ነሐሴ 10 ቀን 2015 ዓ.ም እና ነሐሴ 16 ቀን 2015 ዓ.ም በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ብቁ ዲፕሎማት የሚባለው ማን ነው? በሚል ርዕስ በሁለት ዙር የግል አስተያየቴን ሰጥቼ ነበር። ሶስተኛውና የመጨረሻው ዙር እንደሚከተለው የቀረበ ሲሆን የአጠቃላይ ጽሁፉ ዓላማ አዲስ ለሚቀጠሩና በጅምር ላይ ለሚገኙ ዲፕሎማቶችና በዲፕሎማሲ ዙሪያ ፍላጎት ለአላቸው አንባቢዎች መለስተኛ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው፡፡
ጥሩ አድማጭ የሆነ/የሆነች
የዲፕሎማሲ ሥራ የመናገር ችሎታን ብቻ ሳይሆን በትዕግስት የማዳመጥ ችሎታንም የሚጠይቅ ሥራ ነው። በተለይ ዲፕሎማቶች ከአገር ጥቅም ጋር በተያያዘ ብዙ ውይይትና ድርድር ያከናውናሉ፡፡ በዚህ ሂደት አቻ ወይም ተቃራኒ ወገን የሚናገረውን በአግባቡ በማዳመጥ እንዲሁም ሀሳብን በማስጨረስ ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው፡፡
ብዙ ማዳመጥ የውይይትን ጊዜ ከመቆጠቡ በተጨማሪ የተቃራኒን ወገን ሀሳብ ሰብስቦ በአንድ ምላሽ ለመቋጨት ያግዛል፡፡ የድርድር ክህሎት ላይ ጥናት ያጠኑ ምሁራን የሚሉት በድርድር ወቅት አንድ ዲፕሎማት ሰማንያ ፐርሰንት ያህል አድማጭ፤ ቀሪውን ሀያ ፐርሰንት ያህል ተናጋሪ ከሆነ ስኬታማ ይሆናል ይላሉ፡፡ ብዙ ማድመጥ የተቃራኒን ወገን ፍላጎትና ስጋት ለመረዳት ያስችላል፡፡ በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ ምላሽ ለመስጠት ከመሞከር ይልቅ በቂ ጊዜ ሰጥቶ አድምጦ ምላሽ መስጠት ውጤታማ ተደራዳሪ ያደርጋል፡፡
ተደራዳሪ ወገንን ጊዜ ሰጥቶ ማዳመጥ ሲቻል በተመሳሳይም ተቃራኒ ወገን የምንናገረውን ነገር የማዳመጥ ፍላጎት ይፈጠራል፡፡ መደማመጥ የሌለበት ክርክር ወይም ድርድር ከውይይት አልፎ “ጭቅጭቅ” ይሆንና ዲፕሎማቱ ማግኘት ያለበትን ነገር ሳያገኝ ይቀራል፡፡ ስለሆነም አንድ ብቁ ዲፕሎማት ሌሎችን የማድመጥ እድል ይሰጣል፤ በተመሳሳይ የመደመጥ መብቱን ያስከብራል። በተለምዶ የሰው ልጅ ሁለት ጆሮ እና አንድ አፍ የተሰጠው ብዙ እንዲያዳምጥና ጥቂት እንዲናገር ነው ይባል የለ! ይህ ማለት ግን መድረኩን በሙሉ ለተቃራኒ ወገን መስጠት ማለት ሳይሆን ጥሩ አድማጭ ፡፡ ጥሩ መላሽ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው ለማለት ነው፡፡
ሰጥቶ መቀበል መርህን የሚከተል/ የምትከተል
የዲፕሎማሲ ሥራ በዋናነት የመቀበል ብቻ ወይም የመስጠት ብቻ ላይ ያተኮረ ሳይሆን ሰጥቶ የመቀበል መርህ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ሁለት ዲፕሎማቶች አገራቸውን ወክለው ሲወያዩ አንደኛው ዲፕሎማት እኔ የምፈልገውን ብቻ ስጠኝ ለአንተ ግን ምንም የምሰጥህ ነገር የለም የሚል አቋም ከያዘ መግባባት አይችሉም፡፡ ዲፕሎማሲ የሚለውም ቃል እዚህ ጋር ያበቃል፡፡
ሰጥቶ መቀበል ሲባል ችግሮችን ለመፍታት ይቻል ዘንድ የምንሰጠውና የምንቀበለው መረጃ ወይም ሀብት ሊሆን ይችላል፡፡ በአገሮች መካከል የቦታ እና የድንበር ችግርን ለማስወገድ ሊገለገሉበት ይችላሉ። ሰጥቶ መቀበል ለዲፕሎማቶች ብቻ የሚያገለግል አይደለም፡፡ ሰዎች በየእለት ኑሮዋቸው ውስጥ የሚያከናውኑት ነገር ነው እንጂ። ሰጥቶ መቀበል በከተማ ብቻ የሚከናወን ሳይሆን በገጠሩ ህብረተሰብ መሀከልም የሚከናወን ነው። በእኔ እምነት ከከተማ ሰው ይልቅ የገጠር ሰው ሰጥቶ መቀበልን መርህ የበለጠ ይጠቀሙበታል። ለአብነት የሚያክል እርሻና አጨዳ በመረዳዳት የመሥራት፤ ሰርግንና ግብዣን “አቆልቋይ” በሚል ስያሜ ውለታ የመከፋፈል ወይም ሰጥቶ የመቀበል እና ወዘተ ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ሰጥቶ መቀበል እንደየባህሉ ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ብቁ ዲፕሎማት በሥራው ሂደት ሰጥቶ የመቀበል መርህን በመተግበር የአገርንና ህዝብን ጥቅም ያስከብራል፡፡
የዲፕሎማሲ ፕሮቶኮል የሚጠብቅ/ የምትጠብቅ
ዲፕሎማትና ፕሮቶኮል የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ፕሮቶኮል ሲባል የአለባበስ ብቻ ሳይሆን የአሰራር ሥርዓትንም የሚመለከት ነው፡፡ አንድ ዲፕሎማት የሌላ አገር አቻ ዲፕሎማት ጋር ተገናኝቶ ለመወያየት ሲገናኝ አለባበሱ ማራኪ ከሆነ የመጀመሪያው ግንኙነት ሳቢ ይሆናል። ደረጃውን ያልጠበቀ አለባበስ ካለ ግን በተቃራኒው ወገን የሚታየው ክብር እንዳልተሰጠው ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
በበርካታ የግብዣ ጥሪዎች ላይ ጋባዡ የሚያስቀምጠው የአለባበስ ሥርዓት ይኖራል። ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚገኙበት ግብዣ ከሆነ ሙሉ ልብስ የመልበስ ግዴታ ያስቀምጣሉ፡፡ ይህ ዓይነት ጥያቄ ካለ ጅንስና ስኒከር ጫማ አድርጎ ወደ ግብዣ ቦታ መሄድ ጋባዡን ያስከፋል፡፡ ሙሉ ልብስ ሳይለበስ ባህላዊ ልብስ ቢለበስም የበለጠ ማራኪ ሊሆንም ይችላል፡፡
አምባሳደር ሆነው ወደሌላ አገር የተሾሙ ዲፕሎማቶች የሹመት ደብዳቤያቸውን የሚያቀርቡት ለአገሩ መሪ እንደመሆኑ መጠን በአብዛኛው ሙሉ ልብስ የመልበስ ወይም የአገር ባህል ልብስ የመልበስ ሁኔታ ይታያል፡፡ በሁሉም አገር ያለው ፕሮቶኮል አንድ ዓይነት አይደለም። ለአብነት ያህል ኢራኖች ከረባትን የእኛ ባህል ስላልሆነ አናደርግም ይላሉ፡፡ በመሆኑም ከረባት ሳያደርግ የሚመጣ የኢራን ዲፕሎማት ፕሮቶኮሉን ያልጠበቀና ለእኛ ክብር ያልሰጠ አለባበስ ነው ብለን መውሰድ የለብንም። እንደቻይና ያሉ አገሮች ደግሞ ለፕሮቶኮል የሚሰጡት ቦታ እጅግ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ብቁ ዲፕሎማት ከአቻው ዲፕሎማት ጋር ለሚያደርገው የሥራ ግንኙነት ለአለባበሱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይሰጣል፡፡ ከልብስ ባሻገር ያለውን የፕሮቶኮል ሁኔታ ወደፊት የምመለስበት ይሆናል፡፡
የዲፕሎማሲ አፃፃፍ ሥርዓትን
ጠንቅቆ ማወቅ
በዓለማችን ላይ ሁለት መቶ የሚደርሱ አገሮች አሉ፡፡ እነዚህ አገሮች በሚያደርጉት የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተዘበራረቀ የአፃፃፍ ፎርማት የሚጠቀሙ ከሆነ ለመግባባት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ለዚህም ሲባል አንድ ወጥ የሆነ የአፃፃፍ ሥርዓት እንዲኖር የተደረገ ሲሆን በዋናነት የደብዳቤው መግቢያ እና መዝጊያ ተመሳሳይ እንዲሆን ተደርጓል (NOTE VERBAL)፡፡ በእርግጥ ዋናው መልዕክት እንደጉዳዩ የሚለያይ ሲሆን የሚጻፍበት ቦታ በተቀመጠው የጽሁፍ መክፈቻ እና መዝጊያ መሀከል ነው፡፡
ኖት ቨርባል ከሚባል አፃፃፍ በተጨማሪ ዲፕሎማቶች ሊያውቋቸው የሚገቡ ሌሎችም የአፃፃፍ ሥርዓቶች አሉ፡፡ ለአብነት ያክል Aide Memoire, Non Paper, Recall, Agrèment , Credentials, Demarche, Joint Communiqiè ይጠቀሳሉ። የእነዚህን የአፃፃፍ ሥርዓቶች አጠቃቀም ማወቅና መተግበር የአንድ ብቁ ዲፕሎማት መለኪያ ናቸው። እነዚህን ባለማወቅና አሁን እኔ ይህንን በምፅፈው ዓይነት የሚፃፍ ከሆነ የመልዕክቱ ተቀባይ ወገንን ያስከፋል ወይም ምላሽ እንዲነፈግ ያደርጋል፡፡
የዲፕሎማሲያዊ አፃፃፍ ሥርዓት ከማንበብ ብቻ ሳይሆን ከአንጋፋ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች መማር የሚቻል ነው፡፡ ከኤምባሲዎችም ጋር የተደረጉ የፅሁፍ ምልልሶችን በማየት መረዳትም ይቻላል። የዲፕሎማሲ አፃፃፍ ሥርዓቱን ከማወቅ ባሻገር የሚጠቀሟቸው ቃላቶች በጥንቃቄ የተመረጡ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የአንድ ቃል አጠቃቀም የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ሊያናጋ ይችላል። በመሆኑም በአንድ ብቁ ዲፕሎማት ፅሁፎች ውስጥ ሌላውን ወገን የሚስብ መሆኑ ዲፕሎማቱ/ቷ ያለበትን/ያለችበትን ከፍታ ያሳያል፡፡
ትዕግስተኛ እና ተስፋ የማይቆርጥ/ የማትቆርጥ
አንድ ዲፕሎማት ችግሮችን በጥበብ የመፍታት አገራዊ ኃላፊነት ያለበት ሰው ነው፡፡ በዓለም ላይ የሚከናወኑ ከፍተኛ ጉዳዮችና ለውጦች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የዲፕሎማቱ ሥራ መሆኑ አይቀርም። በዓለም ላይ ደግሞ የሚከሰቱ ጉዳዮች ብዛትና ፍጥነት በዲፕሎማቶች ላይ የሚፈጥረው ጫና ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ሥራው ትዕግስትንና ተስፋ አለመቁረጥን የሚጠይቅ ነው፡፡ ለአብነት ያክል ከግብፅና ሱዳን ጋር ሲደረግ የነበረው ድርድር እጅግ ውስብስብና ትዕግስት የሚፈትን እንደሚሆን መገመት ስህተት አይሆንም።፡ ሆኖም ተደራዳሪዎቹ ሲደራደሩ ለበርካታ ሰዓታት። ቀንና ለሊት መቀመጥና መወያየት የሚጠይቅ በመሆኑ ትዕግስት ያጣ ዲፕሎማት ይህንን ኃላፊነት ሊወጣ አይችልም፡፡
አንድ ብቁ ዲፕሎማት በትንሹ ተስፋ የሚቆርጥ አይደለም፡፡ ዛሬ ባይሳካ ነገ አሳካዋለሁ ብሎ ተግቶ የሚሰራ መሆን አለበት፡፡ አንድ ዲፕሎማት በአገሩ መንግሥት ፍላጎትና በተቃራኒ ወገን በኩል ያለው ፍላጎት የተራራቀ ከሆነ እጅግ ፈታኝ ሥራ ውስጥ ይሆናል። ተቃራኒ ወገንን ለማሳመን የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም፡፡ ይህንን ኃላፊነት ካልተወጣም በመንግሥት በኩል የሚደርስበት ጫናም ቀላል አይሆንም፤ እንደደካማና አቅም የሌለው ተደርጎ ሊወሰድበት ይችላል፡፡ ሥራው የመንፈስ ጭንቀት ሊፈጥርበትም ይችላል፡፡ የግሉ ጉዳይ ሳይሆን የአገር ጉዳይ ነዋ!
ያም ሆነ ይህ ብቁ ዲፕሎማት በትዕግስትና ተስፋ ባለመቁረጥ የአገርን ኃላፊነት የሚወጣ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀጥረው በሚኒስቴር መ/ቤቱ ከሰላሳ ዓመት በላይ ሰርተው ጡረታ የሚወጡ ጉምቱ ዲፕሎማቶች አይኖሩንም ነበር፡፡
ቀድሞ ተመልካችና ምላሽ ሰጪ መሆን
ዲፕሎማሲ ሂደት ነው፡፡ ቀድሞ የሚመለከት ዲፕሎማት (Proactive) ከወዲሁ በቂ ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ያልታሰበና አገርን የሚነካ ንግግሮች ከተከሰቱም እንደአመጣጡ ምላሽ የሚሰጥበትም (Reactive) ሁኔታ ሊከሰት ይችላል፡፡ ዲፕሎማቱ ማስተባበያ የሚያስፈልገውን ጉዳይ እንዳልሰማ አድርጎ ቢያልፈው እንደተቀበለው ተደርጎ ይወሰዳል።
የውጭ ግንኙነት ሥራ በርካታ አጀንዳዎችን ይዞ የሚመጣ ነው፡፡ አንዳንድ አጀንዳዎች በተናጠል ከአንድ አገር ጋር ብቻ የሚሰራ ላይሆን ይችላል። ከነማን ጋር ብሰራው ጥሩ ነው? እነማን አገሮች ጋር ምን ማግኘት ይቻላል? እኔ ጋር ምን አለ? አጋዥ የሚሆኑ ባለድርሻ አካላትስ አሉ ወይ? የሚሉ እና በርካታ ጥያቄዎችን እያነሳ ምላሽ የሚሰጥ ዲፕሎማት ቀድሞ ተመልካች ዲፕሎማት ነው፡፡
ቀድሞ ተመልካች ዲፕሎማት በአገር ላይ ሊደርስ የሚችልን አደጋ የማስቆም እድሉ ከፍተኛ ነው፤ ተጠቃሚነት የሚያመጣም ጉዳይ ካለ ከፊት ተሰልፎ የሚገኝ ነው፡፡ ቀድሞ ተመልካች ለመሆን በአጀንዳው ዙሪያ መለስተኛ የቢሆን ትንተና (Scenarios) ያከናውናል፡፡ በዚህ ትንተና አንድ ውጤት ያልተሳካ ወይም የተሳካ ወይም በከፊል የተሳካ ሊሆን ይችላል የሚል መነሻ ይዞ እያንዳንዱ አማራጭ ክስተት ቢመጣ እኔ ምን ማድረግ አለብኝ? የያዝኩት ጉዳይ እንዲሳካ ሊያደርገኝ የሚችለው ምን ባደርግ ነው? የሚል ሥራ መሥራትን ይጠይቃል፡፡
ቀድሞ ተመልካች ዲፕሎማት ለውይይትና ድርድር ከመሄዱ በፊት በቂ ዝግጅት ያደርጋል። የአንድ ብቁ ዲፕሎማት መለኪያው የወደፊቱን የሚያይ፣ የሚዘጋጅና ለውጤት የሚተጋ ነው፡፡
የማግባባት ክህሎት መኖር (Lobby)
የዲፕሎማሲ ሥራ ደጋፊዎችን በማበራከትና ተፅዕኖ በመፍጠር የሚሰራም ነው፡፡ በተለይ የባለብዙ ወገን ፎረሞች ውሳኔ የሚተላለፉት በድምጽ ብልጫና በመግባባት (Consensus) በመሆኑ ብዙ ድጋፍ ያለው ሀሳብ በውሳኔ እንዲያልፍ ይደረጋል፡፡
አንድ ብቁ ዲፕሎማት አገሩ የጣለችበትን ኃላፊነት ለመወጣት ይችል ዘንድ የአገሩ ፍላጎት ተቀባይ እንዲሆን ከሌሎች የፎረም አባላት ጋር የመመካከር፣ የማሳመን፣ ድጋፍ የመጠየቅና ከፍተኛ ድምጽ ለማግኘት ሊተጋ ይገባል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ነው ሰጥቶ መቀበል መርህ ሊያግዝ የሚችለው፡፡ ድጋፍ የሚጠየቀው አገር ወይም ዲፕሎማት በወቅቱ የሚፈልጋቸው ሌሎች ጉዳዮች ካሉ እነሱን የማጥናትና እኔ የእናንተን አጀንዳ በዚህ ወይም በዚያ መድረክ ላይ እደግፋለሁ፤ እናንተ ደግሞ እኔን በዚህ አጀንዳ ላይ ደግፉኝ የማለትና የትብብር ስሜት መፍጠር የብቁ ዲፕሎማት መለኪያ ነው፡፡
አንድ ዲፕሎማት በእራሱ ሊደርስባቸው የማይችልባቸውን መሪዎችና ሌሎች ባለሥልጣናት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር የማግባባት ክህሎትና ተግባር የሚያከናውኑ ሰዎችንና ተቋማትን ሊጠቀም ይችላል። ይህ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን የግድ አስፈላጊ በሆነ ጉዳይ ግን ትርፍና ኪሳራን በማመዛዘን ሊሰራበት የሚችል ነው፡፡ አንድ ብቁ ዲፕሎማት ኃላፊነቱን ለመወጣት ሲል ከተለያዩ ሰዎች ጋር በመገናኘትና በማግባባት መሥራት የሚችል ሲሆን ብዙ ድካም ያለው ቢሆንም ውጤቱ ያማረ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
ከመላኩ ሙሉዓለም ቀ.
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የውጭ ግንኙነት ተመራማሪ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/2015