አምራችነትን ማሳደግ ለመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርና ዘላቂ እድገት

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እምቅ አቅም ያላት ሀገር ናት። የአገሪቱ ግዙፍ የአምራች ኃይል አቅም፣ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እንዲሁም አመቺ ሕጋዊ ማዕቀፎች ለዘርፉ እድገት አወንታዊ አስተዋፅዖ ከሚያበረክቱ መልካም አጋጣሚዎችና አስቻይ ሁኔታዎች መካከል ይጠቀሳሉ። ሀገሪቱ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራትን አከናውናለች።

በዓይነትም ሆነ በብዛት በርካታ የሆኑት የዘርፉ ችግሮች፤ የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍና በአጠቃላይ የሕዝቡን የተቀናጀ ጥረት የሚፈልጉ እንደሆኑ ሲገለፅ ቆይቷል። ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ብዙ ሙከራዎች ተደርገው የማይናቁ ውጤቶች ቢመዘገቡም፤ ከአገሪቱ አቅምና ከችግሮቹ ስፋት አንፃር ግን መፍትሔዎቹ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ሊያስገኙ እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ተገልጿል።

ዘርፉ በግብዓት (ጥሬ ዕቃ)፣ በሰው ኃይል፣ በቦታ፣ በኃይል፣ በፋይናንስና በውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግሮች ተተብትቦ የተያዘ ነው። የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የአጠቃቀም ፍትሃዊነት መጓደል፣ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተገቢውን ትኩረት አለመስጠት፣ የሥራ ባህል ደካማነት እንዲሁም ዘርፉን ለማበረታታት የሚወጡ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች በአግባቡ አለመተግበር በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያጋጥሟቸው ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ባለሃብቶች ሲገልፁ ይስተዋላል።

በዚህም ምክንያት ኢንዱስትሪዎች እያመረቱ ያሉት ከአቅማቸው በታች እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ። በአሁኑ ወቅት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ከሰባት በመቶ ያልበለጠ ድርሻ ያለው ሲሆን በቀጣይ 10 ዓመታት ይህን ድርሻ ወደ 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል። ከዚህ በተጨማሪም አሁን ያለውን 50 በመቶ የኢንዱስትሪዎች የምርታማነት አቅም ወደ 85 በመቶ የማድረስ እቅድም ተይዟል።

የ‹‹ሀብቴ ጋርመንት›› ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብተሥላሴ ገብረክርስቶስ የአምራች ዘርፉን እድገት የሚጎትቱ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ይገልጻሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ከእነዚህ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ የአመለካከት ችግር ነው።

ዘርፉን የሚመሩት በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙት አካላት የተሻለ ግንዛቤ ቢኖራቸውም፣ ሌሎቹ አካላት ያላቸው አመለካከት የተዛባ ነው። ከአምራች ኢንዱስትሪው ጋር ግንኙነት ያላቸው መስሪያ ቤቶች ለዘርፉ ያላቸው ግምት አነስተኛ ነው። የዘርፉን አቅምና ችግር ከፍተኛ አመራሩ በሚረዳው ልክ አይገነዘቡትም። ይህ የአመለካከት ክፍተት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች እንዳይበረታቱና ከገበያ እንዲወጡ ያደርጋቸዋል።

‹‹መንግሥት ለአምራች ዘርፉ የሚያደርጋቸው ድጋፎች ሊበረታቱ የሚገባቸው እርምጃዎች ናቸው። የግብር እፎይታ የማግኘት፣ ግብዓቶችን ከቀረጥ ነፃ የማስገባት፣ ከሌሌቹ ዘርፎች በተሻለ ለውጭ ምንዛሬን ጥያቄ ቅድሚያ የማግኘትና ሌሎች ማበረታቻዎች ለዘርፉ እድገት በጎ ሚና አላቸው። ይሁን እንጂ በታችኛው የአስተዳደር እርከን ላይ ያሉ የስራ ኃላፊዎችና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ስለነዚህ ማበረታቻዎች ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ የዘርፉን ተዋንያን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈሉት ይገኛሉ›› በማለት የግንዛቤ ችግር በአምራች ዘርፉ እድገት ላይ መሰናክል መፍጠሩን ያስረዳሉ።

የግብዓት አቅርቦት ችግር ሌላው የአምራች ዘርፉ ፈተና ነው። ይህ ችግር አስተማማኝ የሆነ የምርት አቅርቦት እንዳይኖር ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የመሆን እድልን ይዘጋል። ሌላው በዘርፉ እድገት ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ የሚገኘው ወጥነት ያለው የግብር አሰባሰብ ችግር እንደሆነ አቶ ሀብተሥላሴ ይጠቅሳሉ። ‹‹በዘርፉ ከተሰማሩ አምራቾች መካከል ‹ደረሰኝ አዘጋጅተው የሚሰሩ ድርጅቶች ምን ያህል ናቸው?› ብሎ መመርመር ይገባል። ከህግ ያፈነገጡ አሠራሮች ህጋዊ አምራቾችን ከገበያ ያስወጣሉ። ስለሆነም ፍትሐዊ ውድድር መድረክ በመፍጠር ህጋዊነትን ማበረታታ ያስፈልጋል። የግብር አሰባሰብ ስርዓቱ ግልፅ፣ ተከታታይና ዘላቂ መሆን አለበት›› ይላሉ።

ተለዋዋጭ የሆነ የጥሬ እቃ ዋጋ መኖርና የእቃዎቹ ዋጋ መናር አምራቾች በቂ የሰው ኃይል እንዳይቀጥሩ እያደረጋቸው እንደሆነ የሚገልፁት አቶ ሀብተሥላሴ፤ ብቁ የሰው ኃይል እጥረት፣ የብድር አቅርቦት እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ የዘርፉ ችግሮች መሆናቸውንም ያስታውሳሉ።

በኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን የ‹‹ዋንኮ ቡና›› ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ታደለም ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች የዘርፉ ማነቆዎች እንደሆኑ ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪ በህገ ወጥ ንግድ ምክንያት የሚፈጠር የገበያ ችግር በአምራች ዘርፉ እድገት ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ እንደሚገኝም ይገልፃሉ።

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እና በኢባዳን ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ግርማ መንግሥትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ስለአምራች ዘርፉ ችግሮች ብዙ ጥናቶችን ማድረጋቸውን ጠቁመው፣ ‹‹አብዛኞቹ የጥናት ውጤቶች የሚያሳዩት የዘርፉ ችግሮች መዋቅራዊ (Structural Problems) እንደሆኑ ነው›› ይላሉ። ችግሮቹ እንደየዘርፎቹ ነባራዊ ሁኔታ እንደሚለያዩም ያመለክታሉ።

የኃይል አቅርቦት እጥረትና የውጭ ምንዛሬ ችግር የአምራች ኢንዱስትሪው ዋነኛ ተግዳሮቶች ሆነው ቆይተዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የፀጥታ ችግሮች የዘርፉ ተጨማሪ ፈተናዎች ሆነዋል። የኃይል አቅርቦት ችግር አብዛኞቹ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከ30 በመቶ ባልበለጠ የማምረት አቅም እንዲያመርቱ አስገድዷቸዋል።

የወጪና ገቢ ንግድ (ከወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ እና ለገቢ ንግድ የሚወጣው ወጪ) በከፍተኛ ደረጃ ያልተመጣጠነ በመሆኑ የውጭ ምንዛሬ እጥረት የዘርፉ ትልቅ ፈተና እንዲሆን አድርጎታል። የብዙዎቹ ኢንዱስትሪዎች የምርት ግብዐቶች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ናቸው።

የብድር አቅርቦት ችግር በአምራች ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚያጋጥማቸው ሌላው ፈተና መሆኑን የሚጠቅሱት ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፤ ችግሩ በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ላይ የከፋ እንደሆነም ይገልፃሉ። ትልልቅ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ሲሰማሩ ከመጡባቸው ሀገራት ከሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር ብድር የሚያገኙበትን አሠራር ያመቻቻሉ። የሀገር ውስጥ አምራቾች ግን ከውጭ ተቋማት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ በሆነው የሀገር ውስጥ የፋይናንስ አቅም ላይ ብቻ ለመወሰን እንደሚገደዱ ያብራራሉ።

‹‹አምራች ኢንዱስትሪው ለምርት አቅርቦት ችግር መፍትሄ እየሆነ ነው›› የሚሉት አቶ ሀብተሥላሴ፤ መንግሥት እስካሁን ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የበለጠ ማሳደግ እንዳለበት ይገልፃሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ መንግሥት ቢሮክራሲውን በማስተካከል ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ማስፈን ይጠበቅበታል። አንዳንድ አምራቾች ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉት መንግሥት ለአምራች ዘርፉ የሰጣቸውን ማበረታቻዎች ለመጠቀም በማሰብ ብቻ እንደሆነ ይስተዋላል። ይህ ዓይነት አሰራር ሕጋዊ አምራቾችን በመጉዳት ሀገራዊ ኪሳራን ስለሚያስከትሉ መንግሥት አምራች ዘርፉን ለመደገፍ የወጡ ህግጋት በተገቢው መንገድ ተግባራዊ መደረጋቸውን ማረጋገጥ አለበት።

አንዳንድ ጊዜ መንግሥት ‹ማበረታቻዎቹ ላልተገባ ጥቅም ውለዋል› ብሎ ማበረታቻዎቹን ሲሰርዛቸው ይስተዋላል። መፍትሄው ማበረታቻዎቹን መሰረዝ ሳይሆን፣ ማበረታቻዎቹ ተገቢውን አካል ተጠቃሚ ስለማድረጋቸው መከታታልና ማረጋገጥ ነው። ‹‹በአምራች ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች በሌሎች ዘርፎች ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር እኩል መታየት የለባቸውም። የአምራች ዘርፍ ባለሀብቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸው በተጨማሪ በቀዳሚነት ምርት ያቀርባሉ። የምርት አቅርቦት ደግሞ ዋናዎቹን ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት ችግሮች ለመፍታት ሁነኛ መፍትሄ ነው። ስለዚህ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት በእጅጉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት›› በማለት መንግሥት ለአምራቹ ዘርፍ ሊያደርገው ስለሚገባው ድጋፍ አስፈላጊነት ያስረዳሉ።

ባለፉት አራት ዓመታት መንግሥት ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሐ ግብሮችን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል። ከእነዚህ መርሐ ግብሮች አንዱ፣ ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብር (Homegrown Economic Reform Program) ነው። የመርሃ ግብሩ ዓላማ አምራች የሆነውን የሠው ኃይል የሚሸከም የሥራ ዕድል እና የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ በመፍጠር እንዲሁም የግል ዘርፍ መር (Private Sector-Led) የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመገንባት ዘላቂና ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ማስመዝገብ ነው።

የኢንቨስትመንት አዋጅና የንግድ ሕግ ማሻሻያዎች፣ ብሔራዊ የንግድና ቢዝነስ ሥራ አመቺነት ማሻሻያ መርሐ ግብር (National Ease of Doing Business Initiative) እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የግብይት ስርዓት ጋር ዘመናዊ ትስስር ለመፍጠር የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን የተላለፈውን ውሳኔ ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሐ ግብሩ አካል ናቸው። እነዚህ ማሻሻያዎች የማምረቻው ዘርፍ ችግሮችን በማቃለል ዘርፉ በሀገራዊ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ ይታመናል።

ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎቹ ለአምራች ዘርፉ እድገት ስለሚኖራቸው ሚና ሲያስረዱ ‹‹ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተደረጉት የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች የአምራች ዘርፉን ችግሮች ለማቃለል ማስታገሻ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ። የባንክ ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆንና የካፒታል ገበያ እንዲጀመር መወሰኑ ለአምራች ዘርፉ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር አማራጭ መፍትሄ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ መዋቅራዊ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ስለማስታገሻዎች ማውራት ትርጉም ያለው ለውጥ አያስገኝም›› ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የሰላም እጦት መሰረታዊ የአምራችነት ቅድመ ሁኔታዎችን ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱን ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ጠቅሰው፣ ‹‹በብዙ ጥረት በመጡ የውጭ ባለሀብቶች የተከፈቱ ኢንዱስትሪዎች በሰላም እጦት ምክንያት ሲዘጉና አደጋ ሲደርስባቸው ሀገሪቱን ብዙ ዋጋ ያስከፍላሉ።›› ይላሉ። ‹‹ሰላም የኢንቨስትመንት ትልቁ ዋስትና ነው። የሰላም መስፈን ለባለሀብቶች የንብረት ባለቤትነት መብት ይሰጣል። አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብም ሆነ ነባሩን ለማነቃቃት ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ይገባል›› በማለት ይመክራሉ።

በኃይል አቅርቦት ረገድ ስላለው ችግር ደግሞ፣ ሀገሪቱ ችግሩን ለመፍታት ዋነኛ የመፍትሄ አማራጭ አድርጋ እየተጠቀመች የምትገኘው ከውሃ ኃይል የሚገኝ የኃይል አቅርቦትን እንደሆነ ጠቅሰው፤ ችግሩን ትርጉም ባለው መልኩ ለመፍታት እንደ ኑክሊየር ያሉ ተጨማሪ የኃይል ምንጮችን ስለመጠቀም ማሰብ እንደሚስፈልግም ይጠቁማሉ።

የአምራች ዘርፉን ችግሮች በማቃለል ሂደት ውስጥ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በልዩ ሁኔታ የመደገፍ ተግባር ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ዛሬ በምጣኔ ሀብታቸውና በፖለቲካ ተፅዕኗቸው የዓለም ኃያላን የሆኑት ሀገራት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን በመደገፍ ረገድ ትልቅ ተሞክሮ አላቸው። እንዲያውም ለአሁኑ የምጣኔ ሀብት ኃያልነታቸው መሰረት የሆናቸው ከውጭ ጥገኛነት ያላቀቃቸው የአምራችነት አቅማቸው ማደግ እንደሆነ ይታወቃል። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍ ጥረት በብዙ መልኮች ሊገለፅ ይችላል። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የሚያበረታቱ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን በመቅረፅ፣ ፋይናንስን ጨምሮ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን በማሟላት እንዲሁም ቢሮክራሲያዊ የአሠራር ውጣ ውረዶችን በማቃለል ለባለሀብቶቹ ድጋፍ ማድረግ ይቻላል።

ባለሀብቶቹ በኢንቨስትመንት ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ ዘላቂ እንዲሆን መንግሥት የኃይል አቅርቦትን፣ የመንገድና የሎጂስቲክስ አገልግሎቶችን ጨምሮ ለሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮችም መፍትሄዎችን ማበጀት ይጠበቅበታል። የውጭ ምንዛሬን በፍትሐዊነት የማቅረብም ኃላፊነት አለበት።

የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች እንዳሉ ይታወቃል። ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት የሚመጣጠኑ በመሆናቸው ለወቅቱ የሚመጥን ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ የአምራች ዘርፉን ችግሮች መፍታት ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ የመፍትሄ አቅጣጫ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

 አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን    ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You