ዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎችን እያከናወነ ነው

አርባ ምንጭ፡- ጥናት ላይ የተመሠረቱ ማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዳምጠው ዳርዛ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድና ማኅበረሰብ ተኮር የሆኑ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ከብክለት የፀዳ ኢነርጂ ግንባታ፣ በጤና እና ግብርናን በማዘመን ዘርፍ እንዲሁም በነፃ የሕግ አገልግሎት ዘርፍ እየሠራ ይገኛል።

ዩኒቨርሲቲው የአካባቢው ማኅበረሰብ ንፁሕና ደህንነቱ የተጠበቀ ውሃ እንዲያገኝ በጥናትና ምርምር ላይ ተደግፎ ፕሮጀክቶችን በማካሄዱ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በሳውላ ከተማ የተከናወነውን የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለአብነት አንስተዋል። በክልሉ በዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች ፊታውራሪነት እየተገነባ የሚገኘው ፒኮክ የኃይል ማመንጫ ግድብም ዩኒቨርሲቲው ከንፁህ መጠጥ ውሃ ያለፈ ሥራ እያከናወነ የሚገኝ መሆኑን ማረጋገጫ ናቸው ሲሉ አክለዋል።

በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የሚሠራው ሥራ በውሃ ኃይል ማመንጨት ብቻ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ዩኒቨርሲቲው ከጋሞ እና ጎፋ ዞኖች ጋር በመተባበር የፀሐይ ኃይል ስቴሽን እየገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከዚህ በፊት በተገነቡ የሶላር ኃይል ማመንጫ ግንባታዎች የጤና ማዕከላት እና ትምህርት ቤቶች ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውንም አንስተዋል።

በጤናው ዘርፍ በተለይ በቅርቡ ተመርቆ ሥራ የሚጀምረውን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ማገልግል የሚችሉ ስፔሻሊስት የጤና ባለሙያዎችን እያፈራ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንት ዳምጠው አስረድተዋል። ለሪፈራል ሆስፒታሉ አስፈላጊው ግብዓት እና የሰው ኃይል እየተሟላ የሚገኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዩኒቨርሲቲው ያሉ የጤና ምሁራንን በመጠቀም የአርባ ምንጭ ሆስፒታልን በባለሙያ እየደገፈ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የግብርና ሳይንስ ዘርፍ መኖሩን ጠቅሰው ዘርፉ በክልሉ በጥናት ላይ የተደገፉ መፍትሔዎችን በመስጠት ሕዝቡን እየደገፈ ነው ሲሉ አንስተዋል። ለአብነትም በእንሰት እና በአፕል ምርት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዩኒቨርሲቲው በተለይ እንሰት ላይ በመሥራት የእንሰት ተክል ቀለል ባለ ሁኔታ እና ፅዳቱን በጠበቀ መንገድ ለምግብነት ለማቅረብ የሚያስችል ፕሮጀክት ላይ እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ገንዘብ ከፍለው በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ መስተናገድ የማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ በተሠራ ሥራ፤ በ2015 ዓመተ ምህረት 1000 ለሚሆኑ የአካባቢው ማኅበረሰቦች ነፃ የሕግ አገልግሎት መስጠቱን ነው የተናገሩት።

ውብሸት ሰንደቁ

አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You