ከተገዢነት ወደ ገዢነት የተቀየረ የሱስ ሕይወት

ብዙዎች የቅርብ ቤተሰባቸውን አርዓያ ያደርጋሉ። ዮናታን ሊዮን ግን አጎቱን በጥሩ መንገድ አልነበረም አርዓያ ያደረገው። እንደ አጎቱ ሲጋራ ለማጨስ በሰባት ዓመቱ ተለማምዶ እና የሱስ ደረጃውን ከፍ አድርጎ 22 ዓመታትን በሱስ ዓለም ውስጥ እንዲያሳልፍ ተገደደ።

ገና በልጅነቱ የገዛው ሲጋራ ተገዢ አድርጎት ኖረ። እራሱን መንከባከብ ትቶ ሱሱን መንከባከብ ተያያዘው። ለራሱም ሳይሆን ከሰው በታች አደረገው። በጤናው ላይ ጉዳት ደረሰበት። የሚወዱት እና የሚያከብሩት ሰዎች እየራቁት መጡ። በወላጆቹም ‹‹ካሉት በታች፤ ከሞቱት በላይ ነህ›› አስባለው። ከሲጋራ እስከ ማሪዋና ያጨሰው ዮናታን የሱሱ ደረጃ ከፍ በማለቱ የእርካታው መጠን አለፈ። ቢራ እና ድራፍት ለእርሱ ምንም ሆኑ። ምርጫው የሀበሻ አረቄ ሆነ። ከእንቅልፉ ሲነሳ ስምንት መለኪያ አረቄ ካልጠጣ ያንቀጠቅጠው ጀመር፤ ራሱን መቆጣጠር ተሳነው።

የገንዘብ ችግር የሌለበት ዮናታን ከ16 ዓመቱ ጀምሮ በሙዚቃ ዘዋሪነት (ዲጄ)ነት በተለያዩ የምሽት ክበቦች ተቀጥሮ በመሥራት ይከፈለዋል። ሥራው ብዙ ሰዎችን እንዲያገኝ ስለሚያስችለው ከብዙዎች ጋር ይጠጣል። በኢትዮጵያ በበርካታ ክልሎች ተዘዋውሮ ሠርቷል።

ለእርሱ ሱስ በሽታ መሆኑ ግንዛቤ አልነበረውም። አንድ ሕይወቱን ሊቀይር የሚችል አጋጣሚ ተፈጠረለት። ዮናታን ወደ የሚሠራበት የምሽት ቤት ሲያመራ ታክሲ ውስጥ አንድ ሰው ተጠየፈው። ለወትሮው ሲጠጣ ደፋር የሚሆነው ዮናታን ድፍረቱ ከዳው። ‹‹ወድጄ እኮ አይደለም›› ሲል ችግሩንም ለተጠየፈው ሰው ማስረዳት ግድ ሆነበት።

የዮናታንን ችግር የሰማው ሰው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሱስ ማገገሚያ ማዕከል እንዳለ እና ሄዶ እንዲታከም ይነግረዋል። በዚህም መሠረት በጠዋት እየተንቀጠቀጠ (በሱሱ ምክንያት) ወደ ሆስፒታሉ አቀና። ዶክተሩ ፊት እንደቀረበም ‹‹አድነኝ?›› የሚል ተማጽኖውን አቀረበ። ያለውን ነገር ሁሉ በግልጽ ተናገረ፤ የሕክምናውም ሂደት ተጀመረ። በፍጥነት ለውጥ አሳየ። ነገር ግን ‹‹ሁለት ወርህን ጨርሰህ ውጣ፤ አልያ ግን ያገረሽብሃል።›› ቢባል አልሰማ ብሎ ስድስት ቀናትን ብቻ ቆይቶ በፍቃዱ ፈርሞ

 ከማዕከሉ ወጣ። ከስድስት ወራት በኋላም ለመጠጣት ተወሰወሰ። ‹‹አልፎ አልፎ ምን ችግር አለው አንድ ቢራ ብጠጣ?›› በማለት አንድ ብሎ ጀመረ ‹‹ድገም። ድገም።›› አለው፤ ከሁለት ቢራ የዘለለው ዮናታን ‹‹ለካ ተነፋፍቀን ነበር።›› በሚመስል ፤‹‹በቃ ዛሬ አምሽቼ ስዝናና ልደር ።›› እያለ የተወውን ሱስ በአዲስ መልክ ጀመረው።

እንደገና፣ ዳግመኛ ከሱሱ ለመዳን ፈለገ። ሁለተኛ ዕድል ለማግኘት ዶክተሮችን ተማጸነ፤ እነርሱም አላሳፈሩትም፤ እንዲገባ ፈቀዱለት። እርሱ ግን የተከለከለ ነገር አደረገ፤ ስልክ ደብቆ ገባ። ወደ ማዕከሉ በገባ በሰባተኛው ቀን አሜሪካ ኤምባሲ የሚሠራ ጓደኛው ደውሎ ወደ ሰሜን ሸዋ አንድ ሆስፒታል ላይ ጥሩ ክፍያ ሊያስገኝ የሚችል ሥራ እንዳገኘ ይነግረዋል። ለዶክተሯ የሁለት ቀናት ሥራ እንደገጠመው እና ሠርቶ እንደሚመለስ ቢናገርም አልተፈቀደለትም። ለሁለተኛ ጊዜ አሁንም አልፈልግም ብሎ ወጣ፤ በወጣበት ቀን ያቋረጠውን ሱስ ለሦስተኛ ጊዜ አደረገው፤ ሱሱም የበለጠ አገረሸበት። በድጋሚ ደም መትፋት ጀመረ።

‹‹በቃ መሞቴ ነው። አድኑኝ።›› ብሎ በተደጋጋሚ ወደ ማገገሚያ ማዕከሉ የገባው ዮናታን፤ በከባድ ልመና እና ውትወታ እንዲሁም ከሱስ ሲላቀቅ በዚህ ሥራ መሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገልጾ በከባድ ማስጠንቀቂያ ተፈቀደለት። እስከ ዛሬ በሰዎች ግፊት እና ሰዎችን ለማስደሰት ሲል እንዳደረገውም ተረዳ። በዚህ ወቅት ሱስ በሽታ መሆኑን በሚገባ አውቆ ማድረግ ያለበትን ሁሉ አደረገ።

ዛሬ ዮናታን የ“ጉድ ላክ የሱስ ማገገሚያ እና ስልጠና ማዕከል” ግብረ ሰናይ ድርጅት መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ነው። ትናንት ሱሰኛ የነበረው፤ ትናንት ደም ሲተፋ የነበረው እርሱ ከሞት ተርፎ ለብዙዎች እየደረሰ እና ለወደፊት ብዙ እንደሚሠራ እድል ስለተፈጠረለት ‹‹እድለኛው ዮናታን›› ብለው ሲጠሩት ደስ ይለዋል።

የጫት፣ የሲጋራ፣ የመጠጥ እና የአደንዛዥ ዕጽ ሱስ ያለባቸውን ሰዎች በቁጣ እና በምክር ብቻ ማዳን እንደማይቻል በመረዳቱ እንደ ጓደኛ በመቅረብ ብዙዎችን ከሱስ እንዲወጡ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል። በተለያዩ ሱሶች ውስጥ ያሉትን ሰዎች በማግኘት ልምድ ከማካፈል ባሻገር የስብዕና ግንባታ ስልጠናን ጨምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ እያደረገ ነው። ከሱሰኝነት ወጥተው የስኬት ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎችን በመጋበዝ ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ ያደርጋል።

ሁለት ጊዜ ሱሱ ያገረሸበት ዮናታን ‹‹ለምን ያገረሻል? ብዬ ሳስብ ለካ ራዕይ አልነበረኝም። አሁን ግን ራዕይ አለኝ። ለምን እንደሚያገረሽ? እንዴት ከሱስ እንደሚወጣ ልምዴን ባካፍል ብዬ በመገናኛ ብዙኃን እና በየትምህርት ቤቱ በመሄድ ራሴን አስተዋወኩ።›› ይላል። ዛሬ ላይም ሰዎች እርዳታውን ፈልገው እንደሚመጡ ይናገራል።

በእርሱ ምክንያት እስካሁን 2መቶ 55 ልጆች ከሱስ ሊድኑ ችለዋል። መዳን የማይፈልግ ሰው የለምና ሀገራችንን ከሱስ ነጻ የማድረግ ውጥን አለው። በዚህም ግምቱ አምስት ሚሊዮን ብር የሚፈጅ 20 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል የማገገሚያ ማዕከል ለመክፈት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። መንግሥት ማዕከሉ እንዲከፈት ፍላጎቱ ቢኖረውም በጀት እንደሌለው የገለጸላቸው መሆኑን በማውሳት፤ ቢያንስ እያንዳንዱ ሰው አንድ ሱሰኛ ሰው ያውቃልና ሁሉም ሰው የድርሻውን ድጋፍ እንዲያደርግ ይጠይቃል።

ዛሬ ላይ አደንዛዥ እጾች በመጠንም በዓይነትም በዝተዋል። ከልክ በላይ ደስታን የሚሰጡ እጾችን መጠቀምም በተማሪዎች ዘንድ ተበራክቷል። ችግሩ የብዙ ቤት ችግር ሆኗል። ለመተው ግን ውሳኔ ይፈልጋል። ሰዎች ከሱስ ለመላቀቅ አምነውበት ሲሆን ውጤታማ ይሆናል። ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን እንደ እስር ቤት ያዩታል። እድለኛው ሰው አሁን ላይ ደስተኛ ነው። ሌሎች ድነው እና ከሱስ ተላቀው፤ ገዢ እንጂ ተገዢ አለመሆን ደረጃ ላይ ደርሰው ሲመለከት ኩራት ይሰማዋል። ‹‹ሱስ ብዙ ነገሮችን አሳጥቶኛል። እግዚአብሔር ሊያስተምር ሲፈልግ በፈተና መካከል ያሳልፋል። ብዙ የዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ወድቀው ተነስተዋል። እንኳን አልሞትኩ። የሞተ ብቻ ነው መፍትሔ የሌለው። እኔ ተምሬበታለሁ›› ይላል።

ወደፊት ብዙ ሥራዎች የሚጠብቁት ዮናታን፤ ሱሰኝነት የሁሉም ጓዳ ውስጥ ያለ ችግር መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም በቻለው መጠን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል።

 እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 25/2015

Recommended For You