‹‹የሒሣብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ መቋቋም የሀገር በቀል ኢኮኖሚው ውጤታማ እንዲሆን ያስችላል›› አቶ ፍቃዱ አጎናፍር የኢትዮጵያ የሒሣብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር

የኢትዮጵያ የሒሣብ አያያዝ እና ኦዲት በፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ አዋጅ ቁጥር 847/2006 እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 332/2007 የተቋቋመ መንግሥታዊ ተቋም ነው። ቦርዱ በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ሲሆን ዓላማውም የሕዝብ ጥቅምን ማስጠበቅ ነው። ይህ ተቋም ለምን እንደተቋቋምና ምን ምን ተግባራትን እንደሚያከናውን የኢትዮጵያ የሒሣብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍቃዱ አጎናፍር ጋር ቆይታ አድርገናል። አብራችሁን ቆዩ።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ የሒሣብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ምን ምን ተግባራትን ሊያከናውን ተቋቋመ?

አቶ ፍቃዱ፡- የኢትዮጵያ የሒሣብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ አንደኛ በሕግ የፋይናንስ ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ የተጣለባቸውን በተለይም ከፍተኛ የሕዝብ ጥቅም ያለባቸው ሪፖርት አቅራቢ አካላት ኦዲት የተደረገ የፋይናንስ ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡ የማድረግ እና የቀረበው ሪፖርት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ እና የኦዲት ደረጃዎች መሠረት የተዘጋጀ መሆኑን በመመርመር የሪፖርቱን የጥራት ደረጃ የሚያሳድግ ተቋም ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ቦርዱ ለሕዝብ የሒሣብ እና የኦዲት አገልግሎት ለሚሰጡ የሒሣብ እና የኦዲት ባለሙያዎች ፈቃድ መስጠት፣ የሰጡት ሙያዊ አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀ መሆኑን የማረጋገጥ እና አስፈላጊውን ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ ነው።

በሦስተኛ ደረጃ ቦርዱ በሀገር ውስጥ ወይም በውጭ ሀገር ለተቋቋሙ የሒሣብ ሙያ ማኅበራት አክሪዲቴሽን ወይም ዕውቅና መስጠት እና ማኅበራቱን በበላይነት መቆጣጠር ሲሆን ነገር ግን እስካሁን ድረስ መስፈርቱን አሟልቶ በቦርዱ የተመዘገበ የሒሣብ ሙያ ማኅበር የለም።

አዲስ ዘመን፡- በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የሒሳብ ሥራ ለመቆጣጠርና ለማሳደግ ምን ምን ተግባራትን ያከናውናል?

አቶ ፍቃዱ፡- የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የሒሳብ ሥራ ለመቆጣጠርና ለማሳደግ የተቋቋመ ቁልፍ ተቆጣጣሪ የመንግሥት ተቋም ነው። በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የገንዘብ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተመሠረተው ቦርዱ የሒሳብ አያያዝና የኦዲት ሙያ አሠራር ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟሉ እና ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማበርከት ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

ቦርዱ በፋይናንሽያል ሪፖርቶች እና ኦዲት ላይ ግልፅነትን፣ ተጠያቂነትን እና ታማኝነትን የማሳደግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የፋይናንስ አስተዳደርን ጥራት ለማሳደግ በመንግሥት እና በሒሳብ ባለሙያ መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።

ቦርዱ ለሒሳብ አያያዝ ሙያ እድገት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያለመ ሲሆን በዚህም ኅብረተሰቡ በፋይናንሽያል ሪፖርቶች ላይ ያለውን እምነት ለማሳደግ እና የሚመለከታቸውን ሕጎች እና ደንቦች መከበራቸውን ያረጋግጣል።

ከቦርዱ ቀዳሚ ሚናዎች አንዱ በኢትዮጵያ ያለው የሒሳብ አያያዝ ሙያ የሕዝብን ጥቅም ማስጠበቁን ለማረጋገጥ የሒሳብ ባለሙያዎችን እና ኦዲተሮችን የትምህርት እና ሥልጠና ደረጃዎችን በማዘጋጀት ወደ ሙያው ለመግባት የሚያስፈልጉትን መመዘኛዎች ያዘጋጃል፤ ባለሙያዎች ተግባራቸውን በብቃት ለመወጣት አስፈላጊውን ክህሎት እና እውቀት እንዲኖራቸው ያደርጋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ለሒሳብ ባለሙያዎች እና ኦዲተሮች የሙያ ፍቃድ የመስጠት እና የመመዝገብ ኃላፊነት አለበት። ይህ ሂደት የአመልካቾችን ብቃት እና ልምድ በመገምገም በቦርዱ የተቀመጡትን መመዘኛዎች ማሟላታቸውን ማረጋገጥን ያካትታል። ቦርዱ የባለሙያዎችን ሙሉ መረጃ በመያዝ የሙያውን ታማኝነት እና የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ይረዳል።

አዲስ ዘመን፡- ቦርዱ የሒሳብ አያያዝ እና የኦዲት ደረጃዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያለው ሚናን እንዴት ይገልፁታል?

አቶ ፍቃዱ፡- ቦርዱ ከዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች ጋር የሚጣጣሙ የሒሳብ አያያዝ እና የኦዲት ደረጃዎችን በማዘጋጀት እና በመተግበር ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ቦርዱ እነዚህን መመዘኛዎች ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለሀገር ውስጥ ንግዶች እና ድርጅቶች አግባብነት ያላቸው እና ተፈጻሚ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ይህም የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ደረጃዎችን (IFRS) እና የዓለም አቀፍ የኦዲቲንግ ደረጃዎችን (ISA) መቀበልን ያካትታል።

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ በባለሙያዎች እና በድርጅቶች መካከል የተቀመጡ የሒሳብ እና የኦዲት ደረጃዎችን መከበራቸውን ይቆጣጠራል። ይህም ደንቦችን ማክበርን ለማረጋገጥ የሒሳብ መግለጫዎችን እና የኦዲት ሪፖርቶችን በየጊዜው መመርመርን እና ግምገማዎችን የሚያካትት ሲሆን ቦርዱ የሥነ ምግባር መስፈርቶችን በሚጥሱ ወይም የሕግ መስፈርቶችን የማያሟሉ ባለሙያዎች ላይ ቅጣት የመጣል ሥልጣን አለው።

አዲስ ዘመን፡- የሒሳብ ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ የሚሠሩ ሥራዎች ካሉ ቢገልፁልን?

አቶ ፍቃዱ፡- የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ የሒሳብ ባለሙያዎችን እና ኦዲተሮችን ክህሎት እና ብቃት ለማሳደግ፣ የባለሙያዎችን የእውቀት መሠረት ለማሻሻል ያለሙ ወርክሾፖችን፣ ሴሚናሮችን እና የሥልጠና ፕሮግራሞችን ያዘጋጃል።

ቦርዱ በሂሳብ አያያዝ ሙያ ውስጥ የሥነ ምግባርን አስፈላጊነት በማጉላት ሁሉም የተመሰከረላቸውም ይሁኑ የተፈቀደላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ሊከተሉት የሚገባ የሙያ የሥነ-ምግባር ደንብ በማዘጋጀት ታማኝነትን እና ሙያዊ ብቃትን ለማሳደግ ይሠራል። ይህ ለሥነ-ምግባራዊ ተግባራት ቁርጠኝነት የሕዝብ አመኔታን ለመጠበቅ እና በፋይናንሽያል ሪፖርት ላይ ያለውን እምነት ለማሳደግ አስፈላጊ ነው።

ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማለትም ከመንግሥት ኤጀንሲዎች፣ የትምህርት ተቋማት እና የሙያ ማህበራት ጋር በመተባበር የሒሳብ ሥራን ለማሳደግ ይሠራል። ከእነዚህ አካላት ጋር በመገናኘት ቦርዱ አላማውን ከሀገራዊ ልማት ግቦች ጋር በማጣጣም የሒሳብ አያያዝ ሙያ ለኢኮኖሚ እድገት ውጤታማ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ይፈልጋል።

ቦርዱ ስለ የሒሳብ አያያዝ እና የኦዲት ሙያ አስፈላጊነት ግንዛቤን ለማስተዋወቅ በሕዝብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄዎች ላይ በንቃት ይሠራል። በፋይናንሽያል ሪፖርቶች ላይ ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖር በማበረታታት፣ በኢትዮጵያ ያለውን አጠቃላይ የኮርፖሬት አስተዳደር ማሕቀፍ ለማሳደግ ይሠራል።

የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የሒሳብ ሥራን በመቆጣጠር ሙያው ከፍተኛውን የጥራትና የታማኝነት ደረጃ ያሟላ መሆኑን በማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ሲሆን በኢትዮጵያ የፋይናንስ አስተዳደር አሠራሮችን ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት ግቦች ይደግፋል። ጠንካራ እና ሥነ ምግባር ያለው የሂሳብ ሥራን በማጎልበት ቦርዱ በፋይናንሽያል ሪፖርት አቀራረብ ላይ የሕዝብ አመኔታ እንዲጎለብት እና በመንግሥት እና በግሉ ሴክተሮች ውስጥ ግልፅነት እንዲኖር ይሠራል።

አዲስ ዘመን፡- ከላይ ከጠቀስናቸው ተግባራት በተጨማሪ የቦርዱ ሥራ ምንድነው?

አቶ ፍቃዱ፡- ከላይ እንደጠቀስነው ቦርዱ በአዋጅ ከተሰጠው ኃላፊነት ውስጥ ሶስተኛው የሂሳብ ሙያ ማህበራት ፈቃድ መሰጠት ነው። እነዚህ ማህበራት በሀገር ውስጥ ተቋቁመው የሀገሪቱን የሒሳብ ሙያ ማሳደግ ወይም ከውጭ መጥተው መሥራት የሚፈልጉ ላይ እውቅና የሚሰጥ ነው።

የሒሳብ ሙያ ማህበራት ሲቋቋሙ የሒሳብ ሙያውን ማሳደግና በሒሳብ ሙያ ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት ይጠበቅባቸው ነበር። እነዚህ ማህበራት ዳግሞ የሒሳብ ባለሙያዎችን ማፍራት ስለተሳናቸው የሒሳብ ባለሙያዎችን የሚያፈራ ኢንስቲትዩት ማቋቋም ግድ መሆኑን ይናገራሉ።

አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱን ማቋቋም ለምን አስፈለገ?

አቶ ፍቃዱ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት የሒሣብ ሙያ ማኅበራት የተቋቋሙበት ዓላማ የሒሣብ ሙያን ለማሳደግ እና በሙያው ብቁ የሆኑ ባለሙያዎች እንዲኖሩ ለማስቻል ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው ብቁ እና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ማፍራት አልቻሉም።

በሌላ በኩል በውጭ ሀገር ተቋቁሞ በኢትዮጵያ ውስጥ እየሠራ የሚገኝ አንድ የሙያ ማህበር ቢኖርም ለትምህርትና ሥልጠናው የሚከፈለው ክፍያ ለሀገራችን ዜጎች ተመጣጣኝ ባለመሆኑ እና ክፍያው የሚፈጸመው በውጭ ሀገር የመገበያያ ገንዘብ በመሆኑ ትምህርቱን ለመውሰድ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እና ተቀባይነት ያላቸው ብቁ እና በቂ የተመሠከረላቸው የሒሣብ ባለሙያዎችን ለማፍራት፣ የሒሣብ ሙያን ለማሳደግ እና የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ኢንስቲትዩት ማቋቋም የግድ ሆኗል።

አዲስ ዘመን፡- የኢንስቲትዩቱ መቋቋም ፋይዳ ምንድነው?

አቶ ፍቃዱ፡- ኢንስቲትዩቱ የተመሠረተበት ዋና ዓላማ ብቃት ያላቸው የተመሠከረላቸው የሒሣብ ባለሙያዎችን (Certified Public Accountant- CPA) በብዛት ለማፍራት ነው። እነዚህን ባለሙያዎች የማፍራት ጠቀሜታ በርካታ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሀገራችን ኢትዮጵያ የሕግ አካል ያደረገቻቸው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ እና የኦዲት ደረጃዎች በተገቢው ጊዜ እና ሁኔታ ተግባራዊ እንዲደረጉ ያግዛል፤ ቦርዱ ለሕዝብ አገልግሎት ለሚሰጡ የሒሣብ እና የኦዲት ባለሙያዎች ፈቃድ የሚሰጠው ለተመሠከረላቸው የሒሣብ ባለሙያዎች በመሆኑ ይህንን መስፈርት የሚያሟሉ ባለሙያዎች ቁጥር ለማሳደግ ይረዳል፤ የካፒታል ገበያን በተሳካ ሁኔታ ለማስፈጸም እና በዘላቂነት ለማስቀጠል ያግዛል፤ በውጭ ሀገር ተቋማት የሚሰጠውን ሥልጠና/ ትምህርት ለማግኘት የሚከፈለውን የውጭ ምንዛሬ በሀገር ውስጥ ለማስቀረት ይረዳል። ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ሰው የተመሠከረለት የሒሳብ ባለሙያ ለመሆን 13 ኮርስ መውሰድ የሚጠበቅበት ሲሆን በአማካይ እስከ 1,500.00 ፓውንድ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ መዋለ-ንዋይ በማፍሰስ በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የሚሰማሩ የውጭ ሀገር ባለሀብቶች ከሀገራቸው ይዘው የሚመጡትን የሰው ኃይል በውስጥ ባለሙያ ለመተካት ያስችላል፤ እንዲሁም የሒሣብ እና የኦዲት ሥራ አገልግሎት ለውጭ ባለሀብቶች ከሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት እንዲሠሩ ክፍት የተደረገ በመሆኑ በሀገር ውስጥ ብቁ እና ተወዳዳሪ ባለሙያዎች እንዲኖሩ ለማድረግ እና ሀገሪቱ በፋይናንስ ረገድ ያደረገችውን ለውጥ የሚደግፉ ወይም የሚመጥኑ የሒሣብ ወይም የኦዲት ባለሙያዎች እንዲኖሩ ለማድረግ ያስችላል፤ በግል ተቋማት ውስጥ በፋይናንስ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ እና የሚያዘጋጁት የፋይናንስ ሪፖርት ጥራት ያለው እንዲሆን ያግዛል፤ ከሒሳብ እና ሒሳብ ነክ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ብቁ ባለሙያዎች ለማፍራት በተለያዩ ተቋማት የሥልጠና ማዕከላት (ኢንስቲትዩቶችን) ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ወደ አንድ ለማምጣት ያግዛል።

ሀገራችን በቅርቡ የሰነደ-መዋዕለ ንዋዮች ግብይት ማከናወን ጀምራለች። ይህንን ሰነድ ለመግዛት ወይም ለመሸጥ መሠረት ከሆኑት መካከል አንዱ እና ዋነኛው የፋይናንስ ሪፖርት ነው። የአንድ ሪፖርት አቅራቢ አካል (የንግድ ድርጅት) ትክክለኛ የፋይናንስ አቋም ሊታይ የሚችለው ሪፖርቱ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች መሠረት ተዘጋጅቶ ሲቀርብ ነው። ለዚህ ደግሞ ኢንስቲትዩቱ የሚያፈራቸው ባለሙያዎች ሚና የላቀ ይሆናል፡፡

ከኢንስቲትዩቱ የሚሰጥ የተመሠከረለት የሒሣብ ባለሙያ (ሲ.ፒ.ኤ.) የምሥክር ወረቀት የሚሰጠው፤ ትምህርቱ ከንደፈ-ሃሳብ በተጨማሪ የተግባር ልምምድም ታክሎበት ነው። አንድ ሲ.ፒ.ኤ. በአባልነት ከተመዘገበ በኋላ አባል ያደረገው ተቋም ሙያውን እና ሥነ-ምግባሩን በተመለከተ ክትትል እና ቁጥጥር ያደርግበታል። አባል ሆኖ ለመቆየትም በየዓመቱ ተቋሙ በሚያወጣው መስፈርት መሠረት ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ሥልጠና በመውሰድ ራሱን ማሳደግ አለበት፡፡

ኢንስቲትዩቱ የሚሰጠው ትምህርት ዓለም አቀፍ የሒሣብ ባለሙያዎች ፌዴሬሽን ባስቀመጠው የትምህርት አሰጣጥ ደረጃዎች መሠረት ስለሆነ ሥልጠናውን የሚሰጠው አካል የፌዴሬሽኑ አባል እስከሆነ ድረስ ተቋሙ የሚያፈራቸው ባለሙያዎች (ሲ.ፒ.ኤ.) በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው ናቸው። የሚሰጠው ትምህርት በአካውንቲንግ የሙያ ዘርፍ ስፔሻላይዝ እንደ ማድረግ የሚቆጠር ሲሆን በዘርፉ የላቀ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ደረጃ ተደርጎ ይወሰዳል።

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ በፊት የተለያዩ የሒሳብ ሙያዎችን ከዩኒቨርሲቲዎች የተማሩ ሰዎች ብቁ አይደሉም ልንል እንችላለን?

አቶ ፍቃዱ፡- ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚሰጥ ዲግሪ ያላቸው ሙያተኞች የተግባር ትምህርት ስለማይኖራቸው ብቃታቸው ሙሉ አይደለም እንላለን። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቶች ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶችን የያዙ ካሪኩለሞችን አከታው ባለማስተማራቸው የብቃተ ክፍተት ሊታይ ችሏል።

በከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚሰጥ የአካውንቲንግ ዲግሪ የሚሰጠው ትምህርት በአብዛኛው ንድፈ-ሃሳብን (Theory) መሠረት ያደረገ ነው። አንድ ተማሪ ዲግሪውን ከያዘ በኋላ ዲግሪውን በሰጠው ተቋም ምንም ዓይነት ቁጥጥር አይደረግበትም። አንድ ተማሪ ዲግሪውን ከወሰደ በኋላ ዲግሪውን ምንም ዓይነት የሙያ ማጎልበቻ መውሰድ ሳያስፈልገው ዲግሪውን በዘላቂነት ይዞ ሊገለገልበት ይችላል፡፡

ከኢንስቲትዩቱ የሚሰጥ የተመሰከረለት የሒሳብ ባለሙያ (ሲ.ፒ.ኤ.) የምሥክር ወረቀት የሚሰጠው ትምህርት ከንደፈ-ሃሳብ በተጨማሪ ሰልጣኙን በተግባር ልምድን መሠረት በማድረግ በሙያው እውቀት እና ክህሎት የሚጨምርለት ነው። አንድ ሲ.ፒ.ኤ. በአባልነት ከተመዘገበ በኋላ አባል ያደረገው ተቋም ሙያውን እና ሥነ-ምግባሩን በተመለከተ ክትትል እና ቁጥጥር ያደርግበታል፡፡

አንድ ሲ.ፒ.ኤ. በአባልነት ከተመዘገበ በኋላ አባል (ሲ.ፒ.ኤ.)ሆኖ ለመቆየት በየዓመቱ ተቋሙ በሚያወጣው መስፈርት መሠረት ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ሥልጠና በመውሰድ ራሱን ማሳደግ አለበት። ተቋማት የሚሰጡት ትምህርት ዓለም አቀፍ የሒሳብ ባለሙያዎች ፌዴሬሽን ካስቀመጠው የትምህርት አሰጣጥ ደረጃዎች መሠረት ስለሆነ ሥልጠናውን የሚሰጠው አካል የፌዴሬሽኑ አባል እስከሆነ ድረስ ተቋሙ የሚያፈራቸው ባለሙያዎች (ሲ.ፒ.ኤ.) በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው ናቸው። በአካውንቲንግ የሙያ ዘርፍ ስፔሻላይዝ እንደ ማድረግ የሚቆጠር ሲሆን በዘርፉ የላቀ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ደረጃ ነው።

በአጠቃላይ ኢንስቲትዩቱ ወደ ሥራ ሲገባ በሀገራችን አንድ ሺህ እንኳን የማይሞሉትን የበቁ የሒሳብ ባለሙያዎች ቁጥር በብዙ ሺህ እጥፍ የሚያሳደግ በበቃ ባለሙያ የሚመራ የሒሳብ አያያዝ ሥርዓትን የሚዘረጋ በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ኢንስቲትዩቱ ሥራ ጀምሯል?

አቶ ፍቃዱ፡- አሁን የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከወለድ ባንክ ጋር በመተባበር ስለፕሮፌሽናል የሒሳብ አያያዝ ከአፍሪካ ሀገራት ልምድ ለመቅሰም የሦስት ቀን ኮንፍረንስ ተዘጋጅቶ ነበር። በዚህም ላይ እንደተነሳው ግልጽ፣ ተዓማኒና ትክክለኛ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ሪፖርት በማቅረብ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ ፕሮፌሽናል የሒሳብ አያያዝን መከተል ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት መቋቋም ከአፍሪካ ሀገራት እና ከሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመሥራት በእጅጉ የሚረዳ ሲሆን የተቋሙ መመሥረትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አቅም መፍጠር ሀገሪቱ ዘላቂ ልማትን ለማስፈንና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑንም ተነግሯል።

የአፍሪካ ሀገራት በባቡር፣ በኔት ወርክ፣ በኢንዱስትሪ፣ በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በንግድ፣ በኃይል አቅርቦትና በሌሎቹም ዘርፎች የሚያደርጓቸውን የኢኮኖሚ ትብብሮች እና ትስስሮችን ለማሳለጥ የፕሮፌሽናል አካውንታንቶች መኖር ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ አንስተው፤ ይህም ከአጀንዳ 2063 ጋር በቀጥታ የሚደግፍም ነው።

በኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት መመሥረቱ ባለሙያዎች በተለያዩ መንገዶች ሰልጥነው ዓለም አቀፍ የአካውንታንት ብቃት ማረጋገጫ እንዲያገኙ ከማስቻሉም ባሻገር በአካውንታንት መካከል ትብብር እንዲኖር፣ ግልጽና እና ተዓማኒ የኦዲት ሪፖርት እንዲቀርብ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል ድንበር ዘለል የንግድ ሥርዓትን ለማከናወን የሚጠቅምም ነው።

በኢኮኖሚክ እድገት እና በሒሳብ አያያዝ ሥርዓት ውስጥ ግልጽነትና ተዓማኒነት ዋናዎቹ ምሰሶዎች ሲሆኑ፤ ፕሮፌሽናል የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት በተለይም ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ እየተገበረች ላለችው፤ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የጎላ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው፤ እውነተኛ ብቃት ያላቸውን የሒሳብ አያያዝ ሙያተኞችን ማፍራት ሙስናን ለመዋጋትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል ነው ብለዋል። የሒሳብ አያያዝ ባለሙያዎች በውሳኔ አሰጣጥና በገንዘብ አስተዳደር ሥርዓት ላይ ራሳቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም በኮንፍረንሱ ተብራርቷል።

ተቋሙ የልቀት ማዕከል በመሆን እንደሚያገለግል እና ችግሮችን መፍታት የሚችሉና ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉ ፕሮፌሽናል አካውንታትን ለማፍራት የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል፤ ይህም ሀገሪቱ የዘርፉን ሙያተኞች ለማብቃት እየወሰደች ያለችውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል። የተቋሙ መመሥረት ዓለም አቀፍ የአካውንታት ትስስር በመፍጠር እንዲተጋገዙ እንዲሁም መንግሥታዊ ተቋማትም ሆኑ ማህበራዊ ድርጅቶች ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል።

ጠንካራ ሒሳብ አያያዝ ሙያተኞች መኖር ለኢንቨስተሮች መተማመን የሚሰጥ እንደሆነና ኢኮኖሚን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚጠቅም በመሆኑ በቅርቡ ሥራ ጀምሮ የሒሳብ ባለሙያዎችን እጥረት ሙሉ ለሙሉ የሚቀርፍ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ሊያነሱት የሚፈልጉት ሃሳብ ካለ እድሉን ልስጥዎት?

አቶ ፍቃዱ፡- ኢትዮጵያ የ130 ሚሊዮን ሕዝብ ሀገር ናት፤ ፕሮፌሽናል የሒሳብ አያያዝ ሙያተኞች ከ540 የማይበልጡ ናቸው። እነዚህም ቢሆኑ በውጭ ሀገር የተማሩና ልዩ ሥልጠና የወሰዱ እንደሆኑ ገልጸዋል። ኬንያ ከ65ሺህ በላይ፣ ሩዋንዳ ከ6ሺህ በላይ ፕሮፌሽናል የሒሳብ አያያዝ ሙያተኞች አሏቸው። በኢትዮጵያ የፕሮፌሽናል የሒሳብ አያያዝ ሙያተኞች ቁጥር አናሳ የሆነው ኢንስቲትዩቱ ባለመቋቋሙ ነው።

አፍሪካ ውስጥ ፕሮፌሽናል የሒሳብ አያያዝ ኢንስቲትዩት ከሌላቸው ሦስትና አራት ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች። አሁን በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ለመግባት የልምድ ልውውጥ እያደረገ ነው፤ በሒሳብ አያያዝ ሙያ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ጀማሪ ሠራተኞች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አሠራርን ተረድተው ዓለም አቀፍ ሥራ የመሥራት እድል የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል።

በአጠቃላይ ኢንስቲትዩቱ ወደ ሥራ ሲገባ በሀገራችን ከአምስት መቶ የማይበልጡትን የተመሠከረላቸው የሒሣብ ባለሙያዎችን ቁጥር በብዙ እጥፍ የሚያሳድግ፤ ብቁ እና በሥነ-ምግባር የታነጹ ባለሙያዎችን በማፍራት የፋይናንስ ሥርዓቱን ጠንካራ እና ተዓማኒት የሚያደርግ፤ ሀገራችን በፋይናንስ ረገድ እያደረገች ያለውን ለውጥ የሚደግፉ/የሚመጥኑ ባለሙያዎች እንዲኖሩ በማስቻል ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ብቁ የሒሣብ እና የኦዲት ባለሙያዎች እንዲኖሩ የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ስም አመሰግናለሁ።

አቶ ፍቃዱ፡- እኔም እጅግ በጣም አመሰግናለሁ።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You