አዲሱ የትምህርት ዘመንና የትምህርት ቤቶች ዝግጅት

ተማሪዎች ለሁለት ወራት ያህል እረፍት ላይ ነበሩ። እረፍት ላይ ይሁኑ እንጂ እረፍታቸውን ያሳለፉበት መንገድ ግን ከተማሪ ተማሪ ይለያያል። የገጠር ተማሪ ከከተሜው፤ ከተሜ እራሱ ከመሀል ከተሜው እንደሚለያይ ሁሉ፤ የግል ምርጫ ጉዳይ ሲኖር ደግሞ በአንድ ቤት ውስጥ ያሉ ሁለት ወንድማማቾች በፍላጎት እንኳን እንደሚለያይ ግልፅ ነው። በአብዛኛው ግን ተማሪዎች በአካባቢያቸው በሚገኙ ቤተ መፃህፍት ውስጥ የእረፍት ጊዜያቸውን እንዳሳለፉ ይገመታል።

ተማሪ ላምሮት ኪዳነማሪያም አብዛኛውን የእረፍት ግዜዋን ያሳለፈችው መሀል አራት ኪሎ በሚገኘው አብርሆት ቤተመጻሕፍት ውስጥ ያሉና ለእርሷ የሚስማሙ መፅሃፍትን በማንበብ ነው። ካነበበቻቸው መፅሃፍትም በርካታ ቁምነገሮችን፣ እውቀቶችንና መረጃዎችን አግኝታለች። ላምሮት የክረምቱን ወቅት መፅሃፍቶችን በማንበብ ብታሳልፍም ታዲያ አዲስ ዓመት በመቃረቡና የትምህርት ግዜም ሊጀመር በመሆኑ ቀጣዩ ትኩረቷ ትምህርቷን በትጋት መከታተል ነው። ለዚህም በእረፍት ግዜዋ በሚገባ ራሷን አዘጋጅታለች።

አዎ! መስከረም ለሁሉም ሰው አንድ ሆኖ ለመምህራንና ተማሪዎች ግን ይለያል። የልዩነቱ መሰረት ደግሞ ሌላ ሳይሆን ትምህርት ነው። የትምህርት ተቋማት ለሁለት ወራት ተዘግተው ዳግም የሚከፈቱት በአዲሱ ዓመት በወርሃ መስከረም ነው። ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመለሱት አዲስ ዓመት ሲገባ ነው። የዘንድሮው የትምህርት ዘመን መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጀመርም በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ተገልጿል። ትምህርት ቤቶችም ዝግጅታቸውን እያጧጧፉ ይገኛሉ።

በመስከረም ወር ወደ ትምህርት ገበታቸውና አዲስ ወደ ተዛወሩበት የክፍል ደረጃ እንደሚገቡ ያወቁ ተማሪዎች ትምህርት ቤት ተከፍቶ ከጓደኞቻቸው ጋር ለመገናኘት ናፍቀዋል። የአዲሱ ክፍል ትምህርታቸው ምን እንደሚመስል ለማወቅ ልባቸው ተሰቅሏል። ምን አይነት መምህር ለምን አይነቱ ትምህርት እንደሚመደብላቸው ለማየት ጉጉታቸው ከጣራ በላይ ሆኗል። ትምህርት ቤት ነገ ቢከፈት ደስታቸው ነውና ለእነርሱ መስከረም 3 ሩቅ ነው።

ይህ እንዳለ ሆኖ ታዲያ አዲሱ ዓመት መጥቶ፣ በመማር-ማስተማር ሂደት እንቅስቃሴ ውስጥ ወሳኙን ሚና የሚጫወቱት፣ ትልቁንም ድርሻ የሚይዙት ትምህርት ቤቶች መሆናቸው ግልፅ ነው። “የትምህርት ገበታ” የሚለውም የሚያመለክተው ይህንኑ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። የዛሬው ጽሑፍም የበለጠ በትምህርት ቤቶች ላይ ያተኩራል።

የትምህርት ቤቶች መከፈቻ ይፋ የተደረገበት ቀን አገር አቀፋዊ ይዘት ያለው ቢሆንም በጊዜና ስፍራ ውስንነት ምክንያት አዲስ አበባ ያሉ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶችን ዝግጅት ብቻ ወስዶ መመልከቱ በቂ ነው። ይህም የተደረገው በአጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ገፅታቸውም ሆነ እንቅስቃሴና ተግባራቸው በአብዛኛው ተመሳሳይ እንደ መሆኑ ጥቂቶቹ አብዛኛዎቹን ትምህርት ቤቶች ይወክላሉ በሚል መነሻ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በተያዘላቸው ቀነ ቀጠሮ መሰረት ተከፍተው፤ ተማሪዎች ወደየ ትምህርት ቤታቸው መጥተውና አስፈላጊው አቀባበል ተደርጎላቸው የመማር ማስተማሩን ተግባር ለመጀመር ተፍ ተፍ እያሉ ነው። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት እና አፀደ ህፃናት ነው።

የትምህርት ቤቱ መምህርና የመምህራን ልማት ምክትል ርእሰ መምህር አቶ መስፍን ገብረእግዚአብሄሔር እንደሚሉት፣ ተማሪዎችን በጥሩ ሁኔታ ለመቀበል የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። በተለይም የትምህርት ቤቱን አጠቃላይ ሁኔታ መቀየርን በተመለከተ እየተሰሩ ያሉ በርካታ ስራዎች አሉ። ከነዚህ ውስጥም የመማሪያ ክፍሎችን ከማስዋብና ምቹ ማድረግ አንዱ ነው። ሁሉ ነገር አልቆ የመማሪያ ክፍሎች ለእድሳት ዝግጁ ተደርገዋል። ጨረታውን ያሸነፈው አዳሽ ድርጅትም ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ስራ የሚያስገባው በር ላይ ቆሟል።

ከአምናው የትምህርት ቤት ዝግጅት የዘንድሮው የሚለየውም ይሄው የመማሪያ-ማስተማሪያን ስፍራን ምቹና ማራኪ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራ ነው። ይህ ደግሞ ተማሪዎች ወደትምህርት ቤት ሲመጡ ልዩ ስሜት እንዲፈጥርባቸውና ከአምናው የበለጠ ዘንድሮ በትምህርትቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

እንደ ምክትል ርእሰ መምህሩ ገለፃ ትምህርት ቤቱ ተመራጭ እንደመሆኑ መጠን ዘንድሮ በርካታ አዳዲስ የአፀደ ህፃናት ተማሪዎች ለምዝገባ መጥተው ባሉት ጥቂት ክፍት ቦታዎች እንዲመዘገቡ ተደርጓል። ከነበሩት የቢሮና የማስተማሪያ ክፍሎች በማሸጋሸግና ማቻቻል አንድ ራሱን የቻለና ስልሳ ተማሪዎችን የሚያስተናግድ ክፍል ተዘጋጅቷል። የቦታ ችግር በቀጣይ የሚቀረፍ ከሆነ ደግሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ከፍ ይላል። ዘንድሮም የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ወደ 991 ከፍ ብሏል። የትምህርት ጥራትን በማሻሻልና ተማሪዎችን በማብቃት ላይ ጠንከር ያለ ስራ በመስራት የከፍተኛ ውጤት ባለቤት ለመሆንም ርብርብ ይደረጋል። ከትምህርት አይነቶችና ይዘቶች አኳያም ዘንድሮ በተወሰኑ የትምህርት አይነቶች ላይ ማሻሻያ ተደርጓል። ለዚህም የአፋን ኦሮሞ ትምህርት አሰጣጥና የሚሰጥባቸው ክፍሎች ተለይተዋል።

ቀደም ባሉት ዓመታት አፋን ኦሮሞ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ክፍል ደረጃ ነበር የሚሰጠው። በመጪው አዲስ ዓመት ግን ከ3ኛ እስከ 8ኛ ክፍሎች ድረስ ይሰጣል። ከ3ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ደረጃ በሳምንት 3 ክፍለ ጊዜ፣ ለ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ደግሞ በሳምንት 2 ክፍለ ጊዜ እንዲሰጥ ከትምህርት ቢሮ በተላለፈ ደብዳቤ ተገልጿል። በዚሁ መሰረትም ትምህርቱ የሚሰጥ ይሆናል። የአፋን ኦሮሞ ትምህርት እንደ አንድ የትምህርት አይነት የሚሰጥ እንደመሆኑ መምህራን ስለሚያስፈልጉ ትምህርት ቤቱ የቅጥር ማስታወቂያ አውጥቶ የአፋን ኦሮሞ መምህራንን በመቅጠር ሂደት ላይ ይገኛል።

ዘንድሮ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሌላም ተጨማሪ ለየት ያለ ነገር ለመስራት የታቀደ ሲሆን ይኸውም ለመምህራን ከፍተኛ የደሞዝ ማሻሻያ ማድረግ ነው። ለመምህራን ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ ለማድረግ የታሰበውም ዘንድሮ ወላጆች 60 ከመቶ የተማሪ ክፍያ በመጨመራቸው ነው። ጭማሪውም ለውስጥ ስራ፣ ለመምህራንና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ደሞዝ ይውላል። ይህም መምህራንና ሰራተኞች በተነቃቃ ስሜት ስራቸውን እንዲሰሩ ያደርጋል። በተማሪዎች በኩልም ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል።

የዳግማዊ ምኒልክ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አቶ ኤፍሬም አይተንፍሱ በበኩላቸው እንደሚናገሩት አንጋፋው የዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ልምድና አቅም ያለው ነው። በትምህርት ቤቱ የመምህራን ቁጥርም ሆነ የትምህርት ጥራት ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከ80 በመቶ በላይ መምህራን የሁለተኛ ዲግሪ /ኤ ም ኤ/ ባለቤቶች ናቸው። ከዚህ አንፃር የዘንድሮውን የትምህርት ዘመን ለመጀመር ዝግጅቱ ጥሩ ነው።

አጠቃላይ የዘንድሮውን ዓመት የትምህርት ዝግጅት ለመጀመር መርሀ ግብር ወጥቶ እየተሰራ ነው። ከነሀሴ 23 እስከ ጷጉሜ 3 ቀን 2015 ዓ.ም ምዝገባ መካሄድ አለበት በተባለው የግዜ ሰሌዳ መሰረት እየተካሄደ ይገኛል። የዘንድሮውን የምዝገባ ፕሮግራም ከዚህ ቀደም ከነበሩት ለየት የሚያደርገውም ፕሮግራሙ ከተማ አቀፍ በመሆኑ ነው። ዳግማዊ ሚኒልክን ጨምሮ በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ ትምህርት ቤቶች በሙሉ ምዝገባቸውን የሚያካሂዱት በእነዚህ ቀናት ነው። በዚህ ዓመት የሚካሄደው ምዝገባም በሶፍትዌር የተደገፈ የዳታ ምዝገባ ስርዓትን የተከተለ ነው።

ከዚህ አንፃር የዘንድሮው ምዝገባ እንደ ቀድሞው ጊዜ የተማሪው መማር ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም። ምዝገባው የተማሪውን አጠቃላይ ፕሮፋይል ያካትታል። የቤተሰቡንና የራሱን ሁኔታ፣ ወደ ትምህርት ቤት ሲመጣ ስንት ኪሎ ሜትር እንደሚጓዝ፣ አካላዊ ጤንነቱንና የመሳሰሉትን ጉዳዮችን ሁሉ አካቶ ይይዛል። ሌሎች ተማሪውን የሚመለከቱ መረጃዎችም ይመዘገባሉ። ይኸው የምዝገባ ስርዓት ገና ዘንድሮ ወደ ስራ የገባ ነው።

ርእሰ መምህሩ እንደሚያብራሩት ትምህርት ቤቱ ዘንድሮ ባጠቃላይ 2 ሺህ 200 ተማሪዎች ይኖሩታል። ይህም ከዚህ በፊት ከነበረው በቁጥር ከፍ ያለ ነው። የተማሪ/መምህር ጥምርታ አንድ ለአርባ (1 መምህር ለ40 ተማሪዎች) መሆን እንዳለበት ከግንዛቤ ውስጥ ገብቶ ስራ እየተሰራ ነው። ነገር ግን 2 ሺህ 200 ተማሪ ጥምረቱን ትንሽ ከፍ ስለሚያደርገው እዚህ ላይ ትንሽ መስራት ያስፈልጋል። የመምህራንን ቁጥርም መጨመር ይገባል። እንዲያም ሆኖ ግን ዘንድሮ ያን ያህል የጎላ ችግር አይኖርም። 2 ሺህ 200 ተማሪዎችን በአግባቡ ተቀብሎ ማስተናገድ የሚቻልበት እድል አለ።

ባለፈው ዓመት 561 ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ወስደው 79ኙ ብቻ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል። ይህ እንደ አገር፣ ማለትም ከሌሎች ት/ቤቶች ጋር በንፅፅር ሲታይ፣ ጥሩ ውጤት የሚባል ነው። እንደ ትምህርት ቤት ከታየ ግን ብዙ መስራት ይቀራል። በመሆኑም፣ በዚህ ዓመት ይህንን ቁጥር በመቀየር ከፍ ያለ ውጤት ለማምጣ ስራ እየተሰራ ነው። ከመምህሩ ጀምሮ፣ የትምህርት ክፍሎችና በየደረጃው ያሉት ሁሉ መግባባት ላይ ደርሰው ለ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።

በቀጣዩ አዲሱ የትምህርት ዘመን አማርኛን በአፍ መፍቻነት የሚማሩ ተማሪዎች አፋን ኦሮሞን በሁለተኛ ቋንቋነት ይማራሉ። አፋን አሮሞን በአፍ መፍቻ ቋንቋነት የሚማሩ ተማሪዎች ደግሞ አማርኛን በሁለተኛ ቋንቋነት እንዲማሩ ይደረጋል። ይሁንና የትምህርት ቤቱ ዋነኛ ስጋት ምናልባት የአፋን ኦሮሞ ተማሪዎች ቁጥር የሚፈለገውን ያህል ካልሆነ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ትምህርት ቤቱ እንደተጨማሪ ችግር የሚያየው የመማሪያ-ማስተማሪያ መጻሕፍት እጥረት ወይም አለመኖር ነው። በአሁኑ ግዜም ከፍተኛ የመማሪያ-ማስተማሪያ መፃህፍት እጥረት ይታያል። የህትመት ችግር አለ በሚል መፅሃፎች በፒ ዲ ኤ ፍ የተሰራጩ ነው። ይህም ቢሆን የተሟላ አይደለም። አንዳንዱም ከመሃል ምእራፍ ይጎለዋል። በዚህ መልኩ መፅሃፍቶቹን ለተማሪው ለማድረስም ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል።

ለመጻህፍቱ እጥረት የሚነገረው ወይም የሚሰጠው መልስ ውስብስብና በአብዛኛው ከህትመት ጋር መጨመር ጋር የተያያዘ ነው። ከዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲፈቱና የመፃህፍት እጥረቱ እንዲቃለል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግሮች እየተካሄዱ ነው።

እንደ ርእሰ መምህሩ ገለፃ ይህንን ትምህርት ቤቱን ለማሻሻል በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ። ትምህርት ቤቱን ለማሻሻል የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች፤ ማህበረሰቡ፣ የተማሪ ወላጆች፣ እራሳቸው ተማሪዎችና አስተማሪዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል። ተሳትፏቸው አሁንም ቀጥሏል። የተማሪ ወላጆችም የልማት ክፍያ በመፈፀም ለትምህርት ቤቱ ያላቸውን አጋርነት እያሳዩ ይገኛሉ። ይህም የሚሆነው መንግስት ሁሉንም ነገር ለብቻው ማሟላት ስለማይችል ነው። ለዚህም ነው ህብረተሰቡ በዚህ ተግባር አምኖ ገንዘብ እያዋጣ ያለው። የተሻለ ተቋም ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ የሚገባ መሆኑን ስለተገነዘበ ነው በትምህርት ቤት ልማት የሚሳተፈው።

የክረምቱ ወቅት አልፎ ወደ በጋው እየመጣ ነው። ተማሪውም የእረፍት ጊዜውን አገባዶ ወደ ትምህርት ቤት ለመግባት በዝግጅት ላይ ነው። በተመሳሳይ ትምህርት ቤቶችም ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁና ተማሪዎቻቸውን ከደጅ ለመቀበል አቆብቁበው እየተጠባበቁ ይገኛሉ። መስከረም ሁሉንም በሠላም ያጨባብጣቸው ዘንድ ደግሞ የሁሉም ሰው ምኞች ነው። መልካም አዲስ ዓመት!!

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 29/2015

Recommended For You