አምራች መሆን እንዴት ይቻላል?

አምራችነት ትርጉሙ ፈርጀ ብዙ ነው። በኢኮኖሚው ዘርፍ ብቻ የሚገለፅ አይደለም። በርግጥ ስለአምራችነት ሲወራ በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ መገለጫዎቹ አብረው ይነሳሉ። የአምራችነት ፅንሰ ሃሳብ በአብዛኛው የሚመነጨውም ከዚሁ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ነው። ሆኖም አምራችነት ከኢኮኖሚ ውጭ በሌላ አቅጣጫም ሊታይ ይችላል። ለምሳሌ ሙዚቃና ፊልም አንዱ የአምራችነት ዘርፍ ነው።

ወደ ኢኮኖሚ ዘርፍ ሲመጣ ደግሞ ለቁጥር የሚታክቱ የአምራች አይነቶችን መጥቀስ ይቻላል። ከነዚህ ውስጥ በዋናነት የግብርና ምርት አምራቾች፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶች አምራቾች እንዲሁም የፋብሪካ ምርቶች አምራቾች ይገኙበታል። ኢትዮጵያም በአብዛኛው ኢኮኖሚዋ በግብርና ላይ የተንጠለጠለ እንደመሆኑ የግብርና ምርት አምራቾች በብዛት የሚገኙባት ሀገር ናት። የፋብሪካ ምርት አምራቾች ደግሞ ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛሉ።

መቼም ስለአምራችነት ሲነሳ በተደጋጋሚ ‹‹አምራች ዜጋ ለማፍራት›› እየተባለ ለረጅም ጊዜ በመንግሥት ሲነገር ያልሰማ የለም። ይህ የተባለው ያለ ምክንያት አይደለም። ዜጎች በእውቀት ከበለፀጉ በሁለንተናዊ መልኩ አምራች መሆን ስለሚችሉና ሀገራቸውን የመለወጥ አቅም ስለሚኖራቸው ነው። ዜጎች በክህሎት ከደረጁ ከራሳቸው አልፈው ለሀገራቸውም ጭምር መትረፍ ስለሚችሉ ነው። ስለዚህ አምራች ዜጋ ለመሆን እውቀትና ክህሎት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም።

የሆነው ሆኖ አምራችነት የግለሰብ፣ የህብረተሰብ፣ የማህበረሰብና የሀገርን ኢኮኖሚ እንደሚያሳድግ ከግምት ውስጥ በማስገባት ቀን ተሰይሞለት ዛሬ ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም ‹‹የአምራችነት ቀን›› ሆኖ ይዘከራል። ቀኑን መዘከር ብቻ ግን ፋይዳ የለውም። ሁሉም ዜጎች በየተሰማሩበት የሥራ መስክ አምራች እንዲሆኑ ይጠበቃል። ያኔ ነው ግለሰብ፣ ህብረተሰብ፣ ማህበረሰብና ሀገር የሚለወጠው። ለመሆኑ እርስዎ በተሰማሩበት የሥራ መስክ አዲስ ሥራ ጀምረው እንዴት አምራች መሆን ይችላሉ?

1ኛ. ሌሎች ሲስገበገቡና ሲሯሯጡ እርስዎ ይፍሩ። ሌሎች ሲፈሩ እርስዎ ይድፈሩ

በተለይ ወጣቶች ከማንኛውም ሰው በቁም ነገር ሊወስዱት የሚገባው ምክር ልዩ መሆኑን ነው። ሰዎች እንደ ትክክለኛ አመለካከት የተቀበሉትን ነገር መቃወም አለባቸው። ሌሎች ሰዎች የሚያደርጉትን በመመልከት ከእነርሱ በተቃራኒ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህንን ማድረግ ታዲያ ለምን አስፈለገ? በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች እያሰቡ ስላልሆነ ሁሉም ሰው ከሚያደርገው ነገር በተቃራኒ ማድረግ የግድ ስለሚል ነው። በዓለም ላይ ያሉ በርካታ ሰዎች አዕምራቸውን ለመጠቀም ይቸገራሉ። ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ የሚያደርጉት ነገር በማህበረሰቡ ዘንድ ማረጋገጫ የተሰጠውን ነገር ብቻ ነው። ይህም ስህተት ላይ ይጥላቸዋል።

ለምሳሌ ብዙ ሰዎች የአክሲዮን ዋጋ ሲያሻቅብ ብቻ ነው በአክሲዮኖች ላይ ገንዘባቸውን የሚያፈሱት። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ብልጥ ግለሰቦች የዛን ጊዜ ነው አክሲዮናቸውን የሚሸጡት። ሕዝቡ ለመግዛት ሲስገበገብ እነርሱ ይሸጣሉ። ሕዝቡ ለመሸጥ ሲረባረብ ደግሞ እነርሱ ይገዛሉ። ስለዚህ የተለመደው ዓይነት ሰው ከሆኑ ስኬታማ መሆን አይችሉም። ስለዚህ ከሌሎች ሰዎች ተቃራኒና ለየት ያሉ ይሁኑ። ሰው የሚያደርገውን ነገር ይመልከቱ ከዛም ከሁሉም ሰው በተቃራኒ ያድርጉ። ነገሮችን በተለየ መንገድ ለማየት ይሞክሩ፡፡

2ኛ.ትዕግስት ይኑርዎ

ምንም ዓይነት ችሎታና እውቀት ቢኖርዎ ወይም የፈለገ ጥረት ቢያደርጉ አምራችና ስኬታማ ለመሆን ትዕግስት ያስፈልግዎታል። ጊዜም ይወስድብዎታል። በዓለማችን ላይ ያሉ አብዛኛዎቹ ሰዎች ድሆችና ያልተሳካላቸው ቁጥር አንድ ምክንያት ምን ይመስልዎታል? አስቸጋሪ ጊዚያትን በትዕግስትና በፅናት ማለፍ ባለመቻላቸው ነው። እርስዎም ታጋሽ መሆን አለብዎት። ያለበለዚያ ወደ ስኬትና ምርታማነት የሚወስደውን አስቸጋሪና ረቂቅ መንገድ ማለፍ አይችሉም። ታላላቅ ነገሮች ጊዜ ይወስዳሉ። ለውጦች ጊዜ ይፈጃሉ።

3ኛ. ከእርስዎ ከተሻሉ ሰዎች ጋር ይወዳጁ

ከእርስዎ ባህሪ የተሻለ ባህሪ ያላቸው ሰዎችን ወይም ጓደኛዎን ይምረጡና የእነርሱን ባህሪ ይላበሱ። ወጣቶች ከሌሎች ሰዎች በበለጠ የሚያደርጉት አንድ ነገር ከሌላው ጋር ግንኙነት መመስረት ነው። እንዳለመታደል ሆኖ ግን አብዛኛዎቹ ወጣቶች ጓደኛ አመራረጥ አያውቁበትም። ከማን ጋር መቆራኘትና ከማን ጋር መኖር እንዳለባቸው አይገነዘቡም።

ስለዚህ እዚህ ጋር ቆም ይበሉና አብዛኛውን ጊዜ ከማን ጋር እንደሚያሳልፉ ያስቡ። ሁልጊዜ አብረዎት የሚውሉ አምስት ሰዎችን ስም ዝርዝር ይፃፉ። አብዛኛውን ከእርስዎ ጋር የሚያሳልፉትን እነዚህን አምስት ሰዎች የዛሬ አምስት ዓመት የት ሊደርሱና ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ በዓይነ ህሊናዎ ይሳሉ። በሚያሳዝን ሁኔታ እርስዎም የእነርሱ እጣ ፋንታ ነው የሚደርስዎ ማለት ነው። ስለዚህ የእርስዎ ማንነት የሚወሰነው በጓኞችዎ ነው።

ይህን እውነታ ለማረጋገጥ በጣም ቀላል ነው። ወዳጆችዎ ለለውጥ የማይተጉና ስለሕይወት አወንታዊ አመለካከት ከሌላቸው እርስዎ ለለውጥ ፍላጎት ያለዎትና ስለሕይወት አወንታዊ አመለካከት ያለዎ ሊሆኑ አይችሉም። ጓደኞችዎ ከእርስዎ የበለጠ የማያውቁ ከሆኑ እርስዎም ቢሆኑ ከእነርሱ የተሻሉ አዋቂ ሊሆኑ አይችሉም። ስለዚህ አሉታዊ ከሆኑና ምንም ለለውጥ ተነሳሽነት ከሌላቸው ጋር ያለዎን ግንኙነት ያቁሙ። ጓደኞችዎን በጥንቃቄ ይምረጡ። ጓደኛ ካጡ ብቸኝነትዎን ይምረጡ።

4ኛ. ሰዎች እንደጎተትዎ አይሂዱ

አይሆንም! ካላሉ በስተቀር ጊዜዎን ሊቆጣጠሩ አይችሉም። ሌሎች ሰዎች በሕይወትዎ ምን ማድረግ እንዳለብዎና የሕይወት ግብዎ ምን መምሰል እንዳለበት ሊነግርዎት አይገባም። የቦታው ምን ይታይዎታል? የሚያሳንፉና የሚያታልሉ ነገሮች ናቸው አይደል! ማህበራዊ ሚዲያ፣ ቴሌቪዥን፣ ፊልም፣ ጭፈራ፣ ድግስ፣ ዝግጅት፣ ትርኢት….. ወዘተ ሁሉ በጣም የሚያማልሉና የሚዘናጉ ግን ደግሞ ምንም ጥቅም የሌላቸው ነገሮች ናቸው። ስለዚህ ሰው እንደጎተተዎና እንደሳበዎ አይሂዱ። አይሆንም! ፣እምቢ! ፣ ሥራ አለኝ!፣ አይመቸኝም ማለትን ይልመዱ። አብዝተው እንዲህ ባሉ ቁጥር የሚያሳንፉና ከእቅድ የሚያስተጓጉሉ ነገሮች ይቀንሳሉ። በዚህም አብዛኛውን ጊዜዎን በሚጠቅሙ ነገሮች ላይ ማሳለፍ ይችላሉ።

5ኛ. ያለዎት አእምሮ በቂ ነው፤ ከእርስዎ የሚጠበቀው መመሪያ ማክበር ብቻ ነው

ከሌሎች የበለጠ ብልጥ አዋቂና አስተዋይ መሆን አይጠበቅብዎትም። ነገር ግን ከሌሎች የበለጠ ሥነ- ሥርዓት ያለዎ ሊሆኑ ይገባል። ስለተሰጥኦ እና ስለሚወራው ‹‹የአይ ኪው›› ጉዳይ ይርሱት። ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች እንደገበታ ጨው በየቦታው ሞልተዋል። የ200 አይ ኪው ውጤት ያላቸው መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደሃ ቤሳ ቢስቲ ሳንቲም የላቸውም።

ስኬታማና ምርታማ ለመሆን የሚያስፈልጉ ነገሮች በዲስፕሊንና በመርህ መመራት አለባቸው። እርስዎም በዚህ መንገድ መለማመድ፤ ያገኙትን እውቀት ተግባራዊ ማድረግ፣ ራስዎን ለአንድ ነገር ብቻ መስጠትና ፅናት እንዲኖርዎ ያስፈልጋል። ስለዚህ የሚያስፈልግዎ ተጨማሪ ‹‹አይ ኪው›› ሳይሆን ያለዎትን ‹‹አይ ኪው›› በወጉ መጠቀም ነው። ያለዎን ‹‹አይ ኪው›› በወጉ ከተጠቀሙበት ይበቃዎታል።

6ኛ. አደጋ ላይ የሚጥልዎ አለማወቅዎ ነው

በአብዛኛው አደጋ የሚያጋጥምዎ የሚሰሩትን ሥራ በሚገባ ባለማወቅዎ ነው። ለምሳሌ የራሳቸውን ንግድ ለመጀመር ከሚያስቡ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ስለ ንግድ ሥራና በአጠቃላይ በንግዱ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መቶ መጻሕፍትን ይቅርና አስር መጻሕፍትን ለማንበብና ለማጥናት ጊዜያቸውን መሰዋዕት አይፈልጉም። በርካቶች ንግድ መጀመርና ገንዘቡን አንድ ነገር ላይ ኢንቨስት ማድረግ ትልቅ ኃላፊነት እንደሚጠይቅ እያወቁ መጻሕፍትን አያነቡም፤ መረጃም አይሰበስቡም። ትልቁ አደጋ ድንቁርናና አለማወቅ ነው። እርስዎም ስለአንድ የሥራ ዘርፍ ይበልጥ ባነበቡና ባወቁ ቁጥር አደጋውን መቀነስ ይችላሉ። ስለዚህ እውቀትን ይፈልጉ።

7ኛ. ከሱስ ይራቁ

መጥፎ ልማድና ሱስ ሲጀምሩት ቀላል ነው። ከዳበረ በኋላ ግን ከዛ ሱስ ለመውጣትና ለመገላገል እጅግ አስቸጋሪ ነው። የሱስ እስረኛ አላዩም በመንገድ ላይ ሲንገዋለል ከገባበት ሱስ ለመውጣት አቅቶት መጥቶ የሚገላግለው ሰው እየፈለገ? በሕይወትዎ ሊያደርጉት የሚችሉት በጣም ምርጡ ነገር መጥፎ ሱሶችን ባጠቃላይ መራቅ ነው። ወደሱስ ውስጥ ሲገቡ ሞክሬው ቶሎ እወጣለሁ ብለው አስበው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሱስ ልክ በእሳት እንደመጫወት ነው። ባሪያው ያደርግዎታል። ስለዚህ ከሱስ ይራቁ፤ ለሱስ ቦታ አይስጡ።

8ኛ.የሚወዱትን ስራ ይስሩ

በጋሉፕ ጥናት መሰረት 85 ከመቶ የሚሆኑት የዓለማችን ሰዎች የሚሰሩትን ሥራ አይወዱትም። ሥራ በመሥራትና ለመሥራት በማቀድ 50 ከመቶ የሕይወት ጊዜዎን ማባከንዎ ካልቀረ የሚያስደስትዎን ሥራ መርጠው ቢሰሩ ይሻላል። ምንአልባት የሚወዱትን ሥራ ፈልጎ ማግኘት ሊከብድዎና ተስፋም ሊያስቆርጥዎ ይችላል። ነገር ግን የሚከፈለውን ሁሉ ዋጋ ለመክፈልና በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ውስጥ ለማለፍ ፍቃደኛ ከሆኑ ደስተኛና ትርፋማ የሚያደርግዎን ሥራ መፍጠር ወይም ማግኘት ይችላሉ።

9ኛ. ነገሮች በተወደዱበት ጊዜ ግዢ አይፈፅሙ

ነገሮች በተወደዱበት ወቅት ታዋቂና ውድ የሆኑ ነገሮችን መግዛት አያዋጣም። ብዙ ሰዎች አክሲዮን መግዛት የሚፈልጉት ሁሉም ሰው ቀልቡን በአክሲዮን ላይ በጣለበት ጊዜ ነው። አክሲዮን የመፈለጊያው ጊዜ ግን አክሲዮን ፈላጊ በጠፋበት ጊዜ ነው። ስለዚህ ታዋቂና ውድ የሆነን ነገር መግዛት አያዋጣም። ይህ ነጥብም ከመጀመሪያው ጋር ይያያዛል፡፡

አዩ! ማንኛውም ነገር በተወደደበት ጊዜ ሁሉ ጨዋታው አለቀ ማለት ነው። በተለይ በንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ። ብዙ ሰዎች እውቀት ሳይኖራቸው ገንዘባቸውን ዝም ብለው ኢንቨስት ያደርጋሉ። አንድ ነገር ሲረክስ ሳይሆን ሲወደድ ነው የሚገዙት። ይህም ሁሉም ሰው በሚገዛበት ወቅት ነው የሚገዙት ማለት ነው። ሁሉም ሰው በሚሸጥበት ጊዜ ደግሞ ይሸጣሉ። ስለዚህ በተቃራኒው ሁሉም ሰው በሚገዛበት ጊዜ እርስዎ ይሽጡ፤ ሁሉም ሰው በሚሸጥበት ጊዜ እርስዎ ይግዙ። በጫጫታ አይታለሉ። እትራፊውና ትክክለኛው ነገር በሚስጥር የተያዘ ነው። በቶሎ ገሃድ አይወጣም።

ታዲያ ሰው ያላየውን ምርጥ አጋጣሚ እንዴት ላይ እችላለሁ? ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ። ሰው ያላየውን መጽሐፍ ያንብቡ። ሰው ያልሰማውን ትምህርት ይማሩ። ሰው ያላየውን ቪዲዮ ይመልከቱ። ሁሉም ሰው ለመዝናናት ሲሯሯጥ እርስዎ ለእውቀት ፍለጋ ይሯሯጡ። ሰዎች የማያውቁትን ነገር እርስዎ ካወቁ መልካም እድሎችን ሰዎች ቀድመው ሳያዩዋቸው እርስዎ ቀድመው ያዩዋቸዋል።

10ኛ. በማያውቁት የንግድ ዘርፍ ላይ ገንዘብዎን አያፍሱ

የጠቅላላ እውቀት ባለቤት ለመሆን አይሞክሩ። ነገር ግን በአንድ ነገር ላይ ልዩ ባለሙያ ይሁኑ። የሚፈልጉትን አንድ ወይም በጣም የተወሰኑ ዘርፎችን ይምረጡ። ስለዛ ዘርፍ ሰው የማያውቀውን በየእለቱ ያጥኑ። ሆኖም ለሌላ ለማያውቁት ነገር በፍፁም በር አይክፈቱ። ጊዜዎንና ትኩረትዎን ሙሉ በሙሉ ማድረግ ያለብዎ በአንድ ነገር ላይ ብቻ ነው። ስለ ቢዝነስ ለማወቅ መጽሐፍ ማንበብና ማጥናት ካልፈጉ ገንዘብዎን በከንቱ ባያባክኑ ይሻላል። ምክንያቱም የዛን ዓይነት ሥራ ሁሉም ሰው ይሰራዋል።

ለምሳሌ ስለ ‹‹ክሪፕቶ ከረንሲ›› ወይም ‹‹ቢት ኮይን›› ለማጥናት ጊዜ መሰዋዕት ካልቻሉ፣ መጻሕፍቶችን ካላነበቡ፣ በርካታ ቪዲዮዎችን ካልተመለከቱ በዚህ ላይ ገንዘብዎን ባያፈሱ ይመከራል። ምክንያቱም አብዛኛው ሰው ስለ እንደዚህ ዓይነቱ ቢዝነስ ምንም ሳያጠናና ሳያውቅ ነው ገንዘቡን ኢንቨስት እያደረገ የሚከስረው። ስለ አክሲዮን አስር ጥሩ ጥሩ መጻሕፍትን ለማንበብ ጊዜ መውሰድ ካልቻሉ በአክሲዮን ገበያ ኢንቨስት አያድርጉ። ስለ ሪል እስቴት ቢያንስ አምስት ጥሩ መጻሕፍቶችን ሳያነቡ ወደዚህ ቢዝነስ አይግቡ፤ ገንዘብዎንም በከንቱ አያፍሱ። ገንዘብዎን ማውጣት ያለብዎ ለሚያውቁት የሥራ ዘርፍ ብቻ ነው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን    ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You