ኢትዮጵያን በቦክስ ያስጠራው በቀለ አለሙ(ጋንች)

 ብዙዎች «ጋንች» በሚለው ቅፅል ስሙ ያውቁታል። በተለይ የመርካቶ፣ የአውቶቡስ ተራ፣ የአባኮራን ሰፈር ልጆች በዚህ መጠሪያው ነው የሚለዩት። የ82 ዓመት አዛውንቱን በቀለ አለሙን። ቁመተ ለግላጋውን በአካል ለተመለከተው በ60ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ እንጂ እንዲህ ሰማኒያዎችን የዘለለ አይመስልም።በተለይ ለእንደ እነርሱ አይነት ሰው የማይመክረውን ከበድ ያለ ጭነትን አንስቶ ሲሸከምማ እድሜውን ዋሽቷል የማይል አይኖርም።የዕድሜ ባለጸጋነቱንም መጠራጠሩ የግድ ነው።።

በዙሪያው ያሉ ወጣቶች «ጋሼ» እያሉ ይጠሩታል። ማኅበራዊ ተግባቦቱ ደግሞ ላቅ ያለ ስለሆነ ብዙዎቹ ጋንቺዬ ነው የሚሉት።እናም እኛም አንተ ለማለት የደፈርነው ከዚህ አኳያ ነው።ጋንችን ባለውለታ ነው የሚያሰኘው በርካታ ተሞክሮዎች አሉት።አንዱ በሥራ ወዳድነቱና ጥንካሬው ለብዙ ወጣቶች አርአያ መሆኑ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ በዓለም አደባባይ ሀገሩን በአትሌቲክሱ የአስተዋወቀ የመጀመሪያው የቦክስ ተወዳዳሪ መሆኑ ነው።

ጋንች ስያሜውን ሳይቀር ያገኘው ከጠንካራው የቤት መዝጊያ ቁልፍ ነው።በመርካቶዎች ትልቁ የብረት ቁልፍ ጋንች ይባላልና ለእርሱም ስሙን ሰተውታል። ይህ ቁልፍ በቀላሉ የማይሰበር፣ የማይፈለቀቅና ንብረትን ለሌባ አሳልፎ የማይሰጥ ሲሆን፤ እርሱም በቦክስ ፍልሚያ በተወዳደረባቸው ቦታዎች ሁሉ ማሸነፍ እንጂ እጅ የማይሰጥ ነበር።ጋንች ሌላም ትርጓሜም አለው። በልብስ ላይ የሚተከል ጠንካራ ቁልፍም ነው። ቶሎ ተበጥሶ አይወድቅም። ጋንች መኪናን ለመጎተት የሚረዳ የብረት ገመድም ይሆናል። እርሱም ጠንካራ በመሆኑ ከዚህ ጋር ሲያመሳስሉት ስሙን ሰጥተውታል።

ጋንች የትልቅ ጋን ማስቀመጫም የሚል ትርጓሜ አለው። እናም በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ የመከላከል ተግባሩን ስለሚያከናውኑና ጎል ሳይገባ እንዲያሸንፉ በማድረጋቸው የክለቡ አለኝታ ለማለትም ቅጽል ስሙ እንደወጣለትም በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበረው ቆይታ አጫውቶናል።እንደውም በወጉ መካከልም ቀረብ ብሎ ስለ ጥንካሬው ላነሳበት አንድ የሚለው ነገር አለ።«ልብ ያለው ዛሬም ቢሆን መጥቶ ይግጠመኝ»።

ቦክሰኛው በቀለ አለሙ ( ጋንች) በ1933ዓ.ም በጉራጌ ክስታኔ ውስጥ ከሚገኙ 21 ቀበሌዎች ውስጥ አንዱ በሆነችው የከዝን ቀበሌ የተወለደ ሲሆን፤ አባቱን ገና ልጅ እያለ በሞት አጥቷል።እናቱ ደግሞ ሌላ ትዳር በመመስረታቸው ከቤተሰቡ ጋር መስማማት አልቻለም። ስለዚህም መኖሪያውን ከእናታቸው ወንድ አያት ጋር አደረገ። ይህም እድል ፊቱን አዞረበት።አያቱ ሞቱ። ስለዚህም ሌላ አማራጭ ግድ ነውና ከአያቱ ጋር የአያቱ ልጅ አቶ በዳሶ ጋር ለመኖር አዲስ አበባ መጣ።በአዲስ አበባ አባ ኮራ ሰፈርም ሁለተኛ የእድገት ቦታውን አደረገ።

ጋንች በእራስ እምሩ ግቢ ውስጥ ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋችም ነበር። ከጥንካሬው የተነሳም ብዙ ጊዜ የተከላካይ መስመር ተሰላፊ ነው። የቦክስ ስፖርትም ቢሆን ገና በ16 ዓመቱ ነበር የጀመረው።እነዚህን ሁለት ስፖርቶች ደግሞ ህልሙ ላይ አድርሰውታል።በቀለ የቀለም ትምህርትን መማር የጀመረው በራሱ ጥረት ነው።ቀን እየሰራ በማታው ክፍለ ጊዜ የአስኳላ ትምህርቱን ተከታትሏል።በዚህም በቀድሞ ወሰንሰገድ በአሁኑ የካቲት 23 የመጀመሪያው ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምሯል።ነገር ግን ራሱን ከዚህ በላይ ማስተማር አልቻለም።ከዚያ ይልቅ ልጅነት ህልሙ ላይ መትጋቱን ተያያዘው።

ጋንች የተለያዩ ሥራዎችን ሰርቷል።ጨው ነግዷል፤ የፒያሳው ኅብረት ማኅበር ውስጥ ገብቶም የልብስ ዘምዛሚ ነበረ። ልብስ ሰፊም ሆኖ ያውቃል።ከ1968 ዓ.ም በኋላ የቦክስ ውድድሩን ሲያቆም ደግሞ የመጨረሻውንና እስከለተሞቱ ድረስ ለ50 ዓመታት አሽከርካሪ ነበርⵆ የታክሲ አገልግሎት በመስጠት ሥራውን አሀዱ ያለ ሲሆን፤ ቅጥረኝነቱ ሲሰለቸው ደግሞ የራሱን መኪና ገዝቶ የጭነት አገልግሎት መስጠት ጀመረ።ይህ ደግሞ ለእርሱም ሆነ ለቤተሰቦቹ የገንዘብ አቅም ፈጥሮ እንደነበረ አይረሳውም።ስለዚህም በአቶ በቀለ ያልተነዱ የመኪና አይነቶች ጥቂት ናቸው የሚሉት ወዳጆቹ ለምሳሌ እነ ቼንቶትሬ፣ ፎር ኦ ፎር የመሳሰሉት መኪኖች በእጁ ገብተው የተሽከረከሩ ነበሩ።

ባለውለታነት እንዴት

ኢትዮጵያን በታላቁ የኦሎምፒክ መድረክ ስሟ እንዲጠራ ያደረጉ ብዙ እንቁ ስፖርተኞች እና አትሌቶች ተፈጥረዋል።ከእነዚህ የሀገር ባለውለታዎች መካከል ደግሞ በቦክሱ ዘርፍ ኢትዮጵያን በኦሎምፒክ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የወከለው በቀለ አለሙ (ጋንች) ነው።በቀለ ከ59 ዓመታት በፊት በቶክዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈ ሲሆን፤ ኋላም ተከትለውት ለመጡ የቦክስ ዓለም ሰዎች አርአያና መምህር ሆኗል።ምክንያቱም እርሱ ከቶኪዮ በኋላ በነበሩት የኦሎምፒኮ መድረኮች እና የአፍሪካ ሻምፒዮን ላይ ሀገሩን ወክሎ መሳተፍ የቻለ ፈር ቀዳጅ ስፖርተኛ ስለነበር።።

ጋንች የቦክስ ዓለምን እንዲቀላቀል የሆነው ፊልም አይቶ ሲሆን፤ የአሜሪካው የቦክስ ውድድር የቦክሱን ስልጠና እንዲወስድ አስችሎታል።አቶ እስጢፋኖስ የሚባሉ ኤርትራዊ አሰልጣኝ ደጃች ውቤ ቅጥር ግቢ ውስጥ «አዲስ አበባ ወጣቶች» በሚል ክለብ አደራጅተው የተለያዩ ስፖርታዊ ስልጠናዎችን ይሰጡ ነበርና ከፊልሙ በኋላ በቀጥታ ጊዜ ሳያጠፉ ሄዶ ተመዘገበ። ልብስ ስፌቱን ጎን ለጎን በመስራትም ጉጉቱን ወደ ማርካቱ ገባ።ይሁን እንጂ ሌሎች ልጆችን ያሰለጥን ነበርና ቦክስ ማሰልጠን አትችልም ተብሎ ታገደ።በዚህም ሥራው ተቋረጠ።

ሕልሙን ዝም ብሎ የማይተወው በቀለም ሌላ አማራጭ ፈለገ።እድል ቀናውናም በታዋቂው ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ አማካኝነት በተቋቋመው ‹‹ዘርአይ ድረስ›› ክለብ ውስጥ ገባ። አጋጣሚውም የውድድር ዕድል ከፈተለት።በ1959 ዓ.ም የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብን ወክሎም ተወዳደረ።

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ሕጋዊ ሰውነት ሲሰጠው ደግሞ በሀገር ደረጃ ተመርጦ በዓለም መድረክ እንዲወዳደር እድሉን አገኘ።ለመጀመሪያ ጊዜ በሪንግ ውስጥ የገጠመው ቦክሰኛ ሰለሞን ዓለም የተባለ ሲሆን፤ ሰውነቱ ጠንካራና ግዙፍ ነበር። በጊዜው ደረቱ ላይ ድንጋይ ቢፈልጡበት የማይሰማ ቦክሰኛ እየተባለ ይሞካሻል።ሆኖም ዕድልና ትጋት ወደ ጋንች አምርታ ድል የእርሱ ሆነች።ይህ ደግሞ ሀገር ወክሎ እንዲወዳደር መንገድ ከፈተለት።በጊዜው ኢትዮጵያን ለመወከል ከሸዋ፣ ከፋና አስመራ የመሳሰሉት ክፍለ ሀገራት ላይ በመወዳደር በነጥብ ማሸነፍ የግድ ይላል። የጋንች ዕጣ ፈንታም ከዚህ የተለየ አልነበረም። እናም ሁሉንም በዝረራ አሸንፎ ተመረጠ።

በሚሊተሪና በግል ከሚሰለጥኑ ቦክሰኞች ጋር ለውድድር ቀርቦ አንድም ቀን ተረቶ አያውቅም።በ1952 ዓ.ም ጋንች በቦክሱ ዘርፍ በሮም ኦሎምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን ወክሎ ለመሳተፍ ወደ ጣሊያን ሮም ለማምራት ዝግጅት እያደረገ ባለበት ወቅት ግን በበጀት እጥረት ምክንያት የቦክሰ ቡድኑ መቀነሱን ተከትሎ በውድድሩ ላይ የመካፈል እድሉን ሳያገኝ ቀረ።ይሁን እንጂ ነገም ሌላ ቀን እንደሆነ ያምናልና በሮም ኦሎምፒክ ያጣውን የመሳተፍ እድል ለማግኘት የተሻለ ሥራ መስራቱን ቀጠለ።በግል በመሰልጠን የሸዋ ጠቅላይ ግዛትን ወክሎ ተመረጠ።ከአራት ዓመት ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያን ወክሎ ወደ ጃፓን ቶኪዮ ኦሎምፒክ ተጓዘ። በዚህም በተሻለ ስልጠና እና ዝግጅት በኦሎምፒክ ውድድሩ ስኬታማ ሊባል የሚችል ተሳትፎን ማድረግ ቻለ።በውድድር ተሳትፎውም የመጀመሪያ ዙር ላይ ብቃቱን አሳየ።።

በሁለተኛው ዙር ደጋፊዎቹ ነጮች በመሆናቸው ፊላንዳዊውን ለማንቃት ብለው እየጮሁ ተፅዕኖ ፈጠሩበትና ተሸነፈ።ሆኖም ነጭና ጥቁር ሲፈታተሽ የታየበት ጨዋታ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አድናቆታቸውን ቸረውት ነበር። ይህ ደግሞ በትልቁ የዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ያረገበት ነው።በቦክሱ ዘርፍ ሀገሩን ወክሎ በመሳተፍም ፈር ቀዳጅ እና ለብዙ ስፖርተኞች አርአያም የሆነበት ጊዜ ነበር።

ቀጣዩ ጉዞው ወደ ሜክሲኮ የሚወስደው ሲሆን፤ ተስፋ የቆረጠበት ቦታ ነበር።ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የዘር መድሎ፤ በተለያየ ውዝግብ ውስጥ አልፎ ኦሎምፒክ ላይ ተሳታፊ በመሆኑ ከሜክሲኮ መንግሥት ሜዳሊያዎችን የተቀበለበት ነው።በዚህ ተሳትፎውም ዳግመኛ ሀገሩን ከፍ አድርጓል።

በሁለቱ ትልልቅ የኦሎምፒክ መድረኮች ላይ አሰልጣኝና የተሟላ ትጥቅ ሳይኖረው ሀገሩን ወክሎ መሳተፍ የቻለው ጋንች፤ በናይጄሪያ ሌጎስ በተካሄደው የአፍሪካ የቦክስ ሻምፒዮን ላይ አሸናፊ በመሆን ሀገሩን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ማስጠራት የቻለ ስፖርተኛ ነው። ቦክሰኛ በቀለ አለሙ በ2004 ዓ.ም የህይወት ታሪኩን የሚዳሰስ “ያልተነገረለት የሀገር ባለውለታ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ መጽሐፍ ታትሞለታል።

ቦክሰኛ በቀለ በተለይም በወቅቱ በቦክሱ ስማቸው ጎልቶ ይጠራ ከነበሩት ቦክሰኛ ማሞ በየነ፣ ቦክሰኛ አሰፋ ጎሬላ እና ቦክሰኛ ጉዲሳ ሆራ ጋር የሚያደርጋቸው የተለያዩ የቦክስ ውድድሮች ስሙን ይበልጥ ታዋቂ ያደረጉለት ናቸው።እርሱ ከውጭ ሀገር የውድድር ተሳትፎ አልፎም በሀገር ውስጥ በርካታ ውድድሮችን አድርጓል።

የተሻለ ብቃት ያሳየባቸውም በርካታ ውድድሮች አሉ።ከእነዚህ መካከል ግን አንዱ በሁሉም ልብ ውስጥ የማይጠፋው በሲኒማ አዲስ ከተማ የገጠመው ካሜሮናዊ ጉዳይ ነው።ሰውዬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ቶማስ ፍራንሲስ ሲሆን፤ በአገረ ካሜሮን ለአራት ዓመታት የከባድ ሚዛን ሻምፒዮና ቦክሰኛ ነበር። ግን «ከአቶ በቀለ ጋር መግጠም እፈልጋለሁ» ባለው መሠረት በ1956 ዓ.ም በጋንች ጠንካራ ቡጢዎች ተመትቶ ወድቋል።በወቅቱ «አዲስ ድምጽ» የተሰኘው ጋዜጣ ባሳተመው ጽሑፉ «በቀለ የካሜሮኑን ቡጢኛ በቃኝ አስባለው» በሚል ርዕስ እንደጻፈም የታሪክ መጽሐፉ ያስረዳል።

ጋንች የድሮው ማዘጋጃ ቤት፣ ሞስኮብ ሲኒማ፣ ሀገር ፍቅር ቴአትር፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ ፣አደዋ ሲኒማ፣ ራስ ቴአትር፣ ሲኒማ አዲስ ከተማ፣ አምባሳደር ቴአትር፣ ብሔራዊ ቴአትር የመሳሰሉት በዋናነት በሀገር ውስጥ ውድድር ይደርግባቸው የነበሩ ቦታዎች ናቸው።በእነዚህ ቦታዎች በሚዘጋጁ የቦክስ ውድድሮች ላይ በሚሳተፍበት ወቅት ብዙ ደጋፊዎች እንደነበሩት የሚነገር ሲሆን፤ በየሳምንቱ በየሲኒማ ቤቱ በቦክስ አፍቃሪዎች ታጅበው ውድድሮች ሲካሄዱ የበቀለን (ጋንች) ኃይለኝነት ማንም አይረሳውም።በተለይም ግራ ቡጢ ለመመልከት የሚያስችለውን ጥበብ ሲጠቀም ሲኒማ ቤቶች በድጋፍ ይናወጡ ነበር።እርሱ አለ ከተባለም እንዲሁ ሰው በሲኒማ ቤቱ ውስጥ ለመገኘት ይጨናነቅ ነበር።ይህ ደግሞ የሲኒማ ቤቶችን ገቢ ከፍ በማድረግ ሀገር ተጠቃሚ እንድትሆን ያስቻለበት ነው።

በቦክስ ዓለም ከ1949 እስከ 1953 ዓ.ም «በአዲስ አበባ ወጣቶች» ክለብ ሲሰለጥንና ሲወዳደር የቆየው ባለታሪኩ፤ ከክለቡ ምንም ዓይነት ክፍያ አያገኝም ነበር። ለእርሱ ክፍያው እውቅናና ክህሎት ብቻ ነው። ይህ ግን አንድም ቀን ቆጭቶት አያውቅም።ምክንያቱም ሀገሩን ከፍ አድርጎበታል።በዚህም እስከለተሞቱ ድረስ ለሀገሩ በአበረከተው ነገር ደስተኛ ነው።የ11 ልጆች አባት የነበረው ቦክሰኛ በቀለ አለሙ ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በ82 ዓመቱ ነሐሴ 22 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም የተለየ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ሸጎሌ በሚገኘው ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን የቀብር ሥነ- ሥርዓቱ ተፈፅሟል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም

ጽጌረዳ ጫንያለው

Recommended For You