‹‹አሁን የተከሰተው የአንበጣ መንጋ የዛሬ ሶስት ዓመት ከተከሰተው ጋር የሚነጻጸር አይደለም ››አቶ ፈለገ ኤሊያስ – የምስራቅ አፍሪካ የበርሃ አንበጣ መከላከያ ድርጅት ከፍተኛ ባለሙያ

አንድ ጎልማሳ የበርሃ አንበጣ በየቀኑ የራሱን ክብደት ያህል ማለትም ሁለት ግራም ምግብ የሚበላ ሲሆን፣ አማካይ ብዛት ያለው የበርሃ አንበጣ መንጋ ደግሞ የ10 ዝሆኖች ወይም የ25 ግመሎች ወይም 25 ሺህ ሰዎች በቀን ውስጥ የሚመገቡትን ምግብ ይጨርሳል። በወረርሽኝ ወቅት የበርሃ አንበጣ መንጋ እሰከ 29 ሚሊየን ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሰፊ መሬት በመያዝ ወደ 60 ሀገራት ውስጥ የመሰራጨት አቅም አለው እንዳለው የዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት መረጃ ያመላክታል ። ይህም የዓለማችን 20 በመቶ መሬት ማለት ሲሆን፣ የዓለማችንን 10 በመቶ ሕዝብ ኑሮ ያስተጓጉላሉ እንደማለትም ነው።

ሴት የበርሃ አንበጣ ከ95 እስከ 158 እንቅሏል የምትጥል ሲሆን የበርሃ አንበጣ መንጋ በነፋስ እየታገዘ በሰዓት ከ16 እስከ 19 ኪሎ ሜትር ሊጓዝ የሚችል ነው፣ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ከ5 እስከ 130 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላል።

በአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ የበርሃ አንበጣ መንጋ ውስጥ ከ40እስከ 80 ሚሊዮን የሚገመቱ አንበጣዎች ይገኛሉ። የበርሃ አንበጣ መንጋ በአየር ሁኔታ እና ሥነ ምኅዳር ላይ መሠረት በማድረግ ከሦስት እስከ አምስት ወራት በሕይወት መቆየት ይችላል።

እ.ኤ.አ እስከ 1921 ድረስ ሁለት ዓይነት የበርሃ አንበጣ መንጋ ዝርያዎች ብቻ የነበሩ ቢሆንም አሁን ላይ የአፍሪካ፣ የሩቅ ምሥራቅ፣ ቀይ የምሥራቅ አፍሪካ፣ ቡናማ የደቡብ አፍሪካ፣ የሞሮኮ፣ የቦምቤይ፣ የአውስትራሊያ እና የዛፍ የሚባሉ ክፍፍሎች አላቸው።

የበርሃ አንበጣ መንጋ አጭር ቀንድ መሰል ነገር የያዙ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ዝርያዎች አሉት። የበረኃ አንበጦች በዓመት ከ200 ሚሊ ሜትር በታች ዝናብ በሚያገኙ ከፊል ደረቅ እና ደረቃማ የአፍሪካ ክፍሎች፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና ደቡብ ምዕራብ እስያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ይህም አካባቢ በድምሩ 16 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው መሬት እና 30 አገራት የሚያካትት ነው።

የአንበጣ መንጋን ለመበተን ከሚያስችሉ ዘዴዎች መካከል በጎን በኩል ሆኖ ማባረር፣ የአንበጣ መንጋ አንድን አካባቢ ሊለቅ የሚችለው የመንጋውን ሥርዓት እንዲዘበራረቅ በማድረግ ነው። የአንበጣ መንጋን ከኋላ ሆኖ ማባረር እንደማይጠቅም ጥናቶች አረጋግጠዋል። በመሆኑም ከጎን በኩል በመግባት የመንጋውን ሥርዓት ማዛባትና ክፍፍል መፍጠር መንጋው በቀላሉ አንድን አካባቢ እንዲለቅ ለማድረግ ያግዛል። ከጀርባ ለማባረር መሞከር እንደ መንዳት ይቆጠራል ጠቀሜታው ዝቅተኛ ነው።

ሌላው ከፍተኛ ድምፅ ማሰማት ሲሆን የአንበጣን መንጋ ከፍተኛ ድምፅ ያስበረግገዋል። በመሆኑም የጥይት ድምፅ፣ ጥሩንባ እና ጩኸት ማሰማት ጠቃሚ ናቸው። ጎማ ማቃጠል ምንም እንኳን ከአካባቢ ብክለት አንፃር የሚመከር ባይሆንም ጎማ ማቃጠል ግን የአንበጣን መንጋ እንደሚያስበረግግ ጥናቶች ያሳያሉ።

ሌላው ፀረ-ተባይ መድሃኒቶችን መጠቀም ነው፤ ከላይ ከተጠቀሱት ባህላዊ የመከላከያ እርምጃዎች በተጨማሪ በሰው አቅም፣ በመኪና እና በአውሮፕላን የሚረጩ ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን መጠቀም ሳይንሳዊ አማራጭ ነው::

እኛም ካለፉት ሶስት ዓመት ወዲህ ሀገራችን ላይ መለስ ቀለስ የሚለው የበርሃ አንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ከፍ ያለ ጉዳትን እያስከተለ መሆኑን በመገንዘብ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የምስራቅ አፍሪካ የበርሃ አንበጣ መከላከያ ደርጅት ምን እየሰራ ነው? ስንል በድርጅቱ የመረጃና ትንበያ ከፍተኛ ባለሙያ ከሆኑት አቶ ፈለገ ኤልያስ ጋር ቆይታን አድርገናል።

 አዲስ ዘመን፦ የምስራቅ አፍሪካ የበርሃ አንበጣ መከላከያ ድርጅት ዋና የስራ ኃላፊነቱ ምንድን ነው? ከሚለው እንነሳ

አቶ ኤልያስ፦ የምስራቅ አፍሪካ የበርሃ አንበጣ መከላከያ ድርጅት እኤአ በ1962 በዘጠኝ አባል አገራት የተመሰረተ ድርጅት ነው። እነዚህ አባል አገራትም ኤርትራ፤ ጅቡቲ፤ ኢትዮጵያ፤ ኬንያ፤ ደቡብ ሱዳን፤ ሱዳን፤ ሶማሊያ፤ ታንዛኒያና ኡጋንዳ ናቸው።

ድርጅቱ ለመቋቋሙም ዋናው ምክንያት የበርሃ አንበጣ በአንድ ቦታ ተወስኖ የማይቆም፤ ከሀገር ሀገር የሚዞር ድንበር የማያግደው በመሆኑና ይህንን ለመቋቋም የተመሰረተ ድርጅት ነው። ድርጅቱ የሚሰራቸው ስራዎችም በዋናነት የበርሃ አንበጣን መከላከል ቢሆንም አንበጣ የሚከሰተው ግን ሁለት አልያም ሶስት ዓመታትን እየቆየ በመሆኑ በተጓዳኝ ለምን ሌሎች ጸረ ሰብል የሆኑ ተባዮችን አካቶ አይሰራም በሚል የግሪሳ ወፍን፣ ተምችን እንዲሁም ጸጸፍላይን በመሳሰሉት ተውሳኮች ላይ እንዲሰራ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

ዋናው ስራውን እነዚህ ፀረ ሰብል የሆኑ አካላትን በአየር ላይ የማሰስና የመከላከል ስራ ሲሆን ይህንን ተግባር የሚያከናውንባቸው አውሮፕላኖች አሉት፤ ምንም እንኳን እነዚህ አውሮፕላኖች አሮጌ ቢሆኑም በዘንድሮ ዓመት ግን አንድ አዲስ አውሮፕላን ለማግኘት ተሞክሯል።

ሌላው ድርጅቱ የምርምር ስራን ይሰራል፤ ይህ ማለትም እነዚህ ጸረ ተባዮች አካባቢ ላይም ጉዳት ስለሚያደርሱ አማራጭ የሚሆኑ ጸረ ተባዮችን መፈለግ ነው። በዚህም ስነ ህይወታዊ የመከላከል ዘዴ በሚባለው ምርምር ተሰርቶ ብዙ ውጤት ተገኝቶበት ጥቅም ላይ ውሏል።

መረጃን የመሰብሰብ፤ ከዛም የመተንተንና ትንበያን የመስጠት ስራ አባል ሀገራት ላይ ያሉ ተዛማጅ ተባዮችን ያሉበትን ደረጃ የሚገልጽ ሪፖርት በየጊዜው ይሰበሰባል የተሰበሰቡት መረጃዎች ይታያሉ፤ ወደፊት ምን ሊሆን እንደሚችል የመተንበይና ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚያስፈልግበት ቦታ ላይ ማስጠንቀቂያ እንሰጣለን።

ሌላው የድርጅቱ ስራ የሰው ኃይልን የማብቃት ስራ ሲሆን በዚህም ለባለሙያዎች ስልጠናዎችን መስጠት ነው። በአባል አገራት ላይ ያሉ የእጽዋት ጥበቃ ባለሙያዎች የተዛማጅ ተባዮችን እንዴት መከታተልና መቆጣጠር ይቻላል በሚለው ላይ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠናውን በመስጠት የአባል ሀገራት አቅም እንዲጠናከር ይሰራል።

አዲስ ዘመን፦ በአባል ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ኤልያስ፦ እነዚህ አባል ሀገራት ችግሩን በጋራ እንከላከል ለዚህ ደግሞ አንድ ድርጅት እናቋቁም ብለው ወደውና ፈቅደው ያቋቋሙት ነው። ድርጅቱም በዩናይትድ ኔሽን የተመዘገበ ነው፤ አባላቱም በየዓመቱ ስብሰባ ያደርጋሉ፡፡ በተለይም የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተሮች ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሆኑበት እንዲሁም ሚኒስትሮቹ በሚኒስትር ካውንስል ደረጃ የሚሰበሰቡበት፤ በዚህም ስራዎች የሚገመገሙበት እቅድ የሚጸድቅበት አንዳንድ ትልልቅ ውሳኔዎችም የሚሰወኑበት ነው።

ከዓመት ወዲህ ደግሞ በየጊዜው እነዚህ አገራት ከመረጃ መስጠትና መቀበል እንዲሁም ድርጅቱ ስራውን እንዲቀጥል መዋጯቸውን ከመክፈል አንጻር ተሳታፊ ናቸው። በመሆኑም አባል አገራት ድርጅቱ በሁለት እግሩ ቆሞ እስከ አሁን ድረስ እንዲቀጥል ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ማለት ይቻላል። ነገር ግን እነዚህ አባል ሀገራት ዓመታዊ መዋጮን ማጓተት አንዳንድ ጊዜም አለመክፈል የሚታይባቸው መሆኑ ደግሞ ተቋሙ ከዚህ በላይ እንዳያድግና የተጣለበትን ኃላፊነት በሚገባ እንዳይወጣ ተግዳሮት ይሆናል።

ተዛማጅ ተባዮች ድንበር ዘለል ከመሆናቸው አንጻር አንድ ሀገር ብቻዬን እቆጣጠረዋለሁ ቢል የሚሆን አይደለም። በመሆኑም ኢትዮጵያ ላይ መቆጣጠር ካልተቻለ ኬንያ ትወረራለች፤ በተመሳሳይ ኬንያ ላይ ማቆም ካልተቻለ ኡጋንዳ ታንዛንያ ከፍ ያለ ወረራ ይደረግባቸዋል።

ለምሳሌ እኤአ ከ2019 እስከ 2020 ድረስ ያለው የአንበጣ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ እያለ በተቻለ መጠን ቁጥጥር ቢደረግበት ኖሮ ወደ ሌሎች ሀገራት ባልተዛመተ ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያም የገባው በሌሎች ሀገራት ቁጥጥር ባለመደረጉ ነው፡፡ ከተባባሰም በኋለ የቁጥጥር ስራው ጠንካራ ቢሆን ኖሮ ጉዳቱን መቀነስ ይቻል ነበር። እዚህ ላይ ግን መቆጣጠር አቅቶን ሳይሆን የመጣበት መጠን በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ኢትዮጵያን ሁሉ አልፎ ሊሄድ ችሏል።

እዚህ ላይ እንግዲህ እኤአ በ2019 አንበጣ አዲስ አበባ ድረስ የደረሰበት ሁኔታ እንደነበር የምናስታውሰው ነው፤ በወቅቱ ግን እዚሁ እንዳይወጣ የተጠናከረ የቁጥጠር ስራ በመሰራቱ የትም ሳይወጣና ወደሌሎች አገሮች ሳይዛመት መግታት ተችሏል።

ኬንያ ኡጋንዳ ላለፉት 70 ዓመታት አንበጣን አይተው አያውቁም፤ ይህ የሆነውም ጠንካራ የመከላከል ስራ በመሰራቱ ነው።

አዲስ ዘመን፦ እነዚህ ሁለት ሀገራት 70 ዓመታት ያህል አንበጣ ካላዩ ማጥፋት ይቻላል ማለት ነው?

አቶ ኤልያስ፦ በመጀመሪያ ደረጃ አንበጣን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አንችልም። ምክንያቱም አንድ ወይንም ሁሉት አንበጣ እንኳን ቢቀር የመራባት መጠኑ በጣም ከፍተኛ ነው። ሌላው ደግሞ ለመራባት በጣም ፈጣንና በብዛት የሚራባ ነው።

የበርሃ አንበጣ የሚባሉት የሚራቡበት አካባቢ በጣም ወጣ ያለ ሪሞት አካባቢ ነው። ለመራቢያ የሚመርጡት የቀይ ባህር ዳርቻዎችን ሲሆን ቦታዎቹም በጣም ብዙ ናቸው። ይህንን ስናይ አንበጣን የመከላከል ስራው በጣም አድካሚ ይሆናል።

ነገር ግን አሁን ላይ የብዙ ዓመት የመከላከል ልምድ ተቀምሮ የተደረሰበት ነገር ቢኖር በጥሩ የመስክ አሰሳ ገና ሳይራባ ቦታ ይዞ እንዳለ ማግኘትና እዛው ላይ የመከላከል ስራን መስራት ነው።

አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ አንበጣ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ነው፤ የመከላከል ስራችን ደካማ ስለሆነ ይሆን?

 አቶ ኤልያስ፦ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም እኤአ በ2019 የመጣው አንበጣ ሁላችሁም እንደምትረዱት የመን ላይ የነበረው ሁኔታ በጣም መጥፎ የነበረ በመሆኑ በወቅቱ አሰሳ እንኳን ማድረግ አልተቻለም፡፡ በዚህም ከየመን ተነስቶ ወደ ኢትዮጵያ የገባው የአንበጣ መንጋ በጣም ብዙ ነበር።

በአፋር ክልል ላይ 32 ወረዳዎች ከየመን በመጣ አንበጣ ተወረው ነበር። በጣም የሚገርመው ደግሞ የመጣው አንበጣ እንቁላል ለመጣል የደረሰም በመሆኑ ሁሉም እንቁላል ጣለ። ይህንን በገፍ እንቁላል የጣለን አንበጣ የመከላከል ስራው ቢሰራም እንኳን ከአቅም በላይ ነበር።

በሌላም በኩል በዚህን ያህል ደረጃ ይከሰታል ተብሎም ስላልታሰበ በድርጅታችንም ሆነ በግብርና ሚኒስቴር በኩል የነበረው ዝግጁነት ብዙም ስላልነበር ከተፈጠረ በኋላ የተደረገው ርብርብ ውጤታማ አልሆነም።

እዚህ ላይ አንበጣ የሚዛመትባቸው ደረጃዎች አሉ፡፡ አንዱ በትንሽ ቦታ ላይ ለአጭር ጊዜ የሚነሳ ሲሆን ከአንድ ክልል ወደሌላ ክልል የሚተላለፍም ብቻ ነው። ሌላው ደግሞ ሁለት ወይም ሶስት አገሮችን ሊይዝ የሚችል ሲሆን ይህ እዚህ ብቻ የሆነ ሳይሆን ምዕራብ አፍሪካም ላይ እኤአ ከ 2003 እስከ 2005 ድረስ በጣም ከፍተኛ ወረርሽኝ ነበር። በጣም ብዙ ድካምም ጠይቋል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁልጊዜ ይሆናልም ማለት ደግሞ አይደለም። ምንጩ የትኛው ቦታ ላይ እንደሆነ ያልታወቀ አንበጣ በአንድ ጊዜ በሚፈለፈልበት ወቅት የመባዛቱና በፍጥነት የመጓዙ ሁኔታ እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን ይፈጥራል።

አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ አገራችን ውስጥ የተፈጠረው አንበጣም ከአቅም በላይ ሆኖ ነው ወይስ ምክንያቱም ምንድን ነው?

አቶ ኤልያስ፦ አሁን የተፈጠረው የአንበጣ ወረርሽኝ በኤርትራ ቀይ ባህር ላይ የተራባ አንበጣ ወደ ምዕራብ ኤርትራ በመምጣት ላይ ይገኛል፤ ምክንያ ቱ ደግሞ ሞቃታማና ደረቅ መሆኑ ነው። ሆኖም በአሁኑ ወቅት አንዱ ወይም ሁለቱ ነው ወደ ኢትዮጵያ የገባው እንጂ ኢትዮጵያ ላይ የተፈለፈለም ሆነ የተራባ አንበጣ አይደለም።

ምናልባት ሰዎች ግን አገራችን ላይ ተራብቶና ተፈልፍሎ የተከሰተ ሊመስላቸውና እንደዛም ሊሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን አንበጣ እንቁላል ለመጣል ሁለት ሳምንት ከዛም በኩብኩባ ደረጃ ሆኖ ስድስት ሳምንት ይፈልጋል፤ አድጎ ለጥፋት ለመድረስ ሁለት ወር ያህል ይወስድበታል። ይህንን ስናይ ደግሞ አሁን ያለው አንበጣ በፍጹም ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተፈለፈለ መሆኑን እኛም አረጋግጠናል።

ሌላው የንፋስ አቅጣጫ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ስለነበር በአዲግራት እና በኮረም በኩል ወደ ደቡብ ምስራቅ ትግራይ ከገባ በኋላ አፋር ላይ ሙቀትና ምቹ ሁኔታ ስለነበር በዛ አካባቢ ሲዘዋወር የቆየ አንበጣ ነው። ይህ ትግራይ ላይ ያለው አንበጣ ራሱ ተበታትኖ አሁን ላይ በአማራና አፋር ክልል ላይ እንዳለ ነው ሪፖርቶች የሚያሳዩን።

በመሆኑም ይህንን የአንበጣ መንጋ ከዛሬ ሶስት ዓመቱ ጋር ማወዳደር በጣም ከባድ ነው። ምክንያቱም ያለፈው ዓመት በጣም ብዙና ከባድ ወድመትን ያስከተለ ነው የአሁኑ ግን በጣም በተበታተነ መልኩና መጠኑም ትንሽ ሆኖ የመጣ ነው።

አዲስ ዘመን፦ እኤአ በ2019 ዓ.ም ሆነ አሁን ላይ የተከሰተውን አንበጣ እንደ ኢትዮጵያ ለመቆጣጣር ድርጅታችሁ ምን ዓይነት ተግባራትን እያከናወነ ነው?

አቶ ኤልያስ፦ በመሰረቱ እንደ ድርጅት በአባላት አገሮች፤ ትኩረት የሚሰጣቸውም ኢትዮጵያ ሱዳን ኤርትራና ሶማሊያ ናቸው። ከዚህ አንጻር አንበጣ የት አካባቢ ነው ያለው? የሚለው ይታያል፡፡ ለምሳሌ በሱዳንና ኤርትራ በፈረንጆች ሀምሌ ወር መጨረሻ ድረስ አንጠባ ተከስቷል፤ በእነዚህ አካባቢዎችም የመከላከል ስራ ተሰርቶ ጥሩ ውጤት ተመዝግቧል። ለምሳሌ ኤርትራ 1 ሺ 192 ሄክታር አካባቢ መከላከል ተችሏል። ይህ የሚያሳየው ደግሞ በአሁኑ ወቅት ከኤርትራ ይመጣል ተብሎ ስጋት ሊሆን የሚችል አንበጣ አለመኖሩን ነው።

ሱዳን አሁን ላይ አለመረጋጋት ውስጥ ብትሆንም እንኳን 849 ሄክታር አንበጣን የመከላከል ስራ ተሰርቷል። በኢትዮጵያም በያዝነው ወር የመከላከል ስራው ተጀምሯል። በዚህም 732 ሄክታር መሬት ላይ መድሃኒት ርጭት ተደርጎ የመከላከል ስራ ተሰርቷል።

ድርጅቱም አባል አገራት በሚጠይቁት ጥያቄ መሰረት የሚሰራ እንደመሆኑ ጥያቄ በቀረበ ቁጥር የመከላከል ስራው ላይ እንሰማራለን። ሁሉም ሊገነዘበው የሚገባው ነገር ግን እኛ የስራውን ባለቤት ግብርና ሚኒስቴርን እንደግፋለን እንጂ እንደ ባለቤት ተሳትፎ ልናደርግ አንችልም። ነገር ግን የእኛ እርዳታ በሚያስፈልግበትና ጥያቄ በምንጠየቅበት ወቅት ወዲያውኑ ምላሽ ለመስጠት እንዘጋጃለን።

አዲስ ዘመን፦ እንደው የአሰሳ ስራው ምን መልክ ነበረው (ምን ያህል ታሰሰ) እንዲሁም ምን ያህል ቦታ ላይ አንበጣ ታየ?

አቶ ኤልያስ፦ አዎ ይህንን የሚያሳይ ቁጥር አለ። በአጠቃላይም እንደ አገር አፋር ትግራይና አማራ ላይ ነበር የታየው፡፡ አሁን በቅርቡ ግን ምስራቅ ሀረርጌ ላይ ስለመታየቱ ሪፖርት ደርሶናል። ይህንንም የማጣራት ስራውን የግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ክፍል እየሰራ ነው።

ድርጅቱ ምላሽ በሚሰጥበት ጊዜም አንደኛ ቴክኒካል ኮሚቴው ሁኔታው ምን ይመስላል፤ መቆጣጠር የሚቻለው በምን መንገድ ነው፤ ለመቆጣጠርስ ምን ያስፈልጋል፤ ለአሰሳ ምን ያስፈልጋል፤ ቴክኒካል ድጋፉ ለምሳሌ ሎጂስቲክስ እንዴት ነው የሚቀርበው የሚለውን ከተወያየ በኋላ ምክረ ሃሳቡን ለውሳኔ ሰጪዎች አቅርቧል።

በዚህም መሰረት አሁን በኮሚቴው ውሳኔ መሰረት የአውሮፕላን አስፈላጊነት በጣም ስለተሰመረበትና በአጋጣሚም የድርጅቱ አውሮፕላኖች አዲስ አበባ ላይ ስለነበሩ አብራሪዎችን ከናይሮቢ በማስመጣት አንድ አውሮፕላን ኮምቦልቻ ላይ ቆሞ የአሰሳ ስራውን ጀምሯል።

አዲስ ዘመን፦ ከአባል አገራት ጥሪ ካልቀረበ ድርጅቱ በራሱ መንገድ አንበጣን ለማጥፋት ስምሪት አያደርግም ማለት ነው?

አቶ ኤልያስ፦ ስራው የየሃገራቱ የግብርና ሚኒስቴር ስራ ነው። ነገር ግን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዚህን ጊዜና ሰዓት እርዳታ አድርጉልኝ ብሎ ይጠይቃል። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሁሉም አባል አገራት ላይ የሚሰራበት አካሄድ ነው። በነገራችን ላይ ይህ አሰራር አንበጣን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ወፍም ሲመጣ አካሄዱ ተመሳሳይ ነው።

አዲስ ዘመን፦ ከላይ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት 732 ሄክታር መሬት ላይ መድሃኒት ርጭት ተደርጓል ይህ ከምን ያህል ሄክታር ነው በሌላ በኩል ደግሞ አንበጣ በአገራችን ላይ ቢስፋፋ የመከላከል አቅም አለ?

አቶ ኤልያስ፦ የአለፈው የአንበጣ ወረርሽኝ ብዙ ነገሮችን አስተምሮናል። አንደኛ ቅድመ ጥንቃቄ ስራ ላይ ምን መደረግ እንዳለበት፣ ሁለተኛ መቼና የት የመከላከል ስራ መሰራት እንዳለበት ? ምን እንደሚያስፈልግ በደንብ ተምረንበታል።

በዚህ መሰረት አሁን እየታየ ያለው የአንበጣ ወረርሽኝ ከአቅም በላይ የሚሆን አይደለም፤ ቢሆንም ግን የግብርና ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም የቀረቡት በቂ የመገልገያ ግብዓቶች አሉት፤ 5 አውሮፕላኖችን ገዝቷል፤ የእኛ ድርጅትም በፋኦ በኩል አዲስ አውሮፕላን አግኝቷል። ይህ አቅምን ከመገንባት አንጻር ጥሩ ማሳያ ነው።

አሁን አንበጣው የት ነው የሚራባው? ቀጣዩ ሁኔታስ ምንድን ነው? የሚለውን አይተን ቴክኒካል ኮሚቴው ምክረ ሀሳብ አስቀምጧል። በዚህም አፋር ሸለቋማ ቦታዎች ላይ ሊኖር ይችላል በሚል ልየታ ስላለ አካባቢውን የማጥናት ህብረተሰቡ የአንበጣውን በቀለም ለይቶ አውቆ ሲታይ ወዲያውኑ ሪፖርት እንዲያደርግ የማሳወቅ ስራም በመሰራት ላይ ነው።

አዲስ ዘመን፦ ስራውን በውጤታማነት ለማከናወን እየገጠማችሁ ያለው ችግር ምንድን ነው?

አቶ ኤልያስ፦ አንዱ ቅድም ከላይ የገለጽኩት የአባል ሀገራት በወቅቱ መዋጮ አለመክፈላቸው ነው፡፡ ሌላው አውሮፕላን ለማስነሳት እራሱ የሀገራት ፍቃድ ያስፈልጋል። ሌላው ከጸጥታ አኳያ ያለው ነገር እንደልብ በየቦታው ተንቀሳቅሶ የአሰሳ ስራን ለመስራት አስቻይ ባለመሆኑ በተለይም በአማራ ክልል ያለው ኮማንድ ፖስት ይህንን ማመቻቸት ይኖርበታል። በአፋር ክልል ብዙ የመንግስት ስትራክተሮች ባለመኖራቸው የፌደራል ባለሙያዎች በሙሉ በክላስተር ተደራጅተው እንዲሰሩ ሆኗል።

ትግራይ ላይ እራሳቸው አደራጅተው ባለሙያዎች አሰማርተዋል። በነገራች ላይ አሁን ትግራይ ላይ አንበጣ የለም። ትግራይም አማራ ላይም ያለው በሙሉ ወደ አፋር ክልል ነው የሚሄደው ምክንያቱም የትግራይና የአማራ ክልል ተራራማ ቦታዎች ለመራቢያ ምቹ አይሆኑለትም፡፡ በመሆኑም የአፋር ሸለቋማ ቦታዎችን ተመራጭ ያደርጋል።

አዲስ ዘመን ፦ እንደ አገር አንበጣም ለዘለቄታው ለማስቀረት ምን መሰራት አለበት ይላሉ?

አቶ ኤልያስ፦ ከመጣ በኋላ መጮህ ሳይሆን መጀመሪያ አስፈላጊ የሆኑ የዝግጅት ስራዎችን መስራት ይገባል፤ ይህ ስራ ደግሞ በጣም በአስቸጋሪ ጊዜ ሊመጣ ይችላል የሚለውን ከግንዛቤ አስገብቶ መሰራት ያለበት ጉዳይ ነው። ምክንያቱም አንበጣ ቢመጣ ምን አለኝ? ምን ማድረግ አችላለሁ? የሚለውን ሰርቶ ማስቀመጥ ይገባል። ስራው ግን አንድ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ብቻ ሊሰራው የሚችል አይደለም። ብዙ ባለድርሻ አካላት አሉ፡፡ በተለይም የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት߹ የምስራቅ አፍሪካ የበርሃ አንበጣ መከላከያ ድርጅት እንዲሁም ዩኤስ ኤይድ ይሳተፉበታል።

ሌላው ወቅታዊና ቶሎ ቶሎ የሚሆን የመስክ አሰሳን ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህንን ማድረግ ሲቻል ችግሩ ስር ሳይሰድ ማግኘት ያስችላል። በጊዜ ተገኘ ማለት ደግሞ የመከላከል ስራውንም ውጤታማ ያደርገዋል። በተጨማሪም ለባለሙያዎች ተከታታይ የሆኑ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መስጠት ያስፈልጋል። እነዚህን ነገሮች በቅንጅት መስራት ከተቻለ በእርግጠኝነት አንበጣን የመከላከል ስራው በጣም ቀላል ይሆናል።

አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

አቶ ኤልያስ፦ እኔም አመሰግናለሁ

 እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 29/2015

Recommended For You