የማንኖርባቸው «የመልካም ምኞት መግለጫዎች»

የመነሻችን ወግ፤

ዓመታት በተለዋወጡ ቁጥር በየቋንቋውና በየባህሉ «እንኳን አደረሰህ/አደረሰሽ/አደረሳችሁ» መባባል የተለመደ የመልካም ምኞት መግለጫ ነው፡፡ መልካም ምኞቱ በዚህ ብቻ አያበቃም «ዓመቱ የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅርና የስኬት ይሁን» እየተባባሉ መመራረቅም የተለመደ ባህል ነው፡፡ መልካም ምኞትን መመኘት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ውጤታማ የሚያደርገው ምኞትን በተግባር ለውጦ በኑሮ መተርጎም ሲቻል ነው፡፡ ለጊዜው ይህንን አንኳር ሃሳብ እዚህ ላይ ገታ አድርገን ብዕረ መንገዳችንን ተዘውትሮ የሚነገር አንድ የተቃርኖ አባባል እናስታውስ፡፡

ብዙ ዜጎች በጭውውት መካከል፣ አልፎ አልፎም በመደበኛ መድረኮች እና በየሚዲያው ሳይቀር «አዲስ ዓመት» የሚለውን አባባል ክፉኛ ሲተቹና ሲቃወሙ ይደመጣሉ፡፡ ይህንን አባባል ጮክ አድርገው የሚያስደምጡ ወገኖች ምክንያታቸው ባያሳምንም እምነታቸው ግን የሚከተለውን ይመስላል፡፡ እንደነርሱ አባባል «ቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራትና ዓመታት መለዋወጣቸው ወይንም ዞሮ መምጣታቸው የተለመደ አሰልቺ የተፈጥሮ ሥርዓት ስለሆነ ሊያስደንቅና መስከረም ሲጠባ አዲስ ዓመት ሊያሰኝ አይችልም» ይላሉ፡፡

«ሰኞ እንደ ነበረው ያው ሰኞ ነው፡፡ መስከረምም መስከረም፡፡ ክረምትና በጋም መፈራረቃቸው የተለመደ ነው፡፡ አንደኛው ዓመት ተሰናብቶ ሌላኛው ዓመት መተካቱ እንደ አዲስ ሊቆጠር ከቶውንም አይገባውም ወዘተ.» በሚል አመክንዮ መከራከራቸው ውሃ አንስቶ የሚያሳምን እውነታ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ጸሐፊ እምነትና የግል አመላከከት የራስን ሃሳብ በነፃነት መግለጽም ሆነ መከራከር ችግር ይኖረዋል ብሎ ባያምንም፤ ነገር ግን በገሃድ ከሚታይ እውነታና ከተፈጥሮ ባህርይ ጋር በሚቃረን አስተሳሰብ «ግዙፍ እውነታን» መካድና መቃወም አግባብነት ይኖረዋል ተብሎ ሊታመን አይገባም፡፡

እንኳን ወራትና ዓመታት ቀርተው እያንዳንዱ ቀን ሳይቀር አዲስ ስለመሆኑ «ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው…» የሚለውን የቅዱስ መጽሐፍ ማረጋገጫ ማስታወስ ይቻላል፡፡ ይህ ጠንካራ ማስረጃ እንዳለ ሆኖ «አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ የሚተካበትን የተፈጥሮ ዑደትና የሽግግር ሥርዓትን በማስተዋልና በመመርመር ብቻ «አዲስነቱ» አጃኢብ አሰኝቶ እጅን በአፍ ላይ ማስጫኑን ግን መካድ አይቻልም፡፡ ከቅዱስ መጽሐፍ አንድ እውነታ እናክል፡፡

«እነሆ! ክረምቱ አለፈ፣

ዝናቡም አባርቶ አበቃ፤

አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤

የዝማሬ ወቅት ደረሰ፤

የርግቦች ድምጽም በምድራችን ተሰማ፤

በለስ ፍሬዋን አፈራች፤

የአበቡ ወይኖችም መዓዛቸውን ሰጡ፡፡» (መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ምዕ. 2፡11 -13)

ክረምቱ ተጠናቆ ወደ በጋው ወራት የምንገባው በተለመዱ ክስተቶች ብቻ ታጅበን አይደለም፡፡ ደረቀው የነበሩ ዕፅዋት ለምልመው ሲያረግዱ መመልከት በእጅጉ ለነፍስ ሀሴት የሚሰጥ ክስተት ነው፡፡ አበቦች ማንም ሳይዘራቸውና ሳይኮተኩታቸው በየቦታው አብበው አካበቢን ማስዋብ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆችን ስሜት ጭምር የሚያማልሉት በመግነጢሳዊ አፈጣጠራቸው ጭምር ነው፡፡

የደረቀው ለምልሞ፣ የጠወለገው ተነቃቅቶ፣ የደፈረሰው ጠርቶ፤ አእዋፍ በደስታ ሲከንፉ ማስተዋል፣ ከብቶች እምቧ እያሉ ሲቦርቁ መመልከት፣ የምድርና የባህር ፍጥረታት በራሳቸው ዓለም ሲብነሸነሹ ማስተዋል በአዲስነቱ አዲስ ዓመትን መቀበል አዲስ ካልተባለ ሌላ ምን የተሻለ «አዲስ ነገር» ሊገኝ ይችላል?

ስለዚህ፤ «አሮጌው» 2015 ዓ.ም ተሸኝቶ «አዲሱን» 2016 ዓ.ም በመቀበላችን ፈጣሪን እያመሠገንን ተፈጥሮን በማድነቅ «ዕንቁጣጣሽ በየዓመቱ ያምጣሽ!» እያልን በመዘመር በአዲስ ተስፋና ምኞት «በአዲሱ ዓመት» ልንነቃቃ ይገባል፡፡

የማንኖርባቸው የአዲስ ዓመት ምኞቶች፤

ይልቅስ መወያየት ካለብን፣ ወይንም ጠንከር አድርገንም ቢሆን ልንከራከርበት የሚገባው «የዓመታት መቀያየርን አዲስ እንበለው? ወይስ አንበለው?» በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሳይሆን ከአዲስ ዓመት ምኞታችን ጋር በተያያዘ ጉዳይ ሊሆን ይገባል፡፡ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ምኞታችንን የምንገልጽባቸው የተለመዱ አባባሎች እንደነበሩ ሳይበረዙና ሳይከለሱ ከዓመት ዓመት እየተንከባለሉ መሄዳቸው አልተቋረጠም፡፡

«አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የደስታ፣ የብልፅግና፣ የፍቅርና የስኬት ወዘተ. ዓመት ይሁንልን» ብሎ ለዘመድ አዝማድ፣ ለወዳጅና ለጓደኛ፣ በቅርብ ለሚተዋወቁትና በአጋጣሚ ከተገናኙት ሰው ጋር ምኞትን መግለጽ የነበረ፣ ያለና የሚኖር ልማድና ባህል ነው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ አባባሎች የእኛ ነባር ዕሴቶች ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ የጋራ መታወቂያዎች ናቸው፡፡

ቀደም ባሉት ዘመናት የአዲስ ዓመትን ስንቀበል የኖርነው እቅፍ የተፈጥሮ አበቦችን ወይንም ጭብጥ እርጥብ ሣርን ለወዳጅና ለቅርብ ዘመድ በማበርከት «ዓመቱ በሆት ስለገባ!» እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መልካም ምኞታችንን እየገለጽን ነበር፡፡ እያደርም የስልክ አገልግሎት ሲስፋፋ «ሃሎ!» በመባባል ደስታችንን እንጋራ ነበር፡፡ በፖስታ፣ በፖስት ካርድ ወይንም የተለያዩ ማስታወሻዎችን በመላላክም አዳዲስ ዓመታትን ስናከብር ኖረናል፡፡

ዛሬ ሙሉ ለሙሉ ቀርቷል ባይባልም ታዳጊ ሕፃናት በነጭ ወረቀት ላይ አበቦችንና ልዩ ልዩ ወካይ ሥዕሎችን በመሳልና በቀለማት በማስዋብ ቤት ለቤት እየዞሩ በመስጠት የአዲስ ዓመት መግባትን ብሥራት ያበሥሩ ነበር፡፡ የሕፃናቱ ጉብኝት በእግረ መንገዱ የገንዘብም ሆነ የምግብ ዳረጎት ማስገኘቱ እውነት ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ይህ ባህል እየተንገዳገደም ቢሆን እንደቀጠለ አለ፡፡

በዚህ በተያያዝነው ፈጣን የቴክኖሎጂ ዘመንም ከላይ የተዘረዘሩት የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት «አዋጆች» እንዳሉ ሆነው በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ጭምር እጅግ የተዋቡ አበቦችንና ሥዕላ ሥዕሎችን እየመረጡ ለወዳጅ ዘመድ፣ ለጓደኛና ለሥራ ባልደረባ ወይንም ለሰዎች ሁሉ በመላክ «እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገረን!» መባባል በስፋት ባህል ሆኗል፡፡ «ከዘመን ዘመን» መባሉ «ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት» ለማለት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ባህልም እንበለው አዲስ ልማድ ብቻ የሆነው ቢሆንም ሌላውን ደስ ለማሰኘት ቴክኖሎጂውን መጠቀም ክፋት የለውም፡፡

ላንኖርበት የተለበጥንበት «መልካም ምኞት»፤

«አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅር፣ የስኬት፣ ‹የብልፅግና› ይሁንልን!» ተባብለንና ተመራርቀን በተቀበልነው 2015 ዓ.ም ምኞታችንና ግብራችን ተጣርሶ የደረሰብንን ብሔራዊ ኪሳራና ሀገራዊ ጉዳት በሚገባ እናስታውሳለን፡፡ እንርሳውም ብንል በጉልህ የሚታየው የጉዳታችን ጠባሳ ሊሸፈን የሚችል አይደለም፡፡

ከላይ የዘረዘርናቸው ምኞቶች ተዘንግተውም ይሁን ተንቀው በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የሰላም ርግብ በነፃነት እንዳትበር በእብሪት፣ በትምክህት፣ በማን አለብኝነት፣ በእልህና በትዕቢት ወንጭፎች እያሳደድን አቁስለናታል፤ እንዳታገግምም እላይ በላይ እያቆሰልን ገመምተኛ አድርገናታል፡፡

በ2015 ዓ.ም መቀበያ ዋዜማና የአዲስ ዓመቱ መግቢያ ዕለት ስለ ፍቅር፣ ስለ ወንድማማችነትና እህትማማችነት በመዘመር እንዳልተደናነቅን ሁሉ ውሎ ሳያድር ምኞታችንን ገደል ሰደን በሰይፍ እየተሞሻለቅን ኢትዮጵያን የኀዘን ማቅ አልብሰናታል፡፡ ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችንን ተነጋግረን ከመፍታት ይልቅ በልብ ድንዳኔ ጡንቻችንን እየተሞካከርን እርስ በእርስ ተፋልመናል፡፡

«ጤና ይስጥልን!» ብለን በመልካም ቃል አዲሱን ዓመት ተቀብለን ገና የለኮስነው ደመራ «ነዶ ሳያልቅ» ተሽቀዳድመን ከወንድም እህቶቻችን ጋር በክላሽንኮቭ ጠብመንጃ እየተፋለምን እኛው እየጣልን፤ እኛው ወድቀናል፡፡ ስለ ‹ብልፅግና› ቸር ተመኝተን ድህነት እንዲሰለጥንብን፣ የዕለት እንጀራችን እንዲመርብን ጫንቃችንን አደንድነንና ህሊናችንን ደፍነን እልህ ተጋብተን ይዋጣልንን በመምረጥ ገድሎ መሞትን ምርጫችን አድርገናል፡፡ ስለ ስኬት ተመኝተን ዓመቱን በእንባ አሳልፈናል፡፡

ዛሬስ ከምኞታችን ማግሥት የአምናው እልኻችን እንዳለ ይቀጥል?

2016 ዓ.ምን የተቀበልነው እንደተለመደው የመልካም ምኞት መግለጫዎችን እየተለዋወጥን ነው፡፡ «መልካም አዲስ ዓመት» ባልንበት አፋችን እርግማን ማዝነባችንን አንክድም፣ ፍቅርን ባስተላለፈው አንደበታችን «ጠብ መዝራታችንን» ብንክድ ዋሾ እንሆናለን፡፡ ስለ ስኬት ምኞታችንን ገልጸን «ጉስቁልናን መምረጣችንን» አሌ ብንል ከኅሊናችን ጋር ጠብ መፍጠሩ አያዋጣም፡፡ ስለ ተስፋ አውጀን «ሀገራዊ ተስፋችንን ለመቅበር» ጉድጓድ መማሳችንን ብናድበሰብስ እርስ በእርስ ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪ ጋር ሳይቀር መጋጨታችን አይቀርም፡፡

እውነት እውነቱን እንነጋገር ካልን አዲሱን ዓመት የተቀበልነው በደስታና በፈካ ፊት ሳይሆን በትካዜና በኀዘን ውስጥ እየዋኘን መሆኑን ባንገልጽ ኅሊናችን ራሱ ይታዘበናል፡፡ ከንግግር ይልቅ ጥይትን መምረጥ፣ ከውይይት ይልቅ በእልህ መገንነገን፣ ዝቅ ብሎ ለይቅርታ ከማጎንበስ ይልቅ ልብንና መንፈስን እንደ ብረት አደንድኖ እልህ መያያዝ የሚያስታውሰን «ብዙ ጊዜ ተዘልፎ አንገቱን ያደነደነ ድንገት ይሰበራል፤ ፈውስም የለውም» (ምሳሌ 29፡1-2) የሚለውን የጠቢቡን አባባል ነው፡፡

ኢትዮጵያ ታማለች፡፡ ችግሩ በጠና ታማ አልጋ ላይ የወደቀችውን ሀገር እያንዳንዱ ዜጋ ከላይ እስከ ታች ለፈውሷ ከመሥራት ይልቅ በአንደበት ብቻ «ሰላም! ሰላም! ሰላም!» እያለ ከቅን ልብ የሚመነጭ ምኞት አስመስሎ በለበጣ የተሸፈነ ሽንገላን መምረጡ ነው፡፡

«የልማትና የፍትሕ ርሃባችን ማስታገሻ ሰላምና ሰላም ብቻ ነው!» እያሉ በጓዳ የሚንሾካሾኩ እና በአደባባይ የሚደሰኩሩ ፖለቲከኞችም ሆኑ «በነፍጥ የሚፋለሙ ኃይሎች» ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ቢረጋጉ ለእነርሱም ሆነ ለሕዝብ በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ ሀገር በዘርፈ ብዙ መገለጫዎች ቁልቁል እየዘቀጠች ካለችበት አደጋም ልትተርፍ ትችላለች፡፡

ምነው የእኛ መከራ እንዲህ ሊበዛ ቻለ? «ሠፈርተኛው ሁሉ እሣት ጫሪ ነው…» እንዳለው ዜመኛ በጠብ «ገል» ረመጥ ይዞ እሣቱን ለማጋጋል መሞከር ከቶውን ለማን ይጠቅማል? ሲመርቁ «አሜን!» እያልን በረከታቸውን የተቀበልነው የሀገር ሽማግሌዎች የት ገቡ? በመንፈሳዊ ሥልጣናቸው ሲባርኩና ሲመርቁ ዝቅ ብለን መንፈሳችንን ያስገዛንላቸው የሃይማኖት አባቶች ድምጻቸው ስለምን ጮክ ብሎ አልደመጥ አለ፡፡ በሚያራራ ምክራቸውና በእናትነት ቋንቋ ሲገስጹን መልስ ለመስጠት እንኳን የማንዳፈራቸው እናቶች ስለምን ዝምታን መርጠው በየጓዳቸው ተከተቱ፡፡

ፈርተናል! ስለምን ፈራችሁ ተብለን ልንጠየቅ አይገባም፡፡ የፈራነው የነገዋ ኢትዮጵያ ዕድል ፈንታ አላምር ስለሚለን ነው፡፡ ፈርተናል! የፈራነው አዲሱን የ2016 ዓመት ስንቀበል «ዓመቱ የሰላም የፍቅር፣ የጤና፣ የስኬት፣ የበረከትና የብልፅግና ይሁንልን» እየተባባልን መልካም ምኞት መለዋወጣችን ከንቱ ሆኖ የሚቀር እየመሰለን ነው፡፡

ፈርተናል! ስለምን ፈራችሁ ብሎ የሚሞግተን ራሱ ፈሪ ስለሆነ አንፈራውም፡፡ የሚሻለው ይቅር ተባብሎ ጠብመንጃን ወደ ማረሻ መለወጥ ነው፡፡ የሚበጀው ለሰላም ተሸንፎ የጦርን የቦ መዘቅዘቅ ብቻ ነው፡፡ የሚሻለው ለአሸናፊው ማቅራራት ለተሸናፊው ከንፈር መምጠጥ ሳይሆን ራስን የሰላም ሰው ማድረግ ነው። እንደ መልካሙ ምኞታችን ግብራችንም ይስመርልን፡፡ «ልብ ያለው ልብ ያድርግ» በማለት የልብን ስፋት ያስተማሩን ቀደምት ወላጆቻችን እንደም ብልሆች ነበሩ? ሰላም ለሕዝባችን፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ፡፡

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

 የሥነ ጽሑፍና የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ ናቸው። የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርን ለዘጠኝ ዓመታት ያህል በፕሬዚዳንትነት መርተዋል። ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ፤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ታትመው በሚሠራጩ የተለያዩ የኅትመት ውጤቶች ላይ (ዳግላስ ጴጥሮስ) በሚል የብዕር ስሙ በርካታ ጽሑፎችን አስነብበውናል። በግላቸው 12፣ ከሌሎች ጸሐፍት ጋር በርካታ መጻሕፍትን ለአንባብያን አቅርበዋል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You