«ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች»ሀመድ ሙሐመድ – በኢትዮጵያ የኳታር አምባሳደር

አዲስ አበባ:- ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለይ በውሃ ሀብት አጠቃቀም፤ በኢነርጂ ዘርፍ እንዲሁም በኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዘርፎች አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን በኢትዮጵያ የኳታር አምባሳደር ሀመድ ሙሐመድ አስታወቁ።

አምባሳደሩ ከኢትዮ ኳታር ፓርላማ ዲፕሎማሲ ወዳጅነት ቡድን ጋር በሳይንስ ሙዚየም በመገኘት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተዘጋጀውን አውደ ርዕይ ትናንት ሲጎበኙ እንደተናገሩት፤ ኳታርና ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው፡፡ ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ የምትቀጥል ይሆናል።

በኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የተዘጋጀው የሳይንስ ኤግዚቢሽን ኢትዮጵያ ከውሃ ሀብት ጋር በተያያዘ የደረሰችበትን ቴክኖሎጂ ለመረዳት አስችሎናል ያሉት አምባሳደሩ፤ በሀገሪቱ ያለውን የኤሌክትሪክና ውሃ አቅርቦት እንዲሁም የውሃ ሀብት አጠቃቀም ተገንዝበናል ሲሉ ገልጸዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት እያደረገችው ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው። የዚህ ዓይነት የተግባር እውቀት የሚሰጥ አውደ ርዕይ ትውልድ በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ሊቀጥል የሚገባው ነው። በቀጣይም ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር በውሃ ሀብት አጠቃቀም፤ በኢነርጂ ዘርፍ እንዲሁም በኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዘርፎች አብራ የምትሠራ ይሆናል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አቶ አበራ እንደሻው በበኩላቸው፤ የአምባሳደሩ ጉብኝት ሀገሪቱ በውሃ ሀብትና ኢነርጂ አጠቃቀም ረገድ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለማስተካከል እንደሚረዳ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ በተለይም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ እየሠራችው ያለው ሥራ ማንም የሚጎዳ አይደለም። ነገር ግን ጉዳዩ ለሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ችግር እንደሆነ ተደርጎ በብዙኃን መገናኛ ጨምር የሚነገሩ ወሬዎች አሉ። እነዚህ የተሳሳቱ ትርክቶች መሆናቸውን በጉብኝቱ ወቅት ለአምባሳደሩ ማስገንዘብ ተችሏል ሲሉ አብራርተዋል።

መጪው ትውልድ ከራሱ ለራሱ የሚበቃ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይልና የውሃ አቅርቦት እንዲኖረው ለማስቻል የተጀመሩት ሥራዎች በተግባርም በዲፕሎማሲውም ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን፤ በተጨማሪ ለዓባይ ወንዝ ኢትዮጵያ 77 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ እንደምታዋጣና ይህም 86 በመቶውን የሚይዝ መሆኑን እንዲገነዘቡ ተደርጓል።

አምባሳደሩም የተደረገላቸውን ገለጻ በመቀበል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ በትብብር በሚሠራባቸው ጉዳዮች ላይ ለመምክር ውይይቶች ለማድረግ በኳታር እንዲገኙ ጥያቄ ማቅረባቸውንም አቶ አበራ ጠቁመዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን  መስከረም 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You