በቀለኛው አባወራ

በትዳር ብዙ ዘመናት ቢቆጠሩም፤ አልፎ አልፎ በቤተሰብ ውስጥ አለመስማማት መኖሩ የተለመደ ነው፡፡ ባል እና ሚስት፣ አባት እና ልጅ፣ እናት እና ልጅ መጋጨታቸው ትልቅ ጉዳይ ሆኖ የሚቀርብ አይደለም። አቶ ተሾመ ጫካ እና ወይዘሮ ወለላ ተክሌም ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ለ45 ዓመታት በትዳር ሲቆዩ፤ አምስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ባል እና ሚስቱ በእነዚህ ዓመታት በተለያየ ጊዜ ግጭት ውስጥ ገብተዋል፡፡


ባል እና ሚስቱ ብቻ ሳይሆኑ ከሁለቱም አብራክ የተከፈሉ ልጆችም በተለያየ ጊዜ ከአባታቸው ጋር ተጋጭተዋል፡፡ በእነዚህ ዘመናት ያለፉት ግጭቶች በብዙ ቤተሰብ ውስጥ ከተለመዱት የተለዩ አልነበሩም፡፡ መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም የተፈፀመው ዘግናኝ ድርጊት ግን የቤተሰቡን ግጭት እጅግ የተለየ ያደርገዋል፡፡


አባወራው
አቶ ተሾመ ጫካ የተወለዱት ከአቶ ጫካ ባልቻ እና ከወይዘሮ ብሪቱ ጫላ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጨሉሌ ወረዳ ልዩ ስሙ ወሠን ሶዶ አካባቢ በ1945 ዓ.ም ነበር፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በወቅቱ በሲዳሞ ክፍለ አገር ተፈሪ ኬላ ትምህርት ቤት ተከታተሉ፡፡ የ7ኛ እና የ8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ደግሞ በአለታ ወንዶ የተማሩ ሲሆን፤ ደብረብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ገብተው በቲቲአይ ተመርቀዋል፡፡


በ1966 ዓ.ም ጋሞጎፋ አውራጃ ልዩ ስሙ ቦንኬ በተባለ አካባቢ እስከ 1979 ዓ.ም ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ በ1979 ዓ.ም ዝውውር አግኝተው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ኮልፌ በተባለ ትምህርት ቤት በዳይሬክተርነት ትምህርት ቤቱን መርተዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ከስራቸው ጎን ለጎን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በትምህርት አስተዳደር በአድቫንስ ዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ ትምህርት ቤት ከመምራት ባሻገር በአዲስ አበባ ከተማ ዞን 4 የሰው ኃይል አስተዳደር ተመድበው አገልግለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ 4 ኪሎ ስፖርት እና ትምህርት አስተዳደርም ለሰባት ዓመታት ሠርተዋል፡፡


በአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ ዕድሜያቸው በመድረሱ በ2006 ዓ.ም በጡረታ ከመንግስት ሥራ ተገልለዋል፡፡ ከጡረታ በኋላም በግል ትምህርት ቤት በሰው ኃይል አስተዳደር ሲሠሩ የቆዩት አቶ ተሾመ፤ በመጨረሻም በደረሰባቸው የጤና ዕክል ምክንያት ሥራ አቁመው ቤት ለመዋል ተገድደዋል፡፡


አቶ ተሾመ የሚኖሩት ባለቤታቸው ወይዘሮ ወለላ ተክሌ መምህር በመሆናቸው ከመንግስት ባገኙት የጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው፡፡ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ገላን ኮንደሚኒየም ህንፃ ቁጥር 13/18 ውስጥ ሲኖሩ፤ በተደጋጋሚ ‹‹ቤተሰቦቼ እያገለሉኝ ነው፤ እያሉ ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ቤተሰቦቼ ‹አታግልሉኝ፤ ታማሚ ነኝ ተው ተንከባከቡኝ፡፡› ብላቸውም ይሳለቁብኛል፤ ‹ወደ ፈለክበት መሔድ ትችላለህ፡፡› ይሉኛል›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በመጨረሻም አባወራው ወለቴ አካባቢ ቤት ተከራይተው ከቤተሰብ ተለይተው መኖር ጀመሩ፡፡


ሆኖም ለብቻቸው መኖር አልቻሉም፡፡ ቤተሰብ በተለይም ጌታእንዳለ የተሰኘው ልጃቸው መታመማቸውን ሰምቶ ወደ ቤት እንዲመለሱ አግባባቸው፡፡ በልጃቸው አማካኝነት ወደ ቤት ተመለሱ፤ ከቤተሰባቸው ጋር በተቀላቀሉ ሳምንት መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ግን ለቤተሰቡ ከባድ መከራን ይዞ መጣ፡፡


በዕለቱ ማለትም በመጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት ባለቤታቸው ወይዘሮ ወለላ ለባለቤታቸው አቶ ተሾመ፤ ‹‹ራት ምን ልስራልህ?›› የሚል ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አቶ ተሾመ ‹‹ሽሮ ይሠራልኝ›› አሉ፡፡ ሚስቲቱ ለመስራት ወደ ምግብ ማብሰያ ክፍል ሲገቡ፤ ልጃቸው ትዕግስት ተሾመ ተከትላ ገባች፡፡


እናት እና አባት ማለትም አቶ ተሾመ እና ወይዘሮ ወለላ በተደጋጋሚ ሲጋጩ፤ ልጃቸው ትዕግስት ተሾመ ለእናት ተደርባ ትሳደባለች በሚል አባት ቂም ይዘዋል። በዕለቱ ልጃቸው ትዕግስት እናትን ለማገዝ ወደ ምግብ ማብሰያ ክፍል ስትገባ አባት በበኩላቸው ‹‹ የሚሰራውን ምግብ ልትመርዝብኝ ነው›› ብለው ማሰባቸውን ወንጀል ከፈፀሙ በኋላ ለፖሊስ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃላቸው ላይ አስረድተዋል፡፡


የልጅ ጌታእንዳለ ምስክርነት
የአቶ ተሾመ እና የወይዘሮ ወለላ 4ኛ ልጅ ወጣት ጌታእንዳለ መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም እንደተለመደው ቀን ሥራ ውሎ ቤት የገባው 11 ሰዓት አካባቢ ነበር፡፡ ቤት ሲገባ አባቱ አቶ ተሾመ ጫካ እና እናቱ ወይዘሮ ወለላ እንዲሁም እህቱ ትዕግስት ተሾመን አገኘ፡፡ እንደወትሮው ከቤተሰቦቹ ጋር ዜና እየተመለከተ እና ከቢሮ ያመጣውን ሥራ እየሠራ አመሸ፡፡ ለቤተሰቡ እናት ወይዘሮ ወለላ እራት አቀረቡ፡፡ እራት የቀረበው ሁለት ቦታ ነበር። አባት ደም ግፊት ስላለባቸው ጨው ስለማይበሉ ጨው የሌለው ምግብ ለብቻቸው የቀረበላቸው ሲሆን፤ ወጣት ጌታእንዳለ፣ ወይዘሮ ወለላ እና ትዕግስት አብረው እራታቸውን በሉ፡፡ ከእራት በኋላ ሁሉም አንድ አንድ ጠርሙስ ቢራ ጠጥተው፤ በሰላም ወደየመኝታቸው ሔዱ፡፡


ወይዘሮ ወለላ እና ትዕግስት በአንድ አልጋ ላይ አንድ የመኝታ ክፍል ሲተኙ፤ በሁለተኛው መኝታ ቤት አባት አቶ ተሾመ ገብተው ተኙ፡፡ ወጣት ጌታእንዳለ ተሾመም እንደተለመደው ሳሎን ሶፋ ላይ ተኛ፡፡ በግምት ሰባት ሰዓት አካባቢ ወጣት ጌታእንዳለ ድምፅ ሰምቶ ሲነቃ፤ አባት አቶ ተሾመ ጫካ ተነስተው ሶፋ ላይ እጃቸውን ደረታቸው ላይ አድርገው ተቀምጠዋል፡፡ ጌታእንዳለ ‹‹ምን ሆንክ›› ብሎ ሲጠይቅ ‹‹እንደፈራሁት ትዕግስት ምግቡን መርዛ ሰጥታኛለች፡፡ ያመመኝ ለዚህ ነው፡፡›› ሲሉ አባት አቶ ተሾመ ለልጃቸው ምላሽ ሰጡ፡፡ ወጣት ጌታእንዳለ ብዙም አልደነገጠም፡፡ ምክንያቱም አቶ ተሾመ በተደጋጋሚ ይህንን ይላሉ፡፡ ጌታእንዳለ ለአባቱ ‹‹አሁን ግባ እና ተኛ፤ ነገ እንነጋገራለን፡፡›› ብሎ እርሱ ተሸፋፍኖ ተኛ፡፡
ጌታእንዳለ ለሊት 11 ሰዓት አካባቢ ለመጋቢት 18 ማጥቢያ የለበሰው አንሶላ ተገፈፈ፤ እግሩን ቀዘቀዘውና ቀና ሲል አባቱን አየ፡፡ ‹‹ሊቀሰቅሰኝ ነው›› ብሎ አሰበ፤ ነገር ግን አባቱ አቶ ተሾመ በእጃቸው የሽንኩርት መክተፊያ ቢላዋ ይዘው ነበር፡፡ ‹‹ አባ›› ብሎ እየጮኸ እናቱን ተጣራ፡፡ ለመነሳት ሲሞክር አቶ ተሾመ በያዙት ቢላዋ የቀኝ እጁን ወጉት፡፡ ለመከላከል ሲሞክር ግራውንም ሲደግሙት እህቱ ከመኝታ ቤት ተንደርድራ ወጣች፡፡ አቶ ተሾመ ፊታቸውን ወደ ትዕግስት ሲያዞሩ፤ ወጣት ጌታእንዳለ ተነስቶ ከኋላ ሊይዛቸው ሞከረ፤ ነገር ግን ቢላዋ የያዙበትን እጃቸውን መቆጣጠር አቃተው፡፡


አቶ ተሾመ ትዕግስትን እየደጋገሙ ሲወጉ፤ ወይዘሮ ወለላ ከመኝታ ቤት ወጥተው ከአቶ ተሾመ እጅ ቢላዋውን ለማስለቀቅ ቢሞክሩም አልቻሉም። ወይዘሮ ወለላም ከአቶ ተሾመ ጋር ሲታገሉ በቢላዋው ደረታቸውን እና ክንዳቸውን ተወጉ፡፡ ትዕግስት እና ጌታእንዳለ ከአባታቸው ጋር ሲታገሉ ሶስቱም ወደቁ፡፡ ትዕግስት መሬት ሆና አባት አቶ ተሾመ በጉልበታቸው ተንበርክከው ደጋግመው በቢላዋ ሲወጓት፤ እናቷን ወይዘሮ ወለላን ‹‹በሩን ከፍተሽ ውጪ፤ አምልጪ›› አለች። እናት በሩን ከፍተው ወጥተው መጮህ ጀመሩ፡፡ ልጅ ጌታእንዳለ ደም ስለፈሰሰው አቅቶት በደረቱ መሬት ወደቀ፡፡ አቶ ተሾመ ልጃቸውን ወጣት ጌታእንዳለን በተኛበት ከጀርባው የተለያየ ቦታ ወጉት፡፡ ትዕግስት እና ጌታእንዳለ አቅቷቸው መሬት እንደወደቁ አቶ ተሾመ በሩን ቆልፈው ቁልፉን ያዘው ወደ መኝታ ቤት ገቡ፡፡


ጌታእንዳለ ከውጪ ጫጫታ ሲሰማ መሬት ለመሬት እየተንፏቀቀ በር ለመክፈት ቢሞክርም፤ ስለተቆለፈ ሊከፈትለት አልቻለም፡፡ ትዕግስት ደጋግማ ስትጮህ አቶ ተሾመ በተደጋጋሚ እንደገና ትዕግስትን በያዙት ቢላዋ ወጓት፡፡ ወጣት ጌታእንዳለ አባቱ አቶ ተሾመ ትዕግስትን ሲወጓት እርሱም ጮኸ፤ በድጋሚ እንደገና ጀርባውን ወጉት፡፡ አቶ ተሾመ በኋላም ቢላዋውን አጥበው በደም የተጨማለቀ ልብሳቸውን ቀየሩ፡፡


ከደጅ የነበረው ጫጫታ ቆሞ፤ በር ተንኳኳ፤ ‹‹ በር ክፈት ፖሊሶች ነን ›› የሚል ድምፅ ተሰማ፡፡ ድርጊቱን ፈፃሚ አቶ ተሾመ ‹‹ ቁልፉ ጠፍቶብኛል ፖሊስ ከሆናችሁ ሰብራችሁ ግቡ፡፡›› አሉ፡፡ ፖሊሶቹ በሩን ሠብረው ገቡ። አቶ ተሾመ እጅ ሰጡ። ወጣት ትዕግስት እና ወጣት ጌታእንዳለ በፖሊስ መኪና ወደ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ተወሰዱ፡፡ እናት ወይዘሮ ወለላ ቀድመው ወደ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ሔደው የሕክምና እርዳታ እያገኙ ነበር። ትዕግስት ሆስፒታል እስከምትደርስ ሕይወቷ አላለፈም ነበር፡፡ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ግን የወጣት ትዕግስት ሕይወት ማለፉ ተሰማ፡፡


የፖሊስ ምርመራ
ግለሰቡ ማለትም አቶ ተሾመ ጫካ ወንጀል መፈፀሙን ተከትሎ ምርመራ ያካሔደው ፖሊስ ዘጠኝ የሰው ምስክር፤ ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃዎችን ማለትም ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሟች ትዕግስት ተሾመ የአስክሬን የምርመራ ውጤት፤ የጥሩነሽ ቤጂንግ አጠቃላይ ሆስፒታል የግል ተበዳይ የወይዘሮ ወለላ እና ሌላው የግል ተበዳይ የወጣት ጌታእንዳለ የህክምና የምርመራ ውጤት፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ የፎረንሲክ ምርመራ እና የተከሳሽ ቃል አያይዞ ለጠቅላይ አቃቢ ህግ አቀረበ።


በተጨማሪ የወንጀል ቦታ፣ የሟች አስክሬን እና ወንጀሉ የተፈፀመበትን ቢላዋ በፎቶ ያቀረበ ሲሆን፤ ወንጀል ፈፃሚው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 539 (1)(ሀ) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ከባድ የግድያ ወንጀል እና ከባድ የግድያ ሙከራ ወንጀል የፈፀመ መሆኑን በደንብ በሚያሳይ መልኩ አጠናቅሮ አቅርቧል፡፡


የጠቅላይ አቃቢ ሕግ ክስ
ተከሳሽ ማለትም አቶ ተሾመ ጫካ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ገላን ኮንደሚኒየም ህንፃ ቁጥር 13/18 ውስጥ፤ ‹‹ቤተሰቦቼ ያገሉኛል አይንከባከቡኝም፤ ሟች ትዕግስት ተሾመ ደግሞ በልዩ ሁኔታ ምግቤ ላይ መርዝ ልትጨምር ትችላለች፡፡›› በሚል ቂም በመጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ከለሊቱ 11 ሰዓት ለመጋቢት 18 አጥቢያ ጨካኝነቱን እና ነውረኛነቱን በሚያሳይ መልኩ ሟችን በቢላዋ አንገቷን፣ ደረቷን፣ ሽንጧን፣ ትከሻዋን፣ ሆዷን፣ ጭኗን ወግቷታል፡፡ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቿ ላይ በስለት በመወጋቷ ምክንያት ሕይወቷ ማለፉን ተከትሎ በከባድ የግድያ ወንጀል መከሰስ እንዳለበት የጠቅላይ አቃቢ ህግ ክስ አመላክቷል፡፡


ከላይ በተጠቀሰው ቤት እና ሰዓት አባት አቶ ተሾመ ጫካ ‹‹ ከቤተሰብ እገለላለሁ እና በአግባቡ አይንከባከቡኝም›› በሚል በተጨማሪ ወጣት ጌታእንዳለ ተሾመን፤ ጨካኝ እና ነውረኛነቱን በሚያሳይ መልኩ በተኛበት በመውጋት ደረቱን፣ አንገቱን ፣ ግራ እጁን፣ የእጁን ጣቶች እና የግራ እግሩ እና የግራ እግሩ ሶስቱ ጣቶች ላይ ጉዳት በማድረስ በከባድ የሰው መግደል ሙከራ ክስ የተመሠረተበት መሆኑን የክሱ መዝገቡ ያሳያል፡፡


ተከሳሽ አቶ ተሾመ ከልጆቹ በተጨማሪ ከአራት አስርት ዓመታት በላይ አብሯት በኖረች ሚስቱ ወይዘሮ ወለላ ላይም በተመሳሳይ መልኩ ደረቷን እና የቀኝ ክንዷን በመውጋት ደም እንዲፈሳት በማድረጉ በፈፀመው ከባድ ሰውን የመግደል ሙከራ የተከሰሰ መሆኑን መዝገቡ ያትታል፡፡

                             ውሳኔ

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት በአቶ ተሾመ ጫካ ላይ የቀረበውን ክስ አይቶ፤ ማስረጃውን መርምሮ እና ከህግ ጋር አገናዝቦ በሰጠው ውሳኔ ግለሰቡ ማለትም አቶ ተሾመ ጫካ በተከሰሰበት ከባድ ሠው የመግደል ወንጀል በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You