ለአረጋውያን ክብር የሚተጋው ‹‹ክብረ-አረጋውያን››

ሀገራት አረጋዊነትን የሚበይኑት በራሳቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ የአወቃቀር ሁኔታ ላይ ተመስርተው ነው፡፡ አንዳንድ ሀገራት አረጋዊነትን ከዕድሜ ዘመን ቆይታ አንጻር ሲተረጉሙት፣ ሌሎቹ ደግሞ ከዕድሜ በተጨማሪ ከተደጋጋሚ የጤና መታወክና ከመሥራት አቅም ማነስ ጋር ያቆራኙታል። ከጡረታ መውጫ ዕድሜ ጋርም ተያይዞ ሲተረጎም ይስተዋላል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትርጉም መሠረት ደግሞ አረጋውያን የሚባሉት ዕድሜያቸው 60 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ይህ ትርጉም በኢትዮጵያም ተቀባይነት ያለው ሲሆን፣ ይህ የዕድሜ ዘመን ከጡረታ መውጫ ዕድሜ ጋርም ይመሳሰላል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት መሠረት፣ በዓለም ላይ እ.አ.አ. በ2050 ዕድሜአቸው 60 አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን እንደሚደርስ ይተነብያል፡፡ በ1998 ዓ.ም ይፋ በሆነ መረጃ መሠረት፣ በኢትዮጵያ ያለው የአረጋውያን ቁጥር ከሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ የነበረ ሲሆን፣ ይህም ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ሕዝብ አራት ነጥብ ስምንት በመቶ ያህሉን የሚሸፍን ነበር፡፡ በ2014 ዓ.ም ደግሞ ይህ አሀዝ ከአምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ቀደም ብሎ ይፋ ያደረገው የትንበያ መረጃ ያመለክታል፡፡

አረጋዊነት በብዙ ታዳጊ ሀገራት አሉታዊ ትርጉም እንደሚሰጠው ጥናቶች አመላክተዋል፡፡ የታዳጊ ሀገራት አረጋውያን ኅብረተሰቡ ለአረጋዊነት የያዘውን የተዛባ አመለካከት አሜን ብለው በመቀበልና ራሳቸውንም ከተለያዩ ኅብረተሰባዊ ተሳትፎዎች በማግለል፣ አረጋዊነትን ‹‹ምንም ማድረግ የማይቻልበት የዕድሜ ዘመን›› አድርገው ተቀብለው እንደሚኖሩ እነዚህ ጥናቶች አሳይተዋል፡፡ የዕድሜ ዘመን ቆይታን ተከትለው የሚከሰቱ ሥነ-ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ፣ አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ሁኔታ ለውጦች አረጋውያንን ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ያደርጓቸዋል፡፡

የችግሩ ዓይነትና ስፋት ቢለያይም በተለያዩ ዓለም አካባቢዎች የሚኖሩ አረጋውያን ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአረጋውያን ላይ አተኩረው የሚሠሩ ተቋማት ይፋ የሚያደርጓቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አረጋውያን በዕድሜና በሌሎች ተጓዳኝ ምክንያቶች የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፡፡ በተለይም ከኅብረተሰቡ የአስተሳሰብና የአኗኗር ዘይቤ መለወጥ ጋር በተያያዘ ከሚደርስባቸው ሥነ-ልቦናዊ ድቀትና ከጤና መታወክ ባሻገር ጧሪና ደጋፊ በማጣት መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን እንኳን ለማሟላት የሚቸገሩ አረጋውያን በጣም በርካታ እንደሆኑም የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

አረጋውያን በየዘርፉ አመቺ የሆነ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው ለረጅም ጊዜ በልዩ ልዩ የእውቀት ዘርፍ ያካበቱትን ልምድና ተሞክሮ ተተኪ ለሆነው ለአዲሱ ትውልድ በማስተማርና በማስተላለፍ የሀገር ህልውና እንዲጠበቅና ታሪክ፣ ልማትና እድገት ቀጣይ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው እሙን ነው፡፡ አረጋውያን በዕድሜያቸው ያካበቱትን ዕውቀትና ልምድ እንዲሁም ትምህርታዊ ምክርን የማካፈል፣ ማኅበረሰቡን በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ መፍትሔ የመፈለግ፣ የሚከሰቱ ግጭቶችን የመዳኘትና የማስማማት፣ በአጠቃላይ የአካባቢን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ በኩልም ጉልህ ሚና አላቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን አረጋውያንም የዘርፈ ብዙ ችግሮች ሰለባዎች ናቸው፡፡ አረጋውያን ካሉባቸው ብዙ ችግሮች አንፃር በቂ ነው ባይባልም፣ በአረጋውያን እንክብካቤና ድጋፍ በጎ ተግባር ላይ የተሰማሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ ‹‹ክብረ አረጋውያን›› ምግባረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡

የድርጅቱ መሥራችና ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ሙኒኤ፣ ሰውን የመርዳት ተፈጥሯዊ ባህርይና ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ ይህ ባህርያቸው ‹‹አረጋውያንን በመርዳት በጎ ተግባር ላይ ያሰማራኛል›› ብለው አስበው አያውቁም ነበር፡፡ በጎ ተግባር ዓይነቱ ብዙ፣ ወሰኑም ሰፊ ነውና ወይዘሮ ወርቅነሽ ‹‹ከፈጣሪ የታዘዝኩት›› ባሉት ተልዕኮ መነሻነት ለሀገርና ለወገን ብዙ ሠርተው የማምሻ ዕድሜያቸውን በጉስቁልናና በመከራ ለማሳለፍ የተገደዱ አረጋውያንን ለመርዳት ጉዞውን ጀመሩት፡፡

ድርጅቱ የተቋቋመው ከ12 ዓመታት በፊት ነው፡፡ ‹‹ክብረ የተባለውም ለአረጋውያን ክብር ስለሚገባቸው ነው›› ይላሉ ወይዘሮ ወርቅነሽ፡፡ ‹‹ሥራውን ስንጀምር ‹አረጋውያን፣ አረጋውያን የሚሉ አዲስ ሥራ ይዘው የመጡ ሰዎች አሉ› የሚሉን ሰዎች አጋጥመውናል። ለግል ጥቅማችን እንደተነሳን የሚያስቡና ዓላማችንን ያልተረዱልን ሰዎችም ነበሩ፡፡ ሥራውን የጀመርነው በራሳችን ወጪ ነው›› በማለት ሥራው ገና ከጅምሩ ፈተና የበዛበት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ላጋጠሟቸው ፈተናዎች እጅ ሳይሰጡ ተጉዘው የብዙ አረጋውያንን እንባ ማበስ ችለዋል፡፡

‹‹ክብረ አረጋውያን›› ምግባረ ሰናይ ድርጅት ለአረጋውያን የምግብ፣ የጤና፣ የሕክምና ድጋፍና እንክብካቤ የሚያደርግ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ ውስጥ 200 አረጋውያን ድጋፍና እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው፡፡ በተቋሙ ውስጥ የሚኖሩ አረጋውያን በቀን ሦስት ጊዜ ይመገባሉ፤ የሕክምና ክትትልና እንክብካቤም ይደረግላቸዋል፡፡

ወይዘሮ ወርቅነሽ እንደሚሉት፣ ድርጅቱ የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት የአረጋውያንን ቤት በማደስ ተግባራት ላይም ይሳተፍ ነበር፡፡ በርካታ አረጋውያን በገቢ ማስገኛ ተግባራት (Income Generating Activities – IGAs) ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል። ወደ ማዕከሉ ከሚገቡ አረጋውያን መካከል አብዛኞቹ አሳዛኝ ለሆነ ጉስቁልና ተዳርገው የቆዩ ስለሆኑ በማዕከሉ የሚደረግላቸው እንክብካቤና ድጋፍ ሁለገብ ነው። ድርጅቱ በማዕከሉ ውስጥ ለአረጋውያን እንክብካቤ ከማድረግ በተጨማሪ አንዳንዶቹን ድጋፍ አድርጎ ወደመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ የሚያደርግበት አሠራርም አለው፡፡

የማዕከሉ የ12 ዓመታት የበጎ አድራጎት ሥራዎች ለአረጋውያን እንክብካቤ መሠረት የጣሉ ተግባራት እንዲከናወኑና የሚያኮሩ ለውጦች እንዲመዘገቡ እንዳስቻለ ወይዘሮ ወርቅነሽ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በጣም ብዙ ለውጥ አምጥተናል፡፡ ብዙዎች እኛን በማየት ለአረጋውያን እንክብካቤ ተግባር ተነስተዋል፡፡ ዛሬ አረጋውያንን ሲደግፉ ለሚታዩ ግለሰቦችና ተቋማት አርዓያ ሆነናል ብዬ አስባለሁ፡፡ እኛን አይተው ሌሎች የእኛን ፈለግ ሲከተሉ እጅግ ያስደስተናል›› በማለት በጎ ሥራቸውን ይገልጻሉ፡፡

‹‹እኛ ሥራውን ስንጀምር አረጋውያንን የመርዳት ተግባራት አሁን ካለበት ደረጃ በጣም ያነሰ ነበር። ሌሎችን ከማነሳሳታችን በተጨማሪ አረጋውያን ከገቡበት የጉስቁልና ሕይወት ወጥተው ወደ ማዕከሉ እንዲገቡና የምግብ፣ መጠለያና ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ችለናል፡፡ ነገር ግን ገና ብዙ መሥራት ስለሚጠበቅብን ብዙ ሠርተናል ብለን አናምንም። የአረጋውያን ችግር ብዙ በመሆኑ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ እውነተኛና የላቀ ለውጥ የሚመጣው ብዙ ስንሠራና ልምድ እያካበትን ስንጓዝ ነው›› በማለት ያብራራሉ፡፡

‹‹ክብረ አረጋውያን በአረጋውያን እንክብካቤና ጥበቃ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ፈር ቀዳጅ ከሆኑ ምግባረ ሰናይ ተቋማት መካከል አንዱ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ አረጋውያንን ለመርዳት (በቤት እድሳት፣ በምገባ አገልግሎት፣ በቁሳቁስ ድጋፍ…) በሚከናወኑ ተግባራት ትልቅ ኩራትና ክብር ይሰማዋል፡፡ ለአረጋውያን የሚደረግላቸው እንክብካቤ ሀገራችንንና ሕዝቡን እንዳይረግሙ አድርጓቸዋል›› ብዬ አምናለሁ የሚሉት ወይዘሮ ወርቅነሽ፣ ለሥራው መሳካት የሕዝብና የመንግሥት ድጋፍ በዋጋ የማይተመን ትልቅ ግብዓት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ሕዝብና መንግሥት ለድርጅቱ እያደረገ ስላለው ድጋፍ ሲናገሩም ‹‹የሠራነው ሁሉ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያከናወንነው እንጂ ብቻችንን ሆነን አይደለም፤ መንግሥትም ቦታ ከመስጠት ጀምሮ ብዙ ድጋፎችን አድርጎልናል፡፡ ሚዲያውን ጨምሮ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እየተባበረን ነው የሠራነው›› ይላሉ፡፡ ‹ክብረ አረጋውያን› ለአረጋውያን እንክብካቤ የሚያደርገው በዋናነት ከኅብረተሰቡ በሚያገኘው ድጋፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግና አዛኝ በመሆኑ ሕዝቡ በሚያደርገው ድጋፍ አረጋውያኑ ምግብ፣ ልብስና ሕክምና ያገኛሉ፡፡ አረጋውያኑ ድጋፍ የሚደረግላቸው በኅብረተሰቡ ነው፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በፊት ድጋፍ የሚያደርጉ አንዳንድ ተቋማት ነበሩ። በተለያዩ ጊዜያት ድጋፍ የሚያደርጉልን የፋይናንስ ተቋማትም አሉ፡፡ ትንሹን ነገር ፈጣሪ እየባረከልን እዚህ ደርሰናል›› በማለት ስለሕዝቡ ድጋፍ ይገልፃሉ፡፡

የኑሮ ውድነቱ ለአረጋውያኑ በሚቀርበው የምግብና የሕክምና አገልግሎት ላይ ጫና ስለማሳደሩ የሚገልጹት ወይዘሮ ወርቅነሽ፣ በተለይ የሕክምና ወጪው እጅግ ውድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚገልፁት፣ ወደ ማዕከሉ የገቡት አረጋውያን በኑሮ ጉስቁልናና በዕድሜ ምክንያት ብዙ የጤና እክሎች ስላሉባቸው የሕክምና ወጪያቸው ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ ነው፡፡ የሕክምና መድን ቢኖርም የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ስላለ፣ ዋጋው ውድ ይሆናል፡፡ ማዕከሉ እንክብካቤ የሚደረግላቸውን አረጋውያን ቁጥር ለመጨመር በማሰብ እያስገነባው የነበረው ሕንፃ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ግንባታው ቆሟል፡፡ ‹‹ብዙ ችግሮች ቢኖሩብንም በፈጣሪ እርዳታ ተቋቁመናቸው አረጋውያኑን የመንከባከብ ሥራችንን አላቋረጥንም። ሁልጊዜም ከሚደግፉን ኢትዮጵያውያን ጋር ሆነን፣ በፈጣሪ እርዳታ፣ ብዙ አረጋውያንን እየረዳን እዚህ ደርሰናል›› ይላሉ፡፡

ወይዘሮ ወርቅነሽ እንደሚሉት፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥትን ጨምሮ ግለሰቦችና ተቋማት ለአረጋውያን የሚያደርጉት ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ተስፋ የሚሰጥና የሚያስደስት ነው፡፡ በቅርቡ የ‹‹ክብረ አረጋውያን›› ማዕከል አረጋውያን ሁለት ጊዜያት ቤተ- መንግሥት ተጠርተው ግብዣ እንደተደረገላቸውና የተደረገላቸው ግብዣም አስደሳችና የሚበረታታ እንደሆነ ይናገራሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን ለአረጋውያን ሠርተው ያበረከቱት መኖሪያ ቤት እጅግ የሚያስደስትና አረጋውያኑ ትኩረት ማግኘታቸውን የሚሳይ እንደሆነም ወይዘሮ ወርቅነሽ ይገልፃሉ፡፡

‹‹የአረጋውያንን ችግሮች በቅርበት ተመልከተናል፡፡ ብዙና ውስብስብ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በግልም በተቋምም ሠርተዋቸው ያለፏቸው ሥራዎች በተለያየ መልክ ሀገርንና ሕዝብን ጠቅመዋል፡፡ የሀገር ባለውለታ የሆኑ ሰዎች በርካታ አስከፊ ችግሮች ሲገጥሟቸው ሀገርና ሕዝብን ቢረግሙ አይፈረድባቸውም፡፡ አረጋውያንን ተጠቃሚ ለማድረግ ብዙ ሥራ መሥራት ይገባል›› በማለት የአረጋውያን ጉዳይ ሰፊ ሥራ እና የሁሉንም ኅብረተሰብ ክፍል ትብብር እንደሚጠይቅ ያስረዳሉ፡፡

ወይዘሮ ወርቅነሽ ‹‹የኢትዮጵያ አረጋውያን ተከብረው፣ ተመችቷቸው የሚኖሩበት ተሟል ተውላቸው እንዲኖሩ፣ በኢትዮጵያዊ ባህላቸውና ሃይማኖታቸው መሠረት ተደስተው እንዲኖሩ፣ በተደረገላቸው ነገር ኢትዮጵያን እንዲመርቁ እንዲሁም ወጣቱ የአረጋውያኑን ምቾት ተመልክቶ አረጋዊነትን የሚመኝበት ጊዜ እንዲመጣ ምኞቴ ነው›› በማለት ሃሳባቸውን ይቋጫሉ፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 26/2015

Recommended For You