የስራ ባህል፣ ልምድና ጥሪትን አቀናጅቶ በሙሉ አቅም የመሥራት ውጤት

በበዓል ወቅት ከቤተዘመድ ጋር መገናኘትና መጠያየቅ የኢትዮጵያውያን የኖረ ባህል ነው፡፡ መጠያየቅ ሲባል ደግሞ እንዲያው በደረቁ አይደለም። ሰው እንደ አቅሙና ፍላጎቱ አቅሙ የፈቀደውን በማድረግ ወዳጅ ዘመዱን፣ ቤተሰቡንና ጓደኛውን ይጠይቃል፡፡ ፍራፍሬ፣ ዳቦና ኬክ ይዞ ወዳጅ ዘመድን መጠየቅ ደግሞ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ በተለይም በከተሞች አካባቢ በበዓላት ወቅት የኬክ ተጠቃሚ ቁጥር ከፍ የሚል በመሆኑ የኬክ ቤቶች የሥራ እንቅስቃሴም ከአዘቦት ቀን ይልቅ በበዓል ወቅት ይደራል፡፡

ዛሬ በአዲስ ዓመት ማግስት ስለ ኬክ ማንሳታችን ያለምክንያት አይደለም፡፡ የዕለቱ የስኬት እንግዳችን በኬክ ሥራ ሙያ የተሰማራና የካፌ ባለቤት በመሆኑ እንጂ፡፡ ይሕ የስኬት እንግዳችን ይርጋለም ከተማ ተወልዶ ዕድገቱን ሻሸመኔና ሀዋሳ በማድረግ ሕይወት ትርጉም እንዲኖራት ከላይ ታች በማለት ሥራን በትጋት ሠርቷል፡፡ ከትምህርት ጎን ለጎን የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ገና በአፍላነቱ የድርጅት ባለቤት በመሆን በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለም ነው፡፡

‹‹በንግድ ከሚተዳደር ቤተሰብ የተገኘሁ በመሆኔ ገና በልጅነቴ ከትምህርት ይልቅ ለንግድ አደላ ነበር›› የሚለው የዕለቱ እንግዳችን አቶ ያሬድ ጌታቸው፣ በሀዋሳ ከተማ ‹‹ሮም 1960›› የተባለ የካፌ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡ የሥራ መነሻውን ሀዋሳ ከተማ ላይ ያደረገው አቶ ያሬድ፣ በሀዋሳ ከተማ በአምስት የተለያዩ አካባቢዎች ሮም 1960 ካፌን ከፍቶ እየሰራ ነው፡፡ ከሀዋሳ ከተማ በተጨማሪ ቅርንጫፉን በማስፋት ሻሸመኔ ከተማ ላይም እንዲሁ ሮም 1960 ካፌን መክፈት ችሏል፡፡

በቀለም ትምህርቱ ጎበዝ ተማሪ እንደነበር የሚያስታውሰው አቶ ያሬድ፤ ውስጡ የነበረው የፍላጎት ሚዛን ለንግድ ያደላ መሆኑን ይናገራል፤ ወደ 11ኛ ክፍል የተዘዋወረበትን ሰርተፍኬት በክብር አስቀምጦ ነው ገና በልጅነቱ ወደ ንግድ ሥራ የገባው። በ16 ዓመቱ ተማሪ እያለ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ማለትም የእንጨት ሥራ፣ የጋራዥ ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችንና ሌሎችንም ሥራዎች መሥራት በመቻሉ በቀላሉ ገንዘብ ማግኘት ችሏል፡፡ ይሄን ጊዜ ታድያ ከዚህ የበለጠ መሥራት ቢቻል የበለጠ ገንዘብ ማግኘትና ከድህነት መውጣት እንደሚቻል በማመን የንግድ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማመን ወደፊት መቀጠሉን ተያያዘው፡፡

አቶ ያሬድ ከጋራዥና ከእንጨት ሥራው በተጨማሪ አያቱ በኬክ ሥራ የታወቁ በመሆናቸው በቤት ውስጥ ኬክ ሲሰራ እየተመለከተ አድጓል። ከአያቱ የለመደውን የኬክ ሥራም ‹‹ሮም 1960›› ኬክ ቤትና ካፌን መክፈት እንዲችል አግዞታል፡፡ ኬክ ቤቱን ከመክፈቱ አስቀድሞ ከአያቱ የለመደውን የኬክ አሰራር በትምህርት በማስደገፍ በተለያዩ ኬክ ቤቶች ተቀጥሮ ሰርቷል፡፡ ተቀጥሮ በሰራባቸው ኬክ ቤቶች ሁሉ ታድያ ሥራውን በእኔነት ስሜት ይሠራ ስለነበረ ጥሩ ስም ማግኘቱን ያስታውሳል፡፡

የኬክ ሥራን የሙሉ ጊዜ ሥራው በማድረግ ወደ ዘርፉ የተቀላቀለው አቶ ያሬድ፤ ተቀጥሮ በሚሠራበት ወቅት ሙያውን ከማሳደግ በተጨማሪ የሚያገኘውን ገንዘብም ይቆጥብ እንደነበር ነው ያጫወተን፡፡ በወቅቱ የራሱን ኬክ ቤትና ካፌ የመክፈት ራዕይ ሰንቆ ብርቱ ጥረት ሲያደርግ የነበረው አቶ ያሬድ፤ በ45 ሺ ብር መነሻ ካፒታል ‹‹ሮም 1960›› ካፌን ይከፍታል። የገንዘቡ ምንጭም ተቀጥሮ በሰራባቸው አራት ዓመታት ያጠራቀመው 30 ሺ ብር ላይ ከሲዳማ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በብድር የተገኘውን 15 ሺ ብር ተደማሪ በማድረግ ነው፡፡

ገና በጥዋቱ 45 ሺ ብር መነሻ ካፒታል ይዞ የኬክ ሥራን በካፌ ደረጃ መክፈት የቻለው አቶ ያሬድ፣ ሥራውን በጀመረ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ቢሆንም፣ በአንድ ጀምበር ተዘርፎ ባዶ የሆነበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ያም ቢሆን ግን ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ምክንያቱም ሌባ የማይሰርቀው የእጅ ሙያ አለውና ሙያውን ተጠቅሞ እንደገና አንሰራርቷል፡፡

 ‹‹በሕይወቴ ተስፋ መቁረጥ አላውቅም›› የሚለው አቶ ያሬድ፣ ንብረቱ በተዘረፈ ማግስት ይጨነቅ የነበረው እንዴት ወደ ሥራ መመለስ እንዳለበት ነበርና ሌባ የማይሰርቀውን ሙያና ዕውቀት በመያዝ እንደገና ተቀጣሪ ሆኖ በመሥራት ገንዘብ አጠራቅሞ ‹‹ሮም 1960›› ካፌን መክፈት ችሏል፡፡

‹‹ቤተሰቦቼ ጥሩ የሥራ ባህልን አውርሰውኛል›› የሚለው አቶ ያሬድ፤ የሥራ ባህል የሌለው ሰው ገንዘብ እንኳን ቢያገኝ ገንዘቡን በአግባቡ ሊጠቀምበት እንደማይችል ይናገራል፡፡ ለሰው ልጅ ገንዘብ ከመስጠት ይልቅ ጥሩ የሥራ ባህል መፍጠርና ማውረስ በእጅጉ እንደሚጠቅም ራሱን ምሳሌ በማድረግ ያስረዳል፡፡ ‹‹ሰዎች ሙሉ ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውንና አቅማቸውን አሟጠው መጠቀም ከቻሉ ካሰቡበት መድረስ እንደሚችሉ እየተነገረኝ አድጌያለሁ›› የሚለው አቶ ያሬድ፤ ዛሬ ላይ ለደረሰበት ስኬትም ቤተሰቦቹ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውና ትልቁን ሃብት የሥራ ባህልን እንዳወረሱት ነው የሚናገረው፡፡

‹‹ከቤተሰቤ ከወረስኩት ጠንካራ የሥራ ባህል በተጨማሪ በተፈጥሮ ነገሮችን በፍጥነት ለመረዳትና ለጥበብ /አርት/ ሥራዎች ቅርብ ነኝ›› የሚለው አቶ ያሬድ፤ ይህም ለኬክ ሥራው በእጅጉ እንደጠቀመው ጠቅሷል፡፡ በተለይም በጥበቡ ዙሪያ ያለውን ፍላጎት በኬክ ምርቶቹ ላይ እንደሚገልጽም አጫውቶናል። ከአያቱ በልምድ ያገኘውን የኬክ ሥራ በትምህርት አጎልምሶ ዛሬ ስድስት ቅርንጫፎች ያሉትን ካፌ ያስተዳድራል፡፡ በኬክ ሥራ ረዘም ያለ ቆይታ ያለውና ልምድ ያዳበረ በመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ አካላት ስልጠናም ይሰጣል፡፡

‹‹ከፍተኛ የሆነ የሥራ ሱስ ነው ያለብኝ፤ ሌላ ሱስ የለብኝም›› በማለት ተግቶ መሥራት ውጤታማ እንደሚያደርግ የሚናገረው አቶ ያሬድ፤ ድህነትን አብዝቶ የሚጠየፍና ጠንክሮ በመሥራት ሃብታም መሆን እንደሚቻል በጽኑ የሚያምንም ነው፡፡ ሃብታም የመሆን ከፍተኛ ፍላጎትም ከልጅነቱ ጀምሮ እንደነበረው ያስታውሳል፡፡ ለዚህም ጠንካራ የሥራ ባህል ያላቸውና ተግተው በመሥራት ገንዘብ ሲያገኙ የተመለከታቸው ቤተሰቦቹ መሰረት እንደሆኑት ያስረዳል፡፡

‹‹የሃብት ምንጩ ትጋት ነው›› በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሃሳቡን በማጠናከር፤ ሰው ጠንክሮ ከሠራ ስኬታማ መሆን እንደሚችል ይናገራል፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባለች ብዙ በረከት ባላት አገር ላይ ሰርቶ መለወጥ፣ ማግኘትና ከድህነት መውጣት ቀላል እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ለዚህም አገር የሰጠችውን በረከት፣ ጊዜንና ጉልበትን አቀናጅቶ በሙሉ አቅም መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ አስረድቷል፡፡

ከልጅነት እስከ ዕውቀት ስለ ሥራ ክቡርነት እያደመጠ በሥራ ያደገው አቶ ያሬድ፤ ሰርቶ ማደግና መለወጥ እንዲሁም ለሌሎች መትረፍ ዕቅዱ እንደነበር በማንሳት ሠርቶ መለወጥ እንደቻለና ከራሱ አልፎ ለሌሎች መትረፍ እንደቻለም ይናገራል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለአገሩ መሥራት ያለበትን ሠርቶ ማለፍ እንዳለበት በጽኑ ያምናል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በስድስት የ‹‹ሮም 1960›› የካፌ ቅርንጫፎቹ 278 ለሚደርሱ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል፤ በቀጣይም ቅርንጫፎቹን በማስፋት የሠራተኞቹን ቁጥር የማሳደግ ዕቅድ አለው፡፡ ከሠራተኞቹ ጋርም በጥሩ መግባባት እንደሚሠራ በመግለጽ፤ ድርጅቱ የሚመራበትን መተዳሪያ ደንብ አክብረው የሚሠሩና ድርጅቱን እንደራሳቸው የሚያዩ ሠራተኞች እንዳሉት ነው የሚናገረው። ለዚህም የእርሱ አቅርቦት ወሳኝ እንደመሆኑ ከመነሻው ጀምሮ ያለፈባቸውን ውጣ ውረዶች በማስረዳት እነሱም ተግተው መሥራት ከቻሉ ነገ የድርጅት ባለቤት መሆን እንደሚችሉ መምከር የዘወትር ተግባሩ እንደሆነ አጫውቶናል፡፡

‹‹ነብይ በአገሩ አይከበርም›› እንዲሉ አበው፣ ስለ ‹‹ሮም 1960›› ኬክ ቤት መጠሪያ ስም ያጫወተን አቶ ያሬድ፤ የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ስለ አበበ ቢቂላ የተጻፈ ጽሁፍ ሲያነብ የአበበ ቢቂላ ገድሎች ገዝፈውበታል። ይህን ግዙፍ ታሪክ ደግሞ ነጮቹ በታላቅ አድናቆት ተቀብለውታል፡፡ ነገር ግን አትሌቱ በገዛ አገሩ ብዙም ትኩረት የተሰጠው እንዳልሆነ በመረዳቱ ቁጭት ገብቶታል፡፡ ለዚህ ቁጭቱም የካፌውን መጠሪያ ስም ‹‹ሮም 1960›› በማለት ሰይሟል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በሀዋሳ ከተማ ባሉት አምስት የ‹‹ሮም 1960›› ካፌዎች ምክንያት አበበና የማራቶን ገድሉ ይታወሳሉ፡፡ ይህም ከመታወስ ባለፈ ኢትዮጵያን መግለጽና ሁሉንም በአንድነት ሊያግባባና ሊያቀራርብ የሚችል እንደሆነ ይናገራል። ድሉ ከአድዋ ድል የሚተናነስ እንዳልሆነና ነጮች ‹‹ጥቁር አይችልም›› የሚለውን የነጮችን አስተሳሰብ መስበር የቻለ ትልቅ መልዕክት ያለው መሆኑንም ይገልፃል፡፡

‹‹ከእያንዳንዱ ወንድ ጀርባ አንዲት ጠንካራ ሴት አለች›› እንደሚባለው አቶ ያሬድ ዛሬ ላይ ለመድረሱ የባለቤቱ እገዛ ትልቅ ቦታ እንዳለው ይናገራል፡፡ ባለቤቱ ወይዘሮ ሄለን ኃይሉ የጀርባ አጥንት በመሆን ‹‹ሮም 1960›› አሁን ለደረሰበት ደረጃ ጉልህ ሚና አላት ይላል፡፡ ከትንሽ ካፌ ሲጀምር አንስቶ በካፌ ውስጥ ዕቃ አጣቢ ባይኖር ዕቃ አጥባ፣ ባሬስታ ባይሮር የባሬስታ ቦታን ሸፍና ሁለገብ በመሆን ድርጅቱን አግዛለች፡፡ ማርገዝም ሆነ መውለድ ከሥራዋ አልነጠሏትም ይላል፡፡ ወልዳ አራስ ልጆችን ወደ ካፌው ይዛ በመምጣት ጭምር ታግዘው የነበረበት ሁኔታ ዛሬ ለደረሱበት ከፍታ ትልቅ ድርሻ እንዳላት ገልጿል፡፡

በ‹‹ሮም 1960›› ካፌ ውስጥ ኬክን ጨምሮ የሻይ ቡና እንዲሁም የተለያዩ ቀላል ምግቦች እንደ ቺክን፣ በርገርና ሌሎች የምግብ አይነቶች እንደሚቀርቡ ጠቅሶ፣ በአገልግሎት አሰጣጣቸውም በደንበኞቻቸው የተመሰከረላቸው ስለመሆናቸው ነው አቶ ያሬድ ያስረዳል፡፡ ድርጅቱ ካሉት ሠራተኞች መካከል ሰፊውን ቁጥር የሚይዙት ሴቶች ስለመሆናቸው ያነሳው አቶ ያሬድ፤ በመስተንግዶም ይሁን በኬክ ሥራ በርካታ ሴቶች መሰማራታቸውን ይገልጻል፡፡ ከሠራተኞቹ ጋር መልካም መቀራረብ እንዳለው ጠቅሶ፣ ድርጅቱ ከተከፈተ ጊዜ ጀምሮ አብረው እየሠሩ ያሉ ሠራተኞች ስለመኖራቸው ተናግሯል፡፡

‹‹በካፒታል ደረጃ ገንዘብ እንዲኖረኝ አልፈልግም፤ የሚገኘው ገቢ በሙሉ ሥራ ላይ እንዲውል አደርጋለሁ›› የሚለው አቶ ያሬድ፤ ትኩረቱ የሥራ ዕድል መፍጠር ላይ እንደሆነ በማንሳት የሚገኘውን ገንዘብ ወደ ሥራ በመቀየር ድርጅቱን የማሳደግና የማስፋት ሥራ እየሠራበት እንደሆነ ይጠቅሳል፤ ይህም አሁን ከፈጠረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ በእጥፍ ለማሳደግ የሚጠቅም እንደሆነ ነው የገለጸው፡፡

ማህበራዊ ኃላፊነትን በተመለከተ በተለያየ የሕይወት አጋጣሚ ሠራተኞቹ ለሚደርስባቸው ችግር፣ ሀዘን፣ መከራና ደስታ ቅድሚያ በመስጠት በጋራ የሚካፈላቸው እንደሆነ በመጥቀስ፤ ከደመወዝ ባለፈ ወጪያቸውን በመሸፈን ድጋፍ ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪ በታማኝነት የመንግሥትን ታክስና ግብር በመክፈል እንዲሁም መንግሥት ለሚያደርጋቸው ማንኛቸውም ጥሪዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም ይገልጻል፡፡ ከዚህ ባለፈም በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች በመሳተፍ ትምህርት ያቋረጡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ በማድረግ በተቻለው አቅም ሁሉ ለአካባቢው ነዋሪዎች ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ሰፊ ዕቅድ ያለው አቶ ያሬድ፤ በ2016 አዲሱ ዓመት ‹‹ሮም 1960›› ካፌን አዲስ አበባ ላይ ለመክፈት አቅዷል፤ በቀጣይም በአንድ አልያም በሁለት አፍሪካ አገራት ካፌውን የመክፈትና ኢትየጵያን የማስተዋወቅ ዕቅድ እንዳለው አጫውቶናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሪዞርት የመገንባት ፍላጎትና ዕቅድ ያለው አቶ ያሬድ፤ ለዚህም መንግሥት ሥራውን አይቶና ገምግሞ ቦታ ቢሰጠው የተሻለ ሥራ መሥራት እንደሚችል ነው ያመለከተው፡፡ በመጨረሻም ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት እያንዳንዱ ሰው በሥራ ሊተጋ እንደሚገባ በማስገንዘብ ሁሉም ሰው ጠንክሮ መሥራት ከቻለ ኢትዮጵያን ከድህነት ማውጣት እንደሚቻል አስታውቋል፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You