ምሁር ለሚለው ቃል አቻ እንግሊዝኛ ትርጉሙ ኢንተሌክቹዋል የሚለው ፍቺ ነው። የአማርኛ ቋንቋ ደግሞ ምሁር የሚለውን ቃል ከፍተኛ የሆነ የማሰብና የመመራመር ችሎታ ያለው ብሎ ይተነትነዋል ወይም ትርጉም ይሰጠዋል። በትምህርት የሚገኘው ዕውቀት በተግባር ለውጥና መሻሻል ካላመጣ ትምህርት መማሩና ማስተማሩ በራሱ ትርጉም የለውም ይላሉ ብዙዎች። የአንድ ሰው በትምህርት የተገኘ ዕውቀት ፋይዳ የሚኖረው በራስና በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ሲያስችል ብቻ ነው።
የምሁር ዕውቀት የሰዎችን ኑሮና አኗኗር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻሻል የራሱን አስተዋፅዖ ማበርከት እንዳለበት ብዙዎች ይስማማሉ። በእያንዳንዱ የዕውቀት ዘርፍ የሚደረግ ጥናትና ምርምር የሰዎችን ሕይወት በማሻሻል ላይ ማዕከል ያደረገ መሆንም ይኖርበታል። ስለዚህ፣ አንድ ሰው በትክክል “ምሁር” ለመባል ብቁ የሚሆነው ዕውቀቱን ከራሱ አልፎ በሌሎች ሕይወት ላይ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚጠቀምበት ከሆነ ነው። ምሁርነትም ከዚህ አንፃር ታይቶና ተመዝኖ የሚሰጥ ክብር እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።
ሆኖም ሁል ጊዜ ትልቁ የመከራከሪያ ነጥብ ብያኔውን በተመለከተ በግልፅ ማስቀመጥ አለመቻል ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አረዳድ ምሁር ማለት በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አልፎ ዲግሪ የያዘ ሰው ማለት ነው።
ምሁር ምን ማለት እንደሆነ ግን በምሳሌ በቀላሉ እንረዳለን። ሻማ ብንወስድና ሻማ በካርቶን ውስጥ እንዳለ በቤት ውስጥ ቢቀመጥ እንደማንኛውም በቤት ውስጥ እንዳለ ዕቃ ነው። የበራ ሻማ ግን ክስተት ነው። ሻማውን ከብርሃኑ ለይተህ አታየውም። የበራው ሻማ ለራሱ ሲል አይበራም ለሁላችን እንጂ፤ ምሁር ማለት የበራ ሻማ ማለት ነው። የተማረ ማለት ደግሞ ያልበራ ሻማ ማለት ነው፤ የመብራት አቅም አለው ነገር ግን አልበራም።
ስለዚህ ምሁር ማለት በልምድ፣ በትምህርትና በልዩ ልዩ መንገድ ያገኛቸውን ማስተዋሎችና ዕውቀት በሐሳብ መልክ ለኅብረተሰቡ የሚያቀርብ ሰው ነው።
ለዚህ ቃል ብቁ ሆነው የተገኙ ጥቂት የሚባል ቁጥር የሌላቸው በዓለም መድረክ ላይ አዳዲስና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግኝቶችንና ፈጠራዎችን ይዞ ብቅ በማለት የበርካቶችን አንገብጋቢ ችግር የፈቱና ብዙዎችን በስራዎቻቸው ያስገረሙ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ። ከእነዚህም ሰዎች ውስጥ የላፓራስኮፒክ ህክምና ፕሮፌሰር ምትኩ በላቸው አንዱ ናቸው።
ታዋቂው የቀዶ ህክምና እስፔሻሊስት ፕሮፌሰር ምትኩ በላቸው የተወለዱት በምዕራብ ሸዋ ወንጪ ሲሆን እድሜያቸው 12 ዓመት ሲሞላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ፕ/ር ምትኩ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከነበረበት የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጪ የትምህርት እድል አግኝተው ወደ ቤልጂየም በማቅናት የህክምና ትምህርታቸውን ተከታትለው በዓለማችን አንቱ ከተባሉ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስቶች ተርታ መሰለፍ ችለዋል።
ፕሮፌሰር ምትኩ እስከ አስራሁለት ዓመታቸው ድረስ ወደ ትምህርት ገበታ ሳይቀላቀሉ በእረኝነት አሳልፈዋል። ይህም የሆነው በትውልድ አካባቢያቸው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ነው። የቀለም ትምህርታቸውን አንድ ብለው የጀመሩት በጅማ ከተማ ነበር። በኋላም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በመድሃኒዓለም ትምህርት ቤት መከታተል ችለዋል። ከሌሎች የዕድሜ ዕኩዮቻቸው ዘግይተው ማለትም በአስራ ሁለት ዓመታቸው ስለነበር የቀለም ትምህርት የጀመሩት ይህንን ማካካስ ስለነበረባቸው እና የትምህርት አቀባበላቸው ከፍ ያለ በመሆኑ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በሰባት ዓመት በማጠናቀቅ በ19ኝ ዓመታቸው የሕክምና ትምህርት ለመከታተል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለዋል።
የሕክምና ትምህርት ለመከታተል ምክንያት የሆነቻቸው የታላቅ ወንድማቸው ሞት እንደሆነ ፕሮፌሰር ምትኩ ይገልፃሉ። ህመም ሳይታይበት በድንገት የመሞቱ ምክንያት ምንድነው በማለት ለመመራመር እንደተነሱና አንድ ቀን የዚህን ምክንያት ባውቅ በሚል ጉጉት ሕክምና ለመማር እንዳለሙ በአንድ ወቅት ተናግረዋል።
በወቅቱ አንድ ለእናቱ የነበረውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መቀላቀል ቢችሉም በስድስት ኪሎ የህክምና ትምህርት ስላልነበር ለህክምና ቅርበት ወዳለውና አራት ኪሎ ወደሚገኘው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በመግባት ትምህርታቸውን ለአንድ ዓመት ከተከታተሉ በኋላ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የሚሰጥ የስኮላርሺፕ ፈተና በብቃት በማለፍ ወደ ውጭ ሀገር በመሄድ የመማር እድል አግኝተዋል። በዩናይትድ ኪንግደም ወይም በአሜሪካ የሕክምና ትምህርት ለመከታተል እቅድ የነበራቸው ፕሮፌሰር ምትኩ ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ የቤልጂየም መንግስት በሀገረ ቤልጅየም ትምህርት እንዲከታተሉ እድል ሰጣቸው። ከጓደኞችና በአካባቢያቸው ያሉ ሰዎች በቤልጅየም የቋንቋ ችግር ቆይታህን አስቸጋሪ ስለሚያደርገው በቅድሚያ ቋንቋ ተማር የሚል ምክር ስለቸሯቸው ወደ ቤልጅየም በመሄድ ፈረንሳይኛ በመማር ከዚያም የሕክምና ትምህርት በመከታተል በመጨረሻ የላፕራስኮፒክ ቀዶ ጥገና ባለሙያ እና ፕሮፌሰር መሆን ችለዋል።
የተሻሻለውን አፒታይት የሚገድብ በጨጓራ ላይ የሚታሰር የሚጠብ እና የሚሰፋ ቀለበት ወይም በእንግሊዝኛ Laparoscopic adjustable Silicone gastric banding የፈጠሩት ፕሮፌሰር ምትኩ ስለዚህ የፈጠራ ሥራቸው ሲናገሩ፤ ብዙ ደም ሳይፈስና ህመም ሳይኖር የሚሰጥ የሕክምና አይነት መሆኑን አስረድተዋል። ይህም የሆነበት ምክንያት በትንሽ ቀዳዳ በመጠቀም የማይክሮ ካሜራ ወደ ውስጥ በማስገባት በጣም ትናንሽ በሆኑ መሳሪያዎች የሚከናወን የሕክምና አይነት በመሆኑ ከአንድ ሴንቲሜትር ባልበለጠ የሰውነት ቀዳዳ የሚከናወን ሕክምና በመሆኑ ሰዎች ከሰመመን ሲነቁ የሕመም ስሜታቸውን በእጅጉ የቀነሰ ያደርገዋል ይላሉ። ይህም የሕክምና ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕክምና ሳይንስ ትልቅ አብዮት ያመጣ የፈጠራ ሥራ እንደሆነም በአንድ ወቅት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በጥቁር አንበሳ የቀዶ ጥገና ወርክሾፖችን ጨምሮ በብዙ ቦታዎች ያስተማሩት ላፓሮስኮፒክ ቀዶ ጥገና ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገር ተማሪዎች ዕውቀት አስጨብጠዋል። ብዙ ቦታዎች በመጓዝ ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ብዙ የቀዶ ህክምና ዘመቻዎችን እና ተልዕኮዎችን ከ10 እስከ 15 ሰዎች በማዘጋጀት በመላ ኢትዮጵያ ቀዶ ጥገና ማካሄድ እና ስልጠናዎችን ለመስጠት አዘውትረው ሰርተዋል። በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቀዶ ጥገናውን ዲፓርትመንት በማቋቋም ለ3 ዓመታት ስልጠናዎችን በመስጠት ተማሪዎች ለማብቃት ጥረዋል።
የልጅነት ቤታቸው ለሆነው ወንጪ ብዙ ነገሮችን ማበርከት የቻሉት ፕሮፌሰሩ በልጅነታቸው ሁሉም ሰው እሳቸው ያገኙትን እድል እንዲያገኝ ትምህርት ቤት የመገንባት ህልም ስለነበራቸው ተመሳሳይ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎችና አጋር አካለት ጋር በመተባበር በጎ አድራጎት ድርጅት መስርተው በወንጪ ሐይቅ ዙሪያ ትምህርት ቤት መገንባት ችለዋል። በትምህርት ቤቱ ዛሬ ከ1000 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ። በርካቶችም ትምህርታቸውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቀው ከሕክምና እስከ ምሕንድስና እና ህግ ባሉ ዘርፎች ጎበዝ ሆነው ሀገራቸው እያገለገሉ ይገኛሉ።
በአካዳሚክ የላቀ ውጤት ያላመጡ ወጣቶችን እንደ ሽመና ባሉ ዘርፎች በማሰልጠን ወደሥራ ያስገቡት ፕሮፌሰር ምትኩ፣ ወጣቶች ሲሳካላቸው በማየታቸው ኩራት እና ደስታ እንደሚሰማቸው ተናግረው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በትውልድ አካባቢያቸው ወንጪ በሕክምና መሳሪያዎች የተሟላ እና አምቡላንስ ያለው ክሊኒክ በመገንባት የአካባቢ ሕብረተሰብ በአቅራቢያው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ሰርተዋል።
ከልክ ያለፈ የሰውነት ክብደት መጨመር Obesity በሰውነታችን አላስፈላጊና ከፍተኛ መጠን ያለው triglyceride ተብሎ የሚጠራው ስብ (fat) በሆድ፣ በመቀመጫ፣ በላይኛው የእጅ ክፍል፣ በትከሻና በሌሎች የሰውነታችን ክፍል በመከማቸቱ ምክንያት የሚፈጠር የጤና ችግር ነው።
ፕሮፈሰር ምትኩ በላቸው፣ ከመጠን በላይ ውፍረት ሳቢያ የሚከሰት የጤና ችግሮችን ለመቀነስ የሚረዳ የሕክምና ዘዴ ፈጥረው፣ ለበርካቶች የጤና፣ የደስታ የእፎይታ ምንጭ ሆነው፣ በሕክምናው ዓለም ስማቸውን እና የሀገራቸውን ስም ከፍ አድርገው አስጠርተው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለወገናቸው ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ ከፍተው፣ አስተምረው በርካታ በጎ አድራጎት ስራ ሰርተው፣ ከጉዟቸው፤ ከጥንካሬያቸው፤ ከድካማቸው እንድንማር ታሪክን እንድናውቅ ዓለም ስለ መሰረታቸው ስለሀገራቸው ታሪክ፣ ባህል፣ እንዲያነብ፣ ታሪካቸውን በመጽሐፍ ጽፈው እሳቸው እንደሚሉት የሕይወት ተራራን ወጥተው ጉዟቸውን አገባደው ነው ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት።
ከገጠሪቷ ወንጪ የእረኝነት ሕይወት እስከ ሌዥ (ቤልጅዮም) በዘለቀው ስኬት ከባዶ እግር ተነስተው ታዋቂ የቀዶ ጥገና ሀኪምነት አለፍ ሲልም እስከ ሕክምና ሊቅነት የደረሱት እኚህ ጉምቱ ኢትዮጵያዊ ምሁር ፕሮፌሰር ምትኩ በላቸው የአውሮፓ ጋዜጦች Lord of the Ring በሚል ቅፅል ይጠሯቸው ነበር። ለዚህ ምክንያት የሆናቸው ፕሮፌሰሩ የፈበረኩት የፈጠራ ውጤት ነበር።
በውጤቱም አውስትራሊያ፣ አውሮፓ፣ ሞሮኮ፣ ቤኒን፣ ሴኔጋል፣ ቶጎ እና ኮንጎን ጨምሮ ለሕክምና ኮንፈረንስ እና ለማስተማር እና ቀዶ ጥገና ለማድረግ በዓለም ዙሪያ ተመላልሰዋል። በሕክምናው ዘርፍ የፈጠራ ሥራውን ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረጉበትን አጋጣሚ በአንድ ወቅት ሲናገሩ፤ ‘’ከሁለት አሥርተ ዓመታት በፊት በምሠራበት ጊዜ፣ ቤልጂየም በባቫሪያ ሲቪል ሆስፒታል፣ ክብደቷን ለመቀነስ የረዳኋት በከባድ ውፍረት የምትሠቃይ ነርስ ነበረች። በወቅቱ ከመጠን ላለፈ ውፍረት ሕክምና የቀዶ ጥገና መፍትሔ በሰው ልጆች ላይ ገና አልተሞከረም ነበር፤ ውስብስብ ሂደቶችም ያሉት ነበር። ነገር ግን ሌት ተቀን ካጠናሁ በኋላ ለነርሷ የተሳካ ቀዶ ጥገና ማድረግ ቻልኩ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ሆንኩ’’ ይላሉ።
በኢትዮጵያ ምድር የበቀሉ ለሳይንሱ ዓለም አዲስ ነገር የፈጠሩ ግሩም ሳይንቲስት ነበሩ። በህይወት ዘመናቸው 40,000 ቀዶ ጥገናዎችን አድርገዋል። 30ሺ የሚሆኑት በውጪ ሀገራት 10ሺ የሚሆኑትን ኢትዮጵያ ውስጥ አድርገዋል። ከቀዶ ጥገና ስራ ጡረታ ከወጡ በኋላ ህይወታቸው እስከለፈበት ወቅት ድረስ በኢትዮጵያ በተለያዩ ሆስፒታሎች ማለትም በጥቁር አንበሳ፣ በቤቴል እና በቅዱስ ያሬድ የሠሩ ሲሆን እስከ ሕይወታቸው መጨረሻ ድረስ እውቀትና እና ልምዳቸውን ለቀጣዩ ትውልድ እያካፈሉ ቆይተዋል።
የኪሊማንጃሮን ተራራን በ67 ዓመታቸው የወጡ ጠንካራ ሰው፣ ጉምቱ ምሁር በኢትዮጵያና በመላው ዓለም በሕክምናው ዘርፍ ላይ ሰፊ ጥናት እና ምርምር በማድረግ የሚታወቁት ፕሮፌሰር ምትኩ በላቸው በሚኖሩበት ቤልጂየም ሊየዥ ከተማ ባደረባቸው ድንገተኛ ህመም በተወለዱ በ79 ዓመታቸው ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። እኛም ለእኚህ የሀገር ዋርካ እና ባለውለታ ነፍስ ይማር እንላለን።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጳጉሜን ቀን 1 2015 ዓ.ም