አነጋጋሪ የደብተር ውድነትና እጥረት

ያለፈውን ዓመት ሸኝተን አዲሱን 2016 ዓ∙ም ከተቀበልን እነሆ ቀናት እየተቆጠሩ ነው። በዚህ በተቀበልነው አዲስ ዓመት መስከረም ወር ከሁለት ታላላቅ በዓላት በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ይከፈታሉ፤ ላለፉት ክረምት ወራቶች እረፍት ላይ የነበሩት ተማሪዎች ወደየትምህርት ገበታቸው ይመለሳሉ።

ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ወላጆች ለልጆቻቸው በትምህርት ወቅት የሚያስፈልጓቸውን ለማሟላት ከላይ ታች ማለት ከጀመሩ ቆይተዋል። በተለይም ለልጆቻቸው ደብተሮችን ለመግዛት ወዲህ ወዲያ ማለት የጀመሩት ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ነው። የደብተር ግዥውን ከበዓል ዋዜማ ጋር አጣምረው ሲያካሂዱ የተስተዋሉም አልጠፉ።

እነዚህ ወላጆች ቀደም ባለው ጊዜ ሆነ ከአዲስ ዓመት በዓል ገበያ የደብተር ግዥውን ደርበው ለማስኬድ የተገደዱት፤ አንድም ደብተር በገበያ ላይገኝ ይችላል ከሚል ስጋት ሲሆን፤ ሌላው የዋጋው ውድነት ከወዲሁ ስላሳሰባቸው እንደሚሆን ለመገመት የሚከብድ አይደለም።

የደብተር ገበያውም ቢሆን ከወላጆቹ ስጋት በተለየ አቅጣጫ እየሄደ ያለ አይመስልም፤ በአንዳንድ የደብተር መሸጫ መደብሮች / የጽሕፈት መሣሪያ ድርጅቶች / ደብተር የለም። ሌሎች አልቋል፤ ሌሎች ደግሞ ገና አልገባም የሚሉ አሉ ።

እነዚህ ምላሾች በደብተር ሸማች የተማሪ ወላጆች ላይ አንዳንድ ጥርጣሬዎች አሳድረዋል።ጥርጣሬው ደግሞ ከበዓል በኋላ በውድ ዋጋ ለመሸጥ ደብተሩ በሱቅ መጋዘን ተሸሽጓል የሚል ቢሆን አይደንቅም።

ከአምናው ተሞክሮ በመነሳትም የደብተር እጥረት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት በወላጆች ዘንድ ያሳደረው ይሄው የደብተር ነጋዴው ሁኔታ ነው። በምግብ፣ ምግብ ነክ በሆኑና በሌሎች ፍጆታዎች በነጋዴው ዘንድ እየደበቁ በውድ ዋጋ ለመሸጥ ማካበት የተለመደ ባህርይ በደብተር ላይም መከሰቱ የተማሪ ወላጆችን በብርቱ አሳዝኗል።

አሳዝኖ ማለፍ ብቻ ሳይሆን አሁንም እያሳዘነ ይገኛል። ከነሐሴ አጋማሽ በኋላ ደብተር ለመገብየት ገበያ የወጡትም በክረምቱ አጋማሽ እንደወጡት ያህል የተጋነነ አይሁን እንጂ ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሟቸዋል። እነኝህኞቹ ደብተር ሸማቾች ጋር ደብተር ቢገባም በቂ አቅርቦት አልነበረም።

ከደብተር ሸማች ብዛት ዓይናቸው እያየ ሲሸጥ አልቋል የሚባሉ፤ ተሰልፈው ተራ እየጠበቁ ሳሉም አልቆባቸው ሳይገዙ የቀሩ አሉ። ይሄ የተከሰተው ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ባለፈው ዓመት የነበረውን የደብተር እጥረትና መወደድ ከግምት በማስገባት በማዕቀፍ ስምምነት በቂ ደብተር ቀደም ብሎ ማስገባቱን እያስታወቀ ባለበት መሆኑ ነው።

አገልግሎት ባለ 50 ቅጠሉን ሲነር ላይን ደብተር አቅራቢ ተቋማት ጨረታ አሸንፈው ውል እንዲዋዋሉ ያደረገው በ31 ብር እንደሆነም ይፋ ባደረገበት ማግስት የጥረቱም ሆነ የውድነቱ መከሰት እንቆቅልሽ ሆኗል። ችግሩ በቂ ትኩረት የሚሻ መሆኑንም አመላክቷል።

አገልግሎቱ በቂ ደብተሮችን ወደ ገበያው ለማስገባት የተገደደው በእጥረቱ ምክንያት የመማር ማስተማሩ ሂደት ለችግር ተጋላጭ እንዳይሆን ለማድረግ ነው። ቀደም ብሎ ገበያ ላይ መዋሉ ወላጆች ትምህርት ቤት ከመከፈቱ በፊት መግዛት የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ታምኖበት ነው። አገ ል ግ ሎቱ ባዘጋጀው የግዥ ጨረታ ተወዳድረው ያለፉ ተጫራች አስመጪዎች ደብተሩን ቀደም ብለው እንዲያስገቡ መደረጋቸው ለችግሩ ቀድሞ መፍትሄ ለማስቀመጥ እንደሆነ ብዙ የሚያጠያይቅ አይደለም።

ለነገሩ አስመጪዎቹ ደብተሩን ለሚያሰራጩ አካላት እያቀረቡ መሆናቸውን ሲናገሩ የተደመጡበት ሁኔታም ነበር። አቅርቦቱ ከበቂ በላይ መሆኑን፤ ለትምህርት ዘመኑ የሚበቃ ደብተር በመጋዘናቸው መኖሩንም አስረድተዋል። ይህ ከሆነ እጥረቱ ከየት መጣ?።

ስለ ደብተር እጥረት ሆነ ውድነት የሚያነሱ ወላጆች አብዛኞቹ አምስት ስድስት ልጅ ያላቸውና በርከት ያለ ደብተር በደርዘን የሚገዙ ናቸው። እውነታው አሁን ካለው ሀገራዊ የኑሮ ውድነት አንጻር ነገሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚሆንባቸው መገመት አይከብድም። የመንግሥትንም ጥረት ዋጋ የሚያሳጣ መሆኑ አይቀርም።

ቦሌ፣ መገናኛ፣ አራት ኪሎ፣ ካዛንቺስ፣ መርካቶ የደብተር ገበያ ቦታዎች የደብተር እጥረት አዝማሚያ ችግሮች ጎልተው ሲስተዋሉ ከነበሩባቸው አካባቢዎች ይጠቀሳሉ። በተለይ መርካቶ አንዳንድ ቦታዎች ላይ እንደ መጽሐፍት ሁሉ መሬት ተዘርግተው አዳዲስ ደብተሮች በደርዘንና በፍሬ ሲሸጡ ታይቷል።

የዚህ ገበያ ሸማቾች በአብዛኛው የተማሪ ወላጆች ሳይሆኑ ደብተር ቸርቻሪ ነጋዴዎች ነበሩ። ገበያው በወከባና ግርግር ብቻ ሳይሆን በጭንቅንቅም የተሞላ በመሆኑ ጭንቅንቁና ግፊያውን መቋቋም የቻሉ ጥቂት ወላጆች ብቻ ናቸው ደብተር የመግዛት ዕድል ያገኙት። አብዛኛው ደብተር አትራፊ ነጋዴ እጅ ነው የገባው።

አብዝቶ ሲሸምት የታየውም ይሄው አትራፊ ነው። ይሄ የስርጭት ሂደቱ ላይ ጥያቄ ያስነሳል። ብሎም የእጥረቱ ምንጭ ደብተር እያለ የለም ብለው በመደበቅ በውድ ዋጋ ሸጠው ለመበልፀግ ከሚያስቡ ስግብግብ ነጋዴዎች በተጨማሪ ይሄም ዓይነቱ ሥርዓት ያልተከተለ የስርጭት ሂደት ስለመሆኑ ለመናገር የሚከብድ አይደለም።

ከዚሁ ከደብተር ሸመታ ጋር ተያይዞ የራስ ምታት እየሆነ የመጣው የደብተር ዋጋ እጅግ መወደድ ነው። ከካች አምናው 25 ብር፤ አምና ደግሞ ከ35 እስከ 45 ብር ሲሸጥ የነበረው ባለ 50 ሉክ ደብተር ዘንድሮ በአብዛኞቹ ቦታዎች ከ65 እስከ 70 ብር አሸቅቦ እየተሸጠ ነው። አሁንም የዋጋው እጥረት አለ በሚል ሳይወርድ እንደወጣ ይገኛል።

በእርግጥ አንዳንድ መደብሮች ውስጥ ይሄው ባለ 50 ቅጠል ደብተር በ50 ብር እየተሸጠ ያለበት ሁኔታ አለ። 70 ብር የሚሸጡት ነጋዴዎች 50 ብር እየተሸጠ እነሱ ለምን 70 እንደሚሸጡ ሲጠየቁ ያመጡበት ዋጋ ውድ መሆኑን ሲናገሩም ይሰማል ።ባለመቶው ሉክ ደብተር ደግሞ እስከ 150 ብር እየተሸጠ ነው። ባለ 50 ሉኩ 50 ብር ከሆነ ባለ መቶው ለምን መቶ ብር አልሆነም የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው የሉኩ ቁጥር በጨመረ ቁጥር ዋጋው እንደሚጨምር ይመልሳሉ ። እነሱ የሚያመጡበት ዋጋ ይሄንኑ ታሳቢ ማድረጉንም ያነሳሉ።

የደብተር እጥረት አለ ብሎ ለሰጋና ገበያውን ዞር ዞር ብሎ ላላየ ወላጅ ባለ 100 ሉኩን ደብተር እስከ 200 ብር የሸጡም መኖራቸው ተስተውሏል።ለሂሳብ ትምህርት የሚውል ስኮየርና ልሙጥ ደብተሮች በተመሳሳይ ዋጋ ከመሸጥ ይልቅ ዓይነታቸውን ከግምት በማግባት ጨምረው እየሸ ጡ ያሉ ነጋዴዎች አሉ።

በነገራችን ላይ መንግሥት በማዕቀፉ ግዢ ደብተር ማስገባቱ ከእጥፍ በላይ የከተማ አስተዳደሩን የደብተር ወጪ ማዳን አስችሏል። ውድነቱንም ሆነ እጥረቱን በመከላከሉ ረገድም ሚናው የጎላ ሆኗል። በተለይ መንግሥት ምግብና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶች እንደተጠበቁ ሆነው በዘንድሮ ትምህርት ዘመን ደብተር በማቅረብ ማሟላቱ ለወላጆች ትልቅ እፎይታን ሰጥቷል።

ለመንግሥት ትምህርት ቤቶች የደብተር ውድነትም ሆነ እጥረት ጉዳይ ይሄን ያህል አሳሳቢ ላይሆን ይችላል።ቢሆንም ከአምናው አንፃር ጨምሯል ።ግን ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ ወላጆች ውድነቱም እጥረቱም ይፈትናቸዋል። በመሆኑም ስርጭቱን በማስተካከል፤ አቅርቦቱን በማስፋት እንዲሁም ስግብግብ ነጋዴዎችን በመቆጣጠር ችግሩን ማስተካከል ግድ ይላል!

ሰላማዊት ውቤ

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

 አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You