ፍቅረማርያም ያደሳ በኦሊምፒክ ቦክስ ማጣሪያ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቀቀ

በሴኔጋል ዳካር እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ዞን የኦሊምፒክ ቦክስ ስፖርት ማጣሪያ ውድድር በ57 ኪሎ ግራም የተፋለመው ፍቅረማሪያም ያደሳ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። ኢትዮጵያዊው የቡጢ ተፋላሚ በአምስተኛና በመጨረሻው ውድድር ከናይጄሪያው ጆሽዋ ኦሞሌ ጋር እልህ አስጨራሽ የሶስት ዙር ፍልሚያ ቢያደርግም 3ለ2 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ከፓሪሱ 2024 ኦሊምፒክ ውጪ ሆኗል።

ፍቅረማርያም (ጊችሮ ነብሮ) በጀግንነት በተፋለመባቸው የመጨረሻው ውድድር ውጤት ባይቀናውም እስከ ፍፃሜ ተፋላሚነት ድንቅ ብቃት ማሳየት ችሏል። ትናንት ለተካሄደው የፍፃሜ ፍልሚያም የበቃው የአራት ሀገራት የቦክስ ተወዳዳሪዎችን በአስደናቂ ብቃት አሸንፎ ነው።

ፍቅረማርያም በመጀመሪያው ውድድር የኬኒያውን ተወዳዳሪ በአንደኛው ዙር በፍፁም የበላይነትና ድንቅ እንቅስቃሴ በዝረራ በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ የቻለ ሲሆን፣ በሁለተኛው ግጥሚያ የሊቢያውን ተወዳዳሪ በሁለተኛ ዙር በዳኛ ውሳኔ ማሸነፍ ችሏል። በሶስተኛው ፍልሚያ ደግሞ የሞዛንቢክን ተወዳዳሪ በነጥብ አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አልፏል። በአራተኛው ውድድር ለፍፃሜ ለማለፍ የአልጄሪያውን ተወዳዳሪ ገጥሞም በነጥብ 5ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነበር ለትናንቱ ፍፃሜ የደረሰው።

በሴኔጋል ዳካር ከጳጉሜ 4 እስከ መስከረም 4 ድረስ በተካሄደው የአፍሪካ ሀገራት የኦሊምፒክ የቦክስ የማጣሪያ ውድድር 41 ሀገራት የተሳተፉ ሲሆን በመድረኩም 235 ቦክሰኞች መሳተፍ ችለዋል። ኢትዮጵያም በዚህ ውድድር ላይ በአራት ወንድና በሁለት ሴት በድምሩ ስድስት ቦክሰኞችን ማሳተፍ ችላለች::

ኢትዮጵያ ከ1952 ጀምሮ በኦሊምፒክ የቦክስ ውድድር ለመሳተፍ በአስመራና አዲስ አበባ ትልቅ እንቅስቃሴ የተደረገ ቢሆንም ብሔራዊ ፌዴሬሽን ገና ስላልተቋቋመ መሳተፍ አልቻለችም። በ1964 ግን በቶኪዮ ኦሊምፒክ የመጀመሪያ ተሳትፎ ማድረግ ችላለች። ከዚያ በኋላም 1968 ሜክሲኮ፣ 1972 ሙኒክ፣ 1980 ሞስኮ፣ 1992 ባርሴሎና፣ 1996 አትላንታ፣ 2000 ሲድኒ፣ 2004 አቴንስ፣ 2008 ቤጂንግ ኦሊምፒኮች መሳተፍ ችላለች። ለመጨረሻ ጊዜ በተሳተፈችበት የቤጂንግ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ ወደ ውድድሩ ያቀናው የቦክስ ተፋላሚ ክብደት በመጨመሩ መፋለም እንዳልቻለ አይዘነጋም። ከለንደን፣ ሪዮና ቶኪዮ በኋላ በኦሊምፒክ ተሳታፊ ለመሆን ጫፍ የደረሰው ቦክሰኛ ፍቅረማርያም ቶሎሳ ሴኔጋል ላይ ባሳየው ድንቅ ብቃት ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም መጨረሻ ላይ ሊሳካለት አልቻለም።

ኢትዮጵያን በሁለቱም ጾታዎች በማጣሪያ ውድድሩ የወከሉ ቦክሰኞች በ51 ኪሎ ግራም ፍትሐዊ ጡማይ፣ በ63 ኪሎ ግራም አብረሃም አለም፣ እና በ71 ኪሎ ግራም አቤኔዘር ዳንኤል የተሳተፉ ወንድ የቡጢ ተወዳዳሪዎች ናቸው። በሴቶች 51 ኪሎ ግራም ቤተልሔም ገዛኸኝ እና በ54 ኪሎ ግራም ሀገሬ እማኙ ኢትዮጵያን በመወከል ተሳትፎን ያደረጉ ናቸው። በሴቶች ሀገሬ እመኙ ጥሩ ሚባል ፉክክርና ተጋድሎን አድርጋ ሳይሳካላት መቅረተም የሚያስቆጭ ነበር።

ቦክሰኞች ድል ባይቀናቸውም የውድድር ልምድ ያካበቱና በርካታ ውድድሮች ላይ መሳተፍ የቻሉ ሲሆን ብሔራዊ ቡድኑን ከዚህ ቀደም በኡዝቤኪስታን በተካሄደው የዓለም ቦክስ ቻምፒዮና ወክለው መሳተፍ የቻሉ ናቸው። ከነዚህም ዋነኛው ቦክሰኛ ፍቅረማርያም ያደሳ ኢትዮጵያን በመወከል በአፍሪካ ወጣቶች ቻምፒዮና ጥሩ ተሳትፎን ማድረግ ችሏል። ቦክሰኛው በኒያላ ቦክስ ክለብና ቡድኑ ጥሩ ዝግጅትን በማድረግ የስነልቦና እና የራስ መተማመን ደረጃ ላይ ሆኖ ውድድሩን ማድረግ እንደቻለም ታውቋል።

በዚህ የአፍሪካ ሀገራት የማጣርሪያ ውድድር ውጤት የቀናቸው ቦክሰኞች በቀጣዩ የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ አፍሪካን የሚወክሉ ሲሆን በወንዶች በ7 የተለያዩ ኪሎ ግራሞች በሴቶች ደግሞ በስድስት የተለያዩ ኪሎ ግራሞች አፍሪካን ወክለው የሚፋለሙ ይሆናል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You