ቅጥ ያጣው የእግር ኳስክለቦች ገንዘብ አወጣጥ!

 እግር ኳስ በኢትዮጵያ እንደ አትሌቲክስ ውጤት የሚመዘገብበት ባይሆንም የብዙዎችን ትኩረት ማግኘት ከቻሉትና ግንባር ቀደም ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት ስፖርቶች መካከል ዋነኛው ነው። ነገር ግን ዘመኑንም ሀገርንም የሚመጥን መሆን ተስኖታል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ከአፍሪካ ዋንጫ ምስረታ ጀምሮ ብዙ አስተዋጽኦ አበርክታለች።

ነገርግን የታሪኳን ያህል ማደር ተስኗት የበይ ተመልካች ሆና ትገኛለች። የእግር ኳስ ደረጃዋ በዚህ ሁኔታ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ለእግር ኳስ ተጫዋቾች ከፍተኛ ከፍያን ከሚከፍሉ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ መሆና ግን ለሁሉም እንቆቅልሽ ነው።

በኢትዮጵያ እግር ካስ ገንዘቡ ይወጣል እንጂ ተመልሶ አይገባም፣ ይህ አሉባልታ ሳይሆን አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሃቅ ነው። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የሚረጨው ገንዘብ የተጋነነ ብቻ ሳይሆን የሚፈለገውን ውጤት እንደማያመጣ ተደጋግሞ ተነግሯል።

ሰሚ ግን የለም። የሚወጣው ገንዘብ እግር ኳሱን አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ሳይሆን የግለሰቦች ኪስ ማድለቢያና የደላሎች ሲሳይ ከመሆን ማለፍ ተስኖታል። በዚህም ስፖርቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር የሚችሉ ተስፋ ያላቸው ታዳጊዎች የመጫወት እድል እየተነፈጉ ተስፋ በመቁረጥ ከዘርፉ ይወጣሉ።

ምክንያቱም ክለቦች ለዓመታት ትኩረታቸው የነገ ተስፋዎችን አጎልብቶ መጠቀም ላይ ሳይሆን ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች በትላልቅ ገንዘብ ማዘዋወር ላይ ነው። የዓለም እግር ኳስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መቀየሩን ማንም አይክድም። የእግር ካስ ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ሁኔታ እየተመነደገ በመምጣቱ የሚወጣው ገንዘብም የዚያኑ ያህል ነው።

ያን ያህል ረብጣ ገንዘብ ሲፈስ ግን በምክንያት ነው። በኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚወጣውም ገንዘብ ለምን ዓላማ እንደሚወጣና እንዴት እንደሚወጣ የማይታወቅ ሚስጥራዊ የሆነ አሰራር አለው።

ክለቦች ለዝውውሮች የሚያወጡትም እግር ኳሱ የደረሰበትን ደረጃ የማይገልጽ የተጋነነ እና ግልጽ ያልሆነም ጭምር ነው። ለዚህ ደግሞ ከመጋረጃ ጀርባ መመሳጠሮችና ምዝበራዎች የሚበዙበት ዘርፍ መሆኑ ይበልጥ በር ከፍተል።

በዚህ ረገድ ለመገናኛ ብዙኃንም ጭምር በግልጽ መረጃ ለማግኘት አዳጋች ነው። የገንዘቡ ጉዳይ አይጠቀስም። አንድ ተጫዋች ከአንድ ክለብ ወደ አንዱ ሲሄድ የሄደበት የዝውውር ሂሳብ መታወቅ አለበት። እየሆነ የሚገኘው ግን ተቃራኒ ነው።

ክለቦች ተጫዋቾችን የሚያስፈርሙት (የሚያዘዋውሩት) አቅደውበትና ለሚፈልጉት የቡድን ግንባታ እንዲረዳቸው ሳይሆን ከዝውውሩ የሚያገኘውን ጥቅም አስበው ይመስላል። ከዘርፉ መጠቀሙ አይከፋም፣ የሠራ የልፋቱን ማግኘት አለበት፣ ነገር ግን መሆን ያለበት አዋጭ በሆነ መልኩ ነው። ትርፍና ኪሳራው ተሰልቶ መሆን አለበት።

የሚያሳዝነው ነገር እግር ኳሱንም የሚመራው አካል ዝምታን መርጦ ተመልካች መሆኑ ነው። ከዓመታት በፊት የእግር ኳስ ተጫዋቾች ደመወዝ ክፍያ ጣሪያ ነካ ተብሎ ህግ ቢወጣም ሥራ ላይ ሊውል አልቻለም። ለዚህም ክለቦች ወረቀት ላይ የሚያስፈርሙት ሌላ ከጀርባ የሚዋዋሉት ሌላ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ የአንድ ተጫዋች ደመወዝ ከ50ሺ ብር እንዳይበልጥ ያስቀመጠውን ገደብ ሊያነሳ ችሏል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ እየተሟሟቀ የመጣው በተለይ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ነው። የፕሮፌሽናል እግር ኳስ የንግድ እንቅስቃሴ ዋና መሰረት የዝውውር ገበያ ነው። የፕሪሚየር ሊግ ፉክክር በሶስት እና አራት ክለቦች መካከል እየተጠናከረ ከመጣ በኋላ ገበያው ተሟሙቋል ማለት ይቻላል።

የቀድሞው ታዋቂ ተጫዋች መንግስቱ ወርቁ ድሮ ኳስ ተጫዋቾች ስፖርቱን ለፍቅር እንጂ ለገንዘብ አይጫወቱም ይሉ ነበር። ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ በተጨዋችነት ዘመናቸው መጀመሪያ ለጊዮርጊስ ሲጫወቱ ከልምምድ በኋላ ስሙኒ ይከፈላቸው እንደነበር በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር። ዛሬ እንደዚያ ይሁን ማለት አይቻልም፤ ነገር ግን በቅጡ ይሁን።

ካለፈው 4 ዓመት ወዲህ ግን ነገሮች ተቀይረዋል። በ50ሺ ብር የፊርማ ክፍያ ተጀምሮ፤ ወደ 100ሺ ብር ከዚያም ወደ 200ሺ ብር፤ 300ሺብር እየሆነ ቆይቶ ዛሬ የአንድ ተጨዋች የዝውውር ሂሳብ በአማካይ ወደ 500 ሺ ብር ደርሷል። በዚህ የክረምት ዝውውር እንኳን እስከ 15 ሚሊዮን የወጣበት ተጨዋች እንዳለ ያልሰማ የለም።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ የንግድ እንቅስቃሴ እንዳያድግ ተፅእኖ የፈጠረው በከፍተኛ የሀገር ውስጥ ውድድሮች ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች ከሞላ ጎደል በመንግሥት የበጀት ድጎማ መንቀሳቀሳቸው እንደሆነ ሲያከራክር ቆይተል። ለዚህም የቀድሞው የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ከሆነ ዓመት በፊት የሠራውን ጥናት መጥቀስ ይቻላል።

በዚያ ጥናት መሰረት በፕሪሚየር ሊግ ተወዳዳሪ ከሆኑ ክለቦች 84 በመቶ የሚሆኑት በባለቤትነት የሚተዳደሩትና የገንዘብ ድጎማ ያላቸው ከመንግሥት ተቋማት መሆኑን፤ በግል ባለቤትነት የተያዙት 8 በመቶ፤ ሕዝባዊ አስተዳደር ያላቸው 13 በመቶ እንዲሁም በግል እና በህዝብ የሚደገፉ ክለቦች 4 በመቶ እንደሚሆኑ በዝርዝር ማስቀመጡን መጥቀስ ይቻላል።

በመንግሥት ተቋማት የሚደጎሙ ክለቦች በዓመት እስከ 50 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚያንቀሳቅሱ ሲታወቅ እንደ ጊዮርጊስ አይነት ክለቦች በየዓመቱ ከ16 እስከ 25 ሚሊዮን ብር እንደሚያንቀሳቅሱ ይገመታል። ይህ አሃዝ ዛሬ ላይ ከእጥፍም በላይ ማደጉን ልብ ይላል።

ይሄ የበጀት አቅም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን የሌሎች ሀገራት ተጨዋቾች በተፈለገው አቅም ለማሰባሰብ፤ የሀገር ውስጥ ተጨዋቾችን የዝውውር ሂሳብ እና ደመወዝ በከፍተኛ ፍጥነት ለማሳደግ እና የሊግ የውድድር ደረጃን በፕሮፌሽናል ደረጃ ለማጠናከር በቂ አይደለም ተብሎ ይታመናል።

ወደዚያ ደረጃ ለመምጣት ግን አማራጩ የሕዝብ ሀብት በከንቱ መርጨት አይደለም። ስፖርቱን በከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ለማካሄድ የክለቦች ባለቤትነት ከመንግሥት ተቋማት ይልቅ በባለሀብቶች እና በደጋፊ ማኅበራት ማስተዳደር ሁነኛ አመራጭ እንደሆነ በአፍሪካ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች በሚደረጉ ፕሮፌሽናል ሊጎች ተመክሮ በማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ 16 ክለቦች እያንዳንዳቸው በዓመት ለተጨዋቾች ደመወዝ ብቻ በአማካይ 40 ሚሊዮን ብር እንደሚያወጡ ከዓመታት በፊት የነበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዛሬ ላይ ግን እስከ መቶ ሚሊዮን እንደሚጠጋ በመረጃዎች መሞገት ይቻላል። ይህ የሚሆነው ብዙ ቀዳዳ ባለባት አንዲት ድሃ ሀገር መሆኑ ያስተዛዝባል።

የሚመለከተው አካል ለዚህ ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ በሥነ ሥርዓት እና የሀገሪቷን የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ ሊመራው ይገባል። ለእግር ኳስ የሚበጀተው ገንዘብ ታዳጊዎች ተኮር አድርጎ ሥራ ላይ ቢውል እሰየው። ግን አልሆነም።

በተደጋጋሚ እንደሚጠቀሰው ገንዘቡን በተወሰነ መልኩ የእግር ኳስ ታዳጊዎች ላይ አውሎ ለነሱ የሚመች ሁኔታን በመፍጠር የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንዲያድግና ትርፋማ ኢንዱስትሪ እንዲሆን መሰራት አለበት። በዚህም የተጋነኑና ግልጽነት የሚያንሳቸውን ክፍያዎች በማስቀረት የሀገርን ሀብት ከብክነት መጠበቅ ይገባል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You