«ሁለት የጥንቅሽ ዝርያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ እንዲመዘገቡም አድርጌያለሁ»ዶክተር ፋንታሁን ወልደሰንበት የኢንዱስትሪያል ባዮቴክኖሎጂ ዳይሬክተር

 ዶክተር ፋንታሁን ወልደሰንበት ይባላሉ፡፡ በመምህርነት፣ በኮሌጅ ሬጅስትራርነት፣ በኮሌጅ ዲንነት፣ በምርምር ዳይሬክተርነት፣ በዓለምአቀፍ ምርምር ፕሮግራሞች ማኔጀርነት ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ናቸው፡፡ በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም ደረጃ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አስተባብረዋል፡፡ በምርምር ዘርፉም የባለቤትነት መብትን ያረጋገጡበት ሥራዎችን አበርክተዋል።

በ2009 ዓ.ም የባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን በመስራችነት የተቀላቀሉ ሲሆን፤ አሁን ላይ በኢንስቲትዩቱ የኢንዱስትሪያል ባዮቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በተመራማሪነት እና መሪ ሥራ አስፈጻሚነት በማገልገል ላይም ይገኛሉ። ተቋሙ ከብዙ ዓመታት ቆይታና ጥናት በኋላ በሥራቸው ከተመረጡ ሰዎች መካከል አንዱ አድርጎ የመሪ ተመራማሪነት ወይም ፕሮፌሰር የሚባለውን ማዕረግ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሰጥቷቸዋል፡፡

 አዲስ ዘመን፡- የት ተወለዱ፤ ያደጉበት ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

ዶክተር ፋንታሁን፡- አዲስ አበባ በተለምዶ ስድስትኪሎ ምስካዬ ኅዙናን ቤተክርስቲያን አካባቢ ነው የተወለድኩት፡፡ አስተዳደጌም እንደማንኛውም ልጅ ነው። በወቅቱ እኔን ከእኩዮቼ ለየት ያደርገኛል ብዬ የማስበው ለነገሮች ያለኝ ምልከታ ነው፡፡ አንድን ነገር ካየሁና ካነበብኩ መቼም አልረሳውም፡፡ ተግባራትን ስፈጽም ለነገሮች ምላሽ የምሰጥበት ሁኔታም ፈጣንና ብዙዎች የሚፈልጉትን ዓይነት ነው፡፡

በተጨማሪም ቀልድ አዋቂ ልጅ ነበርኩ፡፡ እናም ነገሮችን በማስረዳት በኩል የተካንኩ ዓይነት ልጅ እንደሆንኩ ይነገረኛል፡፡ ሰዎች እንዳይረሱት እያዋዛሁም የመናገር ባህል አለኝ፡፡ ይህ ደግሞ ዛሬ ድረስ የተከተለኝና በቀላሉ ሰዎች ሀሳቦቼን እንዲቀበሉ የማደርግበት ልዩ ተሰጥኦዬ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ትምህርትዎን የት ተማሩ?

ዶክተር ፋንታሁን፡- ትምህርቴን እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ የተከታተልኩት የተወለድኩበት ቀዬ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያውንም ሆነ ሁለተኛ ዲግሪዬን የተማርኩትም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው። የመጀመሪያ ዲግሪዬን በባዮሎጂ የትምህርት መስክ ሲሆን፤ ሁለተኛው አፕላይድ ማይክሮባዮሎጂ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ በትምህርት ጉዳይ የወጣሁት ደግሞ ሦስተኛ ዲግሪዬን ለመማር ሲሆን፤ የሄድኩትም ባህር አቋርጬ ሕንድ ሀገር ነው፡፡ በዚያም ከፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ በማይክሮባዮሎጂ መመረቅ ችያለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የትና በምን በምን ዘርፎች ላይ ሠርተዋል፤ የነበርዎት ኃላፊነትስ ?

ዶክተር ፋንታሁን፡- ሥራዬ የሚጀምረው በመምህርነት ሲሆን፤ ቡርጂ ልዩ ወረዳ ነበር የተመደብኩት። የገጠሪቱን ኢትዮጵያ ባህል በስፋት ያየሁበት ነው፡፡ ከዚያ ከአራት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ከንባታ ጠንባሮ ዞን አንጋጫ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛውሬ ማገልገል ቀጠልኩ፡፡ የትምህርት ዕድል አገኘሁና ዩኒቨርሲቲ ገባሁ፡፡ ቀጣዩ ሥራዬ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የገባሁበት ሲሆን፤ በመምህርነት፣ በኮሌጅ ሬጅስትራርነት፣ በኮሌጅ ዲንነት፣ በምርምር ዳይሬክተርነት፣ በዓለም አቀፍ ምርምር ፕሮግራሞች ማኔጀርነት ለረጅም ጊዜ አገልግያለሁ፡፡

በወቅቱ የሳተላይት የምርምር ማዕከላትን ከጓደኞቼ ጋር በመሆን አቋቁሜያለሁ፡፡ በዓለም አቀፍ የምርምር ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ላብራቶሪዎች እንዲደራጁ አድርጌያለሁ፡፡ በባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከተቀላቀልኩ በኋላም የባዮኢኖቬት አፍሪካ ሁለተኛ ዙር የምርምር እና ልማት ድጋፍ በጥንቅሽ ዕሴት መጨመር ላይ በሦስት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በተከናወነ ምርምር ዋና የፕሮጀክት መሪ ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡

ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በተገኘ ድጋፍ በኢንስቲትዩቱ በተካሄዱ የአፍላቶክሲን ባዮኮንትሮል እና ማይክሮ አልጌ ምርምር ፕሮጀክቶች ላይም ተሳትፌያለሁ፡፡ በዚህም አመርቂ የምርምር ውጤቶችን እና የመጀመሪያውን ብሔራዊ የማይክሮ አልጌ ምርምር ላብራቶሪ ለማቋቋም የተቻለበት ነበር፡፡ በኮቪድ-19 ላይም በተከናወኑ ምርምሮች ከባዮኢኖቬት አፍሪካ እና ከቮልክስዋገን ፋውንዴሽን በተደገፉ የምርምር ፕሮጀክቶች ላይ መሳተፍም ችያለሁ፡፡

ከምርምር አጋሮቼ ጋር በመሆን ሁለት የጥንቅሽ ዝርያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ እንዲመዘገቡም አድርጌያለሁ፡፡ በእንሰት ቴክኖሎጂዎች ላይ አንድ ኢንዱስትሪያል ዲዛይን እና አራት ዩቲሊቲ ሞዴሎች በአጠቃላይ አምስት የአዕምሯዊ ንብረት መብቶችን ማስጠበቅ ችያለሁ፡፡ የእንሰት መፋቂያ፤ መጭመቂያ እና ማብላያ ቴክኖሎጂዎች ለማኅበረሰቡ እንዲደርሱ እና ጥቅም ላይ እንዲውሉም ከፍተኛ ጥረቶችን አድርጌያለሁ። እነዚህ ሥራዎቼም በዓለምአቀፍ ጆርናሎች ላይ የታተሙ ናቸው፡፡ በዚህና መሰል ሥራዎቼ ደግሞ በባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመሪ ተመራማሪነት ማዕረግን በቅርቡ ሰጥቶኛል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ፕሮፌሰር እንደማለት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኢንዱስትሪ ባዮቴክኖሎጂ ምንድን ነው? ፋይዳውስ?

ዶክተር ፋንታሁን፡- የኢንዱስትሪ ባዮቴክኖሎጂ ወይም ነጭ ባዮቴክኖሎጂ ማለት ባዮቴክኖሎጂን ለኢንዱስትሪ ሂደት እና ለኬሚካሎች፣ ቁሳቁሶች እና ነዳጆች ማምረቻነት መጠቀም ማለት ነው። በዚህም በሂደቱ ውስጥ ፋርማሲዩቲካልስ፣ ኢንዛይሞች፣ ባዮፊውል እና አሟሚዎች፣ ቫይታሚኖችን፣ አልሚ ምግቦች እና አዲስ ፖሊመሮች ይካተታሉ፡፡ ወደ ፋይዳው ሲገባ ደግሞ ኢንዱስትሪያል ባዮቴክኖሎጂ ሚናው ብዙ ነው። ለአብነት ምርታማነትን ያሳድጋል፡፡ አነስተኛ ሀብቶችን (ውሃ እና ባህላዊ የኬሚካል ምርቶችን) ለመጠቀም የሚረዳ ነው፡፡ መርዛማ አየርን ልቀት በመቀነስ በኩልም የማይተካ ሚና አለው፡፡ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ጨምሮ የቅሪተ አካል ነዳጆችን አጠቃቀም ይቀንሳል።

አዲስ ዘመን፡- የኢንዱስትሪ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እንደ ሀገር ምን እያከናወነ ነው?

ዶክተር ፋንታሁን፡- ዋናው በኢንዱስትሪ ባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ ምርምር እና ልማት ማካሄድ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የሰውና መሠረተ-ልማት አቅምን መገንባት እና በዘርፉ የማማከር አገልግሎት መስጠት ሲሆን፤ በዚህም የሥራ ክፍሉ በሦስት የምርምር ቡድኖች ተዋቅሮ ይሠራል፡፡ እነዚህም የምግብ ባዮቴክኖሎጂ እና ማቀነባበር፣ የኢንዱስትሪ ባዮኬሚካሎች ምርምር እና ኢንዛይም ቴክኖሎጂና ሥነሕይወታዊ ምርት ሂደት የሚባሉት ናቸው፡፡

ሥራዎቹ ለምግብ፤ ለቆዳ እና ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች የጥሬ ዕቃዎች እና የሂደት ግብዓቶችን ለማምረት ይረዳሉ፡፡ በዚህም በውጭ ምንዛሪ የሚገዙ ግብዓቶችን መተካት፤ ወደ ውጭ ሀገራት ተፈላጊ ምርቶችን በመላክ የውጭ ምንዛሪ ማምጣት እና ሀገርን ባላት ሥነሕይወታዊ ሀብት እንድትጠቀም ማስቻል ነው፡፡ በተለይም ሀብቶችን ለልማት በማዋል ዕድገትን ማምጣት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንዳነሱት ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ናት፡፡ ሆኖም በምርምር ደግፎ ሥራዎችን ከማከናወን አኳያ ክፍተቶች እንዳሉበት ይነሳል፡፡ ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል?

ዶክተር ፋንታሁን ፡- እኔ ሕንድ እና ቤልጂየም እንዲሁም በአፍሪካ ሀገራት ደቡብ አፍሪካ፤ ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ሌሎች ሀገራትን አይቻለሁ፡፡ እነኝህ ሀገራት ምንም ከእኛ የተለየ ነገር የላቸውም፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ እንዲያውም ከእኛ ሀገር ያነሰ መሠረተ ልማት ጭምር አላቸው፡፡ ይህም ሆኖ ግን የዓለም ፐብሊኬሽን በማተም በጣም ጉልህ ተጽዕኖ ያላቸው ሆነው እናገኛቸዋለን። የእኛ ችግር ታዲያ ምንድነው ከተባለ ብዙ ነገሮችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ አንደኛው አንድን ነገር ሥራዬ ብሎ እስከመጨረሻው የመሥራት ችግር አለብን፡፡ ያለንን ደግሞ ባለው አቅም ልክ የመጠቀም ችግርም ጎልቶ ይታይብናል።

ለአብነት አሁን ባለው ደረጃ ዩኒቨርሲቲዎች በጣም ብዙ ላብራቶሪዎች አሏቸው፡፡ በጥሩ ደረጃ ተደራጅተውም ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሥራ ለመቀጠል የሚቸገሩበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንመለከታለን፡፡ ይህ ደግሞ የሥራ ባህላችን ብዙ እንደሚቀረው የሚያሳይ ነው። መንግሥት ብዙ ነገሮችን ይገዛል፡፡ ነገር ግን ዕቃዎች ተገዝተው ጥቅም ላይ ሳይውሉ እንዲሁ የሚቀመጡበት ሁኔታ አለ፡፡ መንግሥት አካባቢ ያሉ ሰዎችም ስለ ሥራው ብዙም ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች አይሠሩም፡፡ የሚሠሩ ሰዎችንም ማበረታታት ላይ ብዙ አይገፉበትም፡፡

ኢትዮጵያውያን ወደ ውጭ ሀገር ከሄዱ በኋላ ለምን ውጤታማ ይሆናሉ፤ በምርምሩም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ላይ የተሳካላቸው ሆነው ናሳ ላይ ሳይቀር ሲሠሩ ለምን እንመለከታለን ቢባል መልሱ አንድ እና አንድ ነው፡፡ የሚያሠራቸው ሲስተም እንጂ እውቀት ብቻ አይደለም። ከሲስተሙ ጋር ተያይዞ የሚተገበረው አስገዳጅ ሁኔታ በቀጥታ መሥራትን ልምድ እንድናደርገው ዕድል ይሰጠናል፡፡ ስለዚህም የሌላ ዓለማት ተመራማሪዎች ኢትዮጵያ ካሉት የሚለዩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሲስተም ውስጥ የገባ ሰውና ያልገባ በሚል መውሰድም ይቻላል፡፡

አንድ ሥራ ሲተገበር ግልጽ የሆኑ እና መሳካት ያለባቸው እቅዶች ይቀመጣሉ፡፡ ያን እቅድ እንዲሳካ ለማድረግ በጀት እና አስፈላጊ ግብዓቶችም ይሟላሉ፡፡ ጊዜ ይመደብለታል፤ በዚያ ጊዜ መሠረት ደግሞ የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ ተግባራቱም ቼክ የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ ምንድን ነው መጨረሻ ላይ ማሳካት የሚጠበቅብህ ? ያንን በተባለው ጊዜ እና ሀብት ተጠቅመህ አሳክተሃል ወይ ? የሚልና መሰል ነገሮች ሞኒተሪንግ ይደረጋሉ፡፡ በመጨረሻም ውጤቱ ጥቅም ላይ ውሏል ወይ የሚለው ይታል፡፡ የወጣው ወጪና የተገኘው ጥቅም ይቀራረባል ወይ ተብሎ ይገመገማል፡፡ እኛ ሀገር ግን ይህ ሁሉ ነገር የለም፡፡ መቼ ተጀመረ? የት ደረሰ ? ከዚያ በኋላ ምንድን ነው የሚጠበቀው የሚሉት ነገሮች ከፕሮፖዛል አያልፉም፡፡ ጥብቅ የሆነ ክትትልም አይደረግባቸውም፡፡

ኦዲት ብንመለከት እንኳን በእኛ ሀገር የፋይናንሽያል ኦዲት እንጂ የፐርፎርማንስ ኦዲት አናይም፡፡ ምርምር በምንሠራበት ጊዜ ከራሳችን ፍላጎት እና ጥቅም አንጻር የምርምር ፕሮጀክቶች እንዲነድፉ ማድረግ ተገቢ ነው የሚለውም አይታይም፡፡ ለምሳሌ፡- ፕሮፖዛል ሲጻፍ በእንግሊዝኛ ነው፡፡ ሪፖርት ሲደረግም በእንግሊዝኛ ነው፡፡ ነገር ግን ስንት በመቶ የሚሆን ሕዝባችን እንግሊዝኛ ይናገራል? ስንል መልሱ ግልጽ ነው፡፡ እናም ለማን እንደምንሠራው እንኳን ሳናውቅ ነው ተግባሩን የምናከናውነው፡፡

ስለዚህ ምርምሮችን ስንሠራ የራሳችንን ሁኔታ ማየት እና ራሳችንን የሚጠቅመንን ነገር ለይተን መውሰድ ካልቻልን መቼም ቢሆን ችግሮች ሊፈቱ አይችሉም፡፡ የምንሠራው ደግሞ ለዓለም ከሆነ እኛን ሳይሆን እነርሱን ነው የምንጠቅመው፡፡ ምክንያቱም ዓለም ያለምንም ጥቅም ሊሠራ ፤ ሊደግፍና እውቅና ሊሰጥ አይችልም። እኛ ላይም ያለው ነገር ይህ ነው፡፡ ዓለምአቀፍ እውቅና ያለማግኘታችን ምስጢር አሠራሩንም፤ ተጠቃሚነቱንም ሳንገነዘብ መስራታችን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በምርምሩ ዘርፍ ከሌሎች ሀገራት ጋር ተባብራ የምትሠራበት ሁኔታ ተፈጥሯል?

ዶክተር ፋንታሁን፡- አዎ፤ ብዙ ባይባልም ከተለያዩ የውጭ ተቋማት ጋር ምርምሮች ይሠራሉ፡፡ እንግዲህ በብዙ ዘርፎች ነው ምርምር የሚደረገው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ተማሪዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህም በትብብር ምርምሮች ውስጥ በርካታ ዕድሎች ይኖራሉ፡፡ አንደኛው ምርምሩ የሚያካትታቸው ቦታዎች ሰፋ ስለሚሉ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ብዙ ልፋትን አይጠይቅም፡፡ ዓለምአቀፍ የምርምር ፕሮጀክቶች ውስጥም ተካተን እንሠራለን። በዚህ ውስጥ መካተት በራሱ በርካታ ተሞክሮዎችን ለመጋራት ያስችላል፡፡ ሁሉም የየራሳቸውን ጥንካሬ ይዘው ስለሚመጡ በቀላሉ ሥልጠና ለማግኘትም ዕድል ይሰጣል፡፡

ሁለተኛ ላብራቶሪዎችን የግድ እዚህ መገንባት ሳያስፈልግ የትኛውም ቦታ ላይ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ሰፊ ፕሮጀክት ሲሆን ተሳታፊ ሰዎችም ስለሚበዙ ለችግሮቹ ጥሩ የሆነ የመፍትሄ ሀሳብ ለማቅረብም ጥሩ ዕድል ነው፡፡ እንዲሁም የመረጃ ስርጭቱ የተሻለ እንዲሆን ያስችላል፡፡ ከዚህ አንጻር እስካሁን እኛ ብዙ የተጠቀምንባቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ባዮ ኢኮኖሚን በማበልጸግ በኩል፤ አሁን ደግሞ የተሻለ ሪጂናል አፕሬተሮች እንዲኖረን ከማድረግ አኳያ ምርምርን በጋራ መሥራቱ ብዙ አራምዶናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛ መንስኤው ሀገራት የሚጋሯቸው ነገሮች መኖራቸው ነው፡፡

እንደባዮ ቴክኖሎጂ የጥንቅሽ ፕሮጀክትን ብቻ ብናነሳ ዑጋንዳን፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያን ያቀፈ ነው። በአጋጣሚ የፕሮጀክቱ መሪ እኔ ነበርኩና ጥቅሙን በሚገባ ማስተዋል ችያለሁ፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ ብዙ ብዝሃ ሕይወት ያላት ሀገር ናት፡፡ ይህ ብዝሀ ሕይወት ደግሞ ትልቅ ሀብት ነውና ከማንኛውም የዓለም ሀገራት ጋር ተቀናጅታ በምርምሩ ዘርፍ እንድትሠራ ያደርጋታል። ጥቅሟም የሚታየው ከዚህ አኳያ ነው፡፡ ስለዚህም መመልከት ያለብን በግለሰብ ደረጃ የተሠሩትን ምርምሮች ብቻ ሳይሆን በአጋርነት የተሠሩትንም ሊሆን ይገባል። ይህ ሲደረግ ግን አንድ ነገር ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡ ይህም የዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መሠረት በአደረገ መልኩ ነገሮች ቢከናወኑም ቅድሚያ ለሀገር መወገን ላይ መደራደር አይገባም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ፕሮጀክቶች ምን መልክ አላቸው፤ ምን ያህል ተጠቃሚ አድርገዋል ብሎ መውሰድ ይቻላል? ከችግሮቹ በመነሳት ምን ምን ነገሮች መሻሻል አለባቸው ይላሉ?

ዶክተር ፋንታሁን፡- የፕሮጀክት ሥራ ሰጥቶ መቀበል መርህ የሚታይበት ነው፡፡ በተለይም በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚመጡ ፕሮጀክቶች የተወሰነ የራሳቸውን ፍላጎት ይዘው የሚመጡ ናቸው፡፡ ፍላጎታቸው እስኪሳካ ሰጥቶ መቀበል መርህን ይከተላሉ። ስለሆነም ያለሽን ይዘሽ ስትቀርቢ ነው ሌላው ላንቺ ሊሰጥሽ የሚችለው፡፡ ወደ ጥቅሙ ሲገባ ከላይ እንዳልነው ነው፡፡ በምርምሩ ላይ የተመለከትናቸው ዕድሎች እዚህም ላይ ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡

ፕሮጀክቶች ብቻቸውን የሚከወኑ ስላልሆኑ የሥልጠና ዕድል ይሰጣሉ፤ ድጋፍ ለማግኘትም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ፡፡ በተመሳሳይ መልካም ተሞክሮዎችን ከሌሎች ሀገራት ለመቅሰም መልካም አጋጣሚዎችን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- እንሰት ላይ አንድ ፕሮጀክት ነበረን፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ሁለት የፒኤች ዲ ተማሪዎች ተመርቀውበታል፡፡ ጥሩ እውቀትም ተገኝቶበታል፡፡

እንሰት በማብላላት ሂደት ውስጥ ቆጮ ሲሠራ ትንሽ በተወሰነ መልኩ ለተጠቃሚው የማይመቹ ነገሮች አሉት፡፡ እሱን ለማስተካከል የተሞከረበት ሁኔታ ነበር። ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እንሰትን እንዴት ነው የሚጠቀምበት? ካልሽ መልሱ ቀላል ነው፡፡ በታዳጊ ሀገራት ያለውን የባህላዊ ምግብ አሠራሮች የዘመናዊው ማኅበረሰብም ማድረግ ነው፡፡ ይህንን አሠራር ሙሉ ለሙሉ ወስዶ ተፈጥሯዊው መንገድ ይታከልበታል፡፡ ያ ደግሞ የአኗኗር ዘይቤውን ከማሻሻል አኳያ የማይተካ ሚና ይኖረዋል፡፡ ይህንን የሚያደርጉበት ምክንያትም እንሰት በልቶ ያደገ ሰው ስታይ አጥንቱ ሰፋፊ ነው፤ ቁመቱም ረዥም ነው፡፡ ጤናማ ከመሆንም አኳያ ማንም አይደርስበትም፡፡

እነርሱ ጤናቸውን፤ የተለየ ሀብታችንን ለመጠቀም ስለሚሹ ትንሹን ድጋፋቸውን ያደርጋሉ፡፡ እኛ ደግሞ ያለንን አሟጠን እንሰጣቸዋለን፡፡ ስለዚህም አንድ መማር ያለብን ነገር አለ የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኛ ከፕሮጀክቱ ውስጥ የምናገኘው ምንድነው የሚለውን በጥልቀት ማየት ነው፡፡ የመጠቀም እንድላችንን ከሁሉም አቅጣጫ ልንመረምረው ይገባል፡፡ ምክንያቱም እነሱ ለምን መጡ?፤ ድጋፍ የሚሰጡን ምን ፈልገው ነው፤ በእነርሱ ፍላጎት ውስጥ የእኛን ጥቅም እንዴት አድርገን ማሳደግ አለብን? የሚሉ ነገሮችን ማጤን ይገባናል፡፡ ከዚያ ወደ ሥራው መግባት አዋጭነት ይኖረዋል፡፡

አንድ ፕሮጀክት ውጤት ማምጣቱ በትክክል የሚረጋገጠው ወደ ማኅበረሰቡ ዘንድ ሂዶ ኢኮኖሚ ውስጥ ገብቶ ለውጥ ሲያመጣ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል ሲፈጥር፣ ሀገርን ከነበረችበት ሁኔታ አንድ ደረጃ ከፍ ሲያደርግ ነው። ካልሆነ ግን ፕሮጀክቱ ልክ እንደምርምሮች ለይስሙላ ተሠርተው የመደርደሪያ ማሞቂያ ነው የሚሆኑት፡፡ ይህ ደግሞ የዘመኑ አስተሳሰብ የሚቀበለው አይደለም፡፡ ዘመኑ ለውጥና ምርት ይፈልጋል፡፡ ምርቱ አገልግሎት ሆኖ ሲቀየር ማረጋገጥን ይሻል፡፡ እናም በዓለም አቀፋዊ ጥናት የምወስደው ሼር እንዳለ ሆኖ ጥቅማችንንም አሁን ባልኩሽ አቅጣጫ ማስተካከል ይኖርብናል፡፡ እስከመጨረሻ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ መሥራት የግድ ይለናል፡፡

አዲስ ዘመን ፡- እንደ ሀገር በርካታ ጥቅም ላይ ሳይውሉ የሚቀሩ በርካታ ፕሮጀክቶች ይስተዋላሉ፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው ?

ዶክተር ፋንታሁን፡- የሰለጠኑት ሀገራት ገንዘብ እንሰጣችኋለን ሲሉ እነሱ የሚፈልጉት ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ገንዘብ አንድ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ገንዘብ ብቻውን የነገሮች አንቀሳቃሽ ሊሆንም አይችልም፡፡ አስቻይ ሁኔታ የግድ ያስፈልጋል፡፡ የተሳለጠ አሠራር ለፕሮጀክቶች መሳካት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ቢኖሩ ግብዓቶች የሚቀርቡበት የተሳለጠ ምቹ ሁኔታ ካልተፈጠረ የፕሮጀክቱ ጉዞ መንገድ ላይ ይቆማል፡፡

አንድ ፕሮጀክት ለማሳካት ሊሟሉ የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው በጀት ሲሆን፤ ሌላኛው አቅም ያለው የሰው ኃይል ነው፡፡ የማይሆን ሰው ፕሮጀክቱ ውስጥ ብታስገቢ “ኮንፊውዥን” እና ሌላ ግጭት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ለዚህ ሁነኛ ሰዎች መኖር አለባቸው፡፡ የተቆረጠ ጊዜ መኖርም አለበት፡፡ ከዚያ የፕሮጀክቱ መከታተያ እና በምን ጠነከረ? ምን ውድቅ ሆነ፣ እንዲስተካል ምን ያስፈልጋልና መሰል ነገሮችን መመልከት ይገባል፡፡ በዚህ ሂደት ከተሄደ ስኬቱ ላይ ይደረሳል፡፡ ሆኖም ብዙ ፕሮጀክቶች በወረቀት ደረጃ ጥሩ ሆነው፤ ገንዘብ የሚለግሱ ሰዎችን ቀልብ መሳብ ችለው በመጨረሻ ግን በመፈጸም ብቃት ጉድለት የወረቀት ጌጥ ሆነው ይቀራሉ፡፡ ለዚህም ነው እንደሀገር ስኬታማ ፕሮጀክቶች እንዳይታዩ የሆኑት፡፡ ወረቀት ላይ ያለው በተግባሩ ባለመታየቱ ማኅበረሰቡን ሲጠቅም አይታይም፡፡

በእርግጥ እንደሀገር ያለው ይህ ብቻ ችግር አይደለም። የመሠረተ ልማት፤ ተሳታፊ ሰዎች፤ የግዢ ሥርዓቱ፤ የሠራተኞች ሞራል፤ ከሰዎች ተጠቃሚነት አንጻር፤ ከአሠራር ሁኔታዎች፤ ከሥራ ባህል ጋር ያሉ አስቻይ ሁኔታዎች አኳያ የፕሮጀክቶች ስኬት ይለካል፡፡ ለዚህም አንድ ማሳያ ላንሳ፡፡ ለተሰጠው ገንዘብ የሚመጥን ሪፖርት ካልተደረገ በድጋሜ ገንዘብ የሚለው አካል አይኖርም፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ፕሮጀክቱ በገንዘብ እጦት እንዲቋረጥ ያደርጋል፡፡

አሁን እንደ ሀገር ከፕሮጀክት አተገባበር አኳያ ብዙ ልናስተካክላቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ የማስተካለል ዕድላችንም ሰፊ ነው፡፡ አንዱ ደግሞ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ከችግሮች ተምሮ ዳግም ስህተት ላለመሥራት መሞከር ነው፡፡ መሥራትን ባህል ማድረግና ለሀገር ሲባል የራስን ጥቅም መተውን ልምድ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች እንደሆነች ይታወቃል፡፡ ያለንን ሀብት በአግባቡ ተጠቅመናል ብሎ መውሰድ ይቻላል?

ዶክተር ፋንታሁን ፡- ኢትዮጵያ በብዝኃ ሕይወትም፣ በማዕድንም፣ በሰው ሀብት እና መሰል ሁኔታዎች ሀብታም ነች፡፡ ነገር ግን ሀብት ሰዎችን ሀብታም የሚያደርገው ያለውን አውቆ ሲጠቀምበት ነው፡፡ በድሃ እና በሀብታም መካከል ሰፊ ልዩነት የሚታየው በፍጥረታቸው ሳይሆን በነገሮች የመጠቀም ብቃታቸው ነው፡፡ ድሃ ሕንፃን ያያል፡፡ ውስጡ ግን ማደር አይችልም፡፡ ምግብ ሰዎች ሲበሉ ይመለከታል፡፡ እርሱ ግን ከፍሎና መርጦ ሊመገብ አይቻለውም፡፡ ስለሆነም ሀብታም ነን ማለት የሚቻለው ያለንን ሀብት ስንጠቀምበት ነው፡፡ እናም ኢትዮጵያውያን ተፈጥሮ የቸረችን ባለጠጎች ብንሆንም ካልተጠቀምንበት ድሃ መባላችን አይቀርም፡፡ ከዚህ አንጻርም ሀብታም ነን ይባል እንጂ ያለንን ሀብት እንኳንስ መጠቀም ይቅርና ነክተነዋል የሚል አምነት የለኝም፡፡

እንዳንጠቀም ያደረጉንን ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ለተባለው ደግሞ ምላሹ ልዩ ልዩ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ጣታችን ወደሌሎች መጠቆምን ብቻ የምንፈልግ መሆኑ ነው፡፡ በሌሎች ከማመካኘት ወደ ውስጥ ራስን መመልከት አንፈልግም፡፡ ሌላው የሥራ ባህላችን ውስን ነው፡፡ ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ የሥራ ባህል እንዲኖረው አላሳየነውም። ሠርተን አርአያ መሆን አልቻልንም፡፡ ያለንን ሀብት ለመጠቀም የተለያዩ ሥልጠናዎች የመውሰድ ክፍተት ይታይብናል፡፡ የግንዛቤ ሁኔታም እንዲሁ ችግራችን ነው።

አሁን ላይ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ስለሆነም ሀገራችን የምትፈልገው እንካስላንትያ ሳይሆን የተግባር ሰው ነው፡፡ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደማኅበረሰብ አሁን ላይ ማተኮር ያለብን ሥራ ላይ መሆን ይገባዋል፡፡ ካልሆነ ግን የሚገጥመን ችግር እጅግ አደገኛ ይሆናል፡፡ ዋጋም ያስከፍለናል፡፡ እውነቱን ለመናገር አሁን ባለን ሥራ ባህል፤ አሁን ባለን ከሥራ የተገነጠለ ትኩረት የትም አንደርስም፡፡ ለመኖር ጭምር እንፈተናለን፡፡ ህልውናችንን አደጋ ውስጥ ይከተዋል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ነገሮችን ማስተካከል ይጠበቅበታል፡፡

አዲስ ዘመን፡- እሴት መጨመር እንደ ሀገር የሚኖረው ፋይዳ ምንድን ነው ?

ዶክተር ፋንታሁን፡- እሴት መጨመር ማለት ከጥሬው ውጪ በጥራትና በተለየ መልኩ ምርትን አምርቶ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በብዛት ከታዳጊ ሀገር ጥቅም ጋር ይያያዛል፡፡ ሀገራቱ ምርቶችን ሲያመርቱ እሴት ሳይጨምሩባቸው በመርከብ እየተጫኑ በርካሽ ዋጋ ወይም በነፃ በሚባል ዋጋ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ሲሉ ይሸጧቸዋል፡፡ ተጠቃሚዎቹ ጥሬ ዕቃዎቹን የሚረከቡት አካላት ናቸው፡፡

ስለዚህም ተጠቃሚ ለመሆን ጥሬ ዕቃዎቻችን ላይ እሴት መጨመር አለብን፡፡ ከዚህ አኳያም እሴት መጨመር ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡

ከእነኝህ መካከልም የመጀመሪያው ለአምራቹ ገበሬ አንድ ምርት እሴት ተጨምሮበት ሲሸጥ የተሻለ ገቢ ያስገኛል፡፡ ሁለተኛ እሴት የመጨመር ሂደቱ የሥራ ዕድል ይፈጠራል፡፡ ለምሳሌ፡- የተወሰነ ምርት በትንሹ መጭመቅ እና ማጣራት ቢኖርበት መጭመቂያ ላይ የሚሠሩ ፤ መጭመቂያውን የሚጠብቁ ፤ የሚያጸዱ የተለያዩ ሰዎች የሥራ ዕድል ያገኛሉ ማለት ነው፡፡

በሦስተኛ ደረጃ እሴት የተጨመረበት ምርት ከፍ ባለ ዋጋ ይሸጣል፡፡ ለምሳሌ፡- ሰሊጥ በኩንታል 12 ሺህ ብር የሚሸጥ ቢሆን እና ዘይቱን ጨምቆ እና አጣርቶ ቢሸጥ ከአንድ ኩንታል 10 ሊትር ዘይት ቢወጣ 10 ሊትሩ ዘይት ከ10 እጥፍ ባላነሰ ዋጋ ይሻጣል፡፡ በተጨማሪም የመጓጓዣውን ዋጋ ይቀንሳል፡፡ ሌላኛው እሴት ሲጨምር የሚጠቅመው ነገር በእሴት መጨመር ሂደት ውስጥ የምግብ ዕቃዎች ከሆኑ ይዘታቸው ይሻሻላል፡፡ ስለዚህ ለተጠቃሚው ራሱ የተሻለ የምግብ ይዘት ያለው ምርት ገበያ ላይ እንዲውል ያደርጋል፡፡ የተጠቃሚውንም እርካታ እና ተጠቃሚነት ይጨምራልም፡፡

እሴት በጨመር ከውጭ ሀገር የምናስመጣቸውን ነገሮች በሀገር ውስጥ ምርቶች እንድንተካም ያደርገናል። ለአብነት በተቋም ደረጃ እየሠራን ያለውን ነገር ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህም የጾም ማኪያቶ ከኖርማል ማኪያቶ ዋጋው ከእጥፍ በላይ ነው፡፡ ይሄን ከውጭ በብዙ ዶላር ከፍለን እናመጣዋለን፡፡ ነገር ግን በቀላሉ መሥራት የምንችለው ነው፡፡ እሴት መጨመር ወደ ውጭ ሀገር እስከመላክ የሚያደርስ ሥራ የሚሠራበት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አትክልት እና ፍራፍሬን ማንሳት ይቻላል፡፡ ወደ ውጭ በጥሬው ጭምር በስፋት በማምረት ይላካል፡፡ ከዚያም አልፎ አሁን አሁን አቮካዶን ዘይቱን እየጨመቁ በከፍተኛ ዋጋ የሚሸጡ አሉ፡፡ በዚህም የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገራችን እየገባ ይገኛል፡፡

አዲስ ዘመን ፡- ስለ ተቋማችሁ ሥራ ብዙ ሰዎች አይረዱም፡፡ እስኪ ትንሽ ይበሉን?

ዶክተር ፋንታሁን፡- የባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች ያከናወነ ተቋም ነው፡፡ ለአብነት የእኔን ዘርፍ ብቻ ብትወስጂ እንደሀገር ብዙ ሥራዎች የተከናወኑበት ነው፡፡ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የእኛ ድርሻ ተደርጎ የተሰጠን በምርምር ምርቶችን እና አገልግሎቶችን ማውጣት ነው። በሰዎች ስልጠናና አቅም ግንባታ እንዲሁም በመሠረተ ልማት ማበልጸግ ዙሪያ እንድንሠራ ኃላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ ይህንንም በሚገባ እያከናወንን እንገኛለን፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የምርምር ሥራ ዋነኛ ትኩረት ተደርጎ ተሰጥቶናልና በምርምር ምርት እና አገልግሎቶችን እናወጣለን፡፡

የማመከር ሥራ እንሠራለን፡፡ ከዚህም በላይ በምርምር የወጡትን ምርቶች ሌሎች ጥቅም ላይ እንዲያውሏቸው ለማድረግና ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ እንዲገቡ ዕድል ለመስጠት የማስተዋወቅ ሥራ እንሠራለን፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ልክ ተቀብሎ ወደተግባር የሚገባ አካል እምብዛም ነው፡፡ ምክንያቱም በምርምር የተገኘው ምርት ከዚያም በኋላ ብዙ ልፋትን ይጠይቃል። ስለዚህም እንደመንግሥት የመተጋገዝ ሰንሰለቱን ካልዘረጋና ተቋማት እርስ በእርስ እንዲሠሩ ካላደረገ ተቋማችን የሚሠራቸው የምርምር ውጤቶች ጥቅም ላይ ሊውሉ አይችሉም፡፡ እናም መንግሥትም ሆነ የግሉ ዘርፍ በትብብር ለመሥራትና ሀገርን ለመለወጥ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን፡፡

ዶክተር ፋንታሁን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 27/2015

Recommended For You