የበጎ ምግባር ተጠቃሚዎቹ አንደበት ይናገራል

የሀገራችንን የመደጋገፍ ባህል የበለጠ የሚያጎሉ ተግባሮች እየታዩ ናቸው። አቅመ ደካሞችን መደገፍ፣ የአእምሮና መሰል ህሙማን መጠየቅ እንዲሁም ተስፋ እንዲታያቸው «አለሁ» ማለት እየጎለበተ መጥቷል። በዚህም መኖሪያ ቤታቸው የዘመመባቸውንና የፈረሰባቸውን ዜጎች ቤቶች በእድሳት እንዲሁም በአዲስ መልክ ገንብቶ በማስረከብ ዜጎችን መታደግ በስፋት እየታየ ነው። በዚህ ተግባር ውስጥ ደግሞ የሀገሪቱን ታላላቅ የመንግሥት ተቋማት የሚያስተዳድሩ ባለሥልጣናት (ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ) የመሪነቱን ሚና እየተወጡ ይገኛሉ።

በአራዳ ክፍለከተማ ወረዳ ስምንት አዋሬ አካባቢ አንድ ግዙፍ አዲስ ሕንፃ ተመለከትን፤ ሕንፃው ባለ አራት ወለል ነው። ከርቀትም ከቅርበትም ለተመለከተው በጣም ያምራል። ገብቶ ለተመለከተው፣ ተጠቃሚዎቹን ላነጋገረው ደግሞ ሌላ ልዩ ስሜትን ያጭራል።

ሕንፃው የተሠራው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ነው። ይህ ትልቅ ሕንፃ በአካባቢው በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተገነባ ዘመናዊ ሕንፃ ነው፤ ከ54ካሬ እስከ 70 ካሬ የሚደርሱ ባለ አንድ፣ ባለ ሁለት እና ባለሦስት መኝታ ክፍሎች ያሉት ሕንፃውን ለመገንባት ሲባል ከስፍራው ለተነሱ 37 አባወራዎች ተላልፏል።

የሕንፃው ግንባታ የክረምት የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት አካል ሲሆን፣ ግንባታው በሰኔ ወር ተጀምሮ በ3 ወር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል። በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙ፣ በኑሮ የተጎዱ፣ የዕለት ጉርስ የሌላቸው እና በጉሊት የሚሠሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ጭምር ተጠቃሚ ያደረገ ነው።

የእነዚህ ቤቶች ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ ኑርሰቤ ሲመላ አንዷ ናቸው። ቤት ማግኘታቸውን ሲያስቡት «ዱንያ ከሆነ መቃብር ዱንያ ወደ ሆነ ጀነት» የተሸጋገርኩ ያህል ነው የምቆጥረው ሲሉ ገልጸዋል። ወይዘሮ ኑርሰቤ ቀደም ሲል ለአርባ ዓመት ያህል የነበሩበት ቤት በፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦ ላይ የተሠራና ጎርፍም የሚያስገባ ነበር። ከላይ ቆጥ በመሥራት ነበር ጎናቸውን የሚያሳርፉት።

«አስከሬን እንኳ ከጥሩ ቤት ሲወጣ የሆነ ጥሩ ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል» ሲሉ የገለጹት ወይዘሮ ኑርሰቤ፣ ቀድሞ ይኖሩበት የነበረው ቤት ከጥበቱ የተነሳ ልጆቻቸው እግራቸውን ዘርግተው ለመተኛት ይቸገሩ የነበረበት መሆኑን ያስታውሳሉ። በዚሁ ቤት ከአምስት ልጆቻቸው ጋር ሰባት ቤተሰብ ሆነው ኖረዋል።

ከቆዩበት አሰቃቂ ሕይወት ወጥተው ለዚህ ደስታ መብቃታቸውን በመግለጽ ዛሬ እግራችንን ዘርግተን መተኛት ችለናል ይላሉ። ለዚህም ከአላህ በመቀጠል ምስጋናዬን ለዶክተር ዐቢይ አሕመድ አቀርባለሁ ያሉት ወይዘሮ ኑርሰቤ፣ ከነበሩበት አስከፊ ሕይወት ወደዚህ አዲስ ሕይወት መሸጋገራቸውን ‹‹ዓለማዊ ወይም ዱንያዊ ጀነት›› ብዬ አስባለሁ ሲሉ ገልጸዋል። የተቸገረ የሰው ልጅ ሁሉ ይህ ዕድል እንዲገጠመውም ተመኝተዋል።

አቶ መንግሥቱ እዝነ የ72 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ናቸው። ፓስተር ጤና ጥበቃ ማባዣ ክፍል ለ28 ዓመታት ሠርተዋል። አሁን በጡረታ ሕይወት ውስጥ ይገኛሉ። እሳቸውም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የመደመር ትውልድ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታው ተጠቃሚ ሆነዋል። በዚህም ደስታቸው ከመጠን ያለፈ ሆኗል።

‹‹ይህን ቤት አገኛለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ መንግሥቱ፣ ‹‹ዕጣ አውጣ ተብዬ የመጨረሻዋን ዕጣ ሳወጣ እዚሁ በቆምኩበት ቦታ ላይ ወጣልኝ›› ይላሉ። ባለ አንድ መኝታ ቤት የደረሳቸው ሲሆን፣ ቤቱ መጸዳጃ ቤት፣ በረንዳ እና ሰፊ ሳሎን አለው። ‹‹ከነልጆቼ ይበቃኛል›› ሲሉም ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል።

እሳቸውም ከዚህ በፊት ይኖሩ የነበረበት ቤት ጎርፍ የሚወርድበት ቆሻሻ የበዛበት እና የሚተላለፍበት ነበር። በእዚያ ቤት ውስጥ ሆነው አራት ወንድና አራት ሴት ልጆች ወልደዋል። ቤቱ ፈተና ነበር፤ በዚያ ቤት ውስጥ ሆኜ ልጆቼን ያሳደኩበትን ሁኔታ መናገር ይከብደኛል፤ ከሚቻለው በላይ ችግር የበዛበት ነበር ይላሉ።

«ሀገራችን አሁን የሚያስፈልጋት ከምቀኝነት ከተንኮለኝነት በመራቅ የሚያገለግል ዜጋ እንዲበዛ ነው፤ ይህ ሲሆን ሰላም ትሆናለች። ተንኮል እና ምቀኝነት ካለ ሀገር አታድግም፤ በፍቅር በአንድነት መኖር ከቻልን ሀገራችን ትበለፅጋለች። በጎነት ፍቅር እና አንደነት ሥራን ሳይንቁ መሥራት ከተቻለ መበልጸግ ይቻላል» ሲሉ አቶ መንግሥቱ ተናግረዋል።

‹‹ቤት ሠርቶ የሚሰጥ መንግሥት በዕድሜዬ አላየሁም›› ያሉት አቶ መንግሥቱ፣ ‹‹አይቼ የማላውቀውን ቤት ስላገኘሁ ለዶክተር ዐቢይ ፀሐይ ይውጣለት፤ መንግሥታችንም ለበጎነት እና ለቅንነት የተነሳ መንግሥት ነው፤ ፈጣሪ ከነቤተሰቡ እንዲጠብቀው ለሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን እመኛለሁ ብለዋል።

የበጎነት የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳቱ ሌላው ተጠቃሚ የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባሉ አቶ መንግሥቴ ሰጠኝ ናቸው። አቶ መንግሥቴ በጉዳት ሳቢያ በ1976 ዓ.ም ነው ጡረታ የወጡት። በአራዳ ክፍለ ከተማ ሸርዓ ፍርድ ቤት አካባቢ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ኖረዋል። በዚህም አካባቢ ትዳር ይዘው ሦስት ልጆች ወልደዋል።

አዋሬ አካባቢም ጌሾ፣ ሽንኩርት እና ቃሪያ እየነገዱ፤ ባለቤታቸውም እንጀራ እየሸጡ ልጆቻቸውን አሳድገዋል። ከዓመታት በኋላ ከባለቤታቸው ጋር በፍቺ ተለያይተው በችግር ውስጥ ማለፋቸውንም ይገልጻሉ። የቀድሞ ቤታቸው አሮጌና እየወደቀ የነበረ ነው። በዝናብ ወቅት አሮጌው ጣሪያ መኝታቸው ላይ ያፈስ ነበር፤ ይህን ለመከላከል ላስቲክም፣ መለጠፊያም ቢያደርጉበትም ለውጥ ማምጣት አልቻለም። የዘንድሮውን ክረምት አንዴት እሆናለሁ ብለው እያሰላሰሉ ባለበት ወቅት ነው የ90 ቀናት ቤት እድሳቱ ዕድል ተጠቃሚ መሆን የቻሉት።

በቤት እድሳቱ ለአራት አባወራዎች ከተገነባው ቤት ባንዱ እሳቸው እንዲገቡ በመደረጉ ደስታቸው የላቀ ሆኗል። ቤቱን በነፃነት እየኖሩበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ጠዋት ማታ ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። ቡናም ራሳቸው ያፈላሉ፤ ባላቸው አንድ ስቶቭ በመጠቀም ያበስላሉ፣ እንጀራ ከውጭ በመግዛት ነው የሚመገቡት።

በእርጅና ጊዜያቸው ብቻቸውን መኖራቸው ይበልጥ ኑሮውን እንዳከበደባቸው ገልጸው፣ «በቅርቡም ሪህ ታምሜ ተኛሁ፤ በሁለተኛው ቀን ራበኝ፤ እንደምንም አብስዬ አንድ ሁለት ጎረስኩና ውሃ ጠጣሁ። በሦስተኛው ቀን እግሬን አሻሽቼ ተነሳሁ።» ሲሉም ከተቸገሩባቸው ወቅቶች አንዱን ያስታውሳሉ።

መንግሥት በተለይ አንደ እኛ ያሉና ተንቀሳቅሰው መሥራት የማይችሉ አዛውንቶችን አስታወሰ ሲሉ ገልጸው፤ በአንድ ወር ከ10 ቀን ውስጥ ግንባታው የተጠናቀቀው የቤት እድሳት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

ይህም ለእሳቸው ትልቅ ደስታን ያጎናጸፋቸው መሆኑን ሲገልጹም፣ ‹‹እንደገና የተወለድኩ ያህል ተሰምቶኛል›› ሲሉ የተናገሩት። ‹‹ለዚህ ትብብር ያደረጉት መምህራን፣ የወረዳ፣ ክፍለ ከተማ አመራሮች እና ሁሉም አካላት ፈጣሪ ውለታቸውን ይክፈላቸው›› ያሉት አቶ መንግሥቴ፣ ‹‹መጪው አዲስ ዘመን የሰላም ይሁንልን፣ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን፣ ከክፉ ወሬ ይሰውረን” ሲሉም መርቀዋል።

በዚሁ አካባቢ በተካሄደው የቤት እድሳት ወይዘሮ ፀሐይ አበበም ተጠቃሚ ሆነዋል። ከዚህ ቀደም ፊት በር አካባቢ ቀበሌ 18 ከባለቤታቸው እና ከልጆቻቸው ጋር ጥሩ ኑሮ ይኖሩ ነበር። ሁለት ልጆችም ወልደዋል፤ የልጆቻቸው አባት ኤርትራዊ ስለነበር ኤርትራውያን ሲወጡ የመጀመሪያ ልጃቸው ከአባቱ ጋር ወደ ኤርትራ ሄደ። አባቱን በስልክ ማግኘታቸውንና ትልቁ ልጃቸው ካናዳ መሆኑን ቢሰሙም፣ ለ27 ዓመታት ያህል አድራሻውን አያውቁም።

ወይዘሮ ፀሐይ ሸራተን አካባቢ ከ13 ዓመት በፊት በልማት ከተነሱት መካከል አንዱ ናቸው፤ በወቅቱም አቅሙ ያለው ኮንዶሚኒየም መምረጡን አስታውሰው፣ እሳቸውም በአቅማቸው በመረጡት የቀበሌ ቤት በአራዳ ክፍለከተማ ወረዳ ሰባት ሸርዓ ፍርድ ቤት አካባቢ ክፍለከተማው በልዋጭ ቢያዛውራቸውም ደስተኛ እንዳልነበሩ ይናገራሉ።

ቅሬታቸውን ለክፍለ ከተማው አመልክተው በአንድ ሺህ ብር ደመወዝ ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበር ውስጥ እየሠሩ ኑሮአቸውን እየገፉ በተስፋ ይኖሩ ነበር። ይህም ለ13 ዓመታት የኖሩበት የቀበሌ ቤት እየወደቀ እና ዝናብ እያስገባ አስቸገራቸው። የአካባቢው ወጣቶች ተባብረው ቢጠግኑትም፣ ከጎን የተያያዘው ሌላኛው ሲሠራ እንደገና ይፈርስባቸዋል። በዚህ የተነሳም በችግር ውስጥ መኖር የግድ ሆነባቸው ይቆያል።

ችግራቸውን የሚያውቀው ክፍለ ከተማው የ90 ቀናቱ ቤት እድሳት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትብብር አድርጎላቸው የቤት እድሳቱ ቱሩፋት ተጠቃሚ ሆነዋል። ለዚህም መልካም ተግባር በተለይ ከልጆቻቸው ጎሮሮ ከፍለው ይሄንን ቤት ያደሱላቸውን እና በጎ አድራጎት ያደረጉላቸውን የትምህርት ጥራት መምህራንን አመስግነዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለሀብቶችን በማስተባበር በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከዓመት በፊት በጎርፍ የተጎዱ 13 ቤቶችን በአዲስ መልክ ገንብቶ በቅርቡ ለነዋሪዎች አስተላልፏል። ሚኒስቴሩ ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ ከ52 በላይ የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶችንና ሱቆችን ገንብቶ ማስረከቡን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያን አገልግለው በዕድሜ መግፋት ምክንያት አቅም ያጡ ወገኖች ማገዝ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የተገነቡ አንድ ሺ 680 ቤቶችን አቅም ላነሳቸውና በችግር ውስጥ ለሚገኙ የሀገር ባለውለታዎች አስረክበዋል። ቤቶቹ አስፈላጊ የመገልገያ ዕቃዎች የተሟሉላቸው መሆናቸውንም ነው ያመለከቱት። በዚህም አቅም ያነሳቸው ነዋሪዎች አዲሱን ዓመት በአዲስ ቤት፣ በአዲስ ተስፋ እንዲቀበሉ አድርገናል ሲሉም ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አብርሃም ታደሰ እንደገለጹት፤ የቤት እድሳቱ በ2015 በጀት ዓመት በ14 ፕሮግራሞች እና 18 መርሃ ግብሮች ነው የተጀመረው። ዓመቱ በቤት እድሳት ደረጃ ከስድስት ሺህ 415 በላይ ቤቶች ታድሰው ለኅብረተሰቡ የተላለፉበት፤ በማዕድ ማጋራትም ከ800 ሺሀ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሆነቡት ነበር። በልዩ ፍላጎቶች ላይም ትምህርትና ሥልጠናዎች በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በቀይ መስቀል ደም ልገሳ መርሃ ግብር፣ የመንገድ ትራፊከ ደህንነት፣ የአካባቢ ሰላም፣ የኪነጥበብ እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና የወሰን የለሽ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጭምር ሲከናወኑ ቆይተዋል።

በአጠቃላይ በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ሰባት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ሥራ ላይ የዋለበት እና ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሆኑበት መሆኑን አስታውሰዋል።

የክረምቱ ወር በጎ ፈቃድ አገልግሎት ግንቦት ወር የተጀመረ እና እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 የሚቆይ ሲሆን፣ ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር የሚገመት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት እና ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ የተጀመረ ነው። በክረምቱ በአጠቃላይ ከተጀመሩት የሦስት ሺህ ሁለት መቶ በላይ ቤቶች እድሳቶች አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በነሐሴ 30 ቀን 2015 የተጠናቀቁ አንድ ሺህ 686 ቤቶች ለነዋሪዎቹ ተላልፈዋል። ቀሪዎቹም በቀጣይ ጊዜ እየተጠናቀቁ ለነዋሪዎች የሚተላለፉ ይሆናል።

በተለይ የቤት እድሳት መርሃ ግብሩ ከሌሎች ሥራዎች ጎላ ብሎ የሚወጣ እና ሰፊ ካፒታል የሚጠይቅ መሆኑን አቶ አብርሃም ጠቅሰው፣ ከተገነቡት ከስድስት ሺህ 415 ቤቶች ከአንድ ሺህ 30 በላይ የሚሆኑት ቤቶች በሕንፃ ደረጃ ተሠርተው የተሰጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በሕንፃ ደረጃ የተገነቡት ቤቶች ከአንድ ወለል በላይ የተገነቡ፣ አመለካከትንም የቀየሩ የነዋሪዎችንም መሠረታዊ ሕይወት በሚቀይር መልኩ የተገነቡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

እነዚህ ቤቶችም በጣም በተጎሳቆለ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን፣ የሀገረ ባለውለታዎችን፣ በኢኮኖሚ አቅም በጤና እጦት እና በዕድሜ መግፋት ምክንያት ለችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሸ የሚያደርጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ይሄንን ሥራ በመደገፍ ረገድ የከተማዋ ባለሀብቶች ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸው፣ ወጣት በጎ ፈቃደኛ ተቋማት ሰፊ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይሄንን ሥራ በአርአያነት እየመራው ያለው አመራሩ መሆኑን ገልጸው፣ እንደ ሀገርም ጠቅላይ ሚኒስትሩም በአርአያነት በመሥራት የከተማዋ ከንቲባም አርአያ ሆነው እየሠሩ መሆናቸውን ተከትሎ ውጤታማ መሆን መቻሉን ነው የተናገሩት።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You