የትራፊክ ፍሰቱን ማሳለጥ የጀመረው መንገድ

የሀገሪቱን የወጪ ገቢ ንግድ እንቅስቀሴ በማሳለጥ አገልግሎት ሲሰጥ የኖረ መንገድ ነው፤ ከአዲስ አበባ ከተማ መውጫና መግቢያ በር መንገዶች አንዱ ሆኖ ሲያገልግል ኖሯል፡፡ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ ፍሰት መሸከም አቅሙን ለማሳደግና አገልግሎቱን ይበልጥ በተሳለጠ መልኩ እንዲችል ለማድረግ በየጊዜው በአዲስ መልክ ሲገነባ፣ ሲጠገን ቆይቷል፡፡ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ፋይዳውን ታሳቢ በማድረግ በአዲስ መልክ መገንባት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲያስገነባው የቆየው ይህ የቃሊቲ ቱሉዲምቱ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሰፊና እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ ፍሰት ለማስተናገድ የሚያስችሉ ትላልቅ ማሳለጫ ድልድዮች እንዲኖሩት ተደርጎ ነው ወደ ግንባታው የተገባው፡፡ ይሁንና ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሳይጠናቀቀ ዓመታት ማለፉን ተከትሎ፣ በህዝቡ ዘንድ ሰፊ ቅሬታ ሲነሳበትም ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታውን ለማጠናቀቅ በወሰደው እርምጃ አሁን አብዛኛው ስራው ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ተደርጓል፡፡ የከተማ መንገዶች ባለስልጣን መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ ግንባታው ተጓትቶ የቆየው የመንገዱ ግራ ክፍል አንድ ዙር አስፋልት እንዲለብስ በማድረግ ነው መንገዱ ሙሉ ለሙሉ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን የተደረገው፡፡ የመንገዱ ተገልጋዮችም የመንገዱ ለትራፈክ ክፍት መሆን መጀመር እፎይታ እንደሰጣቸው እየገለጹ ናቸው፡፡

አቶ ዳዊት ካሳዬን በዚሁ መንገድ ትራንስፖርት ሲጠብቁ አገኘናቸው። ከቃሊቲ ውሃ ልማት አካባቢ ቱሉ ዲምቱ አካባቢ ሁሌም በትራንስፖርት ይመላለሳሉ። ባለፉት ዓመታት ከቃሊቲ አደባባይ እስከ ቱሉ ዲምቱ አደባባይ ያለው የመንገድ ግንባታ ባለመጠናቀቁ ሳቢያ ይደርስባቸው በነበረው እንግልት እሳቸውና የአካባቢው ነዋሪዎች በእጅጉ ሲማረሩ ኖረዋል።

በተለይ አቃቂ-ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አካባቢ የነበረው መንገድ በዝናብ ወቅት ጭቃማ፣ በጸሀይ ወቅት ደግሞ አቧራማ ሲሆን ፈተናው ከባድ እንደነበር ያስታወሳሉ፣ የመንገድ መዘጋጋቱ ደግሞ ሌላው ፈተና ነበር። ይህን ሽሽት ተሽከርካሪዎች በጋርመንት በኩል በፍጥነት መንገድ ማገናኛው መንገድ አማራጭ መጠቀም እንደነበረባቸው ጠቅሰው፣ በዚህ ሁኔታም ለአራት እና ለአምስት ዓመት ያህል ሰፊ የትራንስፖርት እንግልት ውስጥ መቆየታቸውን ያመለክታሉ።

በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ከቤት ወደ ሥራ፣ ከሥራ ወደ መኖሪያ ስፍራ በጊዜ ለመንቀሳቀስ ለእነ አቶ ዳዊት በእጅጉ አዳጋች ነበር። አሽከርካሪዎችም ወደዚህ መስመር ለመምጣት ፈቃደኛ አልነበሩም፤ ተገልጋዩ ህብረተሰብም ባጃጅ ሳይቀር በአማራጭ ለመጠቀም እና አቆራርጦ ወደ ቤቱ እንዲሁም ወደ ስራው መሄድ እንደነበረበት ይገልጸሉ። ይህም ለተጨማሪ ወጪ ያጋልጥ እንደነበርም ነው ያመለከቱት።

ለእነ አቶ ዳዊት አሁን የመንገዱ ግንባታ በአብዛኛው በመጠናቀቁ የትራፊክ ፍሰቱ ሰላማዊ ሆኖላቸዋል። መንገዱ ክፍት ስለሆነ ረጅም መስመር የሚጭኑ ተሽከርካሪዎችን ማግኘት እየቻሉ ናቸው። ከነበረው ችግር አኳያ አሁን ያለው የመንገዱ ሁኔታ ምቹ እና በተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑም በመስመሩ መንቀሳቀስ አቋርጦ የቆየው የአውቶብስ አገልግሎት ወደ ስራ መመለስ ጀምሯል፤ አዳዲስ አውቶቡሶችም ተመድበዋል። በመሆኑም የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት እየታየ ነው ሲሉ ያብራራሉ።

በግንባታው እንዲሁም ግንባታው በተቋረጠበት ወቅት የትራፊክ ፍሰቱ የተጨናነቀ እንደነበር አስታውሰው፣ በጠዋት 12 ሰዓት ከቤት በመውጣት አርፍዶ ሥራ ቦታ የሚደረስበት ሁኔታ በርካታ እንደነበር ይገልጻሉ። አሁን ወደ ሥራ እና የተለያዩ ጉዳዮች እንዲሁም ወደ ቤት በጊዜ መድረስ እየተቻለ መሆኑን ተናግረው፣ አንጻራዊ በሆነ መልኩ ፕሮግራም አድርገን በወጣንበት ሰዓት የፈልግንበት መድረስ እየቻልን ነው ሲሉ አቶ ዳዊት ይገልጻሉ።

አቆራርጠው ለመሄድ ሲሉ በተበላሹ መንገዶች ይጓዙ የነበሩ ተሽከርካሪዎችም ከጉዳት እየዳኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የመንገዱ ሙሉ ለሙሉ ለትራፊክ ክፍት መደረግ በመንገዱ አለመጠናቀቅ ሳቢያ በተሽከርካሪዎች ላይ ይደርስ ከነበረው ጉዳትና የመለዋወጫ ግዢ እንደሚታደጋቸው ያብራራሉ።

አሁን ነጋዴውም ሆነ ሌላው ማህበረሰብ ምርጫውን ወደ ቃሊቲ ቱሉዲምቱ መንገድ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ የንግድ ቤቶች ተፈላጊነትም እየጨመረ መሆኑን እና አካባቢውም የተሻለ እድገት ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በመስመሩ በቂ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት እንደሌለ አቶ ዳዊት ጠቅሰው፣ በተለይ በሥራ መውጫ እና መግቢያ ሰዓት በቂ አውቶቡሶችና የትራንስፖርት አማራጮች አለመኖራቸውን ይገልጸሉ። በዚህ ሳቢያ አሁንም የተወሰነ እንግልት ይታያል ብለዋል።

በዚህ መንገድ ላይ የራይድ አገልግሎት ሲሰጡ ያገኘናቸው ለ15 ዓመታት ያህል በአሽከርካሪነት መሥራታ ቸውን የተናገሩት አቶ አስናቀ ሽመልስ በበኩላቸው፣ መንገዱ የወጪ ገቢ ትራንስፖርት የሚተላለፍበትና በርካታ የትራፊክ ፍሰት የሚያስተናግድበት መሆኑን ይገልጻሉ። መንግሥት ይህን አይነቱን መንገድ በፍጥነት ገንብቶ ወደ ስራ ማስገባት እና በወቅቱ መጠገን እንደነበረበትም ጠቁመዋል።

ይህ መንገድ ከግንባታ ጋር በተያያዘ በተጨናነቀበት ወቅት የጋርመንቱ መንገድ እያስተነፈሰው ነበር የሚሉት አቶ አስናቀ፣ የግራ መንገዱ ሙሉ በሙሉ በማይሰራበት ወቅት 10 ኪሎ ሜትር የማይሞላው መንገድ ከሁለት ሰዓት በላይ ጊዜ ይወስድ እንደነበርም ይገልጻሉ። ይህም ክልል የሚኬድበትን ያህል ጊዜ እንደሆነ ያብራራሉ። ለረጅም ጊዜ መንገዶቹ ተቆፋፍረው መጓዝ እስከማይቻልበት ደረጃ መደረሱን አስታውሰው፣ ቃሊቲ መናኸሪያ የሚል የራይድ ጥሪ ቢገባም ማንም አይቀበለውም ነበር ይላሉ። ይህ በመሆኑም ተጠቃሚውም ይጉላላል፤ ትራንስፖርት ማግኘት አይቻልም ነበር ሲሉ ያመለክታሉ። አሽከርካሪውም ጊዜውን፣ ገንዘቡን እንዲሁም ንብረቱን ያባክን እንደነበር ያስታውሳሉ። በሌላ አካባቢ ሁለት ሶስት ጉዞዎች ማድረግ የሚቻልበት ጊዜ እዚህ መንገድ ላይ ይባክን ነበር ብለዋል።

ለብዙ ዓመታት ከነበረው የመንገዱ ሁኔታ አኳያ አሁን ላይ ያለው ሁኔታ ጥሩ ነው የሚሉት አቶ አስናቀ፣ መንገዱ ግንባታው አልቆ ለትራፊክ ክፍት ቢደረግም፣ አሁንም የተሽከርካሪ ማቆሚያ ፓርኪንግ እንዲሁም የእግረኛ መንገድ ግንባታ አለመጠናቀቁ ለአደጋ ያጋልጣል ሲሉ አስገንዝበዋል፤ ሙሉ በሙሉ ባላለቀ አስፋፓልት ላይ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንገዱ ከወዲሁ እንዳይጎዳ ቀሪ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ሊጠናቀቁ ይገባል ነው ያሉት።

ቃሊቲ ቶታል አካባቢ ያገኘናቸው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የትራንሰፖርት ስምሪት እና ትራፊክ ቁጥጥር አስተባባሪ የሆኑት አቶ ደመላሽ ብርሃኑም ፤ የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ መንገድ መጠናቀቅ እና ለትራፊከ ከፍት መሆን የትራፊክ ፍሰቱን በተወሰነ መልኩ ማቀላጠፍ መጀመሩን በመግለጽ የአስተያየት ሰጪዎቹን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡

መንገዱ ላይ ለታከሲ ተብሎ የተዘጋጀ ማቆሚያ ተርሚናል አለመዘጋጀቱን በችግርነት ያነሳሉ፡፡ ተርሚናል አለመዘጋጀቱ ታክሲዎችን፣ ሀይገሮችን እና አውቶቡሶችን ለይቶ በየመስመራቸው ለማስተናገድ ግን ችግር እየፈጠረበን ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ ተርሚናል ባለመኖሩ ተሳፋሪው ለመሳፈር ሲጋፋ እንደሚታይም ነው ያመለከቱት። በዚህ የተነሳ ስምሪቱን መቆጣጠር ሲገባን ከስራችን ውጪ ሰልፍ ወደማሰለፍ እየገባን ነው ሲሉ ይገልጻሉ። በዚህም ለአደጋ የመጋለጥ እድሉ ሰፊ መሆኑን ጠቅሰው፣ በመንገዱ ግራ እና ቀኝ በኩል መለስተኛ ተርሚናል ተከልሎ መስመር ቢሰመር የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአቃቂ ቃሊቲ ትራንስፖርት የቡድን መሪ አቶ በለጠ ገብረማሪያም በበኩላቸው መንገዱ የመውጫ በር እንደመሆኑ መጠን ብዙ ተጠቃሚ እንዳለው ጠቅሰው፣ በተለይ ብዙኃን ትራንስፖርት ላይ በሰፊው መሰራት እንዳለበት አመልክተዋል። በመስመሩ ከዚህ ቀደም የነበሩ 27፣ 110፣ 114 የአንበሳ አውቶቡሶች ወደ አገልግሎቱ ቢመለሱ አንዲሁም ሸገር ባሶች በብዛት እንዲመደቡ ጠይቀው፣ ተርሚናሉ የተሳለጠ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል። ይህ ሲሆንም የትራንስፖርት እና ትራፊከ ፍሰቱን ይበልጥ የተሻለ ያደርገዋል ብለዋል። ተሳፋሪውም አውቶቡስ ቆሞ እያለ ታክሲ በመጠበቅ መሰለፍ እንደሌለበት ተናግረዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት አንድ አስተያየት የሰጡን ትራፊከ ፖሊስም የአስተያየት ሰጪዎቹን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ የመንገድ ግንባታው መጠናቀቅና ክፍት መደረግ የነበረውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ እያቀለለው መሆኑን ተናግረዋል። የመንገድ መብራት ዝርጋታ አለመጠናቀቅ፣ የመንገድ ምልክቶች አለመስራት፣ የፍጥነት ገደብ አለመኖር እና ከዚህ ጋር ተያይዞ የአሽከርካሪው መንገዱን ጠብቆ የማሽከርከር ችግር እና ለእግረኛ ግምት አለመስጠት እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች መሆናቸውን አመልክተዋል።

መንገዱን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሞሀመድ አህመድ የቃሊቲ ማሰልጠኛ ቱሉ ዲምቱ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰው፣ ይህም የህብረተሰቡ የረጅም ጊዜ ቅሬታ መነሻ ሆኖ መቆየቱንና ቅሬታውም በከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ ምላሽ ማግኘቱን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉትም፤ አሁን የመንገዱ ግንባታ ተጠናቅቆ ለትራፊክ ክፍት ተደርጓል። በዚህም ህብረተሰቡ ደስተኛ ሆኗል። የትራፊክ መጨናነቁ፣ የተሽከርካሪዎች መጎዳቱ እና የህብረተሰቡ እንግልት እየተቀረፉ መጥተዋል። ቀሪ የእግረኛ መንገድ፣ የመንገድ መብራት እና ሌሎች ተያያዥ ስራዎች እስከ ታህሳስ ወር ድረስ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃሉ የሚል የመንግስት አቋም አለ። የመንገድ አካፋዩን አረንጓዴ የማድረግ ስራ ለማህበራት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

የአቃቂ አካባቢ አርሶ አደርም ምርቱን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ወስዶ ለመሸጥም ሆነ የኢንዱስትሪ ግብአቶችን ለማጓጓዝ የትራንስፖርት ፍሰቱ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ምርቶችንም ወደ ውጭ ለመላከ የመንገድ መሰረተ ልማቱ መጠናቀቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። የመንገዱ ግንባታ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ላይ ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው። የተሳለጠ መንገድ ሲኖር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው የተሻለ ይሆናል፤ ሆቴሎች ወደ አካባቢው ይመጣሉ በቱሪዝም በኩልም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ሲሉም ያብራራሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስተባባሪነት በከተማዋ ግንባታቸው እየተካሄደ ያለው የመንገድ ፕሮጀክቶች በመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከትናንት በስቲያ በተጎበኙበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ እንደገለጹት፤ ለቃሊቲ ማሰልጠኛ ቱሉ ዲምቱ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የሚውል ገንዘብ አበዳሪ የነበረው የቻይናው ኤግዚም ባንክ ለአምስት ዓመታት ብድሩን መልቀቅ ባለመቻሉ ግንባታው ለመጓተት ተዳርጎ ቆይቷል፤ ችግሩን ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የመንገዱን ግራ ክፍል ሙሉ በሙሉ የአንድ ዙር አስፓልት በማልበስ ለትራፊክ ክፍት እንዲሆን ተደርጓል።

መንገዱ ወደፊት ለብዙኃን ትራንስፖርት ማስተናገድ በሚያስችል መልኩ ለወደፊት ማስፋፋት እንዲያስችል መሀል ላይ 11 ሜትር ስፋት ቦታ የተተወለት መሆኑን ጠቅሰው፣ ጭስ አልባ ትራንስፖርትን ግምት ውስጥ በማስገባት በሁለቱም አቅጣጫ የሳይክል እና የእግረኛ መንገድን ግምት ውስጥ ያስገባ 6 ሜትር ስፋት ያለው ቦታ እንዳለውም ተናግረዋል።

መንገዱ በአጠቃላይ ስምንት መኪኖችን በሁለቱም አቅጣጫ ማስተናገድ የሚችል እና በሁለት ነጥብ አራት ቢሊየን ብር እየተገነባ የሚገኝ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰዋል። በ2016 ከጥር ወር በፊት ቀሪ ስራዎቹን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።

ኢንጂነር ሞገስ እንደገለጹት፤ በመዲናዋ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት በድምሩ ከ500 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ መንገዶች ዲዛይኖች እየተሰሩ ናቸው። በሚቀጥሉት ዓመታት የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁም የትራፊኩን ፍሰት በማሳለጥ የመንገድ ደህንነትን በማረጋገጥ የጉዞ ወጪን እና ጊዜን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ያስችላሉ። የመንገድ መሰረተ ልማት ከሊህቅ እስከደቂቅ የሚስተናገድበት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ብዜቱን የሚያፋጥን መሆኑን ጠቅሰው፣ ለእዚህም የከተማ አስተዳደሩም ከፍተኛውን የካፒታል በጀት እየመደበለት መሆኑን ተናግረዋል።

የባለሥልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ ሰለሞን በቅርቡ እንደገለጹት፤ 11 ኪሎሜትር የሚሸፍነው እና 50 ሜትር የጎን ስፋት ያለው የቃሊቲ-ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክት በወሰን ማስከበር እና ከፋይናንስ ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት በተለይ የመንገዱ ፕሮጀክቱ የግራ ክፍል ግንባታ ተጓትቶ ቆይቷል።

ከፕሮጀክቱ የትራፊክ ማሳለጫ ድልድዮች አንዱ የሆነው ቃሊቲ ማሰልጠኛ ቀለበት መንገድ አካባቢ 140 ሜትር ርዝመት ያለው ተሻጋሪ የትራፊከ ማሳለጫ ድልድይ ግንባታ አስቀድሞ መካሄዱን ጠቅሰው፣ ድልድዩ የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተሰሩለት መሆኑን ገልጸዋል። መንገዱ የወጪ ገቢ ኮሪደር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የከተማዋዋን ደቡብ እና ምሥራቅ አቅጣጫ የትራፊክ ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ ማቀላጠፍ እንዲያስችል ተደርጎ መገንባቱን አመልክተዋል።

መንገዱ በሁለቱም አቅጣጫ በአንድ ጊዜ ስምንት መኪኖችን ማስተናገድ ያስችላል

አቶ አስናቀ ሽመልስ፤

አቶ በለጠ ገብረማርያም ፤

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 27/2015

Recommended For You