ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በዓለም ታሪክ

 የዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ክስተቶች ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ያስታውሱናል። ወደ ዋናው የዓለም ጦርነት ታሪክ ከመሄዳችን በፊት መጀመሪያ በዚህ ሳምንት የተከሰቱ የሀገራችን ታሪኮችን እና ሌሎች የዓለም ክስተቶችን በአጭሩ እናስታውስ።

ከ92 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ነሐሴ 23 ቀን 1923 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ በ750 ሺህ ፓውንድ መነሻ ሀብት ተቋቋመ። በዚሁ ሳምንት ከ158 ዓመታት በፊት ነሐሴ 24 ቀን 1857 ዓ.ም ምኒልክ የሸዋ ንጉሥ ሆኑ፤ ‹‹ምኒልክ ንጉሠ ሸዋ›› ተብለው ነገሡ።

ከ60 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ነሐሴ 22 ቀን 1955 ዓ.ም አሜሪካዊው የመብት ተሟጋች ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ‹‹ህልም አለኝ›› የሚለውን ዓለም አቀፋዊ ዝና ያተረፈውን ታሪካዊ ንግግር አደረገ። ‹‹March on Washington for Jobs and Freedom›› በተባለው ትዕይንተ ሕዝብ ላይ የቀረበውን ይህን ንግግር፣ ከ250 ሺህ በላይ የሚሆኑ የእኩልነት መብት ደጋፊዎችና አቀንቃኞች ዋሺንግተን ዲ.ሲ በሚገኘው የሊንከን መታሰቢያ አደባባይ ተገኝተው ተከታትለውታል። ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር የሲቪልና የኢኮኖሚ መብቶች እንዲከበሩና የዘር መድሎና መገለል እንዲቆም ጥሪ ያቀረቡበት ይህ ታሪካዊ ንግግራቸው፣ ዛሬም ጭቆናና መገፋት ያንገሸገሻቸው የዓለም ሕዝቦች እንደስንቅና የትግል መዝሙራቸው ይጠቀሙበታል። ‹‹ህልም አለኝ›› የሚለው ንግግርም በብዙ ቦታዎችና አጋጣሚዎች ይነገራል።

ከ84 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ነሐሴ 26 ቀን 1931 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር መስከረም 1 ቀን 1939) የአዶልፍ ሂትለር የናዚ ሠራዊት ፖላንድን ከወረረ በኋላ፤ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ተጣምረው ጀርመን ላይ ጦርነት አወጁ። ይህም ጦርነት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመርን አረጋገጠ። ይህ ጦርነት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ይባላል። በዛሬው ሳምንቱ በታሪክ ዓምዳችን ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት እናስታውሳለን።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ብዙ ዓለም አቀፍ ገጽታዎችን ቀይሯል፤ ብዙ ተቋማትና የሀገራት ጥምረቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል። በብዙ ታሪኮች ውስጥ ስሙ ይነሳል። በተለይም የአውሮፓ ሀገራት ታሪክ፣ የተቋማትና ማህበራት ታሪካዊ ዳራ የሚገለጸው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጋር በተያያዘ ነው። በአጠቃላይ የዓለምን ገጽታ የቀየረ ጦርነት ነው። የዓለም ጦርነት የተባለውም ለዚህ ነው።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመር ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም መነሻ ሰበቧ ግን የጀርመን ፖላንድ ላይ ጥቃት መሰንዘር ነው። ፖላንድ ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ከፖላንድ ጋር ስምምነት ያደረገችው ታላቋ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ከሁለት ቀን በኋላ ነሐሴ 28 ቀን 1931 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ መስከረም 3 ቀን 1939 ማለት ነው) ጀርመን ላይ ጦርነት አወጁ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሀገሮች ፖላንድን ለመርዳት ወታደሮች እና መሣሪያዎችን በፍጥነት ማሰባሰብ አልቻሉም፤ ጀርመን በምዕራባዊው ፖላንድ ድል ከተሳካ በኋላ ሶቪየቶች ከጀርመን ጋር ባደረጉት ስምምነት መሠረት ከአውሮፓውያኑ መስከረም 17 ጀምሮ ፖላንድን ማዳከም ጀመሩ። በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር መስከረም 27 ቀን 1939 ፖላንድ እጅ ሰጠች። ሆኖም ጦርነቱ የተጠናቀቀው በጦርነቱ ለኳሽ በናዚ ጀርመን ሽንፈት፤ በተባበሩት ተጓዳኝ ኃይሎች ማለትም በአሜሪካን በብሪታኒያ በፈረንሳይ እና በሶቭየት ኅብረት ድል አድራጊት ነው።

የተጓዳኝ መንግሥታት (Allied powers) ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት በተገኙበት የናዚ ጀርመን የተለያዩ ክፍለ ጦሮች የበላይ አዛዦች በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ጀርመን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እጅ መስጠቷን በርሊን ከተማ በሀገሩ ሰዓት አቆጣጠር ለእኩለ ሌሊት 15 ደቂቃ ሲቀረው በፊርማቸው አረጋገጡ። ይህም ጀነራል አልፍሬድ ዮሴፍ ፈርዲናድ ዮድል በተባለ የጀርመን የመከላከያ ኃይል ከፍተኛ የጦር አዛዥ በራድዮ ተነገረ። ‹‹እኛ ከዚህ በታች ፊርማችንን ያስቀመጥን የጦር አዛዦች ያለ አንዳች ቅድመ ግዴታ ሀገሪቱ እጅ መስጠቷን እናረጋግጣለን። ስለሆነም በምድር በባህር እና በአየር የተሰማሩ እስካሁን በጀርመናውያን የሚታዘዙ ኃይሎቻችንን በሙሉ በሶቭየት ቀዩ ጦር የበላይ አመራር ስር መሆናቸውን እናረጋግጣለን››

የጀርመንን ሽንፈት በፊርማቸው ያረጋገጡት፤ የናዚ ጀርመን የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ፊልድ ማርሻል ቪልሄልም ካይትል፣ የአየር ኃይሉ አዛዥ ሃንስ ዩርገን ሃንስ ሽቱምፕፍ ና የባህር ኃይሉ አዛዥ አድሚራል ሃንስ ጌዮርግ ፎን ፍሪድቡርግ ናቸው። የሙኒኩ የታሪክ ተቋም ባልደረባ የታሪክ ምሁሩ ዮሐንስ ሁርተር ያኔ የሆነውን ‹‹ጀርመን እጅ መስጠቷን ያረጋገጠው የያኔው የጀርመን መንግሥት ሳይሆን የጦር ኃይሉ ነው። በሕጋዊ አመለካከት ይህ በእነዚያ ቀናት ከተፈፀሙት አስገራሚ ነገሮች አንዱ ነው» ይሉታል።

ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሻ የጀርመን ፖላንድን ማጥቃት እንደ ቅጽበታዊ ሰበብ ቢቆጠርም ጀርመን ይህን ለማድረጓ ደግሞ የሚዘረዘሩ ሌሎች ምክንያቶች አሉ። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ፖላንድ በለስ ቀንቷት ጀርመንን ለሁለት ከፍላ የባህር በር ባለቤት ሆነች። ይህ ደግሞ ጀርመንን አስከፍቶ አለፈ። ጀርመን ፖላንድን ለማጥቃቷ አንድ ትልቅ ምክንያት ተወለደ ማለት ነው። ይህ እና ሌሎች ምክንያቶች በአጠቃላይ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያቶች ተብለው ይጠቀሳሉ። ጀርመን ፖላንድን ለማጥቃቷም ሆነ ለአጠቃላይ መጀመሩ ምክንያት ናቸው የተባሉትን እንጠቃቅስ።

አንደኛው ምክንያት ቬርሳይል ስምምነት የሚባለው ነው። በዚህ ስምምነት በአንደኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊ የነበሩት ተጓዳኝ ኃይሎች (ፈረንሳይ፣ ታላቋ ብሪታንያ፣ ሩሲያ፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ አሜሪካ) በጀርመን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ወሰኑ። ጀርመን ይህን የቬርሳይል ስምምነት እንድትፈርም ተገደደች። በስምምነቱም ጥፋተኝነቷን አምና ካሳ እንድትከፍል ተደረገች። ግዙፍ ወታደራዊ አቅም እንዳትገነባም እገዳዎች ተደረጉባት።

ሌላው ምክንያት የሚባለው በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ምክንያት የኢኮኖሚ መዳከም ነው። ንግድ ቀነሰ፣ የቢዝነስ ሥራዎች ተዘጉ፣ባንኮች ተራቆቱ፣ ሥራ አጥነት ተስፋፋ፤ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ተቃወሰ። በዚህን ጊዜ ሕዝቡ ጠንካራ መሪ መመኘት ጀመረ፤ ይህኔ ነው የወቅቱ የጀርመን መሪ አዶልፍ ሂትለር እነዚህን ሁሉ ችግሮች እንደሚቀርፍና ጠንካራ መንግሥት እንደሚሆን ለጀርመን መንግሥት ቃል የገባው።

ከዚህ በኋላ እንደ ምክንያት የተጠቀሰው እንግዲህ የጀርመን በጦር አቅም መደርጀት ነው። በቬርሳይል ስምምነት ግዙፍ የጦር አቅም እንዳይኖረው እገዳ ቢደረግበትም፤ ሂትለር በምሥጢር የጦር አቅሙን ማጎልበት ጀመረ። ምንም እንኳን ፈረንሳይ እና እንግሊዝ የሂትለርን የጦር ዝግጅት ቢያውቁም፤ ዳሩ ግን የጀርመን መጠናከር ከሩሲያ የሚመጣውን የኮሚኒዝም መስፋፋት ያስቆምልናል በሚል ባላየ አልፈውታል።

በአውሮፓውያኑ 1936 ሂትለር የጀርመን ወታደሮችን ጀርመንኛ በሚናገሩ የፈረንሳይ አካባቢዎች አሰማርቷል። ወደ ኦስትሪያና ችኮስሎቫኪያም አሰማርቷል። በዚህን ጊዜ እንግሊዝም ሆነች ፈረንሳይ የጦር ዝግጅት አላደረጉም ነበር። በዚሁ ዓመት ሂትለር ከጣሊያን እና ጃፓን ጋር አጋርነት (al­liances) ፈጠረ። ይህ የጀርመን፣ ጣሊያን እና ጃፓን የጦር ጥምረት አክሲስ (Axis) ይባል ነበር።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጀመረበት ሌላኛው ምክንያት ግጭትን የማስቀረት ስምምነት (Appease­ment) አለመሳካቱ ነው። በአውሮፓውያኑ 1930ዎቹ መጀመሪያ የተደረገው የቬርሳይል ስምምነት ጀርመንን የበደለ እንደነበር የእንግሊዝና የፈረንሳይ ፖለቲከኞች አመኑ። ስለዚህ የሂትለር እርምጃ የሚጠበቅና ፍትሐዊ ነበር ተብሎ ታመነ። ይህን በማመናቸውም ሌላ ስምምነት ተደረገ። ይህም በአውሮፓውያኑ 1938 የተደረገው የሙኒክ ስምምነት ነው። በዚህ በሙኒክ ስምምነት ጀርመን ችኮዝሎቫኪያ ውስጥ ጀርመንኛ ተናገሪዎች ያሉበትን መሬት እንድትወስድ እንግሊዝና ፈረንሳይ ፈቀዱ። ጀርመንም የተቀረውን የችኮዝሎቫኪያ ክፍልም ሆነ ሌላ ሀገር ላትወር ተስማማች። ሆኖም ግን በአውሮፓውያኑ መጋቢት 1938 ጀርመን ስምምነቷን አፍርሳ የተቀረውን የችኮዝሎቫኪያ ክፍል ወረረች። ጀርመን ይህን ስታደርግ እንግሊዝም ሆነች ፈረንሳይ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ አልተዘጋጁም ነበር። ከዚያም በአውሮፓውያኑ መስከረም 1 ቀን 1938 ጀርመን ፖላንድን ወረረች። እንግሊዝና ፈረንሳይም ወዲያውኑ በጀርመን ላይ ጦርነት አዋጁ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓ ተጀመረ ማለት ነው።

ይህ ሁሉ ሲሆን የመንግሥታቱ ማኅበር (League of Nations) ጦርነቱን ማስቀረት አልቻለም ነበር፤ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ክስተቶች የሚያብራሩ ሰነዶች የማኅበሩን ክሽፈት እንደ አንድ ምክንያት ይጠቅሱታል። በአውሮፓውያኑ የቀመር ቀመር ጥር 10 ቀን 1920 የተቋቋመው የመንግሥታቱ ማኅበር የተቋቋመበት ዋና ዓላማ የዓለምን ሰላም ማስጠበቅ ነበር። ሁሉንም ሀገራት አባል አድርጎ፤ በሀገራት መካከል አለመግባባት ሲፈጠር በድርድርና ውይይት ማስፈታት ነበር ዓላማው፤ ዳሩ ግን በታሰበለት ዓላማ አልሠራም። ሁሉንም የዓለም ሀገራት አባል ማድረግም አልቻለም። አባል ለሆኑትም ፍትሕ ሊጠይቅ አልቻለም፤ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ፊቱን ማዞሩ አንዱ ማሳያ ነው። ጃፓን ቻይናን በወረረችበት ጊዜም ተመሳሳይ አድሎ ፈጽሟል።

የጃፓን ቻይናን፣ ቬትናምን እና ሌሎች እስያ ውስጥ የሚገኙ ግዛቶችን መውረሯ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አካል ተደርጎ ይወሰዳል። በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1931 ጀርመን በከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ተመታች። የጃፓን ሕዝብ በመንግሥት እምነት አጣ። ለገጠማቸው ኢኮኖሚያዊ ችግር መፍትሔው ወታደራዊ አቅምን ማፈርጠም ሳይሆን አይቀርም ብለው አሰቡ። ምርቶችን ለማምረት ጥሬ ሀብት እንደሚያስፈልግ አመኑ። ይህን ማግኘት የሚቻለው ደግሞ ጥሬ ሀብት ያላቸውን አካባቢዎች በመውረር ነው። ጃፓን እንደ ማዕድን ያሉ ጥሬ ሀብቶች ያሉባቸውን የቻይና አካባቢዎች ወረረች። ቻይና ለመንግሥታቱ ማህበር ‹‹አቤት›› ብትልም የመንግሥታቱ ማኅበር አሁንም የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ እንዳለ ነው። ጃፓን በወረራዋ ቀጥላ ወደ ኮሪያ ሁሉ ተጓዘች። እንዲህ እንዲህ እያለ የቀጠለው የጃፓን እንቅስቃሴ ደግሞ በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 1941 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በእስያ እንዲጀመር አድርጓል።

በዚህ አስከፊ ጦርነት ከዛሬ 84 ዓመታት በፊት ዓለም ከ70 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አጥታለች። ያኔ የነበረው የየሀገራቱ የሕዝብ ቁጥር እንደዛሬው አይደለም። በዚያን ዘመን ይህን ያህል ሚሊዮን ሕዝብ ማጣት የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ይቀይራል። እስከ አሁን ባለው የጦርነት ታሪክም በአስከፊነቱ የሚጠቀሰው ይህ ጦርነት ነው።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያቶች አንዱ የአንደኛው የዓለም ጦርነት ጣጣዎች ናቸው። ከዚህ የምንረዳው አንድ ጦርነት ለሌላ ጦርነት ምክንያት እንደሚሆን ነው። ደግነቱ የአውሮፓ ሀገራት ዛሬ ሰልጥነዋል። የዓለም የጦርነት አስጀማሪና የጦርነት ምሳሌ እንዳልነበሩ፣ ዛሬ ግን በሀገራት መካከል ወታደራዊ ድንበር ጠባቂ የላቸውም እስከሚባልላቸው ድረስ ሰልጥነዋል። የሀገራቸው መገናኛ ብዙኃን የ24 ሰዓት የጦርነት ዜናዎቻቸው የአፍሪካና የሌሎች አህጉራት ጦርነቶች ናቸው። አንደኛውንም ሆነ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነቶች የሚያስታውሷቸው በታሪክነታቸው ብቻ ነው።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እነሆ በተለያዩ አጋጣሚዎች በታሪክነቱ ይታወሳል፤ የጦርነትን አስከፊነትም ሲናገር ይኖራል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You