ዘመናዊ አልባሳት ብዙም በማይለበሱበት በቀደመው ዘመን የባህል አልባሳት ብቻ ነበሩ የሚለበሱት። እናቶች የሚለብሱትን ልብስ በእጃቸው ፈትለውና አሸመነው ሲለብሱ ኖረዋል። አሁንም ቢሆን ፈትለው የሚለብሱና ቤተሰባቸውን የሚያለብሱ እናቶች አልጠፉም። ፈትለው ከሚለብሱና ከሚያለብሱ እናቶች በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት የለባሹን ፍላጎቱ ሊያሟሉ የሚችሉ ውብና ማራኪ የሀገር ባህል አልባሳትን በተለያየ ዲዛይን ሠርተው ለገበያ የሚያቀርቡ በርካቶች ናቸው።
ይህን ተከትሎም እነዚህ አልባሳት በጣም ተፈላጊ እየሆኑ መጥተዋል። በተለይም በበዓል ወቅት የሀገር ባህል አልባሳት መዋቢያና መድመቂያ ናቸው። ዘመኑ ለባሹ ሰፊ አማራጭ እንዲኖረው አድርጓል። በመሆኑም በርካቶች የሚፈልጉትን ዓይነት የሀገር ባህል አልባሳት በቀላሉ አማርጠው መልበስ እንዲችሉ አድርጓቸዋል።
የሀገር ባህል አልባሳት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት እንደየአካባቢው የአኗኗር ዘይቤና ባህል ይለበሳሉ። አልባሳቱ ኢትዮጵያዊ መለያ በመሆናቸውም በርካቶች በተለይም በበዓል ወቅት አምረውና ደምቀው ይታዩባቸዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ዓመቱን ሙሉ የሚከበሩ የተለያዩ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት አሉ። በእነዚህ የበዓላት ወቅት ታዲያ አብዛኛው ሰው አቅሙ በፈቀደ መጠን በሀገር ልብስ ደምቆና ተውቦ በዓሉን ማክበር ምርጫው ነው። ለዚህም ነው በዓል ሲመጣ ከምግብና መጠጡ እኩል ለሀገር ባህል አልባሳት ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው። ከአልባሳቱ ጋር የሚስማሙ መዋቢያ ጌጣጌጦችም እንዲሁ አይቀሬ ናቸው።
ሰዎች ለእያንዳንዱ የበዓላት ወቅት የሚሰጠው ክብደት የሚለያይ ቢሆንም አብዛኛው ሰው በሚባል ደረጃ ለበዓል አምሮበትና ለብሶ መታየትን ምርጫው ያደርጋል። ለእዚህ ደግሞ የባህል አልባሳት እየተፈለጉ ናቸው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአዘቦት ቀናት ጭምር ባህላዊ አልባሳትን ማዘወተር እየተለመደ ነው። በተለይም አሁን ላይ ባህላዊ አልባሳቶች በተለያየ መልኩ ባማረ ሁኔታ እየተሠሩ ለገበያ የሚቀርቡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የለባሹን እይታና ፍላጎት የሚጨመሩ እየሆኑ መጥተዋል።
ሸማኔው በጥበቡ የተጠበበባቸውን የሽመና ልብሶች ዲዛይነሮችም የድርሻቸውን አክለውበት ለገበያ ሲቀርቡ ዓይን የሚይዙ ሳቢና ማራኪ ናቸው። እነዚህ አልባሳት ታዲያ ለባሹ እንደፈለገውና እንዳመቸው ሊለበሳቸው የሚችሉ ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ አልባሳት ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ መሆን አለመቻላቸው በብዙዎች የሚያነሳ ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል። ለዚህም ከሰሞኑ ያሳለፍነው የአዲስ ዓመት በዓል አንድ ማሳያ ነው።
በዓሉን በሀገር ባህል አልባሳት አምረውና ደምቀው ማሳለፍ የቻሉ ለባሾችም የሀገር ባህል አልባሳቱ አልቀመስ እንዳለ ምስክርነት ሰጥተዋል። በአዲስ ዓመት ማግስት እጅግ ባማረ የሀገር ባህል ልብስ አምረውና ደምቀው ያገኘናቸው ወይዘሮ ፋንቱ አለሙ አንዷ ናቸው። በበዓል ማግስት በሀገር ባህል ልብስ የተንቆጠቆጡት ወይዘሮ ፋንቱ፤ ቀሚሱ ለበዓሉና ከበዓሉ በኋላ የሚጠብቃቸውን የቤተሰብ ፕሮግራም ታሳቢ በማድረግ ያሠሩት መሆኑን ገልጸዋል። ዲዛይኑም ሆነ የቀለም ምርጫቸው የራሳቸው ሆኖ በትዕዛዝ ማሠራት እንደቻሉ ጠቅሰው ዋጋው ግን የማይቀመስ እንደሆነ ነው ያስረዱት። እሳቸው እንዳሉት ቀሚሱን ለማሠራት 27 ሺ ብር ወጪ ጠይቋቸዋል።
ልብሱ ምንም እንኳን አሁን ገበያው ላይ ካሉት ልብሶች አንጻር ሲታይ የተሻለ ቢሆንም ቀደም ሲል ከነበሩ የሀገር ባሕል ቀሚሶች አንጻር በጥራትና በዲዛይን የተሻለ ውበት እንዳለው ነገር ግን ከዋጋ አንጻር እጅግ በጣም ውድ እንደሆነ ነው ያስረዱት።
የሀገር ባሕል ቀሚስ ከበዓል ቀናት ውጪ በአዘቦትም መልበስ ፍላጎታቸው እንደሆነ የጠቀሱት ወይዘሮ ፋንቱ፤ የሀገር ባህል አልባሳቶቹ እጅግ ውብና ማራኪ በመሆናቸው ከኢትዮጵያ አልፎ ሌሎች ሀገራት ጭምር የሚዋቡበት ተመራጭ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ይሁንና አሁን ላይ ከዋጋቸው አንጻር የሀገር ባሕል አልባሳት ለመልበስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን አንስተው፤ ‹‹የአልባሳቱ ዋጋ የማይቀመስ በመሆኑ እያማሩን ሊቀሩ ነው። እኛ ሳንለብሳቸው እያጓጉን ለሌሎች አሳልፈን እየሰጠናቸው ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት እንኳን ለበዓል ይቅርና ትንሽ ለሚባል ፕሮግራም ሳይቀር የሀገር ባል ልብስ ማሠራት የብዙ ሰዎች ልምድ ነበር›› በማለት የአልባሳቱን ዋጋ መወደድ ገልጸዋል።
ሌላው ቀርቶ ለስጦታ ጭምር የሀገር ባህል አልባሳት አሠርቶ የሚሰጥ እንደነበረ በማስታወስ፤ አሁን ላይ ይህንን ለማድረግ ብዙ ውጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ወደፊት ቀደም ሲል በደጉ ዘመን ያሠሯቸውን የሀገር ባህል ልብሶች አውጥተው የሚለብሱ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
ወይዘሮ ፋንቱ እንደሚሉት የሀገር ባሕል ልብሶችን እኛ ለብሰን አምሮብንና ተውበን ለሌሎች ማስተዋወቅና ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ ማድረግ ያለብን። ስለዚህ ማኅበረሰቡ በራሱ ባሕል እንዲኮራና እንዲያስተዋውቅ አልባሳቱ በተመጣጣኝ ዋጋ የማኅበረሰቡን አቅምና ኪስ ባገናዘበ መልኩ ተሠርተው ለገበያ ሊቀርቡ ይገባል። ለዚህም ዲዛይነሮችን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለጉዳዩ ትክረት መስጠት አለባቸው ብለዋል።
በበዓሉ ማግስት በሀገር ባህል ልብሷ ተውባና በዓል መስላ ያገኘናት ወጣት ቆንጂት ይልማ ናት። ቆንጂት እንደምትለው፤ የሀገር ባሕል ልብስ መልበስ የሁልጊዜ ፍላጎቷ ነው። በበዓላት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሌላም ጊዜ በየምክንያቱ በተለይ ፋሽን የሆኑ ልብሶችን መልበስ ምርጫዋ ነው። በበዓሉ ማግስት የለበሰችው የሀገር ባሕል ቀሚስም ከሁለት ወር በፊት ለዘመዷ ሠርግ እንደነበር ገልጻ፤ ቀሚሱን በምትፈልገው ቀለምና ዲዛይኑ ለአለባበስ በሚመቻት ቅርጽ በ10 ሺ ብር ማሰፋት እንደቻለች ነው ያጫወተችን።
ትምህርት ቤት እያለች ጀምሮ የተለያዩ ፕሮግራሞች ሲዘጋጁ የሀገር ባሕል ልብስ መልበስ እንደምትወድ የምትናገረው ቆንጂት፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ልምድ ሆኖባት በየሰበብ አስባቡ በሀገር ባህል ልብስ መዋብና መድመቅ ትመርጣለች። በተለይ ‹‹አሁን ላይ የሀገር ባሕል አልባሳቱ ዲዛይናቸውም ሆነ ሥራቸው በተለያየ ፋሽን ተሠርተው ሲታዩ አፍዘው የሚያስቀሩ ዓይነት እንደሆኑ ገልጻለች። ይሁንና እነዚህን ልብሶች ሰዎች በሚፈልጉት ዲዛይን አሠርተው ለመልበስ ዋጋቸው ተመጣጣኝና የማኅበረሰቡን አቅም ያገናዘበ አለመሆኑን ገልጻለች።
የሀገሪቱን ቱባ ባህል የሚገልጹ የሀገር ባሕል ልብሶች ተሠርተው አይደለም፤ ተለብሰው እንኳን የሚያልቁ ዓይነት አይደሉም የምትለው ቆንጂት፤ ‹‹እኛ ለብሰን አምሮብን ከእኛ አልፈው ደግሞ ሌሎች እንዲለብሱት ማድረግ አለብን። ለዚህ ደግሞ በቅድሚያ እኛ መልበስ በምንችልበት ተመጣጣኝ ዋጋ ተሠርተው መቅረብ ይኖርባቸዋል›› ባይ ናት።
አሁን ላይ ብዙ ሰው ለበዓልም ሳይቀር የሀገር ባሕል ልብስን እየተወ ሽፎን የሚባለውን ልብስ እየለበሰ መሆኑ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው በማለት፤ በቀጣይ ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚሉ አካላት በሙሉ ኃላፊነት ወስደው ሊሠሩበት የሚገባ እንደሆነ የምታስረዳው ቆንጂት፤ በተለይም ለባሹ የሀገሩን ልብስ ለብሶ በኩራት እንዲያስተዋወቅ የሚያስችል አማራጭ መፍጠር ያስፈልጋል ትላለች።
የባህል አልባሳት አምራቾችና አዘጋጅ ዲዛይነሮች ደግሞ የክርና የመሳሰሉት ግብአቶች አለመገኘት ዋጋው ውድ እንዲሆን እያደረገው መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ይዘናቸው በወጣናቸው ዘገባዎች ጠቁመዋል። እንዲያም ሆኖ ኅብረተሰቡ የባህል አልባሳትን ምርጫው እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ እያንዳንዱን ግለሰብ ያማከሉ አልባሳት ገበያ ላይ እንዳሉም ተናግረዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም