ለዘንድሮ የትምህርት ዘመን የጥናት ፕሮግራም ማዘጋጀታቸውን ተማሪዎች ገለጹ

– የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት በይፋ ተጀምሯል

አዲስ አበባ፦ ለ2016 ዓመተ ምህረት የትምህርት ዘመን የጥናት ፕሮግራም ማዘጋጀታቸውን የዳግማዊ ምኒልክና የአፄ ናኦድ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ገለጹ። የ2016 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት በአዲስ አበባ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ትናንት በይፋ ተጀምሯል።

የዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ኤፍራታ አያሌው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገረችው፤ ባለፈው ዓመት የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስዳ ጥሩ ውጤት በማምጣት በዘንድሮ ዓመት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነች። ዘጠነኛ ክፍል ለ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መሠረት የሚጣልበት በመሆኑም ለብሔራዊ ፈተና የምታደርገውን ዝግጅት ከወዲሁ እንደምትጀምር ተናግራለች።

 የዘጠነኛ ክፍል ትምህርት ከስምንተኛ ክፍል በብዙ ነገሮች የሚጠነክር ይመስለኛል ያለችው ተማሪ ኤፍራታ፤ ነገር ግን መምህራን ሲያስተምሩ በአግባቡ በመከታተል፣ ቤተ መጽሐፍት በመግባትና በማንበብ፣ የግል የጥናት ፕሮግራም በማውጣት ከዘጠነኛ ክፍል ወደ አሥረኛ ክፍል ለመዘዋወር ከወዲሁ እየተዘጋጀሁ ነው ብላለች።

የአፄ ናኦድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሶሊያና ካሳሁን በበኩሏ፤ ዘንድሮ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ መሆኗን በመግለጽ፤ የስምንተኛ ክፍል ፈተና ከባድ እንደሆነ ተማሪዎች ቢናገሩም የመምህራንና የወላጅ ድጋፍ ላይ የራሴን አቅም አሳድጌ ለማለፍ ጥረት አደርጋለሁ ብላለች። ባለፈው ዓመት የደረጃ ተማሪ መሆን አልቻልኩም። በአሁኑ ግን ከአምናው በመማር የደረጃ ተማሪ ለመሆን አቅጃለሁ ብላለች።

«የስምንተኛ ክፍል ፈተና ከሰባተኛና ከስምንተኛ ክፍል የተውጣጣ ነው። ስለዚህ የአምናውን ፈተና ከወዲሁ በማየት ለፈተናው ብቁና ውጤታማ የሚያደርግ የጥናት ፕሮግራም አዘጋጃለሁ። ከሁለት ወር በኋላ የትምህርት ቤት ጓደኞቼንና መምህሮቼን በማግኘቴ ተደስቻለሁ» ስትልም ተማሪ ሶሊያና ተናግራለች።

የአፄ ናኦድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ያደረጉ መጽሐፎችን ቤተ መጽሐፍት ውስጥ አስገብቷል ያለችው ደግሞ ተማሪ መሠረት ያሬድ ነች።

በ2016 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች በስምንተኛ ክፍል ቆይታቸው የደረጃ ተማሪ ብቻ መሆን ሳይሆን የሀገሪቱን ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት መጣር አለባቸው ያለችው ተማሪ መሠረት፤ መምህራን በተቻላቸው አቅም ተማሪዎችን ከበፊቱ የተለያዩ የመማር ማስተማር ሂደት ሊያዘጋጁ ይገባል፤ ወላጆች ደግሞ የልጆቻቸውን ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ቢፈትሹ ውጤታማ ተማሪ መፍጠር ይቻላል ብላለች።

የዳግማዊ ምኒልክ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና መካከለኛ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ግሩም መዝገበ በበኩላቸው፤ በ2016 የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል እና የመማር ማስተማሩን ሂደት ስኬታማ ለማድረግ በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል። ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎች ሳቢ እና ማራኪ እንዲሆን ክፍሎችን የማስዋብ፣ አጥርና ግቢዎችን የማሳመር ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።

የመማር ማስተማር ሂደቱ ፍፁም ሠላማዊ እንዲሆን ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የተማሪው ወላጆች እና መላው የትምህርት ማኅበረሰብ ተቀራርበው መሥራት አለባቸው ያሉት ርዕሰ መምህሩ፤ በተለይ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ ባለፈ ልጃቸው ትምህርት ቤት ምን እንደተማረ፣ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ እና ለልጃቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከመምህራን ጋር መነጋገር አለባቸው ብለዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን  መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You