የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል መስከረም 26 እና 27 ቀን ይከበራል

አዳማ፡- የ2016 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል መስከረም 26 እና 27 ቀን እንደሚከበር የኦሮሞ አባ ገዳዎች አስታወቁ።

የኦሮሞ አባ ገዳዎች ኅብረት የኢሬቻ በዓል አከባበርን አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ በዓሉ መስከረም 26 ቀን በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ ፣ መስከረም 27 ቀን ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ ሃርሰዴ ይከበራል።

የአባ ገዳዎች ኅብረት ፀሐፊና የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኦሮሞ ሕዝብ ከሚያከብራቸው የእርቅና የሰላም ክብረ በዓላት መካከል አንዱ ኢሬቻ አንዱ ነው።

የኦሮሞ ሕዝብ በገዳ ሥርዓት መተዳደር ከጀመረ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል ያሉት አባገዳ ጎበና፤ የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በሆረ ፊንፊኔና ሆራ ሀርሰዴ በድምቀት ይከበራል ብለዋል።

የኢሬቻ በዓል የሰላም በዓል በመሆኑ የኦሮሞን ባህልና ሥርዓት በተከተለ መልኩ መከበር እንዳለበት ገልጸው፤ በዓሉ ባህልና እሴትን ተከትሎ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

የዘንድሮው ኢሬቻ በዓል የገዳ ሥርዓት እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል ሲሉ አባገዳ ጎበና ተናግረዋል።

 የሲኮ መንዶ አባገዳና የኅብረቱ አባል አባ ገዳ አሊይ መሐመድ ሱሩር በበኩላቸው፤ ኢሬቻ እርቅና ሰላም በመሆኑ የዘንድሮው ኢሬቻ በደስታ፣ በአንድነትና በፍቅር ሊከበር ይገባል ብለዋል።

በዓሉ ያለምንም እንከን እንዲከበር ሁሉም በጋራ መቆም እንዳለበት ገልጸው፤ በተለይም ወጣቱ ሚናውን በአግባቡ መወጣት አለበት ብለዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች በዓሉ የተሳካ፣ የእርቅ፣ የፍቅር የአንድነት ተምሳሌት በሆነ መልኩ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሞ ቄሮዎች፣ ቀሬዎችና ፎሌዎች የበዓሉ ባለቤት መሆናቸውን በመግለፅ፤ ኢሬቻ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ማስቻል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

 የመጫ አባገዳና የኅብረቱ አባል አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ እንደተናገሩት፤ በዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ላይ የሚታደም ማንኛውም አካል በይቅርታና በፍቅር መሆን አለበት።

የክብረ በዓሉ ታዳሚዎች የባህል አልባሳትና መዋቢያ ጌጦችን በመልበስ ሊታደሙ ይገባልም ብለዋል።

በተጨማሪም በዓሉን ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በመሆን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በዓሉን ለመታደም የሚገኙ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የባህል ልብሳቸውን በመልበስ፣ የገዳ ባንዲራ በመያዝ በዓሉን በፍቅር፣ በአንድነትና በሰላም ማክበር እንደሚገባም ገልጸዋል።

ማርቆስ በላይ

 አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 7 ቀን ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You