በጎነት የነፍስ ወለባ

ብቻውን ሲሆን ወደተወው ትላንትና ነው የሚሄደው። በሀሳብ ሽምጥ ይጋልባል። ያደገው ከአባቱ ጋር ነው..እንደዛች መቀነቷን ፈታ ያላትን አንድ ሳንቲም እንደጣለችው ድሃ እመበለት ካለው ላይ እየቆረሰ ከሚሰጥ አባቱ ጋር። ሕይወት ማለት ለሌሎች መኖር ነው፣ ካለ ላይ ማካፈል ነው እየተባለ ነው ያደገው። በአባቱ እውነት ውስጥ ዛሬም ድረስ ሰው ነው።

ብቻውን የኖረው ሕይወት የለም። ከሌለው ላይ እየሰጠ በብዙኃን ምርቃት ሰው የሆነ ነው። በዓልን በደስታ የሚያሳልፍበት የሞላና የተረፈ ጥሪት ባይኖረውም ካለው ላይ ግን ያካፍላል። የማለዳዋን ልጃገረድ ጀምበር ተከትሎ ከቤት ወጣ። የበዓልን መድረስ የሚያበስሩ ለምለም እፅዋቶች፣ አደይ የለበሰው ቀዬ እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ ሲሉ ከደጅ ተቀበሉት። ወደ ጎረቤቱ ወደ እማማ አበዛሽ ቤት ጎራ አለ። ግቢው ዝምታ ወርሶት ነፍስ ያለበት አይመስልም። ድህነት የድባቴ በትሩን አሳርፎበት በዝምታ አሸልቧል..ግቢው። ወደ ደሳሳ ጎጇቸው አቅንቶ ‹እማማ አበዛሽ? ሲል ተጣራ።

እማማ አበዛሽ ወደ ውጭ አሻቅበው እያዩ። ‹ግባ የኔ ልጅ! ሲሉ ወደ ውስጥ ጋበዙት።

ሞገስ ካገጠጠው የጣሪያው ወራጅ መላጣውን እየተከላከለ የእንብርክክ ያክል አጎንብሶ ወደ ቤት ገባ። ‹እንዴት ሰነበቱ እማማ አበዛሽ? ሲል እጃቸውን በሁለት እጆቹ ጨብጦ ሳማቸው።

እንዲቀመጥ ወደ ዱካ እያመላከቱት ‹አስታዋሼ! አንተ ባትኖር የአሞራ ራት ነበርኩ። እግዚአብሔር ይባርክህ› ሲሉ ለምን እንደመጣ ሳያውቁ መረቁት።

‹በዓል አይደል ልጠይቆት ብዬ ነው› ሲል በዝምታ ተሰደደ። ቤታቸውን ቃኘው። ከአንዲት ፍራሽ እና ከተቀመጠባት በርጩማ ሌላ ምንም አልነበረም። እንደ ከሳ ገላ ከመራቆቱ በላይ የግድግዳው ጭቃ ረግፎ የውጭውን ብርሃን ያሳያል። በሃሳቡ ከአዲስ ዓመት በኋላ የእነዚህን እናት ቤት ማደስ እንደሆነ ሲያሰላስል ነበር። ምንም የሌለው ሰው ነው። ኖሮትና ተርፎት አያውቅም። ግን ሰውነት ካለ ላይ ማካፈል እንደሆነ ስለገባው ይሰጣል። እጁን ሰዶ ለበዓል መዋያ የሚሆኑ የብር ኖቶችን መዞ በማውጣት ‹የበዓል ቀን መጥቼ እጠይቆታለሁ፣ እስከዛው ግን የሚያስፈልጎትን አንዳንድ ነገሮች በዚህ ይሸምቱ ሲል› የአምስት መቶ ብር ኖት እጃቸው ላይ አስጨበጣቸው።

እጁን አንቀው ይዘው ‹እግዚአብሔር ይስጥህ። አትጣ..አትንጣ። አስታውሰህኛልና ፈጣሪ ብድርህን ይመልሰው። እድሜ ይስጥህ። ተባረክ። ጧሪ ቀባሪ አያሳጣህ› ሲሉ አይበሉባውን ሳሙት።

‹ምንም አይደል እማማ። ሰጪ እግዚአብሔር ነው። መጥቼ እጠይቆታለሁ ሰላም ይዋሉ› ብሎ ወጣ። ከጎን አጥር ወደ ሌለው አንድ ግቢ ሰተት አለ። ጋሽ ፈይሳ ሱሪያቸውን እስከ ጭናቸው ገልበው ሁሌ የሚቀመጡባት ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው አቀርቅረው ገመድ ሲገምዱ በር ላይ አያቸው። ሁሌ ወደ እሳቸው ሲሄድ በሥራ ተጠምደው ነው የሚያገኛቸው። ገመድ ይገምዳሉ፣ ዳንቴል ይሰራሉ፣ የተቀደደ ይጥፋሉ። እንዳያስደነብራቸው ሰግቶ ይሆን እንጃ ጉሮሮውን አጸዳ። ጋሽ ፈይሳ ቀና ሲሉ ሞገስን ፊት ለፊት ወደ እሳቸው ሲመጣ አዩት። እርጅና ያላሸነፈው የሰላ ጆሮ ከበረታ ዓይን ጋር አላቸው። ገና እንዳዩት ፊታቸው እንደ ምስራቅ አናት ጣይ መሰለ። በዚህ ሰው ሁሌ እንደተባረኩ ነው። ሳይጠይቃቸው እና ጎደሏቸውን ሳይሞላ ቀርቶ አያውቅም።

የሚገምዱትን ገመድ ወደጎን ብለው ከተቀመጡበት ሊነሱ ሲሉ ‹አይነሱ ጋሽ ፈይሳ› ሲል በተቀመጡበት አቀፋቸው። ግራና ቀኝ ትከሻውን ሳሙት። ‹እንዴት ሰነበቱ? የበዓል ዋዜማ እንዴት ነው? ሲል አጠገባቸው ካለ ግንድ ላይ አረፍ እያለ ጠየቃቸው።

በእጃቸው ታፋቸው ላይ የተሰበሰበ ቦላሌአቸውን እያጠበቁ ‹ተመስጌን ነው› ብቻ ብለው ዝም አሉ። ነፍሳቸው ግን ወደሆነ ቦታ ስትሰደድ ነበር። ምን ለሌለው ድሃ ይሄን ዓይነቱ ጥያቄ ምን ያክል አሳማሚ እንደሆነ አልጠፋውም። በእሳቸው ፊትም ላይ ያስተዋለው ይሄን ነበር። ገጻቸው እልፍ ባዶነታቸውን፣ እልፍ ማጣታቸውን እኔ ማለት ይሄን ነኝ ሲል አሳየው። አንጀቱ ተላወሰ። በድህነት ላይ ጥርሱን ነከሰበት። እሱ እያለ ማንም እንዲያዝን አይፈልግም። አባቱ ኖሮ ያለፈው ለሰው ነው። እሱም ለሰው ኖሮ ማለፍ እና ሰማይ ቤት እግዜርን ሲያገኘው ‹ከሕግ ሁሉ ትልቁን ፈጽሜ ወደአንተ መጥቻለሁ› ሲል ይነግረዋል። ያኔ እግዜር ፈገግ እያለ እኔም ላንተ የሚሆን ሁነኛ ስፍራ ሳሰናዳ ነበር። ‹ና ተከተለኝ የዘላለም መኖሪያህ ከእኔ ጋር እና ከመላእክት ጋር ነው› ብሎ በብርሃናማ እጁ ጨብጦት ወደነአብርሃም እና ይስሀቅ ጋ ሲወስደው ይታሰበዋል።

ገርበብ ባለው በር ወደ ውስጥ አጮለቀ። ምንም ነገር አልታይህ አለው። ድህነት የተዘባነነበት ቤት፣ ማጣት የተጀነነበት ወለል ተቀበለው። ከአዲስ ዓመት እቅዱ መካከል የእማማ አበዛሽን ጨምሮ የነዚህን አዛውንት ቤት እና የሰፈሩን ድሆች ቤት ማደስ እንደሆነ ለማሰብ ጊዜ አልወሰደበትም።

ዓይኑን መልሶ ወደገጻቸው ሰደደ..አሁንም ድረስ ከሱሪያቸው ጋ እየተጫወቱ ነው። ‹ምንም አያስቡ አባቴ። እንደለመድነው በዓልን አብረን እናሳልፋለን› ሲል ወደኪሱ ገባባ። የእማማ አበዛሽን ያክል ገንዘብ ይዞ ተመለሰ። ‹የበዓል ቀን ደስ ብሎን እንውላለን። እስከዛው ግን አንዳንድ ነገሮችን በዚህ ይግዙ› ሲል ከመቀመጫው ተነስቶ ሰጣቸው።

ጋሽ ፈይሳ የምርቃት ጎርፍ አዘነቡለት። ‹እርጥብ ሁን። ደስታ እንደሆንከኝ እግዚአሄር ደስታ ይሁንህ። መላዕክቱ ከፊትና ከኋላ ሆነው ከክፉ ነገር ይጋርዱህ። ብድርህን እሱ የማያልቅበት ይመልሰው› ሲሉ ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ መረቁት።

ተሰናብቷቸው ወጣ። ወደሚቀጥለው ጎረቤቱ አመራ። ኪሱ እስኪራቆት ያለውን ሁሉ ሰጠ። ፈጣሪ በሚያውቀው የተረፈው አንዳች የለም። በዓልን እንዴት እና በምን እንደሚያሳልፍ አያውቅም። ከእሱ ለሚበልጡ ነፍሶች ያለውን ሰጥቶ ባዶ እጁን ቤቱ ተመለሰ። ግን መስጠት መክበር አይደል? ተርቦ እንደማያድር ያውቀዋል። የሰፈሩ ድሆች ጋ ሄዶ አብሯቸው ያሳልፋል።

የሰው ልጅ ያልገባው ቢገባውም ያልኖረው አንድ ታላቅ ጥበብ በጎነት ነው። እግዜር ራሱን ከሰው ልጆች ጋር ያያያዘበት መርፌና ክሩ መልካምነት ነው። ‹የሚወደኝ ቢኖር ትዕዛዜን ይጠብቅ› ሲል እና ‹ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማል እርሱም ባልንጀራችሁን እንደራሳችሁ ውደዱ› ብሎ ሲናገር ራሱን ከእኛ ጋር እያስተሳሰረ እንደሆነ ቢገባን ድሃ የሚባል ባልኖረ ነበር ብሎ ሲያስብ ቤቱ ደርሶ ነበር።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ዓርብጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You