እርግዝና እና አካል ጉዳተኝነት

የስምንት ወር ነፍሰ ጡር ናት፡፡ ቁመቷ አጭር በመሆኑ ብዙዎች ነፍሰ ጡር መሆኗን ሲያዩ ይደናገጣሉ። ከዚህ ቀደም ኑሮዋን የምትገፋው በ‹‹ቡና ጠጡ›› ሥራ ነበር። አሁን ግን የመውለጃ ጊዜዋ እየተቃረበ በመምጣቱና ድካሙንም ስላልቻለችው ሥራዋን ለመተው ተገዳለች፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስሟ የተቀየረው አይናለም መኮንን፡፡

አይናለም ቁመቷ በማጠሩና የላይኛው ገጽታዋን ብቻ በመመልከት ሰዎች ብዙ ነገር ሲሉ ትሰማች፡፡ ‹‹ፈጣሪ ላያስችል አይሰጥም፤ ስለ ሁሉም ነገር ፈጣሪ ያውቃል›› ትላለች፡፡ ሰዎች እርግዝናዋን አይተው እንደሚጨነቁና እንደሚፈሩም ታውቃለች፡፡ ይህ ጭንቀትና ፍርሃት ታዲያ ከግንዛቤ እጥረት የመጣ እንጂ ሌላ ምክንያት እንደሌለው ትገልፃለች፡፡ ከዚህ አንፃር በተፈጥሮ ቁመታቸው አጭር የሆኑ ነፍሰ ጡር ሴቶች ትኩረት እንደሚሹና ቅድሚያ የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዳለባቸው ትናገራለች፡፡

‹‹ልጅን ያህል ነገር ልወልድ ስለሆነ ድካሙን እረሳዋለሁ፡፡ ምንም ያህል ነገር ቢኖር ከፈጣሪ ጋር እቋቋማለሁ፡፡ አንዳንድ ታክሲዎች ደረጃቸው ከፍ ስለሚል መውጣት እና መውረድ ያስቸግረኛል፡፡ አንዳንዴም ከታክሲ ለመውጣትና ለመውረድ ሰዎችን ደግፉኝ እላለሁ፡፡ በጉዞ ወቅት ታክሲ ጓ! ገጭ ሲል እሳቀቃለሁ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የሚያጋጥመኝን ችግር ሁሉ እየተወጣሁት ነው›› ስትል ትናገራለች አይናለም፡፡

አሁን ላይ የህክምና ባለሙያዎች እንደሌሎቹ ነፍሰ ጡር ሴቶች ለአይናለም ክትትል እያደረጉላት ነው፡፡ የህክምና ምክርም ይሰጧታል፡፡ እሷም ከፈጣሪ በታች ሥራው በህክምና ባለሙያዎች እጅ መሆኑን አምና የእርግዝና ክትትል እያደረገች ትገኛለች፡፡

አይናለም እንደምትለው የህክምና ቦታዎችና የህክምና አሰጣጥ ሂደት አመቺ አይደለም፡፡ አልጋዎች፣ መወጣጫ ደረጃዎች፣ መጸዳጃ ቤቶችም ምቹ አይደሉም፡፡ እነዚህና መሰል ነገሮች ላይ ብዙ መሠራት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ብዙ መሥራት ይቀራል። አካል ጉዳተኞቹን እንደ ጉዳት ዓይነታቸው ለይቶ ከመሥራት አንጻርም ተጨማሪ ሥራ ያስፈልጋል። ከህክምና ተቋማት ውጪ ባንክ ቤቶች፣ ሆቴሎችና ሌላም ዓይነት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አካል ጉዳተኛውን ያማከሉ አይደሉም፡፡ ለተሽከርካሪ የሚመቹ መንገዶችም ውስን ናቸው፡፡

ኤደን እቋር ጋዜጠኛ፣ ገጣሚ እና በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ የግንዛቤ ፈጠራ እና መብት ላይ ትሠራለች፡፡ ‹‹ልሳን ለአካል ጉዳተኞች›› የተሰኘ ድርጅት መሥራችና ዋና ዳይሬክተርም ናት፡፡ በቅርቡ ‹‹እርግዝና እና አካል ጉዳተኝነት›› የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ አብቅታለች፡፡

ኤደን መጽሐፉን ለመጻፍ ምክንያት የሆናት በእርግዝና፣ በወሊድና በአራስነት ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮች ሲታዩ አብዛኞቹ ችግሮች ቀድመው ቢታወቁ በቀላሉ መታለፍ የሚችሉ መሆናቸው ነው፡፡ አካል ጉዳተኛ እናቶች ካላስፈላጊ የሥነ ልቦና እና ተጨማሪ አካል ጉዳት ሊጠብቁ የሚችሉ ናቸው ብሎ በማመን ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ሞያዋ ስትሠራ ብዙ አካል ጉዳተኞች ከወሊድ ጋር ተያይዞ የገጠማቸውን ችግሮችን ስለምታውቅና ከዚህ ያገኘችውን ልምድ ለማካፈል እና ያለውን ግንዛቤ ለመቅረፍ በሚልም ነው መጽሐፉን የፃፈችው፡፡

ከቅድመ ወሊድ ጀምሮ እስከ አራስነት ቢታወቅ እና ቅድመ ዝግጅት ቢደረግባቸው ያግዛሉ ብላ ያሰባሰበቻቸውን መረጃዎች ሌሎች አካል ጉዳተኞች ቢያውቁት ይጠቀሙበታል ብላ መጽሐፉን ከማሳተም በተጨማሪ በነፃ እንዲዳረስ አድርጋለች፡፡

ኤደን እንደ ዕድል ሆኖ መልካም እና ልምድ ያለው ጥሩ ሀኪም በማግኘቷ ይህ ነው የሚባል ችግር አልገጠማትም። ነገር ግን በብዛት ያሉ ችግሮች ከግንዛቤ እጥረት እና ልምድ ካለመኖር የሚመጡ እንደሆነ ታስረዳለች፡፡ በተለይም በወሊድ ወቅት የሚሰጡ ማደንዘዣ ወይም መርፌ አሰጣጥ እና አወጋግ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶች ወይም የአካል ጉዳቱን በደንብ ካለመረዳት የሚመጡ ነገሮች አሉና አካል ጉዳተኛ እናቶች ካለባቸው ክፍተቶች አንጻር በእርግዝና እንዲሁም በወሊድ ወቅት ሊገጥማቸው የሚችለውን ሁኔታ ቀድመው እንዲረዱት ካለመደረግ ጋር ተያይዞ የሚደርሱ የሥነ ልቦና፣ የጤና እንዲሁም እናትንም ልጅንም እስከማጣት የሚደርሱ ችግሮች እንዳሉ ባደረገችው ጥናት ለመረዳት ችላለች፡፡

መጽሐፉ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ቅርንጫፍ እንዲሁም ካሳንቺስ በሚገኘው የድርጅቱ ቢሮ የሚገኝ ሲሆን፤ ድርጅቱ ዲጂታል ተደራሽነትን እውን ለማድረግ በሚያደርገው ጉዞ ውስጥ ከሚያሠራቸው እና ሊሠራባቸው ካሰባቸው መካከል አንዱ የሆነውን ድረ ገጽ ተመርቋል፡፡ መጽሐፋም http://www.lesanfordisability.org ድረ ገፅ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ አካል ጉዳተኞች በቀላሉ አውርደው ማንበብ ይችላሉ፡፡

‹‹አካል ጉዳተኝነት ለሴቶች በጣም ከባድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እርግዝና ሲጨመር ደግሞ በጣም ፈታኝ ነገሮች ይበዙበታል፡፡ እርግዝናን የበለጠ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ መረጃ ምንም ሳይኖር ሲቀር፤ እንዴት ማለፍ እንደሚቻል እና አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን መቼ መውሰድ እንደሚገባ ሳይታወቅ ሲቀር ነው። ተያያዥነት ያላቸው መረጃዎች ካሉ ግን ሁኔታዎች የተሻለ ይሆናል›› ብዬ አምናለሁ ትላለች ኤደን፡፡

‹‹ለምሳሌ እኔ ቀድሜ መረጃ አግኝቼ ቢሆን፤ ሊያጋጥም የሚችለውን ነገር መረዳት እችላለሁ፡፡ በተለይም አሁን ለሌሎች አካል ጉዳተኛ እህቶቼ ይህን መጽሐፍ በሚገባ ቀድመው ተረድተው እንዲዘጋጁ በሚገባ ያግዛል፡፡ ስትልም ትገልፃለች፡፡ በቀጣይ በርካታ እቅዶች እንዳሏትም አስረድታ፤ በተለይም ከዲጂታል ተደራሽነት እና አካል ጉዳተኞችን በጋዜጠኝነት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ከማብቃት፣ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ በኢኮኖሚው አቅሙን ከፍ ከማድረግ አኳያ ሰፊ ሥራ ለመሥራት መታሰቡን ትጠቁማለች፡፡

እርሷ እንደምትለው፣ አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ በሚሠራው ሥራ ያለው መተባበር ሰፊ ክፍተት ይታይበታል፡፡ ይህንን ለመቅረፍ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ በተለይ ድረ ገጹ በዚህ በኩል ሰፊ ሥራ ይሠራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በርካታ ችግሮች እንደማጋጠማቸው በተቻለ መጠን የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ መፍትሄ ላይ በማተኮር የተሻለ ነገር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ እርሷም ሁሉንም መረጃ እና አገልግሎት በተቻለ መጠን እንዲሁም አቅም ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ሆኖ እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን አካታች ሆኖ ማየት ምኞቷ መሆኑንም ትናገራለች፡፡

የማኅበረሰብ ህክምና ባለሙያዋ ዶክተር ሳራ ዮሐንስ በአሁኑ ወቅት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ስፔሻላይዝድ በማድረግ ይገኛሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በአካል ጉዳተኝነት እና በእርግዝና ላይ የተጻፉ መጽሐፍት የሉም። በማኅበራዊ ድረ ገጾችም ጉዳዩ አይነሳም፡፡ አካል ጉዳተኞች በእርግዝና ወቅት የተለየ የሚገጥማቸው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን የፅንሱ እና የእርግዝና ወራቱ እየጨመረ በመጣ ቁጥር የእንቅስቃሴ መገደብ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ከዚያ ውጪ ምንም የተለየ ነገር የለውም፡፡

ከዚህ አኳያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ለእርግዝና ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ ይህም ቅድመ እርግዝና ይባላል፡፡ በዚህም የተለያዩ ምርመራዎችን ማድረግ ያስፈልጋል። ለምሳሌ የስኳር፣ የደምግፊት እና የውስጥ ደዌ ህመሞች ምርመራን ያካትታል፡፡ በሥነ ልቦናም ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡በእርግዝና ጊዜ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ የእንቅስቃሴ ችግር ሊኖር ይችላል፡፡ መጨናነቅ ሊያጋጥም ስለሚችልና በተለይ ‹‹እኔ ወልጄ አቅፋለሁ ወይ?›› የሚለው ጥያቄ በብዛት ስለሚያጋጥም ምርመራዎችን ከማድረግ በተጨማሪ ቫይታሚኖችን መውሰድ እና የደም ዓይነትን ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡

እንደ ዶክተር ሳራ ማብራሪያ፣ እርግዝና በሦስት ወር የተከፋፈለ ሦስት ምዕራፎች አሉት፡፡ አንደኛው ምዕራፍ ላይ የእርግዝና ምልክቶች ይታያል፡፡ የማቅለሽለሽ፣ የማስመለስ፣ የምግብ ፍላጎት መቀየር እና ከሆርሞን ጋር የተያያዘ ሌሎች አካላዊ ለውጦች አሉት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹እስከ ዘጠኝ ወር እደርሳለሁ ወይ? የሚለው ጭንቀት ይበዛል፡፡ ስለዚህ በዚህ ወቅት የህክምና ክትትል ማድረግ ይገባቸዋል፡፡

በሁለተኛው የእርግርና ምዕራፍ ክብደት መጨመር የሚያጋጥም ነው፡፡ በተለይ ፅንሱ ባደገ ቁጥር ፊኛን ስለሚጫን ሽንት ቶሎቶሎ ይመጣል፡፡ በዚህ ጊዜ በክራንች የሚንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኛ እህቶች ጠንከር ያለ የብረት ክራንች ቢይዙ ወይም ደግሞ በተሽከርካሪ ወንበር ቢንቀሳቀሱ ይመረጣል፡፡ ቤታቸውን ለእነርሱ አመቺ እንዲሆን በሚገባ ማስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡ ድጋፍ የሚሰጣቸው ሰው ቢኖራቸውም ጥሩ ነው፡፡

ሦስተኛ ምዕራፍ ሲደርሱ ደግሞ ክትትላቸው ሳምንታዊ ወይም በቀን አንዴ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ «በምንድነው የምወልደው? በቀዶ ህክምና ነው? ወይስ በምጥ?›› የሚለውን ነገር ከሀኪማቸው ጋር በግልጽ መነጋገር ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህ አካል ጉዳተኛ ነፍሰ ጡሮች እርግዝናቸው ከሌላው የተለየ አይደለም። ምናልባትም የጉዳት ዓይነታቸው ከወገብ በታች ከሆነ የህብለ ሰረሰር (ስፓይናል ኮርድ) ችግር ይኖራቸዋልና ማደንዘዣ ከመሰጠቱ በፊት ቀደም ተብሎ ከሀኪሞች ጋር መወያየት ያስፈልጋል፡፡

ሁሉም አካል ጉዳተኛ ነፍሰ ጡር ሴቶች በቀዶ ህክምና ብቻ ነው የሚወልዱት፤ ማማጥ አይችሉም የሚል ነገር እንደሌለ የሚገልጹት ዶክተር ሳራ፤ ማደንዘዣ አሰጣጡ ላይ አጽንኦት መስጠት እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በተመለከተም ነፍሰ ጡር ሴቶች የሚሠሩት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ዶክተር ሳራ ተናግረው፤ አካል ጉዳተኛ ነፍሰ ጡሮች ሀኪማቸውን በማማከር ባሉበት ሆነው ሊሠሩ የሚችሉትን ቀለል ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደሚችሉም ነው የሚጠቁሙት፡፡

በማንኛውም ሰዓት ምጥ ሊፈጠር ይችላልና በሥነ ልቦና ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ በዚህም ሁሉም አካል ጉዳተኛ እናቶች ጤነኛ ልጅ ወልደው ማቀፍ ይችላሉ። ነገር ግን አካል ጉዳተኛ ነፍሰጡሮች በማኅበረሰቡ ከባድ ጊዜ ነው የሚሳልፉት፡፡ ስለሆነም መጨናነቅ የለባቸውም። በተጨማሪም ከአካባቢያቸው ብዙ ርቀው መሄድ የለባቸውም፡፡ የወሊድ ጊዜ ሲቃረብ ለእናትየው ልብስ፤ ለሚወለደው ልጅ መጠቅለያ፣ ዳይፐር እና ልብስ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ቤተሰብም ከእነርሱ መራቅ የለበትም፡፡

በመጨረሻዎቹ የእርግዝና ጊዜያት የእግር እና የፊት እብጠት፣ የድካም ስሜት፣ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የውጋት እና የቁርጠት ስሜት፣ ሽንት ቶሎ መምጣት እንዲሁም ሀሰተኛ ምጥ ይታያል፡፡ ስለዚህም አልትራሳውንድ በመታየት የልጁን እንቅስቃሴ እንዲሁም የውሃ እንሽርት መጠንን መከታተል ይገባል፡፡ ከምንም በላይ የጓደኛ፣ የቤተሰብ እና የቅርብ ዘመድ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ሥነ ልቦናዊ ድጋፍም ያስፈልጋቸዋል፡፡ በእርግዝና ወቅት የሆርሞኖችን መጨመር ተከትሎ ‹‹አማረኝ›› የሚባል ነገር የሚያጋጥም ሲሆን፤ ቤተሰብ፣ ባለቤታቸው እንዲሁም ጓደኞቻቸው ያማራቸውን ነገሮች ማምጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከወሊድ በኋላም ቢሆን የተለያዩ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይገባል፡፡ ከዚህ ቀደም ክራንች የሚጠቀሙ ከሆነ አሁን ደግሞ ሰፋ ያለ ተሽከርካሪ ወንበር መጠቀም አለባቸው፡፡ እረፍት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ምግብ በሚገባ መመገብ ይኖርባቸዋል፡፡ ድህረ ወሊድ ክትትላቸውን ከወለዱበት ተቋም መቀጠል አለባቸው፡፡

በድህረ ወሊድ ወቅት የተለያዩ ለውጦች በመኖራቸው በትዕግስት ማለፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ለአብነትም ከተሽከርካሪ ወንበር ወደ ክራንች ለመሸጋገር ወራትን ሊፈጅ ይችላል። በተጨማሪም ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥመውን ድባቴ ማስወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ ሌላው የመንግሥትም ይሁን የግል ሥራ ያላቸው እናቶች አራት ወር የወሊድ ፈቃድ እንዳላቸው ይታወቃል። በተለይም ለአካል ጉዳተኛ እናቶች ወሩ ላይ ጭማሪ ቢደረግ የተሻለ ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ በመንግሥትም ይሁን በግል ተቋማት ካርድ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ መስማት ለተሳናቸው እና ማየት ለሚቸገሩ ሰዎች የተለዩ የጤና ባለሙዎችን እንዲሁም የምልክት ቋንቋ የሚችሉ የጤና ባለሙያዎች በመቅጠር ብሎም የሰው ኃይል በመጨመር እነርሱ እንዳይጉላሉ እና እንዳይጨናነቁ ማድረግ ይገባል። በጤና ሚኒስቴርም በጤና ተቋማት ላይ በራሪ ወረቀት በማሳተምም ይሁን በሌላ መንገድ እውቀትን የሚስጨበጥ የልምድ ልውውጥ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ነፍሰጡሯ አይንአለምም ለውጥ ለማምጣት ግንዛቤ ላይ በስፋት መሠራት አለበት ትላለች፡፡ ‹‹አካል ጉዳተኞች አይችሉም›› ተብሎ የሚነገረውን ነገር መስተካከል እንዳለበትም ታመለክታለች፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥትም ሆነ ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የድርሻቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው ታሳስባለች፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You