የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ሳይንስ እና ጥበብ

እንቁጣጣሽ፤ ባህል ነው፣ ሃይማኖት ነው፣ ጥበብ ነው፣ ሳይንስ ነው ስንል የልጃ ገረዶችን ጨዋታ ጨምሮ ብዙ ባህላዊ ክዋኔዎቹ ማሳያ ይሆኑናል። ሃይማኖት ነው ስንል በተለይም በኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ ሃይማኖታዊ አከባበር ስላለው ነው። ጥበብ ነው ስንል ከግጥምና ዜማ ጀምሮ ብዙ ጥበባዊ ትውፊቶች ስላሉት ነው። ሳይንስ ነው ስንል የዘመን አቆጣጠራችን መነሻ ስለሆነና ሳይንሳዊ ቀመሮች ስላሉት ነው። ከፊዚክስና ሒሳብ ያልተናነሱ ቀመሮችንም በዚሁ ጽሑፍ እናያለን።

እንቁጣጣሽ ከሌሎች በዓላት ሁሉ ይለያል። ሌሎች በዓላት ሃይማኖታዊ ወይም ባህላዊ ይዘታቸው ይጎላል። ለምሳሌ መስቀል፣ ገና፣ ፋሲካ ብንል ሃይማኖታዊ ይዘታቸው ይበልጣል። ጥምቀት፣ አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ እና ሶለል ብንል መነሻቸው ሃይማኖታዊ ይሁን እንጂ ባህላዊ ይዘታቸው ጎልቶ ይታያል። በሌላ በኩል እንቁጣጣሽ የእነዚህ ሁሉ በዓላት ማስጀመሪያ ነው። ለምሳሌ የ2016 ዓ.ም መስቀል፣ የ2016 ዓ.ም ገና፣ ጥምቀት፣ አረፋ፣ መውሊድ፣ ፋሲካ፣ አሸንዳ… እያልን የምንጠራው እንቁጣጣሽ በቀየረው ዓመት ነው። እንቁጣጣሽ ብዙ ጥበብና ሳይንስ የያዘ በዓል ነው። ይህ ሳይንሳዊ ባህሪው ሃይማኖት ዘለል በዓል ያደርገዋል።

በብዙ ነገሮቻችን ሁሉ ‹‹የራሳችን የዘመን አቆጣጠር ያለን›› እያልን እንጠራለን። ኢትዮጵያ ልዩ የሚያደርጋትም ይሄው ነው። ‹‹የ13 ወር ፀጋ›› በሚል ትታወቃለች። ይሄ ደግሞ ከዓለም ለየት ያደርጋታል። ይሄ ሁሉ የሆነው በእንቁጣጣሽ ጥበብ እና ሳይንስ ነው። እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ ምን ያህል የመጠቁ ሊቃውንት እንደነበሯት ያሳያል። የእንቁጣጣሽ ጥበባዊና ሳይንሳዊ ቀመር ምስክራችን ነው። ብዙዎቻችን ልብ የማንላቸው (አንዳንዴም ሃይማኖታዊ እየመሰለን) ሳይንሳዊ ቀመሮች አሉት። እንቁጣጣሽን በተመለከተ የተለያዩ መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና ሰነዶች የተለያዩ መረጃዎችን አስፍረዋል።

ለምሳሌ የሥነ ጽሑፍና የሥነ ከዋክብት ተመራማሪው መምህር አብነት ስሜ በ2008 ዓ.ም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የሚከተለውን ማብራሪያ ጽፈዋል።

‹‹የሀገራችን የባሕረ ሐሳብ ሊቃውንት የሚጠቀሙበት የጊዜ ስሌት እንደሚከተለው ነው።

1 ዕለት = 60 ኬክሮስ

1 ኬክሮስ = 60 ካልዒት

1 ካልዒት = 60 ሣልሲት

1 ሣልሲት = 60 ራብዒት

1 ራብዒት = 60 ኀምሲት

1 ኀምሲት = 60 ሳድሲት

በዚህ መሠረት አንድ ዓመት 365 ዕለት እና 15 ኬክሮስ ይባላል። 15 ኬክሮስ ሩብ ዕለት ወይም 6 ሰዓት ነው። በሌላ አገላለፅ 1 ኬክሮስ 24 ሰዓት ስለሆነ 15 ኬክሮስ 360 ደቂቃ ነው። 360 ደቂቃ ደግሞ 6 ሰዓት ነው።

365 ዕለት፣ 5 ሰዓት፣ 48 ደቂቃ እና 46 ሰከንድ የተባለው አንድ ዓመት በባሕረ ሐሳብ የጊዜ ክፍፍል 365 ዕለት፣ 14 ኬክሮስ፣ 30 ካልዒት፣ 11 ሣልሲት እና 30 ራብዒት ይሆናል። የ11 ደቂቃ እና 14 ሰከንድ ጉድለት የተባለው በባሕረ ሐሳብ ቅመራ መሠረት ጉድለቱ 29 ካልዒት፣ 48 ሣልሲት እና 30 ራብዒት ነው የሚሆነው። 5 ሰዓት፣ 48 ደቂቃ እና 46 ሰከንድ ሲጠጋጋ 6 ሰዓት እንደሚሆነው ሁሉ 14 ኬክሮስ፣ 30 ካልዒት፣ 11 ሣልሲት እና 30 ራብዒት ወደ 15 ኬክሮስ ይጠጋጋል።

የዓመቱ ዕለት እና ዝርዝሩ ከላይ እንደተቀመጠው ነው፤ ለልዩ ንጽጽር የተፈለገ ለየት ያለ ቀመር ግን ይታያል። ይኸ ቀመር አንድን ዓመት 365 ዕለት፣ 15 ኬክሮስ እና 6 ካልዒት ያደርገዋል።

በዚህ አካሔድ 15 ኬክሮስ ራሱ ተጠጋግቶ የተገኘ ሆኖ ሳለ እንደገና 6 ካልዒት ተጨምሯል። 6 ካልዒት 2 ደቂቃ እና 24 ሰከንድ ነው። ይህ በየዓመቱ በትርፍ የሚገኘው 6 ካልዒት በ600 ዓመት ውስጥ ተጠራቅሞ አንድ ዕለት ይሆናል። 6 x 600= 3600 ካልዒት= 60 ኬክሮስ= አንድ ዕለት። 2 ደቂቃ እና 24 ሰከንድም በ600 ሲበዛ 24 ሰዓት ወይም አንድ ዕለት ይሰጠናል። እንግዲህ በየዓመቱ በተጠጋጋ ተረፍ የሆነው 6 ሰዓት በ4 ዓመት ተጠራቅሞ 24 ሰዓት ወይም አንድ ዕለት አስግቶኝ ጳጉሜን በ4 ዓመት አንዴ 6 እንደሚያደርጋት ሁሉ የ6 ካልዒት ትርፍ በእርግጥ ካለ (የአለ ግን አይመስለኝም) በ600 ዓመት አንዴ ጳጉሜን 7 ትሆናለች››

ቀመራዊ አሰራሩ እንዲህ በቀላሉ የሚገባን አይመስለኝም። ከዚህ የምንረዳው አባቶች ምን ያህል ሊቅ እንደነበሩ ነው። እነዚህን ሽርፍራፊ ቁጥሮች ደማምረው ነው ጳጉሜን የፈጠሯት። ጳጉሜንም አምስት፣ ስድስት እና ሰባት ያደረጓት። የኢትዮጵያ ሊቃውንት ከፈረንጅ ምንም ነገር ሳይኮርጁ እንደሰሩት ማረጋገጫ ይሆናል።

በእንቁጣጣሽ በሚቀየረው ዘመን ዓመቱ የራሱ የሆነ መጠሪያ አለው። ዝርዝር ቀመራዊ አሰራር ቢኖረውም በአጭሩ እንግለጸው። ይሄውም ዓመታቱ ዘመነ ማቴዎስ፣ ዘመነ ማርቆስ፣ ዘመነ ሉቃስ እና ዘመነ ዮሐንስ እየተባሉ እንደሚጠሩ ነው። ዘመኑን ለማወቅ ዓመተ ኩነኔ (5500) እና ዓመተ ምሕረት (አሁን ያለንበትን ዓመት ማለት ነው) በመደመር የሚገኘውን ውጤት ለአራት እናካፍላለን። በዚህ ስሌት መሠረት ቀሪው አንድ ከሆነ ዘመኑ ማቴዎስ ይባላል። ቀሪው ሁለት ከሆነ ዘመነ ማርቆስ፣ ሦስት ከሆነ ዘመነ ሉቃስ እና ያለ ቀሪ ከተካፈለ ደግሞ ዘመነ ዮሐንስ ይባላል ማለት ነው። በዚህ ስሌት መሠረት ዛሬ የተቀበልነው አዲሱ ዓመት 2016 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስ ነው። ምክንያቱም 5500+ 2016 = 7516 ነው። 7516 ለአራት ሲካፈል ቀሪ የለውም።

እንቁጣጣሽ እንዲህ አይነት ሳይንሳዊ ቀመር ቢኖረውም ሃይማኖታዊ ይዘትም አለው። ለአራት የተካፈለበት ምክንያትም በአራቱ ወንጌላውያን (ማቲዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ እና ዮሐንስ) ነው። ጥቅል መጠሪያው (በብዙዎች የሚጠራው) እንቁጣጣሽ በሚለው ቢሆንም ሌሎች መጠሪያዎችም አሉት። እነዚህ መጠሪያዎች ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ናቸው። እንቁጣጣሽ ከሚለው ጀምረን እንያቸው።

ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ የጠቢቡ ሰሎሞንን ዝና ሰምታ ኢየሩሳሌም ተጉዛ ስትመለስ ‹‹እንቁ ለጣትሽ›› በማለት ከእንቁ የተሠራ የጣት ቀለበት ንጉሥ ሰሎሞን እጅ መንሻ እንዲሆናት አበረከተላት። ይህን ታሪክ መነሻ አድርገው ‹‹እንቁጣጣሽ›› የሚለው ስያሜ ከዚያ እንደመጣ የታሪክ ድርሳናት ያስረዱናል፤ አንዳንዶችም አፈ ታሪክ ይሉታል።

በኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ዕለት ምድሪቱ በክረምቱ ዝናብ ውሃ እና ጭቃ ሆና የቆየችው ጭቃና ጎርፉ ተወግዶ በአረንጓዴ እጽዋት ተውባ ሜዳው፣ ሸለቆውና ተራራው በአደይ አበባ ተንቆጥቁጠው የሚታዩበት ወቅት በመሆኑ ዕለቱ ‹‹እንቁጣጣሽ›› እንደተባለም ይነገራል።

ሌላኛው መጠሪያው ‹‹ዘመን መለወጫ›› የሚለው ነው። ይሄ ደግሞ ሳይንሳዊ ምክንያትን የሚከተል ይመስላል። ዘመን መለወጫ መስከረም ወር የሆነበት ምክንያት ብርሃንና ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው የሚሉም አሉ። ሌሊቱ ከቀኑ ጋር ይስተካከላል። የዓመቱ ቀናት 364 እና 365 (የጳጉሜን 5 እና 6 መሆን ተከትሎ) እየተባሉ የሚጠሩትም በዚህ አቆጣጠር ነው። በሃይማኖታዊ ምክንያት ደግሞ በኖህ ዘመን ተጥለቅልቆ የነበረው የጥፋት ውሃ የጎደለበት ወር ስለሆነ መስከረም የዘመን መለወጫ እንደተደረገ የሃይማኖት አባቶች ይናገራሉ።

ቅዱስ ዮሐንስ የሚል መጠሪያም አለው። ይሄኛው መጠሪያ ሙሉ በሙሉ ሃይማኖታዊ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ የተባለውም የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል መነሻ በመሆኑ ነው።

በዚህም ምክንያት በድርሳነ ዮሐንስ (ከገጽ 1 እስከ 3) እንደተገለጸው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር አባቶች ወስነዋል። መጽሐፈ ስንክሳር ‹‹የመስከረም ወር የተባረከ ነው። እርሱም የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው። የዚህ ወር ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12 ሰዓት ነው። ከዚህ በኋላ ቀኑ እየጎደለ ይሄዳል›› ይላል።

ስለእንቁጣጣሽ ስሞችና ቀመሮች ይህን ካልን የዘመን አቆጣጠራችን ከሌሎች የዓለም ሀገራት ለምን እንደተለየ ደግሞ ሊቃውንት የሚነግሩንን እንመልከት። ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ‹‹ባሕረ ሐሳብ›› በሚል መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከምዕራባውያን የተለየበትን ምክንያት ሲገልጹ ‹‹ሮማውያን የሮም ከተማ የተቆረቆረችበትን ዘመን መነሻ አድርገው ይጠቀማሉ፤ ታላቁ እስክንድርም የገነነበት ዘመን መቁጠሪያቸው ሆኖ ነበር›› ይላሉ። የኢትዮጵያ ካህናትም ዘመነ እስክንድር በሚል ይጠቀሙበት እንደነበር መጻሕፍት ይመሰክራሉ።

ሶርያውያን የዘመን አቆጣጠራቸውን የሚለኩት በፀሐይ ቆጥረው የዓመቱን 365 ቀን ለስድስት አካፍለው ከሮማውያን በተዋሱት ጊዜ የዓመቱን መጀመሪያ አዲስ ዓመት ይሉታል። በኋላ የሰማዕታት መታሰቢያ እንዲሆን በ460 ዓመተ ዓለም ወደ መስከረም 1 ቀን ለወጡት። የሀገራችን ሊቃውንትም አዲስ ዓመታችን መስከረም አንድ ቀን እንዲሆን የወሰኑት ይኽንን በመከተል ነው። የዓመቱን መጀመሪያ በመስከረም ማድረግን ከሶርያውያንም ሆነ ከግብጾች ብናገኘውም ጀማሪው በ46 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ይገዛ የነበረው ዩልዮስ ቄሣር ስለነበር የዩልዮስ ባሕረ ሐሳብ ይባላል።

ዩልዮስ ቄሣር በ46 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ባወጣው የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት መሠረት የዓመቱን 365 ቀናት ለስድስት ሰዓት አድርጎ ለአራቱ ወራት 30/30 ቀን ለአንዱ 28 ቀን በአራት ዓመት አንዴ 29 ቀናት፤ ለቀሩት ሰባት ወራት 31/31 ቀናት መድቦላቸው በ12 ቦታ ከፍሎታል። ለዚህም ነው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሁሉም ወሮች 30 ቀናት ያልሆኑት። በኢትዮጵያ አቆጣጠር ግን አሥራ ሁለቱም ወራት 30 ቀናት ይሆኑና ጳጉሜ የተለየች ትሆናለች።

አውሮፓውያኑ የሚጠቀሙበት ይህን አቆጣጠር መነሻ አድርገው ነው። የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያን እንዴት እንደተለየ አሥራት ገብረማርያም ‹‹የዘመን አቆጣጠር›› በሚለው መጽሐፋቸው ሲገልጹ ‹‹ዲዮናስዮስ የተባለው የሮም መነኩሴ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተወለደበት ዘመን በስሌት ለመድረስ የተከተለው መንገድ የታሪክ ክስተትን ነበር።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት ዘመን ለመሰወን የታሪክ ክስተትን አልተከተለችም። ቤተ ክርስቲያናችን የተከተለችው ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን 5500 ዘመንን ነው›› በማለት የልዩነቱን ምክንያት ይገልጻሉ።

የዘመን አቆጣጠር ልዩነት መነሻው የዚህ ክስተት መሆኑን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲያረጋግጡ ‹‹ኢትዮጵያ ዘመነ ብሉይን እንዲህ አስከትላ 5500 ብላ ስትቆጥር ዘመነ ሐዲስ ልዩ ሆኖ ከማንም ቁጥር አይገጥምም። ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ከምስራቆቹም ከምዕራቦቹም ሁልጊዜ በሰባት ዓመት ታጎድላለች። ምክንያቱም ባለታሪኮችን ትታ ወንጌል ተርጓሚዎችን መነሻዋ ስላደረገች ነው›› ይላሉ። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ እና የአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ልዩነት ሊኖረው ቻለ። ይሄ የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን ጨምሮ የዓለምን መፈጠር ምክንያት አድርጎ የተቀመረ ወጥ አቆጣጠር እንጂ ነገሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የሚቀያየር አይደለም።

ስለኢትዮጵያን የቀን አቆጣጠር ካወራን ስለጳጉሜን ማንሳት የግድ ነው። ከዘመን አቆጣጠር ስሌቷ በተጨማሪ ኢትዮጵያን ልዩ የምታደርጋት ይቺ የጳጉሜን ወር ነች። ይቺ ወር አምስት ወይንም ስድስት ቀን ናት። በአራት ዓመት አንዴ ስድስት ትሆናለች። በ600 ዓመት አንዴ ደግሞ ሰባት እንደምትሆን ሊቃውንት ይናገራሉ። ይቺ አሥር ቀን እንኳን ያልሞላች ‹‹ወር›› እየተባለች ትጠራለች። የቤት ኪራይ አይከፈልባትም፣ የወር ደመወዝ አይገኝባትም።

ጳጉሜን በገጠር አካባቢ ‹‹ቋግሜ›› እያሉ ይጠሯታል። በጽሑፍ ደግሞ ብዙ ቦታ ላይ ጳጉሜ ቢሆንም ‹‹ጳጉሜን›› እየተባለም ይጻፋል። ያም ሆነ ይህ ቃሉ አማርኛ ወይም ሌላ የሀገር ውስጥ ቋንቋ ሳይሆን የግሪክ ቃል ነው። ትርጉሙም፤ ቀሪ ዕለታት፣ ቅጥያ፣ ተጨማሪ…ማለት እንደሆነ ይነገራል።

የጳጉሜን ወር ብዙ ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክዋኔዎች ይከወኑባታል። የጳጉሜን ውሃ ከሌሎች ወራት በተለየ ቅዱስ ነው ተብሎም ይታሰባል። በዚህም ምክንያት በተለይም በገጠር አካባቢ ሰዎች በማለዳ በመነሳት ሰውነታቸውን ይታጠባሉ። ጳጉሜን ሦስት ደግሞ ‹‹ሩፋኤል›› ይባላል። በዚህ ዕለት ዝናብ ከጣለ ዓመቱ የሰላምና የበረከት ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡

ይህን ሁሉ ጥበብ የቀመሩልን እንግዲህ ሊቃውንት አባቶቻችን ናቸው። ሃይማኖታዊም ይሁን ሳይንሳዊ፣ ባህላዊም ይሁን ዘመናዊ ይህን የመቀመር ጥበባቸው የሥልጣኔ ጀማሪዎች እንደነበርን ማሳያ ነው።

የየትኛውንም ዓለም የዘመን አቆጣጠር ብንመለከት አንድን ክስተት መነሻ አድርጎ የተቀመረ ነው። ለዚያም ብዙ የዓለም ሀገሮች የሚጠቀሙት አንዲት ሀገር በቀመረችው ቀመር ነው። ኢትዮጵያ ግን ራሷ ቀምራ በራሷ የዘመን አቆጣጠር ትጠቀማለች። ‹‹የራሳችን የዘመን አቆጣጠር ያለን›› የሚባለው ለዚህ ነው።

መልካም አዲስ ዓመት!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You