የተወለደችው ደብረማርቆስ ነው። ከዘጠኝ ዓመት እድሜዋ ጀምሮ ግን አዲስ አበባ ከተማ ነው የኖረችው። በትምህርቷም በፐርቼሲንግ ማኔጅመንት ዲፕሎማ አላት። በተጨማሪም በፋሽን ዲዛይን ተምራ የምስክር ወረቀት አግኝታለች።
ከተማረችባቸው የትምህርት ዘርፎች የመረጠችው የፋሽን ዲዛይን በመሆኑ ሙያውን መተዳደሪያዋ አድርገዋለች።የምትሰራውን የፋሽን ዲዛይን ሥራም ወደ ኢንዱስትሪ ከፍ በማድረግ በፋሽን ኢንዱስትሪው የራስዋን ኑሮ ከመለወጥ ባለፈ ለሀገሯ አበርክቶ ለማድረግ ነው እቅዷ። በዘርፉ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር፣ በተለይም ከሐር በሚዘጋጁ አልባሳት ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ የእቅዷ አካል ነው።
ስለሙያዋና የወደፊት እቅዷ እንዲህ ያጫወተችኝ ሰናይት ደምመላሽ ትባላለች።ሰናይትን አንቺ ያልኳት ቀለል ብላ ስላገኘኋትና ፈቃዷም ስለሆነ እንጂ በትዳር የምትኖር የልጆች እናት ናት። ወይዘሮ ሰናይት እንዳጫወተችኝ ለሙያው ከፍተኛ ፍላጎት ስላላት ዲዛይን የምታደርገውን ብቻ ሳይሆን ዲዛይን ስለምታደርጋቸው የጨርቅ አይነቶችም ትጨነቃለች።ጥናትም ታደርጋለች።ሥራዎችዋ በሀገር ውስጥ ተወስኖ እንዳይቀር በተለያዩ የውጭ ሀገራትም ደንበኞችን ታፈላልጋለች።
የፈትልና የክር ጨርቆችን በተለያየ ዲዛይን በማዘጋጀት ለደንበኞችዋ በማቅረብ ነው ወደ ሙያው የገባችው። አሁን ላይ ደግሞ ከሐር የተዘጋጁ አልባሳትን ማቅረብ ጀምራለች። ከሐር የሚዘጋጁ አልባሳትን ዲዛይን ወደ ማድረግ የተሸጋገረችው በተለይም ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ ደንበኞች በኩል ያለውን ፍላጎት በማጥናት ነው። የሐር አልባሳት በሙቀት ወቅት ሰውነትን ቀዝቀዝ ያደርጋሉ። ለሰውነት ቆዳ ተስማሚም ጭምር ናቸው። ከዚህ አንጻር በውጭው ዓለም ተፈላጊ ምርቶች ናቸው።
በሐር የሚዘጋጅ ልብስ በክርና በጥጥ ፈትል ከሚዘጋጁት በተሻለ ጠንካራ፣የልማት ሥራውም ከአካባቢ ሥነምህዳር ጋር የተስማማ መሆኑ ሌላው መልካም ጎኑ እንደሆነ በተለያየ መንገድ መረዳትዋን ትጠቅሳለች።ሐር በሀገር ውስጥ ተዘጋጅቶ የሚቀርብ ግብአት መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ለምትፈልገው ሥራ ምቹ ሆኖ ነው ያገኘችው።
ይሁን እንጂ የሐር ግብአት የት ይገኛል የሚለው ጥያቄ ፈጥሮባት ነበር። ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ኩሪፍቱ ሪዞርት ውስጥ የገዛችው ከሐር የተሰራ የአንገት ልብስ(ስካርቭ) አንገቷ ላይ አድርጋ ያዩዋት የውጭ ሀገር ዜጎች በጣም በአድናቆት እንደወደዱት ሲገልጹላትና ለመግዛት የሚገኝበትንም ሲጠይቋት በሐር የተዘጋጀት አልባሳት ዲዛይን አድርጋ ለገበያ ለማቅረብ የበለጠ ፍላጎት አደረባት።
ወዲያውም የሀገር አልባሳት መሸጫ ቦታዎች በመሄድ ከሐር የተሰራ ልብስ ነበር የፈለገችው። ማግኘት አልቻለችም።ብትጠይቃቸውም አላወቁትም። በሽመና የሚሰራ ሥራ ሆኖ ግብአቱ ግን አይታወቅም።ኢትዮጵያ ውስጥ ተሰርቶ እየቀረበ በስፋት አለመታወቁ ለእርስዋም አግራሞት ፈጠረባት።
ወይዘሮ ሰናይት ስለ ሐር አልባሳት ተፈላጊነትና በሀገር ውስጥም ግብአቱ እንደሚገኝ መረጃው ቢኖራትም ልማቱ የት ይከናወናል?የሚለውና ግብአቱን እንዴት ማግኘት እንደምትችል ግን እርግጠኛ አልነበረችም።የሐር አልባሳትን ለማዘጋጀት ጥሬ ግብአቱ የሚገኝበትን ማፈላለግ ሌላው ሥራዋ ሆነ። ይህን ያቃለለላት በአንድ የሥራ አጋጣሚ ያገኘችው በዓለምአቀፍ ሥነ ነፍሳትና ሣይንስ ሥነምህዳር ማዕከል (ኢሲፒ) የተባለ ድርጅት ነው። ድርጅቱ የሚሰራው ሥራ እርሷ ከምትፈልገው ጋር የሚጣጣም ሆኖ አገኘችው።
አጋጣሚውን የፈጠረላት ኢሲፒ ከመንግሥት ጋር በትብብር በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በማህበር ለተደራጁ ሴቶች የሙያ ስልጠና በመሥጠትና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ሐር እንዲያለሙ የሚያግዝ ድርጅት ነው ። ፍላጎትዋን የተረዳው ይኸው ድርጅት የሐር ግብአት እንድታገኝ የሐር ልማት ሥራ ላይ ከተሰማሩ ሴቶች ጋርም ትስስር እንድትፈጥር ሁኔታዎችን አመቻቸላት።ይህ እድል ደግሞ እርስዋን ብቻ ሳይሆን አምራቾችንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ሆኖ ነው ያገኘችው።ኢሲፒ ከሐር አምራች ሴቶች ጋር ከማገናኘት ባለፈ ስልጠና በመሥጠትም ስለሐር ልማትና ጥቅም በተሻለ ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲኖራት በማስቻልም አግዟታል።
እርስዋ እንዳለችው ለሐር ግዥ የውጭ ምንዛሪ ማውጣት አይጠበቅባትም። በራስ አቅም ልማቱን ማካሄድ ይቻላል። ከልማት ሥራው ጀምሮ እርስዋ የተሰማራችበት የፋሽን ኢንዱስትሪ ባለው ሂደት ትስስር በመፍጠር ሰፊ ቁጥር ላለው የሰው ኃይል የሥራ እድል ይፈጥራል። በተለይ ደግሞ ሴቶችን ያሳትፋል። ልማቱም፣ ከሐር የሚገኘው ውጤትም ከሴቶች ለሴቶች መሆኑ ደግሞ ሥራዋን ይበልጥ እንደሚያጎላላት ትገልጻለች።
እርስዋ እንደምትለው፣ልማቱ በቀላሉ በቤት ውስጥ የሚከናወን በመሆኑ ለሴቶች ምቹ ነው። የተወሰነ ስልጠና ካገኙ ከፍተኛ ክህሎት የሚጠይቅ እንዳልሆነና ትሉን ከማርባት ጀምሮ ትሉን ወደ ሐር በመቀየር ፈትለውና አዳውረው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ።
የሐር ልማት የቤት ውስጥ ሥራቸውን እያከናወኑና ሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎች እየሰሩ የሚያከናውኑት ቢሆንም ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገውም ታስረዳለች። ከትሎቹ የሚጠበቀውን ምርት ለማግኘት ሂደቶቹ በጥንቃቄ መከናወን አለበት። ትሎቹ ምርት ለመሥጠት የሚያስችል ደረጃ ላይ እስኪደርሱ መመገብ ይኖርባቸዋል። ምግባቸው በአብዛኛው የጉሎ ቅጠል በመሆኑ አቅርቦት መኖር አለበት። ንጽህናም ያስፈልጋል። ምርቱ ከተገኘ በኋላም ተዳውሮ ነው ለገበያ የሚቀርበው። ልማቱ በግለሰብ ከሚከናወን ይልቅ በማህበር ተደራጅቶ መሥራቱ ከፍተኛ ምርት ለማምረት ያስችላል።
በኢሲፒ አማካኝነት ትስስር ከተፈጠረላት በኋላ ቀጥታ ከሴቶቹ ምርቱን በመቀበል እየሰራች ትገኛለች። ትስስር የፈጠረችው በተለያዩ ወረዳዎች በሐር ልማት በማህበር ተደራጅተው ከሚሰሩ ሴቶች ሲሆን፣ በወርም እስከ 10ኪሎ ግራም ይረከባሉ። በዚህ መልኩ ትስስር ከተፈጠረላት ማህበራት የሐር ክር በመቀበል ሽምና፣ ዲዛይን አድርጋ፣ ከሐር የተሰራ አልባሳትን ለገበያ እያቀረበች ትገኛለች።
ገበያው አልባሳቱን ብቻ ሳይሆን እሴት ያልተጨመረበት ክሩን ብቻ የሚፈልጉ የውጭ ሀገር ደንበኞች መኖራቸውንም በሥራዋ አጋጣሚ ተገንዝባለች።በተለይም ካናዳ አሜሪካን፣ፈረንሳይ ሀገሮች ትስስር መፍጠር የሚፈልጉ ደንበኞችን አግኝታለች።በሁሉም አይነት በሰፊው በማቅረብ ገቢ ማግኘት የሚቻልበት እድል አለ።
ወይዘሮ ሰናይት እንደገለጸችልኝ፤ ከማህበራት የምትረከበውን ክር እሴት ጨምራ ነው ለገበያ የምታቀርበው።ሽመናውንም ሆነ በተለያየ ቀለም ማስዋቡን ሥራ የምታከናውነው እራስዋ ናት። የሚያግዟት ባለሙያዎችም አሏት፤ በብዛት ዲዛይን የምታደርገው የአንገት ልብስ(ስካርቭ) ነው። በወር አንድ ካርቶን ወይንም በነጠላ 100 የአንገት ልብሶችን ነው ለገበያ የምታቀርበው። በዚህ የተገደበችው የግብአት አቀርቦቱ አነስተኛ በመሆኑ ነው። የገበያው ፍላጎት ሰፊ ነው። በምርት አቅርቦት ማነስ ምክንያት ፍላጎትን ማሟላት አልቻለችም። በምትፈልገው ልክ መሥራት አለመቻሏ እርሷም በምትፈልገው ልክ ማደግና በሀገር የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ልታደርግ ያሰበችውን አበርክቶም ለማድረግ አላስቻላትም።
በቂ ምርት ለማቅረብ ያልተቻለበትን ምክንያት እንዳስረዳችው፤ ሥራው ከአየር ፀባይ ጋርም የተያያዘ ስለሆነ አንዱ ችግር ቅዝቃዜ ነው። በተለይ ትሎቹ ሂደታቸውን ጨርሰው ወደ ኩክነት ሲቀየሩ ሙቀት ይፈልጋሉ። ይህን ችግር መቅረፍ የሚቻለው በተለይ የቅዝቀዜ ወቅትን ማለፍ የሚቻለው ለዚህ ሥራ የሚውል ማሽንን በመጠቀም ነው። ይህ ደግሞ አቅም ይጠይቃል።
ወይዘሮ ሰናይት ልማቱ ቢጠናከር በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች የኢኮኖሚ አቅም ፈጥረው ኑሮአቸው ሊቀየር እንደሚችል ታምናለች። በተለይም ለገጠሯ ሴት የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን የሚያግዝ ዘርፍ እንደሆነ ትገልጻለች። በገጠር የሚኖሩ አብዛኞቹ ሴቶች የኢኮኖሚ አቅም የሚፈጥሩበት እድል እንደሌላቸውና የባላቸውን እጅ እንደሚጠብቁ ነው ያስረዳችው።
የሥራ ዘርፉ ደግሞ ልጆቻቸውን እየተንከባከቡ፣ የቤታቸው ሥራም ሳይጓደል የሚሰሩት መሆኑ ደግሞ የበለጠ ተመራጭ እንደሚያደርገው አስረድታለች። ዘርፉ የግለሰቦችን ኑሮ በመቀየር ብቻ ሳይሆን በሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ላይም አበርክቶው ከፍ ያለ እንደሆነ አስምራበታለች።
እዚህ ላይ የመንግሥት እገዛ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ የገለጸቸው ወይዘሮ ሰናይት፤ በተለይም ለትሉ ምግብ የሚውል የጉሎ ቅጠል ለማልማት ሰፊ መሬት እንደሚያስፈልግና ትሎቹንም ተንከባክበው የሐር ክር ለማምረት የመሥሪያ ቦታ እንዲሁም ሥራቸውን የሚያቀላጥፍላቸው የማድረቂያ ማሽን፣መፍተያና ማዳወሪያ መሳሪያዎች የሚያገኙበት ሁኔታ ቢመቻችላቸው ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው ያስረዳችው። የፋሽን ኢንዱስትሪውንም ለማሳደግ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ለማሟላት እንዲሁ የመንግሥት የተለያየ እገዛ እንደሚያስፈልግም ገልጻለች።
የጀመረችውን ሥራ ወደ ኢንቨስትመንት በማሳደግ ለሀገሯ የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ትገኛለች። እቅዷንም እንደገለጸችልኝ ‹‹ሎዛ ሐር››በሚል የሚጠራውን የድርጅቷ ስም ወደ ኢንዱስትሪ ከፍ ብሎ የራስዋንና የሀገሯን ስም ማስጠራት ነው። ለማቋቋም ያቀደችውም ኢንዱስትሪ ለትሎቹ ምግብ የሚውል የጉሎ ተክል የሚከናወንበት መሬት ያካትታል። ልማቱም፣ ሽመናውም፣ ዲዛይኑም፣ የሚዘጋጀው አልባሳትም በአንድ ላይ ሲከናወን ጥራቱን የጠበቀ የሥራ ውጤት ለማግኘት ያግዛል። ኢንዱስትሪው ታዋቂ የሚሆነው ሁሉን አቀፍ ሲሆን ነው።
ለጊዜው ለዚህ እቅዷ ማሳኪያ ይሆናል ብላ የገመተችው እስከ 10ሺ ሄክታር እንደሚያስፈልግ ነው። የሥራ ቦታዋን የመረጠችው ባህርዳር ከተማ ነው። ይሄን እቅዷን ሊያሳካላት የሚችል ቅድመ ጥናቷን (ፕሮፖዛል) በማዘጋጀት የሚመለከታቸውን አካላት ሁሉ በማነጋገር ጥያቄ አቅርባለች።
ሥራው ቦታ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ለሥራው የሚያስፈልጉ የተለያዩ ማሽኖችም ከውጭ በግዥ ማስገባትን ይጠይቃል። ለዚህ ሁሉ ኢንቨስትመንት ደግሞ ከፍ ያለ በጀት ያስፈልጋል። ለዚህ ዝግጁ መሆኗንም ላቀረብኩላት ጥያቄ፤ ለጊዜው እስከ 10 ሚሊዮን ብር ነው የመደበችው። ገንዘቡ ከዚህም በላይ እንደሚጠይቅ ግን ታምናለች። የባንክ ብድርን ታሳቢ በማድረግ ነው የተቀረውን ለማሟላት ያሰበችው። እቅዷን ለማሳካት ከፍተኛ ፍላጎት ስላላት ዝግጁ ናት።
ጥያቄዋ ምላሽ ካገኘ ወደ ግንባታ ሥራው ለመግባት ጊዜ እንደማትወስድ ነው ወይዘሮ ሰናይት የምትናገረው።‹ ‹በሙያው ላይ አለሁ። የሰው ኃይልም አለኝ። ቁርጠኝነቱም ስላለኝ ወደ ኋላ የምልበት ምክንያት የለም››በማለት ነው ተነሳሽነቷን የነገረችኝ፡፡
በኢንዱስትሪ ደረጃ ዘርፉን ለማሳደግ ስታቅድ ለዜጎችም ሰፊ የሥራ እድል እንደምትፈጥር በማሰብ ነው። በተለይም በልማቱ ሥራ ላይ የተሰማሩ እናቶችና ወጣት ሴቶችን ምርታቸውን በመቀበል ብቻ ሳይሆን በስልጠናም በማብቃት አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነች ነው የገለጸችው። ‹‹በራሳቸው እንዲቆሙ እፈልጋለሁ።ጥሩ ሥራም እሰራለሁ ብዬ አስባለሁ›› ስትል ገልጻለች።
ወይዘሮ ሰናይት በሐር ልማት የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮ የመረጃ ምንጮች ስትዳስስ አንዳንዶች የደረሱበትን ደረጃ ስታይ በሀገሬ ቢኖር ብላ እንደምትመኝም ገልጻልኛለች።በተለይም ጃፓኖች በሐር ልማት እና የሐር ውጤቶችን በማቅረብ የተካኑ እንደሆኑ ነው የገለጸችው። ጃፓን ሥራውን በትልቅ ኢንዱስትሪ ደረጃ አሳድጋ ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ በማድረግ እየተጠቀመች እንደሆነ ካገኘችው መረጃ መረዳቷንም አስረድታለች። ፍላጎትና ምኞትዋም እንዲህ ያለውን መልካም ተሞክሮ በሀገሯ እውን ማድረግ ነው።
ወይዘሮ ሰናይት የፋሽን ኢንደስትሪውን ለማሳደግ በምታደርገው እንቅስቃሴ የትዳር አጋሯም በማበረታታት ከጎኗ ሆኖ አጋዧ እንዳሆነ ትገልጻለች።እገዛውንም በዚህ መልኩ ታስረዳለች፣በዘርፉ የሥልጠና እድል ባገኘችበት በአንድ ወቅት አራስ ነበረች።ሥልጠናው የሚሰጠው ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ነው።ባለቤቷ ሥልጠናው እንዳያመልጣት አብሯት በመሄድ ራስዋን ጨምሮ ሌሎቹንም ልጆች በመያዝ ስልጠናዋን እንድትከታተል አግዟታል። በሀሳብም ባለቤቷ ከጎኗ እንደሆነ ነው የገለጸችው።
ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ሰው የሥራ ፍላጎትና የሙያ ፍቅር ሊኖረው ይገባል የምትለው ወ/ሮ ሰናይት፤ ውስጥን ማዳመጥ ከተቻለ እና በስልጠና ከታገዘ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ታስረዳለች።
የሐር ልማት የቤት ውስጥ ሥራቸውን እያከናወኑና ሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎች እየሰሩ የሚያከናውኑት ቢሆንም ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገውም ታስረዳለች። ከትሎቹ የሚጠበቀውን ምርት ለማግኘት ሂደቶቹ በጥንቃቄ መከናወን አለበት።ትሎቹ ምርት ለመሥጠት የሚያስችል ደረጃ ላይ እስኪደርሱ መመገብ ይኖርባቸዋል::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም