የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ‹‹ሥም የለኝም በቤቴ›› በማለት ያቀነቀነችውን ዘፈን አንጋፋ ምሁሩና የታሪክ ጸሐፊው በሚገባ ይጋሯታል። እናታቸው የከተራ ዕለት በሰፈራቸው የሚገኘውን የልደታ ታቦት ከቤተክርስቲያን አውጥተው ማደሪያው አድርሰው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ሁሉም ነገር ሰላም ነበር። ከዚያ በኋላ ምጥ ያጣድፋቸው ጀመር። እኩለ ሌሊት ገደማ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ተገላገሉ። ‹‹የበዓሉን ስሜት ይገልጻል›› ሲሉ ‹‹ባህሩ›› ሲሉ ሰየሙት። አባትም የልጃቸው አወላለድ ተዐምር ቢሆንባቸው ‹‹ታምሩ›› ሲሉ ሰየሙ። ምንም እንኳን እንደዋና ሥም ባይጸድቅላቸውም እስከ ዕለተ ሞታቸው ላወጡት ሥም ታምነዋል።
ፍቅሬ፣ መርከቡ፤ በቅላቱ የተማረኩት የእናቱ አክስት ደግሞ ሶላቶ (የጣልያን ወታደር) ካወጡላቸው መጠሪያዎች ጥቂቶቹ ናቸው። ታናናሾቻቸውም የእርሳቸውም ታላቅ የሆነው ካፒቴን ተስፋዬ ባህሩን ‹‹ትልቁ ጋሼ›› ስለሚሉ እሳቸውን ‹‹ትንሹ ጋሼ›› ይሉታል። 12 ልጆች ካሉት ቤት ታላቅ ወንድማቸውን ተከትለው የተወለዱ የቤቱ ሁለተኛ ልጅ ናቸው። ለህጻኑ ባህሩ ከታናሽ ወንድም ጋር መጫወት ትልቁ ምኞታቸው ነበር። በዚህ የተነሳም እናታቸው አርግዛ እስክትወልድ ከእናታቸው እኩል የታናሽ ወንድም ጉጉትን አብረው አርግዘው አምጠው ወልደዋል። ምንም እንኳን ይህ ምኞታቸው እስኪሳካ አምስት እርግዝናዎችን ማለፍ ቢጠበቅባቸውም። የሳቸው አራት ታናሾች ሴት ሆነው በንዴት በግነው ሲያበቁ አምስተኛ ታናሻቸው ወንድ ሆኖ ተክሰዋል። ከአራት የታናሽ እህቶች መወለድና እሱን ተከትሎ ከነበረ ኩርፊያ በኋላ ወንድም ሲወለድላቸው በመደሰታቸው ‹‹አየለ›› ሲሉ የሰየሙት ስም የወንድማቸው ሥም ሆኖ ቀርቷል።
ታላቁንም ሆነ ታናናሾቹን ነገር እየፈለገ እየመታ የሚያናድዳትን እናቱን ቤት በማጽዳት እና ቡና በማፍላት ይክሳታል። ካደገ በኋላ ደግሞ ቋሚ የቤቱ እንጨት ፈላጭ ሆኖ አገልግሏል። በቄስ ትምህርት ቤት የተጀመረው ትምህርት በጎላ ሚካኤል ትምህርት ቤት አልፎና ብዙ መሰረት ይዘው በ1948 ዓ.ም የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሆነው በተስፋ ኮከብ ሲጀምሩ ከዜሮ ክፍል ከመጀመር አላመለጡም። ሆኖም ልጅየው ባህሩ ነውና ከዜሮ ክፍል አንስቶ አጠቃላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመጨረስ ስድስት ዓመታት ብቻ በቅተውታል። በትምህርት ቤቱ በነበራቸው ቆይታ ሂሳብን ከሁሉ አብልጠው ይወዱ ነበር። የተሻለ ውጤትም ያመጡበት ነበር። በመረብ ኳስም ሆነ በእግር ኳስ የነቃ ተሳትፎ ነበራቸው። 1954 ዓ.ም በአሁኑ አዲስ ከተማ መሰናዶ በቀድሞ ልዑል መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርት የጀመሩበት ዓመት ነው።
በዚህ የትምህርት ቤት ቆይታቸውም ‹‹የእንግሊዝኛ አጻጻፌን እንዳልሞት እንዳልሽር እየተቸ መልክ ያስያዘልኝ›› እያሉ ከሚያነሱት የእንግሊዘኛ መምህራቸው ሚስተር ግሬንጅና ሕይወቴን ከታሪክ ትምህርት ጋር ያቆራኘው ነው ከሚሉት ሚስተር ባይንደር ጋር የተገናኙበት ነው። ከታሪክ መምህሩ ጋር ከመገናኘቱ በፊት ታሪክ ለባህሩ አሰልቺ የሰዎችን ሥምና ዓመተ ምህረት መሸምደድ ነበር። እሱ ሲያስተምር ባለፉ ታሪኮች ሕይወት ሲዘራ ‹‹ይህም አለ ለካ›› ማለት ጀመረ። የሱ የማስተማር ዘዴ ከታሪክ ጋር ላይፋታ አጋብቶታል። ውለታ የማይረሳው ባህሩ አድጎ አድራሻውን ፈልጎ ከጻፋቸው መጽሀፎች የሚወደውን ‹‹ፓዮኔርስ ኦፍ ቼንጅ ኢን ኢትዮጵያ›› የተሰኘ መጽሀፍ ‹‹ይህ ያንተ ውጤት ነው።›› ከሚል ጽሁፍ ጋር ፈርሞ ልኮለታል። መምህሩም ተደስቶ ‹‹ተማሪዬ የጻፈው መጽሀፍ›› እያለ ለብዙዎች አሳይቷል።
‹‹የእውቀት አድማሴን ለማስፋት፣ እንግሊዘኛዬን ለማሻሻል ብሔራዊ ቤተ መጻህፍት ወመዘክር የጠቀመኝን ያህል ምንም ተቋም አልጠቀመኝም›› ይላሉ። በተለይ ትምህርት በሚዘጋበት ክረምት ከታላቅ ወንድማቸውና ከጓደኛቸው ጋር መዋያቸው ነበር። ሰዓት አክብረው ከመከፈቻው ቀድመው ይገኛሉ፤ ምሳ መውጫ ጠብቀው ቤታቸው ይሄዳሉ። በጥድፊያ መመለሻ ሰዓት እንዳያልፍባቸው ተጣድፈው ምሳቸውን በልተው መግቢያው ዘጠኝ ሰዓት ከመድረሱ በፊት ለመግባት ሰልፍ ላይ ናቸው። መውጫ 12 ሰዓት ሲደርስ ይወጣሉ። ይሄ ክረምቱን ሙሉ የሚደጋገም ልማዳቸው ነው።
በዩኒቨርሲቲው በነበረ ቆይታቸው የነቃ የተማሪዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተሳትፎ ነበራቸው። በዚህም በርካታ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ተሳትፈዋል፤ በፖሊስ ተሳደዋል፤ ያለመማር አድማንም ተቀላቅለው አብረው አድመዋል። ይሄ ሁሉ አልፎ የሦስተኛ ዓመት ትምህርታቸውን እንደጨረሱ የዩኒቨርሲቲ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ደንቢ ዶሎ አቅንተዋል። በደንቢዶሎ አጼ ዘርዐ ያዕቆብ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲያስተምሩ ከተመደቡበት የእንግሊዘኛ ቋንቋ ባሻገር የአማርኛ መምህር እጥረት በመኖሩ አማርኛ አስተምረዋል።
ስፖርትና ባህሩ የማይለያዩ ናቸውና በትምህርት ቤቱ ውስጥ የእግር ኳስ ቡድን አቋቁመዋል። በተጨማሪም የኪነት ቡድንና የታሪክ ክበብ በማቋቋም ተንቀሳቅሰዋል። በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ ለአገልግሎት በሄዱበት አጋጣሚ የመመረቂያ ጽሁፉቸውን ስለሰሩበት የሌቃ ቄለም ገዥ ስለነበረው ደጃዝማች ጆቴ ቱሉ መረጃ ሰብስበዋል። በደንቢ ዶሎ ከሰውና ከሰነድ የተሰበሰበው መረጃ አዲስ አበባ በሰውና ወመዘክር በሚገኙ ሰነዶች ዳብሮ ከአርትስ ፋካሊቲ በከፍተኛ ውጤት ተመርቀዋል።
በጊዜው በነበረው አሰራር በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የተሻለ ውጤት ይዘው ያጠናቀቁ ተማሪዎች በተማሩበት ተቋም የማስተማር እድል ያገኛሉ። እሳቸውም በዩኒቨርሲቲው ረዳት የታሪክ መምህር በመሆን ተመደቡ። አንድ ዓመት ካገለገሉ በኋላ በእንግሊዝ የለንደን ዩኒቨርሲቲ አካል በሆነው የሩቅ ምስራቅና አፍሪቃ ጥናት ማዕከል እንዲማሩ ተወሰነ። በዛም የመካከለኛውን ምስራቅ ታሪክ እንዲያጠኑ ታሰበ። ሆኖም ለጥናቱ የዐረብኛ ቋንቋ ማወቅ የግድ ሆነ። ለዚህም መጀመሪያ በአዲስ አበባ ቋንቋውን ለመማር ቢጀምሩም አጥጋቢ ባለመሆኑ ማስተማር በጀመሩ ዓመት ከስምንት ወሩ እስራኤል ሂብሩው ዩኒቨርሲቲ በማቅናት የአረብኛ ቋንቋ ተምረዋል። በእስራኤል አራት ወራትን አረብኛ ተምረው ወደ ለንደን በማቅናት ለፒ.ኤች.ዲ ጥናት መሥራትና በተጓዳኝ አረብኛ መማር ቀጥለዋል።
ኤመሬትስ ፕሮፌሰር ባህሩ ‹‹እንኳን ቋንቋ ለትምህርቶት ግድ ነው›› ተብሎ ይቅርና እንዲሁም ቋንቋ መማር ይወዳሉ። በዚህ የተነሳም ሁል ጊዜም ባገኙት አጋጣሚ ይማራሉ። ለዚሁም በርካታ የውጭ ቋንቋዎች መቻላቸው ምስክር ነው። እንግሊዘኛ የመጀመሪያ የውጭ ቋንቋቸው ሲሆን፤ ፈረንሳይኛ እና ጀርመንኛ በቅደም ተከተል የተማሩት የውጭ ቋንቋ ነው። የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ለመከታተል አስፈላጊነቱ የታመነበትን አረብኛ ከሀገር ውስጥ አንስቶ እስራኤል ድረስ ተጉዘው ተምረዋል። በኋላም ከዋና ትምህርታቸው ጎን ለጎን ቋንቋውን ማዳበሩ ላይ በርትተዋል። ይሄ የተለያየ የውጭ ሀገራት ቋንቋዎችን መቻላቸው በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ ሰነዶችን በማገላበጥ የዳበሩ ጥናቶችንና መጽሀፎችን እንዲያዘጋጁ አስችሏቸዋል።
ፕሮፌሰር ባህሩ ለትምህርት በእንግሊዝ ሀገር በነበራቸው ቆይታ ሁለት ነገሮችን ማግኘታቸውን ያስታውሳሉ፤ እነሱም ሴሚናርና የመዛግብት ክምችት ናቸው። በቆይታቸው በየሳምንቱ የነበሩ ሴሚናሮች ላይ በመገኘት የሚቀርቡ ጽሁፎችን የመከታተልና እሱን ተንተርሶ ሀሳብ ሲንሸራሸር መታደማቸውን እንደ ልዩ አጋጣሚ ያዩታል። ለሚጽፏቸው ጽሁፎች በርካታ መረጃዎች የሚገኙበት የእንግሊዝ ብሔራዊ ቤተመዛግብትን ማግኘታቸው ሌላኛው ልዩ እድል ነው። በ1968 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ለግምገማ የቀረበው የመመረቂያ ጽሁፋቸው “የኢትዮጵያና የሱዳን ግንኙነት በምእራብ ኢትዮጵያ ድንበር እ.አ.አ. ከ1898 እስከ 1935” የሚል ርዕስ ነበረው። ጽሁፉ ተቀባይነት አግኝቶ በወቅቱ በሀገር ቤት በነበረው ሁኔታ የአንዳንድ ወዳጆቹ ‹‹አትመለስ እና ተመለስ›› መሃል ለመወሰን ጊዜ ፈጅቶባቸውም ቢሆን፤ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ታዲያ ከእንግሊዝ ሳይነሱ ሁለት ትልቅ ሳጥን ሙሉ መጽሀፍትን በመርከብ ወደ ሀገር ቤት መላክ ቀዳሚ ተግባራቸው ነበር።
ሳይማር ያስተማራቸውን ወገናቸውን ሊያስተምሩና የሀገርን ውለታ ሊመልሱ በመጓጓት በፍጥነት ወደ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ሥራቸው ተመለሱ። በተመለሱ ሦስተኛ ሳምንታቸው ጥቅምት 3 ቀን 1969 ዓ.ም አንደወትሮው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢሮው ውስጥ እያሉ ቢሮአቸው ተንኳኳ። ያንኳኩት ሰዎች ዶክተር ባህሩ መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ ደርግ ጽህፈት ቤት ለአምስት ደቂቃ እንደሚፈለጉ ገልጸው ይዘዋቸው ሄዱ። ‹‹መግቢያው ሰፊ፤ መውጫው ጠባብ›› ብለው በሚገልጹት እስር ቤት ለአምስት ደቂቃ ተብለው ቢወሰዱም ቀጣዮቹን አምስት ዓመታት አሳለፉ።
እስር ቤት ሰፊ ጊዜ አለና ቋንቋ መማር የሚወዱት የያኔው ዶክተር የአሁኑ ኤመሬትስ ፕሮፌሰር ባህሩ የእስር ቤት ቆይታቸው ጣልያንኛ መማር ጀመሩ። በተጨማሪም የጀርመንኛና ፈረንሳይኛው ችሎታቸውን ለማሻሻል ጊዜውን ተጠቀሙበት። በደንቢ ዶሎ ቆይታቸው የሞከሩትን ኦሮምኛና አዲሳቸው የሆነውን ትግርኛ ተማሩ። ከሌሎች ቋንቋ ከመማር ባሻገር እሳቸውም እንግሊዘኛ ቋንቋን ለሌሎች ታሳሪዎች ለማስተማር ሞክረዋል። ሁሉም ታሳሪዎች የለመዱትንና ያዳበሩትን ቋንቋ ይበልጥ ለማሳደግ በቋንቋው የተጻፉ ልብወለድ መጽሀፎችን ባገኙት አጋጣሚ አንብበዋል። ከእንግሊዝ ያመጡት መጽሀፍ በርካታ በመሆኑ ለእስር ቤት ቆይታቸው ጠቅሟቸዋል።
ለአምስት ደቂቃ ተብለው ገብተው አምስት ዓመታትን እንዳሳለፉበት ሁሉ ነሀሴ 14 ቀን 1973 ዓ.ም ድንገት ተጠርተው ፎቶ ከተነሱና አሻራ ከሰጡ በኋላ ከእስር መለቀቃቸውን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ሰጥተው አሰናበቷቸው። ለምን እንደገቡ በተገቢው መልኩ እንዳልተነገራቸው ሁሉ ለምን እንደተለቀቁም በቅጡ የነገራቸው የለም። ለቤተሰቦቻቸው ‹‹መጥታችሁ ውሰዱኝ›› ብሎ ስልክ መደወያም ሆነ የትራንስፖርት መሄጃ ሳይኖራቸው አውላላ ሜዳ ላይ ‹‹ነጻ›› ተባሉ። ስልክ ለመደወል ሲፈሩ ሲቸሩ ለምነው በተሰጣቸው 20 ሳንቲም ወደ ወላጆቻቸው ቤት ቢደውሉ ስልኩ አይሰራም። ሳንቲሙን የቸራቸው ሰው አዝኖ ከቢሮው ቢያስደውላቸውም ስልኩ ሊሰራ አልቻለም። ይሄው ለጋስ ሰው ከባልደረቦቹ ጋር አዋጥተው የአምስት ብር ጌታ አደረጓቸው። በተሰጣቸው አምስት ብር ኮንትራት ታክሲ ተኮናትረው የቤተሰቦቻቸው ቤት ገጃ ደረሱ። በዛም ከአምስት ዓመት ሰቆቃ በኋላ ለተገናኘው ቤተሰብ ተድላ ሆነ።
ከዚያም ወደ ዩኒቨርሲቲ ሥራቸው ተመለሱ። ከዚያው እኩል ያለፉትን አምስት ዓመታት ያመለጧቸውን በርካታ የታሪክ ጽሁፎች ወደ ማገላበጥ አተኮሩ። ከተፈቱ ዓመት ሳይሞላቸው የታሪክ ትምህርት ክፍልን የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው በብቃት ተወጥተውታል። ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ሀገራቸው ሲገቡ በተማሩበት የትምህርት መስክ ሀገራቸውን ከማገልገል ጎን ለጎን በውስጣቸው ትዳር ለመያዝ ዝግጁ ሆነው ነበር። ማሰብ ሌላ መፈጸም ሌላ ሆነና ሀገራቸው በገቡ በሦስተኛ ሳምንቱ ለእስር ተዳረጉ። አምስት ዓመት ብዙ ነውና እኩዮቻቸው የነበሩት አብዛኞቹ ሴቶች ከእስር ሲወጡ ትዳር መስርተው የልጅ እናት ሆነው ጠበቋቸው።
ይሁን እንጂ የታሪክ ተማሪ የሆነችውንና ዶክተር ባህሩ የሚያማክሯትን ጓደኛዋን ተከትላ ቢሯቸው የመጣችው የአራተኛ ዓመት የማኔጅመንትና ሕዝብ አስተዳደር ተማሪ መሰንበት ሸንቁጤ እንዳያት ልባቸው ቢደነግጥም በወቅቱ ምንም አላሉም። ፈጣሪ ሲፈቅድ ሰፈራቸውም ተቀራራቢ ሆነና ገጃና ልደታ ከጊዜ በኋላ በትዳር ተጣምረው የሁለት ልጆች ወላጆች ሆነዋል። እንደ እርሳቸው የትዳር አጋራቸውም ለስፖርት ፍቅር ያላት በመሆኑ ‹‹አብዛኛው ቤት እንዳለው የቲቪ ሪሞት ጥል አልገጠመንም›› ይላሉ። ትዳራቸው ካሌብ እና ጽዮን በተባሉ ልጆች ደምቋል።
ፕሮፌሰር በርካታ ሀገሮችን የመመልከት እድል አግኝተዋል። ከእነዚህ ሀገሮች መካከል ስዊድን፣ እንግሊዝ፣ ምስራቅ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ቱርክ፣ ጣልያን ይገኙባቸዋል። በአፍሪካ የሄዱበትን ከሚጠሩ ያልሄዱበትን ሀገራት መቁጠር ይቀላቸዋል። ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይጎበኛሉ፤ የተለየ አጋጣሚያቸውን ይመዘግባሉ፤ የታሪክ ድርሳናትን ያገላብጣሉ።
የጃፓን ጉብኝታቸውን “ከጎበኘኋቸው ሀገራት ሁሉ ልዩ ትዝታ ጥሎብኝ ያለፈ” በማለት ያስታውሱታል። ‹‹አንድ ሰው ጃፓንን ሳይጎበኝ አለምን አየሁ ሊል አይችልም›› የሚል ድምዳሜ ላይ አድርሷቸዋል። የሃያኛው መቶ ዓመት መባቻ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ላይ ለሚያጠናው ጥናት ከጃፓን ቤተ መጽሀፍት በርካታ መጽሀፍትና ሰነዶችን ኮፒ አድርገው መጥተዋል። እነዚህ ሰነዶች “ፓዮኔርስ ኦፍ ቼንጅ ኢን ኢትዮጵያ” ለተሰኘው መጽሀፍ የመጀመሪያ ምዕራፎች መሰረታዊ መረጃ ሆነው አገልግለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከማስተማር ባሻገር የኢትዮጵያ ጥናት ተቋምን ለሦስት ዓመታት በዳይሬክተርነት መርተዋል። በአመራርነት ዘመናቸው ተቋሙ የነበረበትን የቦታ ጥበት ለመቅረፍ የራስ መኮንን አዳራሽ ለቤተመጽሀፍት አገልግሎት እንዲውል ማስፈቀድ ችለዋል። የአድዋ ድልን መቶኛ ዓመት በድምቀት እንዲከበር ማድረግ ችለዋል። ከሦስት ዓመት የአመራር ዘመን በኋላ ወደ ታሪክ መምህርነታቸውና ወደ ጥናት ሥራቸው ተመልሰው አገልግለዋል። በ1993 ዓ.ም 55 ዓመት ሲሞላቸው ጡረታ በመውጣት ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተለያይተዋል። ሆኖም ጡረታ ከወጡ ከሁለት ዓመታት በኋላ ዩኒቨርሲቲው ኢመደበኛ በሆነ መልኩ አገልግሎታቸውን ስለፈለገ የኤሜሬትስ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል። ከዛን ጊዜ አንስቶ የፒ.ኤች.ዲ ተማሪዎችን ያማክራሉ።
እንደ አብዛኛው የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የኢመሬትስ ፕሮፌሰር ባህሩ መጽሀፍትና የምርምር ሥራዎች በእንግሊዘኛ ቋንቋ ብቻ የተገደቡ ነበሩ። ሆኖም የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ ዓመት ታሪክ ብቻ አድርጎ በሚቆጥሩ ጎራዎችና ኢትዮጵያ ከሦስት ሺ በላይ ታሪክ ያላት ሀገር ነች በሚል ጎራ መሃል ያለውን ብዥታ ለማጥራት “ኢትዮጵያ የሦስት ሺ ወይስ የመቶ ዓመት ታሪክ” በሚል ርዕስ በመጽሄት የወጣው ጽሁፋቸው በብዙኃኑ እየተባዛ የሀገሬውን ሕዝብ በሚገባው ልክ በሚገባው ቋንቋ እየደረሱት እንዳልሆነ አንቅቷቸዋል። ከዚያ በኋላ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ መጽሀፋቸውን፣ ሀብቴ አባ መላ የተሰኘው የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን የሕይወት ታሪክ፣ በ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአውሮፓና በመካከለኛው ምስራቅ በሚል ርዕስ በ1903 ዓ.ም በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የተጻፈው ዜና መዋዕልና “ፓዮኔርስ ኦፍ ቼንጅ ኢን ኢትዮጵያ” የተሰኘውን መጽሀፋቸውን ፋና ወጊ የለውጥ አቀንቃኞች በሚል ርዕስ አሰናድተው ለአማርኛ አንባቢዎች አቅርበዋል። ይሄም ሥራዎቻቸውን በአማርኛ የመተርጎም ጅምር ከምሁራኑና ከምዕራባውያን በተጨማሪ በብዙኃኑ ዘንድ እንዲታወቁ ረድቷቸዋል። በ2015 ዓ.ም ለሕትመት ያበቁት “ኅብረ ሕይወቴ” የተሰኛው የሕይወት ተሞክሯቸውን የሚዳስሰው መጽሀፋቸው በአንባቢያኑ ዘንድ ምሁሩን ይበልጥ ለመረዳት በር ከፍቷል።
‹‹ስፖርት በጣም እወዳለሁ›› የሚሉት ፕሮፌሰር ባህሩ በተለይ ለእግር ኳስ ያላቸው ስሜት ያይላል። የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ የስፔኑ ላሊጋም ሆነ የጀርመን ቡንደስሊጋ አይቀራቸውም። ሰዎች በመገረም ፕሮፌሰርና እግር ኳስ ምንና ምን ናቸው ሲሉ እንደሚጠይቁ ያነሳሉ። እሳቸው ግን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የስፖርት መምህራቸው ተጽእኖ ውጤት መሆኑን ይገምታሉ። ሜዳ ቴኒስ መጫወቱም ሆነ የሌሎችንም ጨዋታ መከታተሉ ያዝናናቸዋል።
ማህበራዊ ሕይወት፣ በስፖርት፣ ከጓደኞች ጋር መዝናናትና መሰል ነገሮች ‹‹ለሕይወት ጣዕም የሚሰጡ ቅመም›› በማለት ይገልጿቸዋል። እሳቸው መዝናናትን የማየው ለበለጠ ሥራ እንደመዘጋጀትና አዕምሮን አድሶ የበለጠ ለመስራት እንደአነሳሽ ነው ይላሉ። እሳቸው በቻሉት አቅም ሕይወትን በሙሉ አቅማቸው መኖርን ይመርጣሉ። ለመሰል የአካዳሚው ሰዎችም ‹‹ቀለሜዋ› የሚለው ታፔላ ሊለጠፍብን አይገባም›› ይላሉ።
በቤት ውስጥ ሞያ ረገድም አይታሙም። ባለቤታቸው እውቋ የፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ መሰንበት ‹‹በተለያየ አጋጣሚዎች ሥልጠና ስሰጥ ለሴቶች የምመክረው ያላገባችሁ እንደ እኔ ባል አይነት የሚያግዛችሁና የሚረዳችሁ ባል አግቡ›› ብዬ እመክራለሁ የሚሏቸው ልብን የሚያሳርፉ አባወራ ናቸው።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም