«ማንኛውም ዜጋ ለቀጣዩ ትውልድ የማስረክበው ምንድን ነው ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት»-  የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ:- ማንኛውም ትውልድ ለቀጣዩ ትውልድ ምን የማስረክበው ጉዳይ አለ ብሎ ራሱን መጠየቅና መሥራት እንዳለበት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

«ኢትዮጵያ የትውልዶች ድምር» በሚል መሪ ሃሳብ የትውልድ ቀን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተከብሯል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እንደገለጹት፤ ማንኛውም ትውልድ ምን ሠርቼ ለቀጣዩ ትውልድ ምን ማስረከብ አለብኝ የሚለውን ራሱን መጠየቅ አለበት።

የአሁኑ ትውልድም ለቀጣዮቹ የኢትዮጵያ ተረካቢዎች ምን የማስተላልፈው ሥራ አከናውኛለሁ የሚለውን መጠየቅና ከትውልዱ የሚጠበቀውን ግዴታ መፈጸም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የምናደርጋቸው ክንውኖችና ውሳኔዎች የግለሰቦችን ወይም የቡድኖችን ፍላጎት ማሟላት ብቻ ሳይሆን ተተኪውን ትውልድ ያገናዘቡ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ የሚታየውን ያለፈውን ትውልድ  የመውቀስና የአሁኑ ትውልድ ደግሞ በአግባቡ ሳይሠራ የማሞገስ ዝንባሌ ሊፈተሽ ይገባል ሲሉም አመላክተዋል። ተጠያቂነቱን ሁሉ የቀድሞው ትውልድ ላይ ከመጣልና የአሁኑን ወጣት ያለአግባብ ከማወደስ ይልቅ ሚዛናዊነቱን የጠበቀ አካሄድን በመከተል የትውልድ ሽግግሩ ጥሩ መስመር እንዲይዝ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

መወቃቀስ ሳይሆን የመፍትሄ ሃሳብ ይዞ መምጣት ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ትውልዱን ሊያንጹ የሚችሉ ንባብና ምርምርን በማጠናከር ተደራጅቶ እንዲወያይ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ማንኛውም ሀገር የተገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ ነው፤ በትውልዶች መካከል የዕውቀትና የልምድ ልውውጥ ማድረግ የማይናቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

በትውልድ ቅብብሎሹ ወጣቶች ተደራጅተው የሚነጋገሩበት መድረክ መኖር እንዳለበት አመላክተው፤ አንድ ላይ መነጋገር የትውልዱን የማሰብ ኃይል እንደሚያጎለብተው አስገንዝበዋል። ዕውቀት ላይ የተመሠረተ አካሄድ ትውልዱ ሁሉንም አሜን ብሎ ሳይሆን አውቆ እንዲቀበል ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል።

መጪው ትውልድ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉት የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ፤ በትውልድ ቅብብሎሹ አዳዲስ የችግር መፍቻ መንገዶችን እንደየዘመኑ መጠቀም ቢገባም የታማኝነትን የጠንካራ ሠራተኝነትና የሀገር ፍቅር ስሜት ሊለወጡ የማይገባቸው ዕሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ የአሁኑ ትውልድ ከእኛ ትውልድ ተምሮ ሀገሩን መውደድ ዕሴቱ ማድረግ እንዲሁም ሃሳብና ማሰላሰል ላይ ማተኮር ይገባዋል ብለዋል።

በእኛ ዘመን በጠባብ ዕይታ ቢሆንም ንባብ ወሳኝ ጉዳይ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፤ የአሁኑ ትውልድ በማኅበራዊ ሚዲያ ጩኸት ዓለምን ማወቅ አይችልምና በሰፊ ዕይታ ማንበብና ጠንቅቆ የተማረ መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል። ወጣቱ ጭንቅላቱን መጠቀምና ሀገሩን በሥልጣኔ ጎዳና መምራት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የእኛ ዓላማም ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ማፍራት ነው። በዚህ ረገድ በትምህርት ዘርፉ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ጥረት እያደረግን ይገኛል ብለዋል። ትምህርት ቤቶች የትውልዱን ግብረገብነት የማሻሻል ኃላፊነት አለባቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ሲባል የግብረገብነት ትምህርት በስፋት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

መርሀ-ግብሩን የትምህርት ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የፍትሕ ሚነስቴር በጋራ አዘጋጅተውታል። በመድረኩ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ፣ አባት አርበኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገተኝተዋል።

ጌትነት ተስፋማርያም

 አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 6 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You