በኢትዮጵያ የግብርናው ሥራ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሁለት ዋና ዋና ወቅቶች ተከፋፍሎ ነው በስፋት ሲከናወን የኖረው፤ በበልግና በመኸር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የበጋ ወቅት የመስኖ ስራ ሌላው ሰፊው የግብርና ስራ ሆኖ መጥቷል።
ሀገሪቱ አሁን በመኸር ወቅት የግብርና ስራ ላይ ትገኛለች። ክረምት ወይም የመኸር ወቅት የግብርናው ስራ በስፋት የሚከናወንበት እንደመሆኑ ይህ ወቅት አርሶ አደሩ ዝናብ፣ ብርድ፣ ጭቃ ሳይል ቀን ከሌት የሚተጋበትና ነገን ተስፋ አርጎ የሚሰራበት ነው። በሰኔና ሐምሌ የበረታ ገበሬ የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱን ያገኛል። ለዚህም ነው አርሶ አደሩ በዚህ ወቅት በሕይወቱ ትርጉም ያለው ሥራ የሚሰራው፤ ለከተሜውም በአጠቃላይም ለሀገር የሚተርፍ ተግባር የሚያከናውነው።
የግብርና ስራ የሀገርና ህዝቧ ዋልታና ማገር መሆኑን የተገነዘበው መንግስትም ከአርሶ አደሩ ባልተናነሰ ለእዚህ ወቅት የግብርና ስራ ተግቶ ይሰራል። የግብርናው ዘርፍ ተዋንያንም በዚህ ወቅት ላይ ለአርሶ አደሩ መረጃ በማድረስ፣ ቴክኖሎጂ በማቅረብ፣ ምክር በመስጠት፣ ሌሎች የተለያዩ ድጋፎችን በማቅረብ በትኩረት ይሰራሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚትሮሎጂ ኢንስቲትዩትና የግብርና ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ሰሞኑን ከሰጡት መግለጫ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው።
የኢትዮጵያ ሚትሮሎጂ ኢንስቲትዩት በመግለ ጫው መነሻውን ያደረገውም ያለፈውን ዓመት የክረምት ወቅት ትንበያ ነው። እስከ ቀጣዩ በጋ ድረስ የዘለቀ ትንበያም ተሰጥቷል። እስከ 2016 ዓ.ም ያለው የበጋ ወቅት ጭምር ምን ያህል መጠን ያለው ዝናብ በየትኛው አካባቢ ይኖራል በሚለው ላይ ሰፊ ትንታኔ ሰጥቶበታል።
በተመሳሳይ የትንበያው ቀጣይነትም በመድረኩ ላይ በምን መልኩ እንደሚከናወን የተነሳ ሲሆን፤ ግብርና ሚኒስቴርም ከወጡት ትንበያዎች ጋር በተያያዘ የግብርና ሥራውን በምን መልኩ እያስኬደ እንደሆነ፤ ቀጣይ የሚሰሩ ሥራዎችና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ መረጃዎችን በሚኒስቴሩ በሚኒስትር ዴኤታው በኩል አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ ለተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት የሚሰጠውን ወቅታዊ የአየር ጠባይ ትንበያ አገልግሎትን ይበልጥ ለማጠናከር በተለይም ለአየር ሁኔታና ጠባይ ተጋላጭ የሆኑ ተቋማትን ከየተቋማቸው አኳያ በተሰጠው ትንበያ መሰረት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ለማስቻል በየወቅቱ የአየር ጠባይ ግምገማ ያደርጋል፤ ምክረ ሀሳብም ይሰጣል። ከዚህ አኳያም ብዙ ሥራዎች ውጤታማ ሆነው ታይተዋል። በተለይም ከግብርናው ጋር በተያያዘ ብዙ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማሳየት ተችሏል።
የባለፈው ክረምት 2014/15 ዓ.ም ወቅትን ብቻ ብንመለከት በተሰጠው ትንቢያ መሠረት ዝናቡ እንደተጠበቀው በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ላይ ቀድሞ መጀመሩን አስታውሰው፣ የዝናቡ መጠንና ስርጭትም በአብዛኛው የሀገሪቱ የወቅቱ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ የተስፋፋና የተጠናከረ እንደነበር ጠቅሰዋል። ከሰኔ እስከ ነሐሴ የነበረው ዝናብም ለክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ መስጠቱን ገልጸው፣ በዚህም አርሶ አደሩ በተገቢው መጠን እንዲጠቀምበት ማስቻሉን አብራርተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የክረምቱ ወቅት መደበኛ ዝናብ ብቻ ሳይሆን ከባድ መጠን ያለው ዝናብም አስተናግዷል። ስለዚህም የተሰጠው ትንበያ ይህ ባጋጠማቸው መካከለኛው፤ ሰሜን ምስራቅ እና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የጎርፍ ክስተት ስለነበረ ቅድመ ማስጠንቀቂያው ደርሷቸው ከአደጋ ድነዋል። ትንበያው እለታዊ ተጽእኖውን መቋቋም እንዲቻልም አድርጓል ይላሉ። በተጨማሪም ያለውን አወንታዊ ነገር ያሳየ በመሆኑ ማለትም ቀጣዩ ወቅት እርጥበትን የያዘ እንደሚሆን በመንገሩ አርሶአደሩ ያንን እድል እንዲጠቀምበትም ማስቻሉን ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያመለከቱት።
አቶ ፈጠነ የዘንድሮ የክረምት ዝናብም እንዲሁ ያለውን ትንበያ መሰረት ያደረገ መሆኑን አንስተዋል። እርሳቸው እንዳሉትም፤ ይህ ወቅት በምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ እንዲሁም በሰሜን ምስራቅና የምስራቅ መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ ይስተናገድበታል። በአንዳንድ አካባቢዎች ይኸው የመኸር ወቅት ዝናብ በከፍተኛ ሁኔታ ተለዋዋጭነት የሚያሳይበት ሁኔታም ይኖራል። ይህም ሁኔታ እንዲፈጠር የሚያደርገው የትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት ከመደበኛው በላይ መሆኑ ነው። ስለዚህም ኢሊኖ የመሆን አጋጣሚን ይፈጥራል። ይህ ደግሞ ለአርሶ አደሩ የግብርና ሥራ እንቅስቃሴ እንዲሁም ለተፋሰሶች የውሃ አቅርቦት በማሻሻል ረገድ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል።
አቶ ፈጠነ የመጪውን የበጋ ማለትም የ2016 ዓ.ም የአየር ጠባይ ትንበያን በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ በዚህ ትንበያ መሠረትም ‹‹ መጪው በጋ የትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ ከመደበኛ በላይ የባህር ወለል መሞቅ ስለሚያመጣ ኢሊኖ ይፈጠራል። ይህ ደግሞ የሰሜናዊ ህንድ ውቅያኖስ ከመደበኛ በላይ የባህር ወለል የሙቀት መጠን አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ። ስለዚህም አርሶአደሩና በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ማንኛቸውም ሰራተኞች የወቅቱ ዝናብ አጀማመር በአብዛኛው የበጋ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ቀድሞ እንደሚጀምር አውቀው ልዩ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል›› በማለት አስረድተዋል።
ዝናቡ በአወጣጥ ደረጃም ይዘገያል ያሉት አቶ ፈጠነ፤ በዚሁ መሰረት የዘንድሮ የበጋ ወቅት ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራል ሲሉ ጠቁመው፣ ይህንን አጋጣሚ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ። በተመሳሳይ የምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖርባቸው ተናግረው፣ ከዚህ አኳያም ሁኔታውን አውቆ መስራት እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ።
በአሁኑ ወቅት እየተስተዋሉ ከሚገኙት የአየር ሁኔታ ክስተቶች በመነሳት በሰሜን፤ በመካከለኛው፥ በምስራቅና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊፈጠር እንደሚችልም ዋና ዳይሬክተሩ ይጠቁማሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን በሰሜን ምስራቅ፤ መካከለኛውና በምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ ከአምስት ዲግሪ ሴልሽየስ በታች ሊሆን እንደሚችል ያመላክታሉ። ከዚሁ ጋር አያይዘው ህብረተሰቡ በሚቀጥለው የበጋ ወቅት የሚጠበቀውን የአየር ጠባይ ትንበያን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እና የሚገኘውን የዝናብ መጠንና ሰርጭት በአግባቡ በመጠቀም በዚህ ወቅት የሚካሄደውን የግብርና እንቅስቃሴ እና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎችን ከባለሙያዎች ጋር በመመካከር መከወን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትሮዎሎጂ ኢንስቲትዩት በየጊዜው የሚያወጣቸው መረጃዎች ለግብርና ሥራው እጅግ ወሳኝ ናቸው። በመሆኑም መረጃዎቹን መሰረት በማድረግ እንደ ግብርና ሚኒስቴር በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። አንዱ ደግሞ በዚህ በመኸር ወቅት የተከናወነው ተግባር ነው።
ትንበያው በሰጠው መረጃ መሰረት ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል አንዱ ከዝናብ ጋር ተያይዞ የተሰራው ሥራ ሲሆን፤ ያጋጠሙ ችግሮችን በተለያየ መልኩ ለመፍታት ተሞክሯል። የዝናብ እጥረት ሲያጋጥም እጥረቱ ያጋጥማቸዋል በተባሉ አካባቢዎች ላይ ሌሎች የውሃ አማራጮችን መጠቀም የሚያስችሉ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል። በተመሳሳይ ከአየር ንብረቱ ጋር የሚስማሙ ሰብሎች እንዲዘሩ የማድረግ ሥራም ተከናውኗል። ይህ ደግሞ አርሶ አደሩ ችግሩን በመፍትሄ እንዲያቀለው አድርጎታል ይላሉ።
ዶክተር መለሰ አክለውም፤ ትንበያው በሰጠው መረጃ መሰረት መሥራት የተባይ ክስተት ከመከላከል አኳያም ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውቀዋል። ለአብነት በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ በነበረ የዝናብ ወጣ ገባነት ምክንያት ተምች ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው፣ ቀድሞ መረጃው ስለነበርና መሬቱ እርጥበት የያዘበት ሁኔታ በመፈጠሩ ክስተቱ ቢፈጠርም ምንም አይነት ጉዳት ሳያስከትል መከላከል ተችሏል ብለዋል። በሌላ በኩል የበረሃ አንበጣ ክስተትም የተፈጠረ ቢሆንም ይህንንም ክስተት እንዲሁ ጉዳት እንዳያደርስ ተደርጎ መመከት ተችሏል ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የበረሃ አንበጣው የተፈጠረበት ምክንያት ደረቃማ ሁኔታዎች በመኖራቸው የተነሳ ነው። በተለይ በሀገሪቱ ሰሜናዊው ክፍል ችግሩ በስፋት ታይቷል፤ ከጅምሩ ለማጥፋት ትንበያው ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። የአየር ጸባይ ትንበያው መረጃ በመኖሩ ምክንያት እየተከታተሉ መከላከል ላይ የመስራት ተግባር ተከናውኗል። በዚህ ደግሞ አሁን ላይ መጀመሪያ የተከሰተበትን ትግራይን ጨምሮ አፋርና አማራ ክልልን ከአንበጣ ነጻ ማድረግ ተችሏል።
ይህ የበረሃ አንበጣ በሌሎች አካባቢዎች ላይ እየታየ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ቀደም ብሎ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ የለም ይባል እንጂ ዳግመኛ አይከሰትም ተብሎ መወሰድ እንደሌለበት ተናግረዋል፤ በቀጣይም እነዚህ አካባቢዎች ላይ ዝናብ ወጣ ገባ ሊሆን እንደሚችል የአየር ትንበያው እንደሚያሳይ ጠቅሰው፣ በዚህም ላይ ቀደም ብሎ እንደተሰራበትና ጉዳት ሳያደርስ ችግሩን መመከት እንደተቻለ ሁሉ አሁንም ለሚከሰቱ ችግሮች በተጠንቀቅ ሆኖ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
እንደ ግብርና ሚኒስቴር እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ትንበያዎች በሚያመላክቱት መልኩ የሚሰራ ይሆናል። በሰው ኃይል፣ በአውሮፕላን እንዲሁም በኬሚካል የመከላከል ሥራውም ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የዝናብ ሁኔታው ትንበያ እየታየ ክትትልና ቁጥጥርም የሚደረግ ይሆናል ብለዋል። በተለይም የአንበጣ መንጋው ከዚህ በፊት ያደረሰው ጫና ስለሚታወቅ እጭ ጥሎ እንዳያድግ ከማድረግ አኳያ ግብርና ሚኒስቴር በሁሉም ሁኔታ ራሱን አዘጋጅቶ አሰሳ እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በየጊዜው የሚሰጠው ትንበያ በተለይም ለግብርናው ሥራ ወሳኝ መሆኑን የሚናገሩት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ በሚሰጠው ትንበያ መሠረት ቅድመ ዝግጅት ሁሌም እንደሚደረግና ሚኒስቴሩ እየተጠቀሙበትም እንደሆነም ያስረዳሉ። ለዚህም አብነት የሚያደርጉት ደግሞ በክረምት ወቅት በተሰጠው ትንበያ መሠረት ለግብርናው እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ዝግጀት በማድረግ ውጤት መመዝገቡን ነው።
15 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ለተቻለበት ሁኔታ ትንበያው አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰው፤ አሁንም ዘር በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ላይ ትንበያውን መሰረት በማድረግ እየተሰራ መሆኑ ጠቁመዋል።
በመርሃግብሩ ላይ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ የአደጋ ስጋቶችን ቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮረ “ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለሁሉም” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክት ተግባራዊ እንደሚደረግም ተጠቁሟል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃም አዱኛ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ “ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለሁሉም” የሚለው ፕሮጀክት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረ ነው። የሰው ልጅ ከአስጊ የአየር ሁኔታ፣ ከአየር ንብረት ክስተቶችና ከውሃ ዑደት ለውጥ ጋር በተገናኘ ከሚከሰቱ ችግሮች እንዲጠበቅ የሚያደርግ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ ከውሃና አየር ንብረት ለውጥ ክስተቶች ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቀነስና የተጎጂውን ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ ያግዛል።
ፕሮጀክቱ በዓለም የሜቲዎሮሎጂ ድርጅት ዋና አስተባባሪነት የሚተገበር ሲሆን፤ ለፕሮጀክቱ 30 ሀገራት ተመርጠዋል። ከእነዚህ መካከልም በአፍሪካ ደረጃ ምርጫው ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ዩጋንዳ ናቸው። ኢትዮጵያ በዚህ ፕሮጀክት ተመራጭ እንድትሆን ያደረጋት ደግሞ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያደረገች ያለችው አስተዋጽኦ እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ እንደሆነ ዶክተር አብረሃም ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ ከ2023 እስከ 2028 ለአምስት ዓመታት እንደሚቆይም አስረድተዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2015