ናቸው።

ሆኖም ግን ከላይ የጠቃቀስኳቸውን አብረውን ለዘመናት የቆዩትን በርካታ እሴቶች፣ ባህሎችና ትውፊቶቻችንን ያላሉብን የፖለቲካ ችግሮች ለማከም ተጠቅመንባቸዋል ብዬ አላስብም። ፊደል ቆጥረናል ተምረናል የሚሉት አብዛኞቹ የፖለቲካ ተዋንያን/ ልሂቃን ሳይቀሩ ለዴሞክራሲ ባህል ባይተወር ናቸው።

እነርሱ ጋር ዴሞክራሲ በቃል እንጂ በተግባር የለም። መወያየት፣ መነጋገር መመካርን… እንደ ግጭት መፍቻ መሣሪያ ከማሰብ ይልቅ እንደ ሽንፈት የመቁጠሩ ሁኔታ ተለምዷል። የዴሞክራሲ እሴቶች በሚፈለገው ሁኔታ አልዳበሩም። ይህ ደግሞ የምንፈልገውን ዓይነት ኅብረተሰብ ሊፈጥርልን አልቻለም። አሁን እያጨድን ያለነው የዚህን ፍሬ ነው።

አንዳንዴ ሳስበው «የኢትየጵያ ሕዝብ ቅኔ ነው» የሚለው አባባል በብዙ ሁኔታ እውነትነት አለው። ለምሳሌ በአንድ በኩል የተነሱብንን የውጭ ጠላቶች በጋራ መክተን ሀገርን ጠብቆ የማቆየት አኩሪ እሴት ሲኖረን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የራሳችን ጠላት እኛው፣ የራሳችን ፀሮች እኛው ሆነን እርስ በርስ የተጎዳዳንበት፣ የተገዳደልንበትና የተጠፋፋንበት ጊዜ መብዛቱ ያስገርማል።

የውጭ ጠላትን በጋራ መክተን ያቆየነውን የነፃነታችንን ፍሬ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል፣ የመቻቻልና የመከባበር ባህልን ለመገንባት… አልተጠቀምንበትም። ይህ በእጅጉ ያሳዝናል፤ ያስቆጫልም።

በእኔ እምነት ያልተላቀቀን የድህነታችንና የኋላቀርነታችን ትልቁ ምክንያት በተለያዩ ሰበቦች የምናካሂዳቸው ደም አፋሳሽ ግጭቶችና ጦርነቶች ናቸው። ከዚህ ችግራችን አልተማርንም። እንዳልተማርን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየናቸው ያሉት ነገሮች በቂ ማሳያዎች ናቸው።

አርባ እና ሃምሳ አመት ሙሉ አንድ ዓይነት ስህተት እንዴት እንሳሳታለን? ከስህተታችን ትምህርት ወስደን እንዴት መሻሻል አቃተን? ዓለም ሁልጊዜም በለውጥ ሂደት ውስጥ ነች። ይሄውም ከጨለምተኝነት ወደ ተስፈኝነት፣ ከአይቻልም ባይነት ወደ ይቻላል ባይነት፣ ከስሜታዊነት ወደ ምክንያታዊነት፣ ከኋላቀርነት ወደ ሥልጣኔ፣ ከድህነት ወደ ብልጽግና፣ ከአሮጌው ወደ አዲሱ ተስፋ፣ ከኋላቀር ወደተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት…. ወዘተ የሚወስደን ጉዳይ (ጎዳና) ነው።

ከዚህ አኳያ የዛሬው ፖለቲካ ከትናንቱ ካልተሻለ ምን ለውጥ አመጣን? ከመተባበር ይልቅ መገፈታተርን፣ ከመደጋገፍ ይልቅ መጠላለፍን፤ ከአብሮነት ይልቅ ልዩነትን ካራገብን ምን የአስተሳሰብ ወይንም የባህሪ ለውጥ አመጣን? ትውልዱ የሚራገቡ ሀሰተኛ ትርክቶችን በሰከነ መንፈስና በብስለት ሳይፈትሽ ያንኑ ከደገመ ምኑን ወደፊት ተራመድን? የጀግንነት ውሃ ልክን ከጦር አውድማ፣ ከትጥቅ ትግል፣ ከመበቃቀል፣ …ጋር ብቻ የምናያይዝ ከሆነ ምኑን ጊዜ ተለወጠ ?

የተመላለስንበትን የተጣመመ መንገድ አቃንተን በሁሉም መስክ እንደሌሎች በርካታ ሀገሮች ማደግና መለወጥ ተስኖናል። ባጭሩ ኢትዮጵያ ከአንድ የፖለቲካ አዙሪት ወደሌላው እየገባች ዜጎች ከዛሬ ነገ ይሻል ይሆን በሚል ተስፋ የሰቀቀን ኑሮ የሚገፉባት ሀገር ሆና ኖራለች። ላለፉት አርባ እና ሃምሳ አመታት የሀገራችን ፖለቲካ ያሳየን ነገር ይሄንኑ እውነታ ነው። ለእኔ የ «እንዘጭ- እንቦጭ »ፖለቲካ ሲባል ትርጉሙ ሌላ ሳይሆን እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ይመስለኛል።

ፖለቲካው በኖረበት አዙሪት እንዲቀጥል ስለፈቀድንለት ጦሱ አሁንም አልለቅም ብሎናል። የሚያንገላታን ፖለቲካዊ ትብታብ አልበቃ ብሎ ተጋግዘንና ተደጋግፈን ያሳለፍነውን የጋራ ታሪክ ዘንግተን አሁን ደግሞ ለያዥ-ለገናዥ እያስቸገረ ላለ ፉክክር ተጋልጠን በመገፋፋት እና በመጠፋፋት ላይ ተጠምደናል። በጎራ ስም የመቧደን በሽታም ዋና መለያችን ከሆነ ሰነባብቷል።

ካለፉት አራትና አምስት አመታት ወዲህ ኢትዮጵያዊ እሴታችንን የሚሸረሽሩ እና የቆየውን አብሮነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ በርካታ እኩይ ተግባራት ገጥመውናል። የባንዲራ ትርክት፣ የበዳይ ተበዳይ ትርክት፣ ልዩነትን የማጉላት ፖለቲካ፣ ጥላቻን ማቀንቀን…ወዘተ የየዕለቱ routine የፖለቲካ ክስተት መሆኑን ቀጥሏል። እነዚህ ሁኔታዎች በየቦታው ካለው ዱለታ፣ ፉከራ፣ መገፋፋት፣ ፉክክር፣ የመጠፋፋት እሳቤ…ወዘተ ጋር ተደማምረው ሀገርንና ሕዝብን ወደማያስፈልግ አቅጣጫ እየገፉ ነው።

በአሁኑ ሰዓት በነባሩ የፖለቲካ ችግራችን ላይ ተደርቦ ስንተኛም ሆነ ስንነሳ ለስጋትና ለሰቀቀን እየዳረገን ያለው ዋና ጉዳይ ሀሰተኛ ትርክት ወይም የጥላቻ ንግግር ነው። አሁን አሁን በሕዝብ ውስጥ ችግር ሳይኖር ችግር እንዳለ አድርገው የሚያራግቡ እንዲሁም ትናንት የነበሩ ትርክቶችን ከተገቢው በላይ በማጎን ማኅበረሰቡን ለአመጽና ለብጥብጥ የሚያነሳሱ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ አካላት እየተበራከቱ መጥተዋል።

ከትንሽ እስከ ትልቅ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ…. የዲጂታልና ሜይንሰትሪም ሚዲያን በመጠቀም የውሸት ትርክትና የጥላቻ ንግግር ፈብራኪ ሆኗል። «ሊሂቁ» አለኝ የሚለውን ጥያቄ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ አምጥቶ መወያየት አይደፍርም። መደማመጥ፣ መከባበር የለም። ይህ የተለመደ ክስተት( trend) ከመሆኑ ባሻገር ነውርነቱ እየቀረ መጥቷል።

በዚህም ምክንያት እነዚህ አካላት የፖለቲካ ፍላጐታቸውን ለማስፈጸም የእኔ ብሔር አባል ነው የሚሉትን ማኅበረሰብ እንዳሻቸውና በፈለጉት አቅጣጫ በመጋለብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር እንዲጋጭና እንዲቃቃር ያደርጉታል። ዛሬም ምንም የፖለቲካ ዝንባሌ የሌለው ባተሌው ሕዝባችን የሥነ ልቦና ባለሙያዎች displaced anger አንዳንዴም misplaced anger እንደሚሉት የተዛባ ትርክት እና ዋልታ ረገጥ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ የወለደው ቂም ማወራረጃ ሆኖ በአሰቃቂ ሁኔታ ይገደላል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ለወግ ማዕረግ ከበቁበት አካባቢ በግፍ ይፈናቀላሉ፣ ይሰደዳሉ።

በዚህ ሰዓት ብዙ ሰዎች በሰቆቃ እና ፈተና ውስጥ እንዲኖሩ ተገደዋል። ነገን ማሰብ ከባድ ሆኗል። ይህ ሁኔታ የትም አላስኬደንም። የትም አያስኬደንም። እናም ብዙ ሰው ሳይሞት፣ ብዙ ደም ሳይፈስ እና ትውልድ ሳይጎዳ ከተሳሳተው ወደ ትክክለኛው መንገድ መመለስ አለብን። ዛሬ ላይ ሆነን በትናንት ትርክት መኖርን በቃ ልንለው ይገባል። እንደ ሩዋንዳ የመሳሰሉት ሀገራትን መንገድ ተከትለን እኛም ይህን ታሪካችንን ልንዘጋ ግድ ይለናል።

ኢትዮጵያውያን ከሚያለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ነገሮች ይበዛሉ። ሕዝባችን ተዋዶና ተፈቃቅሮ የመኖር ችግር የለበትም። ይህ ዘመናትን ባስቆጠረው የታሪክ ሂደት በተግባር ታይቷል። ከጥንት ጀምሮ ያለው የአኗኗር ዘይቤያችን በራሱ ኅብረትና ትስስር እንዲኖረን የሚያስገድደን ነው። በግሌ ዋናው ችግር የፖለቲከኞች የሥልጣን ሽኩቻና የጥቅም ሽሚያ ነው ብዬ አምናለሁ።

ሌላው ችግር ነው ብዬ የማስበው በታሪክ ሂደት የነበሩ ትርክቶቻችን በውስጣችን ተክለው ያኖሩት የሥነ ልቦና ችግር ወይም እውነታን የምናይበት ዓይን ነው። ይሄ የሥነ ልቦና እንቅፋት መሰበር አለበት። ያለንበትን ክፉ ጊዜ ለማለፍ የአቅጣጫና የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልገናል። ከመሪዎችም ሆነ ከሕዝቡ ከፍ ያለ አስተዋይነት ይጠበቃል። ያሉትን የእርስ በርስ ጥርጣሪዎች፣ ስጋቶች፣ አለመተማመኖች፣ ውጥረቶችን…. ጋብ ማድረግ (deescalate) ያስፈልጋል። ሀገርን ለማዳን የሥልጣን ሽኩቻው ልጓም ሊበጅለት ግድ ይላል።

በአጠቃላይ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ሊገነባ የሚችለው ሌሎች ሀገሮች ከደረሰባቸው ኪሳራ ተምሮ ለመነጋገር፣ ለመወያየትና ለመደራደር ዝግጁ ሆኖ በመገኘት እንጂ የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር ነጋም ጠባ የኃይልና የግጭት መንገድን በመከተል እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። የኃይልና የግጭት አማራጭ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለው ውጤታማነት ከዜሮ በታች መሆኑን በተደጋጋሚ አይተነዋል።

ውይይትንና ንግግርን ማስቀደም ያሉንን ልዩነቶች ፈትሸን አንድ የጋራ እውነት ላይ ለመድረስ ያስችለናል። ለዚህ ባህሉ አለን። ትውፊቱ አለን። የሚያስፈለገው ነገር ቢኖር እነዚህን እያሳደጉና እያጎለበቱ (scale-up ) ለችግሮቻችን ጥቅም ላይ ማዋል ነው። ያኔ የሚያታግለንን ለማሸነፍ ፣ መጻሂ ዕድላችንን ብሩህ ለማድረግ ዕድሉ ይኖረናል።

መልካም አዲስ አመት !

ዳግም መርሻ (በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የህዝብ አስተያየት
ጥናት ተመራማሪ )

አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You