
አዲስ አበባ:- የኪነጥበብ ባለሙያዎች ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎች በሚታደሙባቸው መድረኮች ላይ ሲሳተፉ ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማቶች መሆናቸውን በመገንዘብ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አርቲስት ጸጋዬ ደንደና ገለጸ።
አርቲስት ጸጋዬ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበረው ቆይታ እንደገለጸው፤ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የኅብረተሰብ መስታወት እንደመሆናቸው ንግግራቸው የተቆጠበ፣ አለባበሳቸው ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የተላበሰና ድርጊታቸውም መልካም ስነምግባር ያለው መሆን አለበት።
ሆኖም ግን አሁን የሚስተዋለው በውጭ ሀገር ባህል መዋጥና መሳብ ነው ያለው አርቲስት ጸጋዬ፤ በማኅረሰቡም ሆነ በኪነ ጥበብ ባለሙያው ከሀገር ባህል ያፈነገጠ፣ ወጣ ያለ አለባበስ ከለበሰ እንደሰለጠነ የመቁጠር እሳቤ ስለሚስተዋል መታረም ይኖርበታል ብሏል።
“መሰልጠን ባህልን ማክበር ነው፣ ሀገርን ሆኖ መገኘት ነው። ባሕልን ጠብቆ መሰልጠን ይቻላል። ስልጣኔ አዳዲስ አሰራር እና ቴክኖሎጂን በማስገባት መሆን ይኖርበታል። አርቲስቱ ሙያውን የሚያከብር፣ ለሀገር አንድነት የቆመ፣ ሕዝቡን የሚያከብር መሆን ይጠበቅበታል” ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል።
በተለይም ከግብረሰዶማዊነት መራቅ አለባቸው። ድርጊቱን በመቃወምና በመኮነንም ትኩረት አድርጎ መስራት፣ ኅብረተሰቡንም ድርጊቱ ከግብረገብነት ተቃራኒ የሆነ፣ ሊወገዝ እንደሚገባው በማስገንዘብ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል።
የትውልዱን ስነምግባር በማስተካከል በኩል የኪነጥበብ ባለሙያዎች ኃላፊነት አለባቸው። ነገር ግን አንዳንድ ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን በሚገባ እየተወጡ አይደለም ብሏል። ግብረሰዶም በኢትዮጵያ ባህል ነውር የሆነ፣ የስነምግባር ብልሽት በመሆኑም ራሳቸው ማራቅ አለባቸው፣ እንዳይስፋፋም መታገል ይጠበቅባቸዋል ብሏል።
እንደአርቲስቱ ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያውያንም ከማይመጥናቸው ተግባር መራቅ ይጠበቅባቸዋል። ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሀገር እንደመሆኗ ስሟንም ክብሯንም ጠብቃ እንድትቆይ የድርሻቸውን ሊያበረክቱ ይገባል። ሆን ተብሎ ግብረሰዶምን ለማስፋፋት የሚደረገውን እንቅስቃሴ መቃወም ያስፈልጋል።
የኪነጥበብ ባለሙያዎች ይህ ድርጊት እንዳይስፋፋ መታገልም መዋጋትም ይጠበቅባቸዋል። አሁን በጣም ወሳኝ በመሆኑ የኪነጥበብ ባለሙያው የገጠመውን ችግር ለመከላከል መስራት አለበት።
ለሀገር ሰላም መስፈን፣ ለሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እና ለአንድነት ድርሻቸውን መወጣት አለባቸው። የኪነጥበብ ሥራ ሕዝብን ማቀራረብ እንደመሆኑ ባለሙያዎችን ለማቀራረብም እርስ በእርስ እንዲከባበር እና እንዲፋቀር ማኅበራዊ ድርሻን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
የኪነ ጥበብ ባለሙያው ማኅበራዊ ሥራዎች ላይ ኃላፊነት ተጥሎበታል ያለው አርቲስት ጸጋዬ ፤ሕዝብን በመልካም ሥነ ምግባር በማነጽ በሀገር ግንባታ ሥራ ላይ እና በሀገር አንድነት ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።
የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከግብረሰዶማዊነት ራሳቸውን ማራቅ አለባቸው። በሚለብሱት እና በሚያሳዩት እንቅስቃሴ ያልተገባ መልእክት ላለማስተላለፍ ሊጠነቀቁ እንደሚገባቸውም መክሯል። በተለይም በመድረክ ስራዎቻቸው በአለባበስ ቁጥብ በመሆን ለትውልዱ አርአያ መሆን እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያሳሰበው።
የኪነጥበብ ባለሙያዎች ውይይት በማካሄድ ድርጊቱን መኮነን ይጠበቅባቸዋል። በሕዝቡ መካከልም መተማመን እንዲኖር፣ ሰላም እንዲሰፍን እና ፍቅር እንዲጠነክር የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
ባለሙያዎቹ ከሕዝብ እድገት እና ከኅብረተሰቡ ወቅታዊ ሁኔታ እና ስነልቦና አንጻር የተቃኘ ሥራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። የኢትዮጵያን ባህል፣ ወግና ልማድ ለማበላሸት ከውጭ ሀገር ተቀድተው የሚገቡ ልማዶችን መኮነን ይገባል ብሏል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም