ያልተሰሙ ድምጾች…

እንደመነሻ

ዕለቱ አዲስ ዓመት ሊገባ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀሩት የዓውደ ዓመት ዋዜማ ነው፡፡ ሁሌም ዓመት በዓል ሲደርስ የሚኖረው ግርግርና ዝግጅት ዛሬም ቀጥሏል፡፡ አዎ! አውደ ዓመት ነው፡፡ ያውም አዲስ ዓመት፡፡ ይህን ጊዜ ሙስሊም ክርስቲያኑ በእኩል ይጋራዋል፡፡ አዲስ ዓመት የእከሌ ብቻ አይባልም፡፡ ሁሉም በአንድ ያከብረዋል ፡፡

ዘመን መለወጫ ለብዙዎች የአዲስ ብስራት ምልክት፣ የመኖራቸው ብሩህ ተስፋ ነው፡፡ በርካቶች አሮጌውን ሸኝተው አዲሱን ሲቀበሉ ውስጣቸው ለሌላ ዕቅድ ይዘጋጃል፡፡ አዲስ ዓመት ሲመጣ ከፊት ከጀርባው መልካም ትርጉም ይዞ ነው፡፡ ይህ ጊዜ ከበዓላት ሁሉ ይለያል፡፡ ከአውደ አመቶች ልቆና ደምቆ ይታያል፡፡

በአዲስ ዓመቱ ዋዜማ በ‹‹በጎ ፈቃድ ቀን›› ከፊቴ የቆሙት ወገኖች ግን ይህ ዓይነቱ የተስፋ ጭላንጭል ውስጣቸው ያለ አይመስልም፡፡ በሁሉም ገጽታ ኀዘን ከጉስቁልና ይነበባል፡፡ አብዛኞቹ በትካዜ እንደተዋጡ ነው፡፡ ገሚሶቹ የውስጣቸውን እያወጉ ስለብሶታቸው ማልቀስ፣ ማንባት ይዘዋል፡፡

ከወላጆቻቸው ጋር የመጡት ሕፃናት ይህ እውነት የገባቸው አይመስልም፡፡ እንደ ልጅነታቸው ከወዲያ ወዲህ ይቦርቃሉ፣ ይሮጣሉ፡፡ ነፍስ ያወቁት ደግሞ የእናቶቻቸውን ስሜት ተጋርተዋል፡፡ ፊታቸው ያለ ሳቅ ፈገግታ ይነበባል፡፡

 ዕለቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ታስቦ የሚውለው ‹‹የበጎ ፈቃድ ቀን›› ነው፡፡ በዚህ ቀን በርካቶች ሌሎችን በበጎነት ይጎበኛሉ፣ የአቅማቸውን አካፍለው፣ የውስጥ ስሜትን ይጋራሉ፡፡ አሁን ላይ ይህ የአብሮነት ባህል መለመድ ጀምሯል፡፡ ዕንባን የሚያብሱ፣ ችግርን የሚጋሩ ወገኖች እየበረከቱ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመሰብሰቢያ አዳራሽ የታደሙት ሴቶች ለቤቱ እንግዶች አይደሉም፡፡ አምናም ይህን ጊዜ በዚህ ስፍራ ተገኝተው የቀኑን ትርጉም ተጋርተዋል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ለየት ባለ ዝግጅት የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች ከዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ጋር በመቀናጀት ‹‹አለናችሁ›› ብለዋቸዋል፡፡

ለዓውደ ዓመቱ ጓዳ ለእያንዳንዳቸው ሃምሳ ኪሎ ዱቄት፣ ማካሮኒና ፈሳሽ ዘይት ለስጦታ ተዘጋጅቷል። አብዛኞቹ ዓይናቸውን አላመኑትም፡፡ በአድናቆት የሚያተውሉ፣ በሆነላቸው ሁሉ አብዝተው የሚያመሰግኑ ወገኖች ገጽታቸው ወገግ ብሏል፡፡

ሕፃናት ልጆቻቸው ለእነሱ የሚበጁ የትምህርት ቁሳቁሶች በመኖራቸው ተደስተዋል፡፡ ሁሉም የዝግጅቱን መጀመር እየጠበቁ ነው፡፡ የበጎ ቀን ስጦታዎች ከመበርከታቸው በፊት በአዳራሹ የተገኙት ወገኖች የልባቸውን ይተነፍሱ ዘንድ ዕድል ተሰጣቸው፡፡

በዝግጅቱ ከታደሙት መሀል የመጀመሪያዋ ተናጋሪ ከነበረችበት ተነስታ በድንገት ስትወጣ አየኋት። አስቀድማ አምርራ እያለቀሰች መቆየቷ ትዝ አለኝ፡፡ ልክ እንደኔ ሁሉ ሌሎች ዓይኖች አተኮሩባት፡፡ ወደ መሀል ቀርባ ንግግር ከመጀመሯ ፊቷ መለዋወጥ ያዘ። ኀዘን ያጠላው ገጽታዋ በዕንባ ሊታጠብ አልዘገየም፡፡ በምስጋና የታጀበው ቃል ደግሞ ብቻውን አልተገለጸም። የሕይወት ምስጢራት ፣ የኑሮ ፈተናዎችን ማሳየቱ አልቀረም፡፡

ወጣቷ ተናጋሪ የታዳሚውን ውስጠት በኀዘን አስደፋች፡፡ ከአንደበቷ የሚፈልቁ እውነታዎች የእያንዳንዱን አድማጭ ስሜት ሊፈትኑት ግድ ሆነ፡፡ በዕንባ የታጀበ ሀቅ፣ በኀዘን የተሰበረ እውነታ እንዲህ መሰማት ጀመረ፡፡

‹‹እማዬ ! ዱቄቱ ላይ ተኝተን ፎቶ እንነሳ ››

‹‹አንድ ወር ሙሉ የደከምኩበትን ገንዘብ ያገኘሁት ዛሬ ነበር፡፡ አንድ ሁለት ብዬ ሰባት መቶ ብር ቆጠርኩ። ይህ የላቤ ወዝ፣ የጉልበቴ ዋጋ ነው፡፡ አማራጭ የለኝም። ገንዘቡ ውሎ ካደረ ይጠፋብኛል፡፡ በዚህ ብር ላደርግ የምችለው ደግሞ ጤፍ መግዛት ብቻ ነው፡፡ ሰባት መቶ ብሩን ይዤ ከገበያ ሄድኩ፡፡ አምስት ኪሎ ጤፍ ተመዝኖልኝ ይዤው ወጣሁ፡፡ ወዲያው ምን እንደማደርገው ጨነቀኝ፡፡

ጤፉን ማበጠር፣ ማነፈስ አልፈለኩም፡፡ ይህን ከሞከርኩ ሊያልቅብኝ ነው፡፡ አሁንም ጭንቅ ጥብብ አለኝ፡፡ ስጋት ቢይዘኝ ጤፉን ማበጠር ተውኩት። በዚህ ስሜት ሳለሁ በድንገት አንድ የስልክ ጥሪ ለጆሮዬ ደረሰ፡፡ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ወይዘሮ ብርሃኔ ደመቀ ነበረች።

የደወለችበትን ምክንያት ስትነግረኝ በእጅጉ ደነገጥኩ፡፡ ልክ እንደአምናው እርዳታ ሊሰጠኝ መሆኑን ስሰማ በእጅጉ ገረመኝ፡፡ ውስጥ ደርሼ ሃምሳ ኪሎ ዱቄቱን ስመለከት ደግሞ ሸርተት ያልኩ እስኪመስለኝ ውስጤ ካደኝ፡፡ ዓይኔን አላመንኩም፡፡

‹‹ኧረ ጉድ ፈላ!›› ስል ጮህኩ አሁንም በዓይን አላመንኩም፡፡ እውነት ይህ ሁሉ ዱቄት እኔ ቤት ሊገባ ነው? ስል ራሴን ጠየቅሁ፡፡ መለስ ብዬ ማኮሮኒውን፣ አምስት ሊትሩን ዘይት አየሁት፡፡ እሱም የእኔ ነው፡፡ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡

ከጎኔ የነበሩት እማማ ለምን ታለቅሻለሽ ሲሉ ተቆጡኝ። በእርግጥ ዛሬ ማልቀስ አልነበረብኝም፡፡ ግን ምን ላድርግ እጅግ ደስ ብሎኝ ነው፡፡ አዎ! ዛሬ አለኝ፣ ሀብታም ነኝ። ወግ ደርሶኛል፡፡ ቡና አፍልቼ ጎረቤቶቼን እጠራለሁ። አስተዳደጌ በድርጅት ውስጥ ነው፡፡ ቤተሰብ የለኝም፡፡ ዘመዶቼን አላውቅም፡፡

እኔ በሕይወቴ ሁለት ጊዜ ‹‹ሰርፕራይዝ›› ሆኛለሁ። አንዱ ባደኩበት ድርጅት አብሮ አደጎቼ ‹‹ዛሬ ልደትሽ ነው›› ብለው ኬክ የቆረሱልኝ ቀን ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ በእናንተ ፊት የተደረገልኝ ስጦታ ሁለተኛዬ ሆኗል። ከጎኔ ያለችው ልጄ በሆነው ሁሉ ተገርማለች፡፡ እሷም እንደኔ ዓይኗን አላመነችም፡፡ እናም ደጋግማ እንዲህ አለችኝ ‹‹እማዬ ዱቄቱ ላይ ተኝተን ፎቶ እንነሳ››

እኔም «እውነትሽን ነው ልጄ ቤታችን ስንገባ ሁላችንም ተሰባስበን ፎቶ እንነሳበታለን›› አልኳት። የሁሉም ታዳሚ ስሜት እንደተረበሸ ቀጣይዋ እናት ከወንበሯ ተነሳች፡፡

ይህቺ ሴት በአካል እራሷን ከምትመስል ልጅ ጋር አይቻታለሁ፡፡ አዎ! አልተሳሳትኩም ልጇ ነች፡፡ እናት ጎስቋላ ፊቷ ብዙ ይናገራል፡፡ ከንግግሯ በፊት ዕንባ እያነቃት ነው፡፡ ሆድ በባሰው አንደበቷ የውስጧን ለመተንፈስ ሞከረች፡፡ ሳግ የያዘው ድምጽ እንደምንም አሸንፎ መሰማት ጀመረ፡፡

‹‹ልጄ ሊደፍሯት ባሉ ሰዎች በጩቤ ተወግታለች››

እኔ ቤተሰቦቼን አላውቅም፡፡ ያደኩት በሌሎች እጅ ነው፡፡ አስራ አንደኛ ክፍል ሳለሁ ከአንድ ሰው ጋር ተዋወቅሁ፡፡ አብረን መኖር ጀመርን፡፡ አረገዝኩ፡፡ ሴት ልጅም ወለድኩ፡፡ ይህን ያወቀው ባለቤቴ አብሮኝ መዝለቅ አልፈለገም፡፡ በድንገት ከነልጄ ትቶኝ ጠፋ፡፡ ከዚህ በኋላ የነበረው ሕይወት የፈተና ሆነ፡፡ እሷን ይዤ ጎዳና ለጎዳና መንከራተት ያዝኩ፡፡

መኖሪያችን ጎዳና ቢሆንም በውጣ ውረድ ልጄ እንደምንም አደገች፡፡ የጎዳና ሕይወት ግን ብዙ ችግር አመጣብን፡፡ ልጄ ሊደፍሯት በሞክሩ ጎረምሶች በጩቤ ተወጋች፡፡ ይህን ችግር ያስተዋለው ወረዳ ዘጠኝ እንደ ቤተሰብ ሆነኝ፡፡

በአሁኑ ጊዜ የወረዳው ሴቶችና ሕፃናት በቀን የመደብ እየከፈለልኝ በቤት ውስጥ አድራለሁ፡፡ እኔ እስካሁን ወገን ዘመድ እንደሌለኝ አስብ ነበር፡፡ አሁን ግን በእናንተ ሁሉን አግኝቻለሁ፡፡ ስላደረጋችሁልኝ በጎነት ሁሉ ምስጋናዬ ከልብ ነው፡፡

‹‹ተጠልቼ የኖርኩ ሰው ነኝ››

ያለአባት የሚያድጉ የሁለት ልጆች እናት ነኝ። የአስራስድስት ዓመቱ ልጄ በድንገት ወድቆ የነርቭ ታማሚ ሆኗል፡፡ ከዚህ ቀድሞ በሰዎች እገዛ በዌልቸር ይሄድ ነበር። አሁን ግን በመጠኑ ተሽሎት በእግሩ እየተራመደ ነው። በኑሮዬ ችግረኛ ነኝ፡፡ የእኔ አቅም ጨው በርበሬ ከመግዛት አያልፍም፡፡ ጓዳዬን የምታውቅ አንዲት ሴት ግን ሙሉ የቤት ወጪዬን ትሸፍናለች፡፡

ማንኛውንም ሥራ አልንቅም፡፡ ወንዶች የሚሠሩትን ሁሉ እየተሸከምኩ ልጆቼን አሳድጋለሁ። ዕውቀት የሚያስፈልገውን ግን ትምህርት ስለሚጠይቅ አልሞክረውም። እንዲያም ሆኖ ሰዎች ሊቀርቡኝ አይፈልጉም፡፡ ህመሜ ስለሚታወቅ ተገልዬ፣ ተጠልቼ የኖርኩ ሰው ነኝ፡፡

ዛሬ መንግሥት ቤት ሠርቶ አስረክቦኛል፡፡ ይህ ሲታወቅ ትናንት በሩቁ የሚሸሹኝ ሁሉ ለሰላምታ እጃቸውን ይዘረጋሉ፡፡ በሕይወቴ ብዙ ሰዎች ቤቴን አንኳኩተዋል። እናንተ ደግሞ በዛሬው ቀን ለበዓል የሚያስፈልገኝን አሟላችሁልኝ፡፡ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ ፡፡

‹ዘንድሮም አስታወሳችሁን››

ይህች ሴት ተናግራ እንደገባች አንዲት ትልቅ እናት ወደ መድረኩ ብቅ አሉ፡፡ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ከአንዲት ልጃቸው ጋር ተቀምጠው ይጫወቱ ነበር፡፡ የእናትና ልጅ ቀረቤታ ዓይን ይስባል፡፡ ልጅ በየምክንያቱ እያቀፈች ትስማቸዋለች፡፡ እሳቸውም በተለየ ስስትና ፍቅር ያስተውሏታል፡፡

ወይዘሮዋ ሰውነታቸው ወፍራም በመሆኑ ችግር አይቷቸው የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ገጽታቸው ፈገግ፣ ፈካ ያለ ነው፡፡ ያያቸው እንዲህ ይገምት እንጂ ንግግር ከመጀመራቸው የታዳሚውን አንገት በኀዘን አስደፉት ፡፡

‹‹አንቆርጫ›› ከሚባለው ሰፈር ተከራይቼ እኖራለሁ። የስኳር ታማሚ ነኝ፡፡ በየቀኑ ለበሽታው መድኃኒት መውሰድ ግዴታዬ ነው፡፡ እኔ ግን አንዳች መተዳደሪያ የለኝም፡፡ ለነፍስ ያሉ አጉርሰው ያለብሱኛል፡፡ ልጆቼን የማልስ የማቀምሰው የለኝም፡፡ እነሱን ለማኖር ስል ግን ‹‹ቡሌ›› እየወሰድኩ አሳድጋቸዋለሁ፡፡

ከዚህ በፊት ሠርቼ ለመብላት ጉልበቴ የበረታ፣ ውስጤ የጠነከረ ነበር፡፡ አሁን ህመሙ እቅሜን አዳክሞታል። ከቀናት በፊት የምቀምሰው፣ የምልሰው አልነበረም፡፡ በቀደም በባዶ ሆዴ ከቤት ወጣሁ፡፡ ከመንገድ በድንገት ራሴን ብስት አንዲት ሴት ስኳር ሰጥታኝ ሕይወቴ ተረፈ፡፡

ልጆቼን ይዤ በኪራይ እኖራለሁ፡፡ ለቤቱ እከፍለው የለም፡፡ ይህች ትንሽ ልጅ ግን ማስቲካ እየሸጠች የወሩን ኪራዩን ትሸፍናለች፡፡ አምና ይህን ጊዜ ለልጆቻችን ደብተር ሰጥታችሁን ነበር፡፡ አሁንም ጊዜው ትዝ ብሎኝ ሳስባችሁ ቆይቻለሁ፡፡ እናንተ ግን ፈጽሞ አልረሳችሁንም። ዘንድሮም አስታወሳችሁን፡፡ ከምስጋና ውጪ ምን ልል እችላለሁ፤ ብድሩ ይግባችሁ እንጂ፡፡

‹‹የሃያ አምስት ዓመት ፀበልተኛ ነኝ››

ያመኛል፡፡ ለህመሜ ፈውስ ለመሻት እንጦጦ ማርያም መጠመቅ ከጀመርኩ ከሃያ አምስት ዓመት በላይ ሆኗል። አንዲት ልጅ አለችኝ፡፡ ይዣት ስመጣ የሦስት ዓመት ሕፃን ነበረች፡፡ የምኖረው በቤት ኪራይ ነው፡፡ አከራዮቹ እንዳሻቸው ውጪ ግቢ ይሉኛል፡፡ እንዲያም ሆኖ ኪራይ የምከፍልበት ቋሚ ገቢ የለኝም፡፡ ዛሬ ይህ ድርጅት ድጋፉን ሲሰጠኝ ከልብ ተደሰትኩ፡፡ በሆነልኝ ሁሉ ከልብ አመስግኛለሁ፡፡

የሴና እናት ሌሊሴ

ፈገግታ ያበራው ገጽታ ጆሮን ከሚስብ አንደበት ሲዳመር የሌሊሴ ውበት ይበልጥ ይጎላል፡፡ ሌሊሴን የማያውቅ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሠራተኛ የለም፡፡ እሷ የፕሬስ የቅርብ ቤተሰብ ሆናለች፡፡ ደስተኛ ልጇ ሴና በሠራተኛው ዕቅፍ ያደገች እንቦቃቅላ ናት፡፡ እንደ እናቷ ፍልቅልቅ የሆነች ሳቂታ ሕፃን ፡፡

ሌሊሴ ከዓመታት በፊት ከድርጅቱ አጥር በአጭር ርቀት ተቀምጣ ትውል ነበር፡፡ የእሷ መቀመጥ ለሚለውጥ ሥራ አልነበረም፡፡ አላፊ አግዳሚው ያለውን እንዲጥልላት ለመለመን እንጂ፡፡ ደግነቱ በርካታው መንገደኛ አይቶ አያልፋትም፡፡ ቆንጅዬዋን ሕፃን ያየ ሁሉ በኀዘኔታ የእጁን ይጥልላታል፡፡

የሌሊሴ ሕይወት ግን በዚህ መስመር አልቀጠለም፡፡ ከቀናት በአንዱ በአንዲት መልካም ሴት ዓይኞች ተጎበኘች፡፡

ይህች ሴት ቀረብ ብላ ስለሥራ፣ ስለራስን መቻል አዋየቻት፡፡ ይህ እውነት የሌሊሴም ነበርና ዓይኗን አላሸችም፡፡ ከቀናት በኋላ የድንች መጥበሻና አስፈላጊ ቁሶች ከእጇ ደረሱ፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቅርብ አጋሯ ሆነ፡፡ ሌሊሴ ልመናን ተጠይፋ ወደ ሥራ ገባች፡፡

ትናንት ለምጽዋት እጃቸውን የዘረጉላት ዛሬም ገንዘብ ይዘው የላቧን ዋጋ ገዟት፣ ቀመሱላት፡፡ ደንበኞቿ በረከቱ። ስለሆነው ሁሉ ‹‹አድናቂዎቿ ቃል አጠራቸው፡፡ ትንሽዬዋ ሴና ከድርጅቱ የሠራተኛ ልጆች እንደኛዋ ሆና በሕፃናት ማቆያ መዋል ጀመረች፡፡ ሌሊሴ ታሪኳ ፍጹም ተቀየረ፡፡ በየጊዜው ጥሩ ትርፍ ማግኘት ያዘች፡፡ ዕቁብ ገባች፡፡ ገንዘብ ቆጠበች፡፡

ዛሬ ሌሊሴ ከእንግዶቹ መሀል አንደኛዋ ሴት ሆናለች። እሷ ግን እንደሌሎቹ የከፋ ችግሯን እያወራች አይደለም፡፡ በጣፋጭ አንደበቷ ደግማ ደጋግማ ‹‹አመሰግናለሁ›› እያለች ነው፡፡

አዎ! ዘንድሮ የትናንትናዋ ሴና ተማሪ ልትሆን ወግ ደርሷታል፡፡ ለዚህ ሕጋዊነት አስፈላጊውን ሁሉ ያሟላላት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነው፡፡

ፕሬስ እንደ እናት በሚጦራቸው እማማ ግምጃ የሴናን ሕጋዊ የትምህርት መታወቂያ ለማውጣት ችሏል፡፡ ወደፊት በትምህርት ዓለም ለሚኖረው ማንኛውም ድጋፍም ከጎኗ አይርቅም፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ሌሊሴ አሁን እየሠራችበት ከሚገኘው የፕሬስ ድርጅት አካባቢ ያለአንዳች ችግር በሥራው እንድትቀጥል በሰነድ የተደገፈ ሕጋዊ ማረጋገጫ አግኝታለች፡፡ ዛሬ የሌሊሴ ድምጽ ከሌሎች ሁሉ ይለያል። የትናንት ታሪኳ ከዛሬው ፍጹም ተቀይሯል፡፡ ስለነገው አሁን ላይ ቆማ በብሩህ ተስፋ ትሮጣለች ፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You