የትምህርቱ ዘርፍ የዓመቱ አበይት ክንውኖች

የ1983 ዓ.ምን ለውጥ ተከትሎ ወደ መሬት ከወረዱትና ሲያጨቃጭቁ ከኖሩት ፖሊሲዎች መካከል ፊት መሪው «አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ» ስለ መሆኑ ማንም ዋቢ አያስጠራም። ጉዳዩ በሁሉም ዘንድ የተወገዘ፤ በሁሉም ዘንድ የተጠላ፤ ሁሉንም ያማረረና ከናካቴውም ሀገርና ትውልድን ወደ እንጦሮጦስ ይዞ በመውረድ ላይ የነበረ በመሆኑ በሁሉም ዘንድ በሚገባ ይታወቃል።

ይህ መለወጡን በጉጉት ስንጠብቀው የነበረው «አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ» ጥያቄ ምልክት ውስጥ ከወደቀና ከነ ግሳንግሱ መነቀል ከጀመረ እነሆ ሁለት/ሦስት አመታትን በማስቆጠር ላይ ይገኛል።

ይህ የተገረሰሰው «አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ» ካስገኛቸው አገላለፆች መካከል «የዘመኑ ዲግሪ የሙቀት እንጂ የእውቅት መለኪያ አይደለም»፤ «ዮዲት ጉዲት»፣ «ሳይማሩ የሚያስተምሩ (ያስተማሩን)»፣ «የሀሰት የትምህርት ማስረጃ»፣ «ድንጋይ ማምረቻ»…. እና የመሳሰሉትን ሲሆን፤ በተለይ ከትምህርት ጥራት አኳያ ፖሊሲው ትውልዱን አዘቅጥ ከትቶ ማንበብና መፃፍ እማይችሉ ምሩቃንን እስከ ማፍራት ድረስ ዘልቆ እንደነበር ሁሉም ያውቀዋል፡፡ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ትምህርት ሚኒስቴርም ደጋግሞ ኀዘኑን የገለፀበት አደገኛ ሀገራዊ ጉዳይ ነው።

በመሠረቱ፣ ትምህርት አይደለም በዚህ ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን በ1ኛውም ቢሆን ወሳኝ ነው። ያለ ትምህርት ሰብእና ግንባታ ብሎ ነገር የለም። ያለ ትምህርት የአእምሮ መዳበር፣ የአመለካከት (አስተሳሰብ) ለውጥ፣ ልማት፣ እድገት፣ ብልፅግና፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በመልካም አስተዳደግ የተቀረፀ ትውልድ ፈጠራ ወዘተ ብሎ ነገር የህልም እንጀራ ነው። ሥልጣኔ፣ ቴክኖሎጂ፣ እኩልነት፣ ፍትሐዊነት፣የሕግ የበላይነት፣ ሕገመንግሥታዊነት (እዚህ ላይ እየተነጋገርን ያለነው አጠቃላይ በሆነ መልኩ መሆኑን ልብ ይሏል)፣ ዲፕሎማሲ ፌዝ ይሆናል።

በአሁኑ ጊዜ ያለ ትምህርት ከድህነት መውጣት አይታሰብም። ከድንቁርና መፋታት ቀልድ ነው። ዓለም አቀፋዊ መሆን «ርቆ የተሰቀለ ዳቦ» ይሆንና መንደርተኛነት ይስፋፋል። ፈጠራና ፈጣሪነት ይደርቃሉ። ፈጣሪ የሰጠንን የተፈጥሮ ፀጋ መጠቀም አይቻልም። በመሆኑም፣ በትምህርት አይቀለድም። አይቀለድም ማለት ግን አልተቀለደም ማለት አይደለም፤ ተቀልዷል።

በ2014 ዓ.ም በ12ኛ ክፍል ተማሪዎች (ተፈታኞች) የተመዘገበው የፈተና ውጤት ምን እንደነበረ የሚታወስ ብቻ ሳይሆን «አስደንጋጭ» ተብሎ እንደነበረም አይረሳም።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ጂንካ ላይ ባደረጉት ንግግር «በቅርብ በተደረጉ ጥናቶች እንደተረጋገጠው 3ኛ ክፍል ከደረሱ ተማሪዎች መካከል 65 በመቶዎቹ ማንበብ አይችሉም። ለዚህ ምክንያቱ ባለፉት 27 አመታት በትምህርቱ ላይ የተሠራው አሻጥር ነው።» ማለታቸው እየተነጋገርንበት ላለው የትምህርታችን መዝቀጥ ጉዳይ ሁነኛ ማሳያ ሲሆን፤ በ2014 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት ማምጣታቸው አነጋጋሪ ስለሆነበት ምክንያትም ምላሽ ይሰጣል። ፕሮፌሰሩ ነሐሴ 29/2015 ዓ.ም በአማሮ ኬሌ ተገኝተው «የትምህርት ሥርዓቱ አንደኛው ችግር የትምህርትና የፖለቲካ መቀላቀል» መሆኑን መግለፃቸውም የነበረው የትምህርት ፖሊሲ ዝቅጠት ሌላው ማሳያ ነውና የመለወጥ ትግሉ ከባድ ነው።

እንደ ሚኒስትሩ የአማሮ ኬሌ አገላለፅ ትምህርት የዜጎች ሕይወት የሚወሰንበት ዋነኛ መሣሪያ በመሆኑ ከፖለቲካ ጋር ፈጽሞ ሊቀላቀል አይገባውም። ካለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ጀምሮ በመንግሥት እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች አንዱ ፖለቲካና ትምህርትን የመለያየት ሥራ ሲሆን፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የራሱ ራስ ገዝ አስተዳደር ያለው፣ ራሱን የቻለ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን የተደረገው ትምህርትና ፖለቲካን ለማላቀቅ ጭምር ነው።

የቀድሞው «አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ» በምሁራን፣ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ብቻም አልነበረም ሲተች የነበረው፣ በራሳቸው በተማሪዎችም የተተቸ ጉዳይ ነው።

በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው፣ የባህርዳሩ ተማሪ ሄኖክ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ «የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱ የሞተ ነው። በተግባር የተደገፈ አይደለም። ፅንሰ-ሐሳብ ነው የምንማረው። ክፍል ውስጥ ትምህርቱን የተረዳ ውጤት ያመጣል። ይህ ዓይነት የትምህርት ፖሊሲ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም።» የሚል አስተያየት መስጠቱን እዚህ መጥቀሱ የፖሊሲውን ቀሽምነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል።

ያ «አስደንጋጭ» የተባለ ውጤት እንዳመለከተው ለፈተና ከተቀመጡት ከ980 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል 30 ሺህ ገደማ ብቻ ናቸው ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ማግኘት የቻሉት። «ታዲያ ቀልዱ የቱ ጋ ነው?» የሚል ካለ፣ ቀልዱ የነበረው ከፈተናው በፊት በነበሩት አመታት ኩረጃ ባህል ሆኖ የቆየ መሆኑ ጋ ነው። ወደ ጉዳያችን፣ በ2015 ዓ.ም ስለተከናወኑትና በ2016 ዓ.ም ስለሚከናወኑት አበይት ተግባራት እንመለስ።

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም እኩለ ቀን ላይ በጽሕፈት ቤታቸው በመገኘት ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተው ነበር። በወቅቱ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች መልስ የሰጡት ፕሮፌሰር ከዚህ ቀጥለው ያሉት አንኳር አንኳር የተቋሙ ተግባራት ነበሩ።

እንደ ሚኒስትሩ መግለጫ፣ በትምህርት ዘርፉ የተወሰዱና በቀጣይ የሚተገበሩ የለውጥ አጀንዳዎች በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፉ ያሉ ስብራቶችን ለመቅረፍ በተለይም የትምህርት ፖሊሲውን ቀድሞ ከ1ኛ- 4ኛ የመጀመሪያ ደረጃ የመጀመሪያ ሳይክል፣ ከ5ኛ- 8ኛ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ ሁለተኛ ሳይክል፣ 9ኛ እና 10ኛ ክፍል ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም 11ኛ እና 12ኛ ክፍል መሰናዶ ትምህርት የነበረውን የትምህርት ሥርዓት ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ፣ 7ኛ እና 8ኛ ክፍል የመካከለኛ ደረጃ እና ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሆን ከማስተካከል ጀምሮ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት በመቅረጽ በመጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ በዚህ አመት ሙሉ ትግበራ የተደረገ ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ 9ኛ እና 10ኛ ክፍል የሙከራ ትግበራ ላይ የነበረው ሥርዓተ ትምህርት በ2016 ሙሉ ትግበራ በቀለም ትምህርቶች የሚካሄድ ይሆናል።

በዚህ ረገድ ከመጻሕፍት ህትመትና ስርጭት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከመንግሥት ጋር በመነጋገር በከፍተኛ ትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

እንደ ሀገር ከፍተኛ የሞራል ውድቀት ገጥሞ የነበረ ሲሆን፣ የትምህርት ምዘናና ፈተና አስተዳደር ሥርዓትን ለማስተካከል ባለፉት ሁለት ዓመታት በተሠራው ከፍተኛ ሥራ ኅብረተሰቡ ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው ለውጥ ተመዝግቧል። ይህ ወደ ኋላ እንዳይመለስ በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈተናን ለመስጠት በትኩረት የሚሠራ ይሆናል።

አሁን በሀገራችን ያሉ ትምህርት ቤቶች አብዛኞቹ ከደረጃ በታች ከመሆናቸው የተነሳ ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ አይደሉም። በመሆኑም ይህንን ለመቅረፍ «ትምህርት ለትውልድ» የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሀገራዊ ንቅናቄን በሀገር አቀፍ ደረጃ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የተጀመረው በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን ሁሉም ገንዘቡ፣ እውቀቱና ጉልበቱ ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲደግፉት የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

ከዚህም በተጨማሪ ግብዓታቸው የተሟላላቸው ከሁሉም ክልሎች በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ተመርጠው የሚገቡባቸው 50 ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመላ ሀገሪቱ ለመገንባት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፤ በቀጣይም ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ግንባታቸው የሚከናወን ይሆናል።

በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የሚስተዋሉትን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ ምሩቃን ብቃታቸው የተረጋገጠና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በዚህ አመት የተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናን በተሳካ መልኩ በሁሉም የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች መስጠት የተቻለ ሲሆን ይህም ወደፊት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ፕሮግራሞች አከፋፈት ዩኒቨርሲቲዎቹ ባላቸው ከባቢያዊ ጸጋ መሠረት እንዲሆን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮና ትኩረት መስካቸው የማደራጀት ሥራ የተሠራ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ሲቀበሉ በተለዩበት የትኩረት መስክ ይሆናል።

በቀጣይም በዩኒቨርሲቲዎች የሚከፈቱ አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞችም በትኩረት መስክ ልየታቸው መሠረት ይሆናል። ትምህርት ሚኒስቴር ቀደም ሲል በሦስት አመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ይሰጥ የነበረው የቅድመ ምረቃ ዲግሪ ሰልጣኞች የሚጠበቀውን ክሂሎትና ብቃት ይዘው እንዲወጡ የሚያስችል አለመሆኑ በጥናት የተረጋገጠና በትምህርት ጥራቱ ላይም አሉታዊ ችግር የፈጠረ በመሆኑ የቅድመ ምረቃ ትንሹ የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ጊዜ ከሦስት ወደ አራት ዓመት እንዲሆን ተደርጓል። በዚህ ዓመት (2015)ም ለመጀመሪያ ጊዜ የአራት ዓመት ፕሮግራምን አጠናቅቀው ተመርቀዋል፡፡

የድህረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች አከፋፈትና የተማሪዎች ቅበላን በተመለከተ ሁሉም የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን የመግቢያ ፈተና በመስጠት መቀበል እንዳለባቸው ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን፤ ከ2016 ጀምሮ በትምህርት ሚኒስቴር ለሁሉም የድህረ ምርቃ ፕሮግራም ተማሪዎች የመግቢያ ፈተና ተዘጋጅቶ ይሰጣል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚክ ነፃነት እንዲረጋገጥ፣ ከፖለቲካዊም ሆነ አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው የመማር ማስተማር እና የምርምር ሥራዎችን በላቀ መልኩ መፈጸም የሚያስችላቸው፣ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑ የሚፈቅድ በአዋጅ 1294/2015 ጸድቋል። በዚሁ መሠረትም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው 23ኛው መደበኛ ስብሰባ በደንብ ቁጥር 437/2015 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ተወስኗል።

በመቀጠልም፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋም የመጀመሪያው የአዲሱ ራስ ገዝ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ተሹመዋል። ከቻንስለሩ በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት በመሆን ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ተሰይመዋል፡፡

በመጨረሻም

የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ከዚህ ሁሉ ማጥ፣ በተለይም ከላይ ከዘረዘርናቸው ውትብትቦች ውስጥ ለመውጣት የትምህርት ተቋማት ዕውቀትና ዕውነት የሚፈለግባቸው ስፍራዎች በመሆናቸው በየደረጃው በሚገኙ የትምህርት ተቋማት በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የመማር-ማስተማር ሥራን ዕውን ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። የትምህርት ቤቶች አስተዳዳሪዎች በአዲስ መልክ እየሰለጠኑ እንደሚገኙ የተገለፀ ሲሆን፤ ይህም በመምህራንና በተማሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት በመከባበር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማድረግ በኩል አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነው። የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ «ትምህርት ለትውልድ» በሚል መሪ ቃል የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሻሻል ያለመ ሀገራዊ ንቅናቄ እየተካሄደ ይገኛል፤ ተጠናክሮም የሚቀጥል ይሆናል።

የኢንዱስትሪውን መሠረታዊ ችግር በመፍታት በቂ እና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት የትስስር ሥራዎችን ለመሥራት ያለመ፤ በከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ምርምር ተቋማት እና ኢንዱስትሪው መካከል ምቹ የሆነ የእርስ በእርስ ትስስር በመፍጠር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የሚያስችል አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ አዋጁን ሙሉ ለሙሉ መሬት ለማውረድ እየተሠራ ይገኛል።

የድህረ ምረቃ ተማሪዎች የመግቢያ ፈተና /Gradu­ate Admission Test/ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ እንደ ሀገር በሁሉም ፕሮግራሞች ይሰጣል። የዩኒቨርሲቲዎቹም ቅበላ በዚሁ ፈተና ውጤት ይሆናል። የተማሪዎችን የመማሪያ መጻሕፍት ችግር ለመቅረፍ በልዩ ትኩረት ተይዞ እየተሠራ ነው።

በመጨረሻው መጨረሻም፣ የሀገራችን ትምህርት ጉዳይ የተጋረጠበት አደጋ እጅግ ከባድና ከፍተኛ ትግልን የሚጠይቅ ነው። ትውልዶችን ከማጥፋቱ በፊትም ዛሬ ነገ ሳይባል ችግሮቹ ሊቀረፉ የግድ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ የመላው ሕዝብ ድጋፍና ትብብር አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም በሚችለው ሁሉ ሊተባበር ይገባል የሚለው የሚመለከታቸው ሁሉ ጥሪ ነው።

 ግርማ መንግሥቴ

 አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You