የሰው ልጅ በባህሪዩ ማህበራዊ ፍጡር ስለሆነ ከአብሮነት ውጭ ብቻውን መኖር አይችልም በማለት ይገልጹታል። ይህ የሰው ልጅ ማህበራዊነት ዓለም አቀፋዊ ባህሪይ ያለው ስለመሆኑና አብሮነት ደግሞ የሰው ልጅ ልዩ ባህሪይ እንደሆነ ይናገራሉ። የኃይማኖት አስተማሪዎችም ይህንኑ ሃሳብ በማጠናከር ፈጣሪ የሰውን ልጅ ሲፈጥረው ብቻውን እንዳይሆን ረዳት እንዳበጀለት ከቅዱሳት መጻሕፍት በማጣቀስ ሃሳቡን ያጠናክሩታል። ከዚህም ባሻገር የሰውነት አካላት በተግባርም ይሁን በዓይነት የተለያዩ መሆናቸውን፤ ነገር ግን አንዱ ለሌላው እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እነዚሁ አስተማሪዎች ያብራራሉ።
አብሮነት ለሰው ልጆች ማህበራዊ መስተጋብር ወሳኝ ሚና ያለው መርሆ ነው። አብሮነት የተለየ ማንነትን፣ ባህልን ወይም ሃሳብን የሚያከብርና የሚያስተናግድ በሰላም አብሮ ለመኖር መሠረት የሆነ ነው። አብሮነት የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ መቻቻል ከሚለው ጋር በማፈራረቅ ጥቅም ላይ ሲውልም ይታያል።
በብዙዎቻችን ዘንድ አዲስ ዓመት የአዲስ ተስፋ መጀመሪያ ብስራት ነጋሪ ነው፡፡ በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን ዘመን ስንቀይር ሁሌም ቢሆን ራሳችንን ካለንበት ሁኔታ በማውጣት ብዙ እቅዶችና ሃሳቦችን በመያዝ የተጣላነውን በመታረቅ የበደልነውን በመካስ ዘመንን የምንሻገር ህብረተሰብ ነን፡፡ ይህ ደግሞ በዓሉን ከፍ ያለ ዋጋ የሚያሰጠው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ አስደሳች እንዲሁም የዓለምን ሕዝብ አስደማሚም ተግባራችን ነው።
ይህንን አብሮነታችን በተለያዩ ኃይማኖት ውስጥ ባሉ በዓላት በተለያየ ሁኔታ የሚገለጽ ቢሆንም ቅሉ አዲስ ዓመት ወይም ዘመን መለወጫ ግን የሁሉም በመሆኑ አብሮነቱም በዛው ልክ ከፍ ያለና የጎላ ይሆናል፡፡ ይህንን አብሮነታችንን ከእንኳን አደረሰህ አደረሰሽ መልዕክትና መልካም ምኞት መለዋወጥ ጀምረን ስጦታ በመሰጣጣት አብሮ በመብላት በመጠጣት የተቸገረን በመርዳት ስንገልጸውም ኖረናል፡፡ አሁን ላይ ይህ አብሮነታችን የሳሳ የሚያስመስሉ ነገሮች እዚህም እዚያም እየተፈጠሩ ቢሆንም ዛሬ ኢትዮጵያውያን እንደ ዘመን መለወጫ ዓይነት በዓላትን ስናከብር ግን የወትሮውን አብሮነታችንን እናሳያለን፡፡
ዛሬ ላይ ሆነን የኋላውን ስናስብ ብዙ የአብሮነት ዘመናችን ትዝ ይለናል ምክንያቱ ደግሞ ዛሬ ከሚያግባቡን ይልቅ በማያግባቡን ትርክቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ያንን ማንነታችንን ለማውደም ዳር ዳር እያልን ያለን ማህበረሰቦች በመሆናችን ነው፡፡ ነገር ግን ያንን አብሮ የኖረና አንተ ትብስ አንቺ እየተባባል ዘመን መለወጫን ጨምሮ በርካታ በዓላትን እንዲሁም ሀዘንና ደስታን ብቻ በአጠቃላይ ብዙ ነገሮቻችንን በቁርኝት ያሳለፍን ኢትዮጵያውያን ይህንን ለማጥፋት መጣራችን አስነዋሪም አስገራሚም በመሆኑ በተለይም ለራሳቸው ትርፍ በማሰብ ባህል ኃይማኖታችንን ሊሸረሽሩ ከሚነሱ ፖለቲከኞች መራቅ አስፈላጊም አንገብጋቢም የወቅቱ አጀንዳ ነው፡፡ አዲሱን ዓመትም በዚህ መንፈስ ልንቀበለው ይገባል፡፡
“ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ነብር ዥንጉርጉርነቱን” ለቆ አያውቅም የሚሉን ደግሞ አዲስ ዓመትን አስመልክተን ያነጋገርናቸው የኃይማኖት አባቶች ናቸው፡፡ ምንጊዜም ቢሆን የምንታወቅበትን አብሮነትና አንድነታችንን ሊሸረሽሩ የተለያዩ አካላት ጥረት እያደረጉ በጥቂቱም ቢሆን የተሳካላቸው እየመሰላቸው ነው ነገር ግን እውነቱ ይህ አይደለም።
በምሥራቅ ሐረርጌ በቀርሳ ወረዳ የላንጌ ቢላል መስጊድና የቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን አሰሪ መላከ ሕይወት ቆሞስ አባ አክሊለማርያም ኃይለሥላሴ እንደሚሉት ኢትዮጵያ በዓለም ሕዝብ ዘንድ የምትታወቀው የአብሮነት ምድር በሚል ነው፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ አንዱ የሰው ልጅ መገኛ ምድር መሆኗ ሲሆን ሌላው ከክርስትናም ከእስልምናም በፊት የነበረች ሁሉንም የሰው ልጅ ተቀብላ አቅፋ አብረው እንዲኖሩ የምታደርግ ሀገር ስለነበረች ነው።
ኢትዮጵያ ብቻዋን መልካም እናት ናት የሚሉት አባ አክሊለማርያም መልካም እናት ደግሞ ለልጆቿ ታስባለች ሀገራችን ደግሞ ከልጆቿ አልፋ እሷን መጠጊያ ብለው ለሚኖሩ የዓለም ሕዝቦች በሙሉ የምታስብና ጥሩ መጠጊያ የሆነች ናት፡፡ እስከ ዛሬ በኖርንበት ዘመን ብዙ ነገሮችን አይተናል ሀገራችን ላይም ብዙ ዓይነት የዓለም ሕዝቦች መተው እየኖሩ በርካታ ኃይማኖቶችም በሰላም እየተመለኩ ነው እኛ ሀገር ላይ አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች አድርጎ የማየት ሁኔታ ፈጽሞ አልነበረም ሀገራችንም ይህንን ሳትፈቅድ ብዙ ዘመናትን ተሻግራለች ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ የሰው ልጆች ከተፈጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ነው የሚነሳው ከዛን ወቅት ጀምሮም የፈጠራትን የምታውቅ እሱንም አብዝታ የምታመልክ ሆኖ ነው የኖረችው፤ ክርስትናም ከተቀበለች በኋላ ከልደቱ አንስቶ እስከመስቀሉ ሞቶም ተቀብሮ ኋላም እስከ ማረጉ ድረስ ያለው ሁኔታ የተከናወነው በእስራኤል ሀገር ነው፤ ነገር ግን ያ ሁሉ በእስራኤል ሀገር ቢደርስበትም አልተወደደም ነበር ፤ በኢትዮጵያ ግን በፍጹም ፍቅር ነበር ተቀባይነትን ያገኘው ይህ ደግሞ የሰው ልጆችን አብረው እንዲኖሩ የምታደርግ ልዩ ምድር ስለመሆኗ ማሳያም አድርገን ልንወስደው እንችላለን ይላሉ አባ አክሊለማርያም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የእስልምናው መስራች የመካ መዲና ንጉስ የዓለም እስላም ወንድሞቻችን መሪ የሆኑት ነብዩ ሙሀመድ ውልደታቸውና እድገታቸው መካ ቢሆንም በዙሪያቸው የነበሩት በሙሉ ግን ኢትዮጵያውያን ነበሩ፤ በዚህ ምክንያት ለኢትዮጵያውያን የነበራቸው ፍቅር ከፍ ያለም ነበር፤ እሳቸውም በስደት ብዙ ስቃይ ካዩ በኋላ ማረፊያቸውን ኢትዮጵያ ሲያደርጉ ከፍ ያለ ፍቅርን ነበር ያገኙት በማለት የኢትዮጵያውያንን ኃይማኖተኝነት ያብራራሉ።
በመሆኑም እስልምናንም ክርስትናንም በእኩልነት ያኖረች ሀገር ናት፡፡ ይህንን ዓይነት ነገር የሚያደርግ ሀገር ደግሞ በዓለም ላይ ቢፈለግ አይገኝም፡፡ ስለዚህ እኛ ልዩ ሀገር ያለን ልዩ ሕዝቦች መሆናችንን ትውልዱ በሚገባ ሊገነዘብ ከሚነጣጥሉና ከሚከፋፍሉ ሃሳቦች ራሱን ሊቆጥብና ቆም ብሎ ሊያስብ ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ አመሠራረት እግዚአብሔራዊ ነው፡፡ ይህም ማለት ሀገራችን መሰረቷ እግዚአብሔር ነው በእሱም ሕግና ሥርዓት እንዲሁም ፍላጎት የምትመራ ናት፡፡ የሚገርምሽ እንዲህ ስል ብዙ ሰዎች ይገረማሉ ለመገረማቸው ዋናው ምክንያት ደግሞ ትውልዱ ከዚህ የራቀ ስለሚመስላቸው ነው ነገር ግን አሁንም ቢሆን ትውልዱ በዚህ ውስጥ ነው ያለው ምንም የራቀው የወጣው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ትንሽ ሥራ አይጠይቅም ብዬ ማለት አልችልም በማለት ያስረዳሉ።
እኔ የሙስሊምም የክርስቲያንም አባት ነኝ ብዙ ሙስሊሞች እየመጡ አባ ይህንን አድርጉልን እንደዚህ ሆንን በማለት አባታዊ ምክርና ድጋፍ ይጠይቁኛል የሚሉት አባ አክሊለማርያም ይህ የሆነው ደግሞ ሀገራችን አሁንም በሕገ እግዚአብሔር የመመራቷ መንፈስ ስላለ ነው፡፡ በመሆኑም ወጣቱን በዚህ መንፈስ እንዲያስተውል ካደረግነው አሁንም ወደቀደመው አብሮነታችንንና ማንነታችን ከመመለስ የመጡብንን ችግሮች ሁሉ ድል ከመንሳት የሚያግደን አንድም ነገር የለም በማለት ያብራራሉ።
“….የኢትዮጵያን ሕዝብ በእምነት ለመለያየት የሚጥሩ ሰዎች ዘርና ብሔርን በማምጣት ለመከፋፈል የሚሞክሩ ስግብግቦች ማወቅ ያለባቸው ነገር ይህ ሃሳባቸው ወይም ድርጊታቸው መቼም ቢሆን የሚሳካ አለመሆኑን ነው” ይላሉ።
ዘርና ብሔር በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚታወቅ አይደለም የሚሉት አባ አክሊለ ማርያም የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ዘር የእህል እንጂ የሰው ሊሆን ስለማይችል ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትታወቀው እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮታል በማለቷ ነው። በመሆኑም ዛሬ ተነስተን ብሔራችንን ወይም ኃይማኖታችንን እናስቀድም ብንል በሰውም በአምላክም ዘንድ ተቀባይነታችን በጣም የወረደ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩልም የኃይማኖት አባቶች በሙሉ ወደ ሙያቸው መመለስ ይጠበቅባቸዋል የሚሉት አባ አክሊለማርያም ብሔሩን ያወቀ የኃይማኖት መሪ የማንም አባት ወይም መካሪ ሊሆን አይችልም ፤ ስህተት ነው ምክንያቱም እሱ የኃይማኖት እንጂ የብሔር አባት አይደለምና። ካሉ በኋላ እኔ የኃይማኖት አባት ነኝ ነገር ግን ብሔርና ዘር ከያዝኩና ለምመራቸው ተከታዮቼ ካስተማርኩ የእኔ ኃይማኖት አባትነት እዛ ላይ ያበቃል በመሆኑም አሁን ላይ ልጆቻችንን ከጥፋት መመለስ ትክክለኛውን መንገድ ማሳየት ከማንም ሳይሆን ከእኛ የኃይማኖት አባቶች የሚጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው በማለት ያብራራሉ፡፡
ልዩነታችን ካለያየን መጥፊያችን እየደረሰ መሆኑን መገንዘብ አለብን በመሆኑን እኛ ከሚያለያዩን ይልቅ በሚያስተሳስሩን ነገሮች ላይ ትኩረት በማድረግ የመጣብንን ችግር መዋጋት አንድነታችንን ከሚያጠፋ ክፉ ቫይረስ ራሳችንን በማራቅ የሰይጣንና የሰይጣናውያን መጫወቻ ላለመሆን መጠንቀቅና ቶሎ ብለን መንቃት ይኖርብናል ይላሉ።
“የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ሲዘምት ነው የሚያምርበት፤ አንድ ክልል አልያም አንድ ብሔር ብቻውን ምንም ውበት የለውም፤ አባባሉም ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይለቀም ነው ስለዚህ ሁሉም ትውልድ ይህንን ሊያስብብት ይገባል” በማለት ይናገራሉ።
ይህንን ዘር የሚባለውን ነገር ያመጡት አንዳንድ ፖለቲከኞች ሕዝቡን ለመለያየት እንዲጠቅማቸው ነው እንጂ ኢትዮጵያ በዚህ አትታወቅም ይህም በሚገባ ሊሰመርበት የሚገባ ነገር ነው ስለዚህ ትውልዱ ይህንን በጥልቀት መመልከት የቅዱሳን መጻሕፍትን መልዕክት መመሪያ ማድረግ ይጠበቃል በማለት ሃሳባቸውን ይሰጣሉ።
ኢትዮጵያውያን በዚህ መልኩ አንድነታችንን ካላጠናከርን እነ ሶሪያን ላለመሆናችን ምንም ዋስትና የለንም ፤ በመሆኑም እነሱን ላለመሆን አባቶቻችንን ለመምሰል መጣር እርስ በእርሳችን ከመዋጋት ይልቅ አባትና ልጅ መሪና ተመሪ እንዳይስማማ እንዳይደማመጥ ያደረገውን ሀጥያት መዋጋትን መልመድ ይገባናል።
በአዲሱ ዓመትም ከድግሱ ከመብላት ከመጠጣቱ ባሻገር ያለፈውን ሁሉ በመተው አዲስ ለመሆን መጣርም ይገባል የሚሉት አባ አክሊለማርያም በአዲሱ ዓመት ዋና ሥራችን ሊሆን የሚገባው ከሀጢያታችን ካለመደማመጣችን ጋር መዋጋት ነው፡፡ ሌላው አፉን ከፍቶ ሊውጠን የተዘጋጀውን ድህነትን ተዋግተን በማሸነፍ የሀገራችንን ኢኮኖሚ ማሳደግ ሀገራችን ጥቂቶች በልተው አብዛኛው ተርቦ የሚኖርባት ከመሆን እንድትድን ማስቻል ሊሆን እንደሚገባም አባታዊ መክራቸውን አስተላልፈዋል።
የፌዴራል እስልምና ጉዳዮች የምርመር ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት ሼህ እንድሪስ አሊ በበኩላቸው ሰው አብሮ ሲኖር ተከባብሮ ተቻችሎ ተፈቃቅሮና ተዛዝኖ ነው መኖር ያለበት፡፡ የሰው ልጅ ከአውሬ አልያም ከጂኒ ጋር መኖር አይችልም መኖር የሚችለው ከአምሳያው ሰው ጋር ነው በዚህ አብሮ መኖር ውስጥ ደግሞ መጋጨቶች አለመስማማቶች ይፈጠራሉ ነገር ግን እነዚህን ሁኔታዎች በመቻቻልና በመደማመጥ አልፎም በመተላለፍ መጓዙ ጠቅም እንጂ ጉዳት የለውም።
አብሮ ለመኖር ኃይማኖት ወይም ብሔር አያስፈልገንም ይልቁንም ሰው መሆናችን ብቻ በቂ ነው፤ በመሆኑም ኃይማኖቱም የሚያዘው ተቻችለን ተፈቃቅረን ብንችልም ተረዳድተን እንድንኖር ነውና ሁላችንም በዚህ መንፈስ ችግሮቻችንንና ልዩነቶቻችንን ከማጉላት ይልቅ አንድነታችንን አጥብቀን በመያዝ መኖር ሀገራችንንም እኛንም ያሻግራል ይላሉ ሼህ እንድሪስ።
ከመቻቻልና ከአብሮነት ብዙ ትርፍ አለ የሚሉት ሼህ እንድሪስ በተለይም የዘመኑ ትውልድ ይህንን ወጋችንን ቢጠብቅ ከምንም በላይ ሰላሙን ያተርፋል ሰላም አተረፈ ማለት ደግሞ ብልጽግና ሥራ እድገት መጣ ማለት ነው በዚህም ሕይወቱን ቀይሮ ከስደት ራሱን ያድናል ብለዋል።
ከእኛ የቀደሙት ሰዎች ኃይማኖታቸውን አክባሪ ስለነበሩ አብሮ ለመኖር ብዙ አይቸገሩም ነበርና ብዙ ዓመታትንም ምንም ሳይሆኑ አብረው ኖረዋል፤ እኛ ግን ዛሬ በተለያዩ ነገሮች እየተጠመድን ሀገራችንን ላይ ችግር እያመጣን ነው ይላሉ።
ትውልድ አብሮ ሲኖር ሀገርም ተጠቃሚ ናት በተለይም ሰላሟ የተረጋገጠ ዜጎቿ አብረው የሚበሉ የሚጠጡ ያላቸውን የሚካፈሉ ዜጎች ባሏት ልክ ሰላሟ የተረጋገጠ በጦርነት የምትወድመው ቀርቶ ልማት የሰፈነባት በጠቅላላው ዜጎቿ ጠግበው የሚኖሩባት ትሆናለች።
በመጪው አዲስ ዓመትም በተለይም ለእኩይ ተግባር ተሰልፈው ያሉ ሰዎች እጃቸውን መሰብሰብ የእነሱ መሣሪያ የሚሆነው ወጣቱም ቆም ብሎ በማሰብ ልዩነቱን አቻችሎ አንድ በሚያደርጉት ነገሮች ላይ አንድ ሆኖ መራመድ ይጠበቅበታል ብለዋል ሼህ እንድሪስ፡፡
የኢትዮጵያ ኃይማኖት ጉባኤ መሥራችና የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የቦርድ አባል መጋቢ ዘሪሁን ደጉ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን የኖርንበት ብዙ ነገሮችን ያተረፈንበት በቋንቋ በብሔር በኃይማኖት ሳንከፋፈል ከውጫዊ አንድነታችን ይልቅ ውስጣዊ አንድነታችንን አስቀድመን የኖርን ሕዝቦች ነን ይላሉ፡፡
በተለያየ ጊዜ የገጠሙንን ፈተናዎች ያለፍነው በአንድነታችን ነው ይህ የሚያሳየው ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ማለት በራሱ ህብረትና አንድነት ማለት መሆኑን ነው፡፡ ይህም ለዘላለም ጸንቶ የኖረ የእኛነታችን መገለጫ ነው፡፡
እንደ መጋቢ ዘሪሁን ገለጻ ዛሬ ላይ የገጠሙን ችግሮች በሙሉ የቤት ሥራችንን በደንብ ያለመሥራታችን ውጤቶች ናቸው፡፡ አሁን ላይ ልዩነታችን ጎልቶ አንድነታችን እየኮሰሰ መጥቷል፤ ይህንን ለማብራራት በአንድ ምሳሌ ባስረዳ ” አንድ ሰው ቤቱ ገብቶ ቁልፉን በኪሱ እንደያዘ መብራት ይጠፋበታል፤ ቤቱ በጣም ስለጨለመው ቆልፎ ወደደጅ ለመውጣት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ቤቱን የሚቆልፍበት ቁልፍ ያጣው ሰውዬው ቤቱን እያመሳቀለ ቁልፍ መፈለግ ይጀምራል፤ እንደዛም ሆኖ አላገኘውም፤ ወደውጭ ሲያይ ብርሃን ነው በቃ እዛ ሆኜ ልፈልግ በማለት ብርሃኑ ላይ ቁልፍ ይፈልጋል ጓደኛውም ይመጣና ምን እየሰራህ ነው ሲለው የቤቴን ቁልፍ ጥዬ ነው በማለት ይመልስለታል፤ የት ጣልከው ሲለውም ቤት ውስጥ መሆኑን ይነግረዋል ታዲያ የጣልክበት ለምን አትፈልግም ሲለው እዚህ የቆምኩበት ብርሃን ነው ቤቱ ግን ጨለማ ነው ይለዋል ጓደኛውም ቤቱ ጨለማና ችግር ያለበት ቢሆንም ቁልፍህም መፈለግ ያለብህ ቤትህ ውስጥ ነው ይለዋል።
ይህ ምሳሌ ከእኛ አሁናዊ ሁኔታ ጋር ከፍ ያለ ቁርኝት አለው፤ ምክንያቱም የእኛ ችግር ሊፈታ የሚችለው በሌላ በማንም ሳይሆን በራሳችን ለዛው የቀደመውን የአባት የእናቶቻችንን አብሮ የመኖር የመቻቻል የመደማመጥና የመከባበር ባህልን በማምጣት መሆኑን ያሳያል ይላሉ፡፡
በአውሮፓና አሜሪካ በጥሩ የኢኮኖሚ ደረጃ እየኖሩ የኢትዮጵያን ችግር እፈታለሁ የሚሉ ሰዎች በእውነት ለእኛ መፍትሔ የሚያመጡ ሳይሆኑ እንደውም የተዳፈነን እሳት እየቆሰቆሱ በሰው ቁስል እንጨት እየሰደዱ እንድንበተን የሚገፋፉ በመሆናቸው ለእኛ ችግር እኛው ነን ባለመፍትሔዎቹ ብለን መነሳት እንዳለብንም ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ ከማንም በላይ የምታስፈልገው ለእኛ ነው ይህ እንዲሆን ደግሞ በጋራ በአንድነት በመተባበርና በአብሮነት መሥራት ያለብንን የቤት ሥራ ሁሉ መሥራት አለብን ይህ የማይሆን ከሆነ ግን እጣ ፈንታችን በጣም የሚያስፈራ ከእኛም የማይጠበቅ ነው የሚሆነው ይላሉ።
በሌላ በኩልም ተጠራቅሞ የፈነዳ እየመሰለን ያለውን ውስብስብ ችግራችንን የሆነ አካል ላይ ጥለን ቁጭ ማለቱ መፍትሔ የሚያመጣ አይደለም፡፡ ከዛ ይልቅ ሁላችንም የመፍትሔ አካል ሆነን መቆም መቻል ነው ያለብን ይህንን ስናደርግ አቅማችን ይጎለብታል ችግራችንንም እንሻገራለን ይላሉ።
“….አዲስ ዓመት ሁሌም አዲስ ተስፋ የሚታይበት ከመሆኑ አንጻር ትላንትን በይቅርታና በምህረት መዝጋት ያስፈልጋል። ምናልባት ይህ በብዙ ነገሮች ውስጥ ላለፈን ለእኛ ሊከበድ ይችላል ነገር ግን ብቸኛው መፍትሔ ይህ ብቻ ነው። ስለዚህ ይቅርታ ለመስጠትና ለመቀበል ራስን ማዘጋጀት ይገባል። ይህ ደግሞ ከቤት ከራሳችን መጀመር አለበት እያደገ ሄዶም ተቋምና ሀገር ይሆናል። መኪና ትልቁ መስታወቱ ያለው ወደፊት የሚያሳየው ነው። ወደኋላ የሚያሳዩት ምንም እንኳን ጠቃሚ ቢሆኑም ትንንሽ ናቸው፤ ስለዚህ ትኩረታችን ነገ ላይ በማድረግ ወደፊት መመልከት ይገባል”ብለዋል።
ሀገራችን ለሁላችንም ታስፈልገናለች በዚህም ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችን ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባናል በዚህም የኃይማኖት አባቶች ፖለቲከኞች ምሁራን እንዲሁም የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉ የመፍትሔ አካል ሆኖ መቅረብ አለበት በማለት ሃሳባቸውን ያጠቃልላሉ፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 6 ቀን 2015 ዓ.ም