ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ የምርምር ስራዎችን ለማከናወን ብዙውን ጊዜ መማር መሰልጠን አልያም በተሻለ የኑሮ ደረጃ መገኘት ይጠይቃል። በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎ ከምርምር የተገኙ የተመሰከረላቸው ጠቃሚ ውጤቶችን በነጻ ለተጠቃሚ ማበርከት ደግሞ ለሀገር ያለን ቀናኢነት የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን ልዩ የሕዝብና የሀገር ፍቅርንም የሚጠይቅ ነው። ይህንን ለማድረግ የሚታደሉት ታዲያ ጥቂቶች ብቻ ናቸው። የሚገኘው ጥቅም ደግሞ ብዙሃኑን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፤ ለሰሪውም ሆነ ለተመልካች የሚፈጥረው ደስታ እጥፍ ድርብ ይሆናል።
እንዲህ አይነት የበጎነት አገልግሎት ተግባራት በወቅቱ ከሚሰጡት ጥቅም ባለፈ ለትውልዱም የሚያስተላልፉት መልእክት ይኖራል። ማለትም አንድ ግለሰብ ለሀገርና ለሕዝብ የሠራቸውን አበርክቶዎች በማየት ነገ እኛም እንዲህ ብናደርግ ምስጋናና ፍቅርን እናገኛለን የሚል ትውልድ መፈጠሩ አይቀርም። የዛሬው የሕይወት አምድ እንግዳችን አቶ ተገኑ አየለ ይባላሉ። በመደበኛው የትምህርት ሂደት እዚህ ግባ የሚባል ደረጃ ባይኖራቸውም ከራሳቸው አልፈው በርካቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ ለመስራት የቻሉ ናቸው። እኚህ አባት ዛሬም ድረስ በእርጅና ዘመናቸው ላይ ሆነው የልፋታቸውን ውጤት ለሌሎች ለማዳረስ በራቸውን ክፍት አድርገው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
ውልደትና እድገት ፤
አቶ ተገኑ አየለ የተወለዱት በ1941 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ልዩ ስሙ ጉንዶ መስቀል በሚባል አካባቢ ወሬ ሁላ በተባለች መንደር ነው። የአቶ ተገኑ ቤተሰቦች በዘመናቸው ባላባት የሚባሉ የተትረፈረፈ ሀብት ያላቸው አዛዦችም ነበሩ። እናታቸው ወይዘሮ እናኑ አለሙ ገና የሶስት ዓመት ልጅ እያሉ ሳይታሰብ አይናቸው የጠፋ ቢሆንም፤ የባላበት ልጅ በመሆናቸው በወቅቱ ትዳር እንዲመሰርቱ ተደርገው ይኖሩ ነበር። በዘመድ አዝማድ በተከበበ መንደር ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ይኖሩ የነበሩት የአቶ ተገኑ ቤተሰቦች በአንድ ጥሩ ያልሆነ ወቅት የቤተሰቡን አቋም የሚያናጋ አጋጣሚ ተፈጠረ። በ1953 ዓ.ም በአካባቢው በስፋት ተከስቶ የነበረው የወባ በሽታ የአቶ ተገኑን አባት ጨምሮ በርካታ ቤተሰባቸውን ለሞት ዳረጋቸው።
በዚያ ጊዜ አቶ ተገኑ ቤተሰብ ለመንከባከብ የሚያበቃቸው አቅም ባይኖርም ትልልቆቹ ሰዎች በሙሉ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው እናታቸውን እና ታናናሽ ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን የመጠበቁ ኃላፊነት በእርሳቸው ጫንቃ ላይ ወደቀ። የተፈጠረውን ነገር በፀጋ የተቀበሉት አቶ ተገኑ ደከመኝና ሰለቸኝ ሳይሉ ማየት የተሳናቸውን እናታቸውን ጨምሮ መላውን ቤተሰብ የመንከባከበቡን ኃላፊነት መወጣት ቀጠሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ፤ አንድ ቀን የክትክታ እንጨት ሲፈልጡ የተፈናጠረች የእንጨት ስንጣሪ የቀኝ አይናቸው ውስጥ ገባች። በወቅቱ በአካባቢው በቂ ሕክምና ባለመኖሩ እና ቤተሰባቸውንም ትተው መንቀሳቀስ ስላልፈለጉ ያቺን ስንጣሪ በአይናቸው ውስጥ እንደገባች ለረዥም ዓመት አቆይዋት። ከዚህ በኋላ ነገሮች እየተባባሱ ሲመጡ ከአንድ ጓደኛቸው ጋር በመሆን በ1959 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ወሰኑ።
በወቅቱ በቂ የሚታረስ መሬት ስለነበር እናታቸውን እንዲንከባከቧቸው ለአራት ወንድምና እህቶቻቸው ትተው ወደ አዲስ አበባ ያቀናሉ። አዲስ አበባም እንደ ደረሱ እርሳቸው በቅርበት የሚያውቁትና ያዘጋጁት የኔ የሚሉት ማረፊያ የሚሰጥ የሚያስጠጋ ዘመድ ስላልነበራቸው፤ መዳረሻቸው ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ አብሯቸው ከመጣው ጓደኛቸው ዘመድ ቤት ነበር። እዛም ተቀምጠው ለተወሰነ ጊዜ የቀን ሥራና ሌሎች ስራዎችንም እየሰሩ ቆዩ። ከጊዜ በኋላ ችግራቸውን የተገነዘበ በቅርበት የሚያውቃቸው አንድ የበግ ነጋዴ በአንድ ግለሰብ ቤት እንዲቀጠሩ ሁኔታዎችን አመቻቸላው። ጥያቄውን የተቀበሉት አቶ ተገኑም እዚያ ቤት ለስራ በገቡበት አዲሱ ቤት ጥበቃን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወኑ ለዓመታት ሲያገለግሉ ቆዩ።
በ1960 ዓ.ም ግን በሕይወታቸው አዲስ ምእራፍ የሚጀምርበት አጋጣሚ ተፈጠረ። በቤታቸው ሲያሰሯቸው የነበሩት ግለሰብ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የሚሠሩ መሀንዲስ ነበሩ። እናም የአቶ ተገኑን ቅልጥፍና እና ታዛዥነት በማየት እርሳቸው የሚሰሩበት ተቋም ውስጥ እንዲቀጠሩ አደረጓቸው። አቶ ተገኑ ሥራቸውን የጀመሩት በቀን ሰራተኝነት የፓንፕ ኦፕሬተር በመሆን ነበር። የሥራ ቦታቸው ደግሞ እዛው ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ በሚገኝ ትልቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ግቢ ውስጥ ነው። በዚህ ሁኔታ ከቆዩ በኋላ የደርግ መንግስት በመጣበት ወቅት መንግስት ለበርካታ ተቋማት ያስተላለፈው ውሳኔ እርሳቸው የሚሰሩበት መስሪያ ቤትም ይደርስና ቋሚ ሰራተኛ ለመሆን በቁ። ከዚህ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት በቆጣሪ ምርመራ ክፍል፤ በቴክኒሺያንነት፤ በሲኒየር ቴክኒሺያንነት ደረጃ ለመሥራት በቅተዋል። በእነዚህ ጊዜያትም ቀልጣፋ ስለነበሩና የተሻለ አፈፃፀምም ስለነበራቸው በአዲስ አበባ ዋና ዋና በሚባሉት አካባቢዎች ለአስቸኳይ ስራ ሰራተኛ ሲፈለግ ከሚመሩት መካከል ሆነው ይመደቡ የነበሩትም እርሳቸው ነበሩ። አቶ ተገኑ ብሔራዊ ቤተ መንግስት፤ ኢዮቤልዩ ቤተ መንግስት፤ ፓርላማ፤ ጥይት ቤት፤ አፍሪካ ሕብረት፤ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እና ሌሎችም አካባቢዎች ላይ ይሠሩ ነበር።
የቤተሰብ ሁኔታ
አቶ ተገኑ ትዳር መስርተው አዲስ ሕይወት መኖር የጀመሩት በ1964 ዓ.ም ነው። ዛሬ ድረስ የትዳር አጋራቸው የሆኑትንና «እዚህ ለመድረሴ ምክንያት ነች» የሚሏቸውን ባለቤታቸውን ያገኙበትንም አጋጣሚ እንዲህ ያስታውሱታል። «እኖር የነበረው አሁን ያለሁበት አካባቢ በቤት ኪራይ ነበር፤ ከባለቤቴ ወይዘሮ የሻረግ ገብረህይወት ጋርም የተገናኘነው እዚሁ አካባቢ ነው። ትውልዷ አንኮበር አካበቢ ሲሆን፤ በወቅቱ እኛው ሰፈር ሰው ቤት ተቀጥራ ትሰራ ነበር። ግንኙነታችን የጀመረውም በዚሁ አጋጣሚ ነው። ካየኋትና መግባባት ከጀመርን በኋላ እራሴው ጥያቄ አቅርቤ ፈቃደኛ በመሆኗ ወዲያው ትዳር ለመመስረት በቃን። ባለቤቴ ጥሩ ጸባይ ያላት ብቻ ሳትሆን ጓደኛም ሰው ነበረች። ከተጋባን ጊዜ ጀምሮ አንድ ቀን ችግር የሚባል ነገር ገጥሞኝ አያውቅም።
በ1975 ዓ.ም ቦታ ተመርተን ቤት ሰርተናል። ላለፉት አርባ ዓመታትም የራሴን መኪና ገዝቼ ሳሽከረክር ቆይቻለሁ። ባለቤቴ ለኔም ጥሩ ሚስት፤ ለልጆቼም ጥሩ እናት ነች። በትዳር ዘመናችን ሰባት ልጆችን ወልደን አስራ ስድስት የልጅ ልጆችንም ለማየት በቅተናል። እሷ በሁሉም ነገር ከጎኔ ትቆምና ታበረታታኝ ስለነበር አቅጄ ያላሳካሁት ነገር አልነበረም። ልጆችን በማሳደግ ረገድም የተዋጣላት ነበረች። ልጆቻችን ጥሩ ስነ ምግባር ያላቸው ስራ የሚወዱና ታዛዥ ናቸው። ለዚህ ደግሞ እርሷ ብዙውን ሥራ ሰርታለች። ዛሬም ድረስ የሚሰማኝ የእናቴ ምትክ እንደሆነች ነው » ይላሉ።
የምርምር አበርክቶ
አቶ ተገኑ በተቀጠሩበት መስሪያ ቤት ጠንካራና ጎበዝ ከሚባሉት ቀዳሚ ሰራተኞች መካከል ለመሆን በቅተዋል። በቆጣሪ የምርመራ ክፍል፤ በቴክኒሺያንነትና በኮሌጅ ምርመራ ዘርፍ በሊኒየር ቴክኒሺያንነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ይህም ሆኖ አቶ ተገኑ የሁኔታዎች አለመመቻቸትም ሆነ የአንድ አይናቸው ጉዳት ለመማር ለማወቅ የነበራቸውን ፍላጎት አላገደውም። የነበሩት ሁኔታዎች ምቹ ባይሆኑም ያለውን አጋጣሚ በመጠቀም ሚያዚያ 23 መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ እስከ ስምንተኛ ክፍል ለመማር ችለዋል። አቶ ተገኑ ወደ ምርምር ስራ የመራቸውንና በተለያዩ ጊዜያት አስከ መሸለም ያ ደረሰ ውጤት ያስገኘላቸውን ሥራ የጀመሩበትን አጋጣሚ እንዲህ ያስታውሱታል።
«አንድ ቀን በቀድሞው የፍትህ ሚኒስቴር ሕንጻ አካባቢ ውሃ እየፈሰሰ እንደሆነ መረጃ ይደርሰንና ለመጠገን እንቀሳቀሳለን። እዛ ደርሰንም ችግሩ የተፈጠረበትን ቦታ ለመለየት ያደረግነው የተለያየ ሙከራ እንደሌላው ጊዜ በቀላሉ ውጤታማ ሳይሆን ቀረ። ከብዙ ልፋት በኋላ ከውጪ ሀገር ጃፓን ተምረው የመጡ ባለሙያዎች እኛ በወቅቱ እንድንጠቀምባቸው የማይፈቀዱልንን «ሳውንዲንግ ባር» እና «ቦሪንግ ባር» በመባል የሚታወቁ መሳሪያዎችን በመጠቀም ችግሩን ይለዩታል። ለካስ ቧንቧው የተሰበረው እዛ አካባቢ ሳይሆን በርቀት ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ ነበር። ከዚያ በኋላ ባለሙያዎቹ የተጠቀሙባቸው መሳሪያዎች ምንድን ናቸው? ብለን ስናጣራ «ሳውንዲንግ ባር» በተለያዩ ምክንያቶች የቧንቧ መስመር ተበላሽቶ ውሃ እየፈሰሰ ከሆነ ያለበትን ቦታ በድምፅ ለመለየት የሚያስችል ነው። ሌላኛው « ቦሪንግ ባር » ደግሞ ተመሳሳይ ችግር በአስፋልት እና ኮንክሪት ንጣፍ ባለባቸው ቦታዎች ላይ ሲደርስ አስፋልቱ ሳይቆፈር በመሬት ውስጥ እርጥበትን መነሻ በማድረግ ችግሩ ያለበት ቦታ የሚለይበት መሳሪያ መሆኑን ስረዳ እነዚህን መሳሪዎች ለማግኘት ወይም ለመስራት ተመኘሁ።
ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያትም በየእለት ከእለት ሥራችን እነዚህን መሳሪያዎች ለመጠቀም የምንፈልግ ቢሆንም እንከለከል ስለነበር ማግኘት ሳንችል ለረዥም ግዜ ለመቆየት ተገደድን። በእነዚያ ጊዜያትም ስራችንን እናከናውን የነበረው አካባቢውን በመቆፈር በተለመደው አድካሚና ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ ብዙ ኪሳራም የሚያስከትል አሰራር ነበር። በዚህ አጋጣሚ እነዚያ መሳሪያዎች እንዲኖሩኝ ነገሩን ተከታትዬ ለማወቅ መጣር ጀመርኩ። ነገር ግን መሳሪያዎቹ ከውጪ የመጡና ውድ በመሆናቸው ይበላሻሉ በሚል ሰበብ ከባለሙያዎች ውጪ ማንም እንዲጠቀምባቸውም ሆነ እንዲነካቸው አይፈቀድም ነበር።›› ይላሉ።
ያ ዘመን በአንድ ወገን መላው የከተማ ነዋሪ በቂ ውሃ የሚያገኝበት ጊዜ አልነበረም። በአንፃሩ ደግሞ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በግለሰቦች ግቢ ውስጥም ሆነ በመንገድ ላይ እዚህም እዛም እየፈሰሰ የሚውል ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ነበር። ይህ ነገር ደግሞ አቶ ተገኑን በእጅጉ ያበሳጫቸው ያሳስባቸውም ነበር። ውሃው በመንገድ ላይ የሚፈስ ቢሆንም እንደ ሀገር የሚያስከትለው ችግር አለ። የሚፈሰው ደግሞ በግለሰቦች ቤት ሲሆን ያልተጠቀሙበትን እንዲከፍሉ ከማድረግ ባሻገር ባለቤቶችን ከተከራይ እና ከውሃ ፍሳሽ ሰራተኞች ጋር ተገቢ ወዳልሆነ እሰጥ አገባ ውስጥ ሲከታቸው በተደጋጋሚ ይስተዋላል። ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድ ቦታ የውሃው መስመር ተበላሽቶ ውሃ ወደውጪ መፍሰስ ጀመረ ማለት ውሃ በጠፋበት ወይንም በተቋረጠበት ወቅት መስመሩ በአካባቢው ያለውን የተበከለ ቆሻሻ ውሃ ወደመስመሩ ስቦ ያስገባዋል። ይህ ከግለሰብ አልፎ ለማህበረሰብ ጤና ጠንቅ የሚሆን ነው። በዚህም የተነሳ አቶ ተገኑ የመሳሪያዎቹ በስፋት መመረትና ወደ ስራ መግባት የግድ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደረስኩ። ይላሉ።
አቶ ተገኑ ይህን ሀሳባቸውን ይዘው ባለበት ወቅት አንድ ቀን የቅርብ አለቃቸው እቃዎቹን መኪና ውስጥ ትቶ ሲሄድ፤ አጋጣሚውን በመጠቀም በደንብ አገላብጠው እያንቀሳቀሱ የመመልከቱን እድል ያገኛሉ። በወቅቱ የተረዱትና ለራሳቸው የነገሩት ነገር ቢኖር መሳሪያዎቹን ራሳቸው መስራት እንደሚችሉ ነበር። በዚህም መሰረት ብዙም ጊዜ ሳይሰጡ እቅዳቸውን ለማሳካት መንቀሳቀስ ይጀምራሉ። በዚህም በቅርብ በአካባቢያቸው ያገኟቸውን እንደ ፌሮዎች ያሉ ብረቶችን በመሰብሰብ መስራት ይጀምራሉ። በዚህ እንቅስቀሴ ሊሳካ እንደሚችል የሚያመላክት የተወሰነ ውጤት ቢያገኙም አመሳስሎ የመስራቱ ነገር በፈለጉት መልኩ ሳይሳካለቸው ይቀራል።
ከተወሰነ ጊዜያት በኋላ የመጀመሪያ ስራቸው ያልተሳካው የብረቱ አይነት የተለየ መሆኑን በመረዳት ለዛ የሚሆን ብረት ለመፈለግ ወደ መርካቶ ሱማሌ ተራ ያቀናሉ። ከጥቂት ውጣ ውረድ በኋላ አላማቸውን ሊያሳካ የሚችል ብረት ለማግኘት ይበቃሉ። ይጠቅሙኛል ያሏቸውን ግብአቶች ሰብስበው በመሄድ ስራቸውን በድጋሚ እንዳዲስ ይጀምራሉ። ነገሩን በደንብ ተረድተውት ስለነበር ብዙም ሳይለፉ መሳሪያዎቹን ከውጪ ከመጡት ጋር አመሳስለው ለመስራት ይበቃሉ። በራሳቸው መስፈርትም መሳሪያዎቹን ሞክረው መስራታቸውን ያረጋግጣሉ። ቀጥለውም ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ወጪ ወደ ሀገር ቤት የገቡት መሳሪያዎች በምን መስፈርት ተመርምረው ይሆን ወደ ሀገር ቤት የገቡት የሚል ጥያቄ በአእምሯቸው ይመጣል። ይህም ሆኖ እርሳቸው ያረጋገጡትን ነገር ብቻ ይዘው ምንም ነገር ለማድረግ ስላልፈቀዱ አማራጭ ያደረጉት ውጪ ሀገር በመሄድ ሰልጥነው የመጡ ባለሙያዎች ትክክለኛነቱን እንዲመረምሩላቸው መጠየቅ ነበር። ባለሙያዎቹም የተሰሩትን ነገሮች አቅማቸው በፈቀደ ፈትሸው የፈጠራ ስራው ትክክል መሆኑን እና ከውጪ ከመጣው ጋር ተመሳሳይ ስራ ሊሰራ የሚችል መሆኑን ያረጋግጣሉ።
አቶ ተገኑም እነዚህን ውጤቶች መነሻ በማድረግ መሳሪያዎቹን ወደመስሪያ ቤታቸው በመውሰድ በስጦታ ያበረክታሉ። የተቋሙ ኃላፊዎችና ሰራተኞች መሳሪያዎቹ መስራት የሚችሉ መሆናቸውን ቢያረጋግጡም፤ ነገሩ በሌላ ሶስተኛ ወገን መረጋገጥ ስላለበት ለጥራትና ደረጃዎች መዳቢ ባለስልጣን ደብዳቤ ይፅፉና ይልኳቸዋል። ጥራትና ደረጃዎች መዳቢ ባለስልጣን ግን የእዚህ አይነቱን መሳሪያ የሚመረምርበት ማሽን ስለሌለው እንደማይችል ያስታውቃል። እንደ ግለሰብ አቶ ተገኑ እየተገለገሉባቸው ቢሆንም መሳሪያዎቹ ግን ለዘጠኝ ዓመት ያክል እውቅናም ክልከላም ሳያገኙ በእንጥልጥል ይቆያሉ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ አቶ አሊ አብዶ የከተማዋ ከንቲባ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ግን አዲስ ታሪክ የሚጀምርበት አጋጣሚ ይፈጠራል። ግምገማ መካሄድ ስለነበረበት ሁሉም ሰራተኛ የተሰበሰበበት የውይይት መድረክ ሲካሄድ አቶ ተገኑ የሆነውን ነገር ሁሉ ለከንቲባው ያሰረዳሉ። ከንቲባውም ይህ ነገር ራሱ የመልካም አስተዳደር ክፍተት መኖሩን አመላካች እንደሆነ በመግለፅ ለቦርድ እንዲቀርብና በተገቢው ደረጃ ታይቶ ለጉዳዩ መልስ እንዲሰጥ ትእዛዝ ያስተላልፋሉ። በዚህም መሰረት ዘጠኝ ዓመት የተቀመጠው ጉዳይ በሶስት ወር ውስጥ ምላሽ ለማግኘት ይበቃል። በመልሱም መሳሪያዎቹ ከውጭ ሀገራት ከመጡት ጋር ተመሳሳይ ደረጃ ላይ እንደሆኑ በመግለፅ በብዛት ቢመረቱም ከውጪ የሚመጣውን ሊተኩ የሚችሉ መሆናቸው ማረጋገጫ ይሰጣቸዋል። አቶ ተገኑም መሳሪያዎቹ ተባዝተው በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላው ሀገሪቱ መዳረስ አለባቸው ብለው ስላሰቡ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ስራቸውን ያቀርባሉ። ሳይንስና ቴክኖሎጂም የተወሰነ ጊዜ በጥናትና ምርምር መሳሪያዎቹን ፈትሾ ችግር የሌለባቸው መሆናቸውን በማረጋገጥ እውቅና ይሰጧቸዋል።
ከዚህ በኋላ የአቶ ተገኑ የልፋት ውጤቶች ይፋ በመሆኑ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ በተደጋጋሚ ይቀርቡ ነበር። ይህም በማህበረሰቡ ዘንድ እውቅና እና አድናቆትን አስገኝቶላቸው ቆይቷል። በዚህም ደሴ ባቲ ጠቅላላ ሆስፒታል ተመሳሳይ ችግር ገጥሞት ለረዥም ዘመን ቆይቶ ነበር። በእርሳቸው በኩል የሆስፒታሉ ችግር ተቀረፈ። የሆስፒታሉ ባለቤትም በተሰራው ስራ በመደነቅ ከገንዘብ ክፍያ ባለፈ ሁለት ኩንታል ጤፍ በመስጠት አቶ ተገኑን እቤታቸው ድረስ ይመልሷቸዋል። በተመሳሰይ አዲስ አባባ ዋሪት ሕንፃ፤ ጌጅ ኮሌጅ፤ አገልግሎቱን አግኝተው ለአቶ ተገኑ የምስጋና ደብዳቤ ካበረከቱላቸው ተቋማት መካከል ይጠቀሳሉ።
የጡረታ ሕይወት
አቶ ተገኑ በዚህ ሁኔታ በሞራል በመስሪያ ቤታቸው ሲሠሩ ቢቆዩም በ1996 ዓ.ም እርሳቸው ባይፈቅዱም የሕይወታቸውን መስመር የቀየረ አጋጣሚ ይፈጠራል። ወቅቱ መንግስት የትምህርት ማስረጃን መሰረት በማድረግ የሰራተኞች ድልድል ማድረግ የጀመረበት ጊዜ ነበር። ይህንንም ተከትሎ በአቶ ተገኑ ስር ይሰሩ የነበሩት ሰዎች የተሻለ የትምህርት ማስረጃ አላቸው ስለተባለ ሁሉም እንዲያድጉ ጥቂቶቹም የእርሳቸው ኃላፊ እንዲሆኑ ይደረጋል። ተቋሙም ኃላፊዎቹም ሆነ ሰራተኞቹ አቶ ተገኑ ትጉህ ሰራተኛ ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው የሰሯቸውን ስምንት መሳሪያዎች ያለምንም ክፍያ ለተቋሙ ያበረከቱ መሆናቸው እየታወቀ በድልድሉ ካሉበት ደረጃ ዝቅ እንዲሉ ይደረጋሉ። አንዳንዶችም የደረጃ እድገቱን አስመልክተው አቶ ተገኑን ተመራማሪው… ባለግኝቱ … እያሉ ያሾፉባቸው ስለነበር እርሳቸውም መረበሽ ይጀምራሉ። በዚህም የተነሳ ግንቦት ሰላሳ ቀን 1996 ዓም በፈቃዳቸው ጡረታቸውን አስከብረው ስራቸውን ለመልቀቅ ይገደዳሉ።
አቶ ተገኑ በዚህ አይነት መገፋት ሊባል በሚችል ደረጃ ለሰላሳ አምስት ዓመታት ያህል ያገለገሉበትን መስሪያ ቤት በፈቃዳቸው ቢለቁም፤ ከስራቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ግን አልተቋረጠም ነበር። ምንም እንኳን ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር የገንዘብ ችግር ባይኖርባቸውም ብዙ የተመሰገኑበትን ስራቸውን በግላቸው መስራት ይጀምራሉ። ቦሌ መንገድ ወሎ ሰፈር አካባቢ «ተገኑ የውሃ ብክነት ምርመራ ድርጅት » የሚል በማቋቋምም ስራቸውን ይቀጥላሉ። በእነዚህ ጊዜያትም እርሳቸው ጋር እየቀረቡ የስራ እድል ከማግኘት ባለፈ እውቀት ለማግኘት የበቁ በርካታ ወጣቶች ነበሩ።
ይህ እንዳለ ሆኖ በተቋም ደረጃ እውቀትና ልምዴን ለትውልድ ማስተላለፍ አለብኝ ብለው የሚያምኑት አቶ ተገኑ የነጻ ስልጠና ለመስጠት የሚመለከታቸውን አካላት ሁሉ ሲጠይቁ ቆይተዋል። ከእነዚህም መካከል ይሰሩበት ከነበረው ተቋም ውጪ የሚከተሉትን በደብዳቤ ጠይቀው ነበር። በወቅቱ የአቅም ግንባታ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ፤ በተጨማሪ ለአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በየወቅቱ ለነበሩት ኃላፊዎች በነፃ ስልጠና እንድሰጥና ሞያዬን እንዳካፍል ይፈቀድልኝ ሲሉ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። ይህም ሆኖ አቶ ተገኑ በ71 ዓመታቸው ዳሸን ባንክ ከአርትስ ቴሌቪዥን ጋር ባካሄደው የስራ ፈጠራና የንግድ ውድድር ላይ ለመሳተፍ በቅተዋል። በዚህም ነሐሴ 26 ቀን 2012 ዓ.ም ውድድሩን ደረጃ በመያዝ አጠናቀው የሰርተፍኬትና የአምስት ሺ ብር ሽልማት ለማግኘት በቅተዋል።
በእኛ ዘመን የውሃ በቆሻሻ መበከልና ያለአግባብ መፍሰስ በስፋት ይስተዋል ስለነበር የአዳር ሰራተኞች ተመድበው በየሌሊቱ እየተሽከረከሩ ቁጥጥር እስከማድረግ የደረሰ እርምጃ ይወሰድ ነበር። ይህ ችግር በአሁኑ ወቅትም አለ። የሚሉት አቶ ተገኑ በዚህ ዘመን ደግሞ ነገሩን የባሰ የሚያደርገው አብዛኛው የውሃ መስመር ከውሃ መፍሰሻ ቦዮች ጋር አንድ ላይና የተቀራረበ መሆኑ የውሃ መስመሮችን ለመበከል ቅርብ ያደርጋቸዋል። በዛ ላይ ሁሉም የከተማዋ የውሃ መፍሰሻ ቦዮች በቆሻሻ ፍሳሽ የተሞሉ በመሆኑ የቧንቧ ውሃው የመበከል እድሉ ሰፊ ነው። አንዳንድ ጊዜ በየቤታችን የሚቀዳው የደፈረሰ ውሃም ለዚህ ምስክር ነው። በመሆኑም ችግሩ እንዲቀረፍ ዛሬም ብዙ መስራት ይጠበቃል ይላሉ።
መልዕክት
እኔ በአሁኑ ወቅት ሰባ ስድስት ዓመት ሆኖኛል። በወጣትነቴ የአቅሜን ተሯሩጬ ስለሰራሁ የሚቸግረኝ ነገር የለም። በፈጣሪ እርዳታ ልጆቼም ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ በቅቺያለሁ። ነገር ግን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በየሰፈሩ ያለ ስራ ተቀምጠው የሚውሉ ወጣቶችን ስመለከት እረበሻለሁ። እነዚህን አልባሌ ቦታ እንዳይውሉና ለሱስ እንዳይዳረጉ የማድረጉ ኃላፊነት የመንግስት ብቻ ሳይሆን የእኛም ነው። እኔ እድሉን አግኝቼ ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ ወጣቶችን አሰልጥኜ ስራ ቢይዙ የአእምሮ እረፍት አገኛለሁ። ወጣቶችም ሁኔታዎች ሙሉ ለሙሉ እስኪመቻቹላቸው ከመጠበቅ ተንቀሳቅሰው ለፍተው ራሳቸውን ሊያበቁ ይገባል እላለሁ።
በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት የአዲስ አባባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የሚሰሩትን እያየሁ ነው። በጣም የሚያስደስት ስራ ነው። በየመንገድ ዳርቻ የመፀዳጃ ቤት እየተገነባ ነው። ለዚህም አስር የእጅ መታጠቢያ የመጸዳጃ ቤት መቀመጫና ሌሎች አንዳንድ ነገሮችንም በስጦታ ለማበርከት ያዘጋጀሁ ሲሆን፤ ሁኔታዎች ሲመቻቹ የማበረክት ይሆናል። በእንዲህ አይነቱ ስራ መተባበር ከሌሎችም የሚጠበቅ ይሆናል ሲሉም አቶ ተገኑ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም