ሙያና ሙያተኛን ማገናኘት- የትውልድን መንገድ መጥረግ

በቱሪዝም ዘርፍ ላይ አተኩረው የሚሰሩ የትምህርት ተቋማት ተቀዳሚ ድርሻ ዘመኑ የሚጠይቀውን እውቀት ማስጨበጥ፣ በተግባርና በንድፈ ሃሳብ የተሻለ እውቀት እንዲኖር ማስቻል ነው። በተለይ ኢትዮጵያ ያላትን የመስህብ ሀብቶች ያማከለና መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ ሳይንሳዊ እውቀትን ለትውልዱ ማስታጠቅ የተቋማቱ ተቀዳሚ ተግባር ይሆናል። ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብቶችን፣ የመዳረሻ ልማቶችን፣ የገበያና የማስተዋወቅ ስልቶችን ሊያግዙ በሚችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው የሚሰሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከላይ ካነሳነው ተግባርና ኃላፊነታቸው በተጨማሪም የሚጠበቅባቸው ሌላም ግዴታ አለ። ይህም በስነ ምግባር የታነፁ፣ የአገልጋይነት ስሜትን የተላበሱ፣ የቱሪዝሙን መላ እንቅስቃሴና አገራዊ ግብ የሚረዱ ንቁ ትውልዶችን ከመፍጠር በተጓዳኝ፣ ተቋማቱ በእውቀትና በክህሎት የቀረፁትን የሰው ሃይል ተግባራዊ ስራ ላይ ከተሰማራው የኢንዱስትሪው አንቀሳቃሽ ጋር የሚያገናኝ ድልድይ መዘርጋትም አለባቸው።

ቱሪዝም ላይ መሰረት ያደረጉ እነዚህ የትምህርት ተቋማት ከላይ ያነሳናቸውን ኃላፊነቶች መወጣት ከቻሉ በኢትዮጵያ አምስት ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዋልታዎች መካከል አንዱ የሆነው የቱሪዝም ዘርፍ በብቃቱና በክህሎቱ በሚመሰገን አዲስ ትውልድ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ የራሳቸውን ዐሻራ ማኖር ይችላሉ። በባህሪው ሰፊ የሰው ሃይል የሚይዘውና ለስራ እድል ፈጠራ ጉልህ ድርሻ ያለው የቱሪዝም ዘርፍም አሁን ካለው በተሻለ አዲስ ወደ ኢንዱስትሪው የሚቀላቀሉ ባለሙያዎችን የሚያስተናግድ እንዲሆን ደግሞ የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

የዝግጅት ክፍላችን ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ምሳሌ ይሆናል ያለውን አንድ ተቋም “ከተቀመጡት መመዘኛዎች አንፃር ምን እየሰራ ነው? የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን አስተምሮ ካስመረቃቸው ተማሪዎች ጋር በምን መልኩ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ያመቻቻል?” የሚሉ ጉዳዮችንና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ሃሳቦችን ለማንሳት ወድዷል። ይህ ተቋም የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ሲሆን፣ ባሳለፍነው ሳምንትም የሆቴልና የሆስፒታሊቲ ዘርፉን በቱሪዝም ልዩ ልዩ ሙያዎች ካስመረቃቸው ተማሪዎች ጋር የሚያገናኝ መርሀ ግብር (job fair) አዘጋጅቶ ነበር። ያነጋገርናቸው በዚህ ዝግጀት ላይ የተገኙ ቀጣሪ ሆቴሎች፣ የትምህርት ተቋሙ አመራር እና ስራ ፈላጊዎች እንዳስታወቁት፤ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የሚሰሩ የትምህርት ተቋማት፣ ቀጣሪ ድርጅቶችና ምሩቃን የሚገናኙበት መድረክ መፈጠሩ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡

አቶ ይታሰብ ስዩም የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ መንግሥት ከግንቦት እስከ መስከረም የሚቆይ ክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራ ተግባራዊ ለማድረግ ልዩ የአምስት ወር እቅድ የሚያስተገብር ፕሮጀክት ነድፏል። ይህም በተለይ ለአዲሱ ትውልድ (ለወጣቶች) የስራ እድል መፍጠርን ግብ አድርጎ ያስቀመጠ ነው። እንደ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ይህ ሂደት በክህሎትና ብቃት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በልዩ ልዩ ሙያዎች ተምረው የተመረቁ ከተቋሙና ከተቋሙ ውጪ የመጡ ባለሙያዎችን ከቀጣሪዎች ጋር የሚያገናኝ መርሀ ግብር (job fair) ተዘጋጅቷል።

“ይህን መሰል ሙያና ሙያተኛውን የሚያገናኝ መርሀ ግብር ስናዘጋጅ ለሁለተኛ ጊዜ ነው” የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ የመጀመሪያው ሚያዚያ ላይ መካሄዱንና ውጤታማ ሆኖ መጠናቀቁን ይናገራሉ። ከሃምሳ በላይ የኢንዱስትሪው አንቀሳቃሾች ተገኝተው በርካታ ቁጥር ያላቸው ሙያተኞች በቀጥታ ቅጥር እንዲፈፅሙ አድርገዋል። ድርጅቶቹም ተገቢውን ሙያና ክህሎት ያዳበሩ የቱሪዝም ባለሙያዎችን አግኝተዋል። በሁለተኛው መርሀ ግብር ላይም ተመራቂዎች ከባለ አምስት ኮኮብ ሆቴሎች ጀምሮ በርካታ ሆቴሎች፣ ቱር ኦፕሬተርስ እና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጨምሮ ከአርባ እስከ ሃምሳ የሚደርሱ ተሳታፊ እንደሆኑ ይናገራሉ። እነዚህ ድርጅቶች በአማካኝ እስከ ሠላሳ የሚደርሱ ባለሙያዎችን ለመቅጠር እቅድ ይዘው በስፍራው መገኘታቸውን ይናገራሉ።

አቶ ይታሰብ ኢንስቲትዩቱ ሰፋ ያለ ተግባርና ኃላፊነት ከመንግሥት እንደተሰጠው ይገልፃሉ። የመጀመሪያው ስልጠና ሲሆን በሁለተኝነት ዘርፉን ለማሳደግ በሚደረግ ሂደት ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ እንዲሁም የማማከር አገልግሎት መስጠት ነው። ሌላው የሚያሰለጥናቸውን ተማሪዎች በዘርፉ ሙያዊ ክህሎታቸውን ተጠቅመው እንዲያገለግሉ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ይሳተፋል። ይህንን መሰረት በማድረግም “በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዴት መስጠት ይቻላል” በሚል ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይትና ምክክር በማድረግ ጭምር መፍትሄ አመላካች ጥናታዊ ውጤቶችን እንደሚያቀርብ ይገልፃሉ። ይህንን መሰሉ ሙያና ሙያተኛን የማገናኘት ተግባርም የዚሁ ጥረት ውጤት መሆኑን ይናገራሉ።

“በመላው ሀገሪቱ እስከ ሰባ የሚደርሱ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ የሚያሰለጥኑ የፖሊ ቴክኒክ ተቋማት አሉ” የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ብቁና በክህሎቱ ውጤታማ የሆነ ባለሙያ ለማፍራት ከእነዚህ አካላት ጋር እየተሰራና የአቅም ግንባታ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ይገልፃሉ። በዚህ ስልት መላው ሀገሪቱ ላይ ያሉ በቱሪዝም ሙያ መሰልጠን የሚፈልጉ ወጣቶች እድሉን እንዲያገኙ እየተመቻቸ መሆኑን ይናገራሉ። ሙያዊ ብቃት ሲይዙም ከኢንዱስትሪው ጋር ተገናኝተው ወደ ስራ የሚገቡበትን መርሀ ግብር እንደሚመቻች ነው የገለፁት።

በተለይ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲመሩ በማድረግ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይናገራሉ። አቶ ይታሰብ ስዩም እንደሚሉት፤ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በርካታ የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ነው። በተለይም የመዳረሻ ስፍራዎች በብቁ ባለሙያ መመራት በዘርፉ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር የሚያግዝ ነው፡፡ ይህም ዘርፉ ለሀገራዊ አጠቃላይ ምርት የሚኖረውን ሚና ከማሳደግ በዘለለ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ያለው ሚና የላቀ ነው። ከዚህ አንጻር ኢንስቲትዩቱም አጫጭርና ረጃጅም ሥልጠናዎች በመስጠት ለዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ሚናውን እየተወጣ እንደሚቀጥልም ነው የሚገልጹት።

 በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ የሚገኘው የዘ-ሀብ ሆቴል ተወካይ የሆነችውና በስራ ቅጥር መርሀ ግብሩ (job fair) ላይ ባለሙያዎችን በመመልመል ላይ የተሳተፈችው ሃና ተገኝ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳለችው፤ ሆቴሉ በሆስፒታሊቲ ዘርፍ ላይ ሙያዊ ብቃት ያላቸው አዳዲስ ምሩቃንን ለመቅጠር የመርሀ ግብሩ ተሳታፊ ሆኗል። የበርካታ ልዩ ልዩ ሙያ ያላቸው ምሩቃንን ግለ ታሪክና መረጃም መሰብሰብ ችላለች፤ መረጃውን መሰረት በማድረግ ቅጥር የሚፈጸምም ይሆናል።

“ይህን መሰል መርሀ ግብር ሙያና ሙያተኛውን በቀጥታ የሚያገናኝ በመሆኑ መልካም አጋጣሚ ነው” የምትለው ወጣት ሃና፣ በተለይ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ተምረው የት መቀጠር እንዳለባቸው ለቸገራቸው ወጣቶች ትልቅ እድል መሆኑን ትናገራለች። የእነርሱ ኢንተርናሽናል ሆቴልም እንግዶችን በሥነ ምግባር እና በአገልጋይነት ስሜት የሚቀበል ባለሙያ ለማግኘት የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ የከፈተው አጋጣሚም ተጠቃሚ እንዳረጋቸው ገልፃለች።

ወጣት ስሜነህ አለማየሁ በአፍሪካ ህብረት አካባቢ የሚገኘው ባለ አራት ኮከቡ ኪንግስ ሆቴል ስራ አስኪያጅ ነው። ኢንስቲትዩቱ ባዘጋጀው የአዳዲስ ተመራቂዎች የስራ ቅጥር መርሀ ግብር ላይ ባለሙያዎችን ለመመልመል መምጣቱን ይገልፃል። በተለይ በሆስፒታሊቲ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ የሰራተኛ ፍልሰት መኖሩን ጠቅሶ፤ ይህን መሰል ሙያና ሙያተኛን የሚያገናኝ መድረክ መፈጠሩ የሚፈጠረውን ክፍተት በቶሎ ለመሙላት እንደሚያስችል ይናገራል።

“ከዚህ ቀደም ከትምህርት ተቋማት ጋር ተናበን ለመስራት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም ነበር። የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ ግን ይህን ክፍተት ደፍኖልናል” የሚለው የኪንግስ ሆቴል ስራ አስኪያጅ፤ ሰልጣኞቹ ከመመረቃቸው በፊት የተግባር ልምምድ ሲያደርጉ፣ ጥናታዊ ፅሁፍ ሲያዘጋጁ ጭምር ከተቋሙ ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ ይናገራል። ይህ መልካም ግንኙነት በስራ ቅጥር መርሀ ግብሩም የቀጠለ መሆኑን ገልፆ፤ ለአሰሪውም ሆነ ለሰራተኛው መሰል መድረኮች መዘጋጀቱ የሚበረታታ እንደሆነ ይናገራል።

ወጣት ሙሉቀን አዲሴ በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የዘንድሮ ተመራቂ ነው። ተቋሙ ባዘጋጀው የስራ እድል የሚፈጥር መርሀ ግብር ላይ በሙያው ለመመዝገብ እንደመጣ ይናገራል፡፡ የቱር ጋይድ ሙያን በሌቭል ሶስት ተምሮ ያጠናቀቀ ቢሆንም በልዩ ልዩ ምክንያት የማስጎብኘት ስራው መቀዛቀዙን ይናገራል፤ በዚህ የተነሳም ወደ ሆቴል ዘርፍ (በሆስፒታሊቲው) ስራ ለመግባት ማሰቡን ይገልፃል። ለዚህ የሚሆኑ ተያያዥ ስልጠናዎችንም በትምህርት ቆይታው ወቅት ማግኘቱን ጠቅሶ፤ በመርሀ ግብሩ ላይ በተገኙ ቀጣሪ ድርጅቶች ማስረጃዎቹን ማስገባቱንና መመዝገቡን ይናገራል።

“የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በቂ እውቀትና ሙያዊ ስልጠና ሰጥቶናል። አሁን ደግሞ የስራ እድል አመቻችቶልን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ፊት ለፊት እንድንገናኝ እያገዘን ነው” የሚለው ወጣት ሙሉቀን፤ ይህንን መሰል አጋጣሚ መፈጠሩ ከእንግልት እንደሚታደጋቸው ይገልፃል። ድርጅቶቹም ባለሙያዎችን ከትክክለኛው የትምህርት ተቋማት ስለሚያገኙ ግንኙነቱና ጥቅሙ የጋራ መሆኑን ይናገራል።

ወጣት ቤተልሄም ሀብታሙ በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በሆቴል ማኔጅመንት የዘንድሮ ተመራቂ ነች። የስራ ቅጥርን ለአዳዲስ ምሩቃን ለማመቻቸት በተዘጋጀው መርሀ ግብር ላይ ተሳታፊ እንደሆነች ትናገራለች። መድረኩ በሙያዋ ወደ ስራው ዓለም ለመግባት የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረላት አንስታ፤ በዝግጅቱ ላይ ከተገኙት ባለ አራትና አምስት ኮኮብ ሆቴሎች ጋር የሚያስፈልገውን መስፈርት አሟልታ እንዳመለከተች ትገልፃለች።

“ኢንስቲትዩቱ አስተምሮ ከማስመረቅ ባለፈ ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ይህን መሰል መርሀ ግብር ስላዘጋጀልን ደስተኞች ነን” የምትለው ወጣት ቤተልሄም፤ እድሉን ተጠቅማ የምትወደው ሙያ ውስጥ በመሰማራት የቱሪዝምና የሆስፒታሊቲ ዘርፉን ለመደገፍ መቻሏ እንደሚያስደስታት ነው የተናገረችው። ይህንን መሰል መርሀ ግብር ሁሉም መሰል ተቋማት ሊያዘጋጁት እንደሚገባ ገልፃ፤ ይህንን ማድረግ ሲቻል ሙያና ሙያተኛውን ያለምንም ችግር ማገናኘትና የቱሪዝም ዘርፉን ማሳደግ ያስችላል የሚል አስተያየት ሰጥታለች።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትም በጥናት ላይ የተመሰረተ የመፍትሄ አቅጣጫ እያቀረበ ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የኮይሻ፣ ጎርጎራና ወንጪ ፕሮጀክቶች የሚፈጥሩትን የሥራ እድል ታሳቢ ያደረገ የሰለጠነ የሰው ኃይል ከወዲሁ የማዘጋጀት ሥራ እየተሰራ ነው። በመጪው የትምህርት ዘመን በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ የሚያስፈልጉ ተጨማሪ የትምህርት ዘርፎችን በመለየት ጭምር ሥልጠና ለመስጠት መዘጋጀቱን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል። ማሰልጠኛው አሁን ላይ ወደ ሁለት ሺ ለሚጠጉ ተማሪዎች በቀንና በማታ መርሀ ግብር ሥልጠና እየሰጠ መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን     ጳጉሜን  5 ቀን  2015 ዓ.ም

Recommended For You