በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ክስተቶች ለኢንቨስትመቱ ዘርፍ መሰናክል እንደነበሩ በተደጋጋሚ ተገልጿል። ከጦርነቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የኢትዮጵያ ከ‹‹አጎዋ›› (AGOA) መታገድ እና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጫና የኢንቨስትመንት ዘርፉን ከፈተኑት ተግዳሮቶች መካከል ይጠቀሳሉ። ዋናው የጦርነቱ ቀጣና የነበረው የትግራይ ክልል ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች ደርሶበታል። የክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ደግሞ ጦርነቱ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸው ዘርፎች መካከል ይጠቀሳል።
የትግራይ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል መኮንን ጦርነቱ በክልሉ እጅግ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ማስከተሉን አመልክተው፣ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማነቃቃት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ በአሁኑ ወቅት በአብዛኞቹ የክልሉ አካባቢዎች አንፃራዊ ሰላም መኖሩን ተከትሎ ነባሩን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ይህን ለማሳካት ደግሞ ምላሽ ማግኘት ያለባቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉ። ባለሃብቶች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የሼድ ኪራይና ወለድ ስረዛ፣ የብድርና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት፣ የካሳ ክፍያ፣ የተፋጠነ የንግድና የሥራ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሁም የግብር እፎይታ ይጠቀሳሉ።
ባለሀብቶቹ ብዙ ጥያቄዎችን እያቀረቡ ነው። ‹ላልተጠቀምንበትና ላልሰራንበት ሼድ ኪራይ መክፈል የለብንም፤ ለደረሰብን ጉዳትና ኪሳራ የኢትዮጵያ መንግሥት ካሣ መክፈል አለበት፤ ጥሬ እቃ ከውጭ ስለምናስገባ የውጭ ምንዛሪ ይቅረብልን፤ የሥራ ማስኬጃ ብድር ያስፈልገናል፤ ሠራተኞቻችን ተበታትነዋል፣ ስልጠና ያስፈልገናል፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ግልፅ የሆነ ጥሪ ይደረግልን…› የሚሉ ጥያቄዎች አሏቸው።
‹‹አብዛኛው ባለሀብት በብድር እንደሚሰራ ይታወቃል። ይህ ብድር በእያንዳንዱ ቀን ወለድ እየቆጠረ ነው። በጦርነቱ ምክንያት ባለሀብቱ ገንዘቡን አልተጠቀመበትም፤ ገንዘቡን ካለመጠቀሙ፣ ከውድመቱና ከኪሳራው በተጨማሪ ብድሩ በየቀኑ ወለድ እየቆጠረ ነው። ስለዚህ ባለሀብቶቹ የወለድና የእዳ ስረዛ እንዲደረግላቸው እንዲሁም ካሳ እንዲከፈላቸው… እየጠየቁ ናቸው›› ሲሉ ጠቀሰው፣ ነባሩን ኢንቨስትመንት ለማነቃቃትም ሆነ አዳዲስ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የባለሃብቶች ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።
ለውጭ ባለሃብቶች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ይፋዊ ጥሪ ሊደረግላቸው እንደሚገባና በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የላቀ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይናገራሉ። ለባለሃብቶች ጥሪ አድርጎ፣ አወያይቶ፣ የሚያቀርቡትን ጥያቄ ሰምቶ እና ድጋፍ አድርጎ ወደ ሥራ በማስገባት ረገድ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኃላፊዎች ጋር በተደጋጋሚ ንግግር መደረጉን አስታውሰው፣ የተገኘው ተግባራዊ ምላሽ ግን አመርቂ ባለመሆኑ ቀጣይ ሥራ ይፈልጋል ሲሉ አቶ ዳንኤል አመልክተዋል።
የክልሉን ኢንቨስትመንት በማነቃቃት ረገድ ትልቅ ሚና ካላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የኢንቨስትመንት ሕግጋትን የማሻሻልና አዳዲስ መመሪያዎችን የማዘጋጀት ተግባር እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ዳንኤል፣ ይህ ተግባር በዋናነት የፌዴራል መንግሥቱን እንደሚመለከት ያብራራሉ። ‹‹የኢንቨስትመንት ሕግጋት በሀገሪቱ የፌዴራል መንግሥት ሕጎች መሠረት ተደርገው የሚከናወኑ ናቸው። ስለሆነም እነዚህን ሕግጋት የማሻሻልና የማዘጋጀት ኃላፊነት የፌዴራል መንግሥት ስልጣን ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።
ክልሉ በጦርነት ውስጥ በነበረባቸው ጊዜያት የተሻሻሉና በቅርቡ የተሰረዙ የኢንቨስትመንት ሕግጋት እንዳሉትም አስታውሰው፣ እነዚህ በትግራይ ክልል የሚገኙ ባለሃብቶች ሳይጠቀሙባቸው እንዲሰረዙ መደረጋቸው ተገቢ እንዳልሆነ ባለሃብቶች ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ፕሮጀክቶች ብድር እንዲያገኙ እና የተለየ የቀረጥ ነፃ ሥርዓት፣ የግብር እፎይታ፣ የብድርና ወለድ ስረዛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችለው አሰራር ተግባራዊነት መቀጠል ይኖርበታል ሲሉም ጠይቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከጦርነቱ በፊት የግብር እፎይታ የተሰጣቸው ባለሀብቶች ነበሩ። ይሁን እንጂ በጦርነቱ ምክንያት ባለሃብቶቹ ይህን የግብር እፎይታ እድል አልተጠቀሙበትም። የግብር እፎይታ የመስጠት ተግባር የፌዴራል መንግሥቱ ኃላፊነት ስለሆነ የግብር እፎይታ እንዲራዘምላቸው ጥያቄ ላቀረቡ ባለሀብቶች ምላሽ መስጠት አለበት።
የውጭ ባለሀብቶች ከውጭ ለሚያመጧቸው ባለሙያዎች የሥራ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ የሥራ ፈቃድ ለማግኘት እንዲሁም የኢንቨስትመንት ግብዓቶችን ከውጭ ለማስመጣት ባለሃብቶች የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች ብዙ ናቸው ይላሉ። ስለሆነም እነዚህን ተግባራት ለማሳለጥ ቀላል፣ ፈጣንና ምቹ አሰራሮችን መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ በነበሩ የፖለቲካ ቀውሶች ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ችግሮች ጉዳት ለደረሰባቸው ባለሀብቶች የፌዴራል መንግሥት ግልፅ የሆነ መመሪያ አዘጋጅቶ ካሣ የሚከፈልበት አሰራር ተፈጥሮ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዳንኤል፣ በትግራይ ክልል የሚገኙ ባለሃብቶችም ይህን ጥያቄ እያነሱ እንደሆነ ያስረዳሉ። ‹‹የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም ለወደመባቸው ንብረት ካሣ እየጠየቁ ነው። ከዚህ ቀደም በሌሎች ክልሎች ለወደሙ ንብረቶች የተሰጠው ካሳና ሌሎች ማበረታቻዎች በትግራይም ተግባራዊ መደረግ አለበት ነው ያሉት።
የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር እንዳሉት፤ የትግራይ ልማት ማለት የኢትዮጵያ ልማት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክት የነበረው ከትግራይ ክልል ሲመረት የነበረው ወርቅና ሰሊጥ ነው። ትግራይ ውስጥ ያለውን ባለሀብት መደገፍ ማለት ኢትዮጵያን መደገፍ ማለት ነው። ትግራይ ውስጥ ያለውን ኢኮኖሚ ማነቃቃት፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማነቃቃት ነው። የክልሉ ኢንቨስትመንት በሥራ እድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በውጭ ምንዛሪ ግኝት ትልቅ ድርሻ ነበረው። ስለዚህ በዚህ እሳቤ የተቃኘና ጉዳቱን መሠረት ያደረገ መፍትሄ መሰጠት አለበት። ይህ አለመደረጉ የክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በተፈለገው ልክ እንዳይሄድ አድርጓል›› በማለት ዘርፉ አስቸኳይ መፍትሄ እንደሚሻ ያስረዳሉ።
ብሔራዊ ባንክ የወሰዳቸው ርምጃዎች የፋይናንስ ችግር ውስጥ የገቡ ባለሀብቶች አዲስ ብድር እንዲያገኙና የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው እድል የሚፈጥሩ መሆናቸውንና ለባለሃብቶች እፎይታን እንደሚሰጡ ጠቁመው፣ ርምጃዎቹ የሚበረታቱ ቢሆኑም በቂ እንዳልሆኑ ያስረዳሉ። ‹‹የፌዴራል መንግሥቱ የደረሰውን ጉዳት መሠረት በማድረግ ሊያሻሽላቸው የሚገቡ ሕጎች፣ የድጋፍ ማዕቀፎች፣ አሰራሮች፣ አሉ። ነገር ግን እነዚያ በተሟላ ሁኔታ ባለመከናወናቸው በርካታ እንቅፋቶች እያጋጠሙ ነው። የደረሰውን ውድመት ሊጠግን የሚችል የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ጉዳቱን ሊያካክስ የሚችል ዝርዝር ሥርዓት መዘጋጀት አለበት›› ይላሉ።
የፌዴራል መንግሥቱ ኃላፊነቶች እንደተጠበቁ ሆነው የክልሉን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማነቃቃት ክልሉ በርካታ ችግሮች እያሉበትም ኃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት እያደረገ ይገኛል ያሉት አቶ ዳንኤል፣ በዚህ ረገድ ‹‹በርካታ ችግሮች አሉብን›› ብለዋል።
አቶ ዳንኤል እንዳስታወቁት፤ የሰላም ሁኔታው ሙሉና ዘላቂ መሆን አለበት። መሻሻል የሚገባቸው የሕግ ማዕቀፎች አሉ። የመሠረተ ልማት ችግሮች መፈታት አለባቸው። ከዚህ ቀደም ኢንቨስትመንቱን ያሳልጣሉ ተብለው የታቀዱ በርካታ ፕሮጀክቶች ነበሩ። እነዚህን ማስቀጠልና አዳዲስ ፕሮጀክቶችንም ማስጀመር ይገባል። የገበያ ትስስሩ እንዲጨምር የፌዴራል መንግሥቱም እገዛ ማድረግ አለበት።
የበጀት ጉዳይ ትልቅ ችግር እየሆነ ነው። ክልሉ ጦርነት ላይ ስለነበር ግብር እየሰበሰበ አይደለም። ከፌዴራል የሚመጣው ድጎማም ቢሆን ለመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ የሚበቃ አይደለም። ከተሞች በአሁኑ ወቅት ካሳ ከፍለው ለኢንቨስተሩ መሬት ማቅረብ አይችሉም። ስለዚህ አዲስ መሬት በመስጠት ረገድም ከፍተኛ ችግር አለ።
እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም የክልሉ መንግሥት ለኢንቨስትመንት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት በመታመኑ ለባለሃብቶች ጥሪ እያደረግን ነው ሲሉም አቶ ዳንኤል ይገልጻሉ። አብዛኞቹ የኢንቨስትመንት ሕግጋት የፌዴራል መንግሥትን የሚመለከቱ ቢሆኑም፤ በክልል ደረጃ መሻሻል የሚችሉትን የክልሉን ሕጎች ለማሻሻል እየሞከርን ነው ይላሉ። ‹‹ማሽን ይዘው የሚመጡ ባለሃብቶች በቀጥታ መሬት እንዲያገኙ እያደረግን ነው። ከጦርነቱ በፊት ካሳ የተከፈለባቸውን መሬቶች ግልጽ በሆነ መንገድ እያስተላለፍን ነው። ክልሉ አቅም ስለሌለው ባለሃብቱ ካሳ ከፍሎ የሚገባበትንም ሥርዓት እያመቻቸን ነው። በተለይ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ ኢንቨስትመንቱን ለማነቃቃት ያለው ተነሳሽነት መልካም ነው። ከፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ጋር ግንኙነት እየፈጠርን ነው። ባለሀብቱ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲያገኝ እየተሰራ ነው›› ሲሉ አብራርተዋል።
በጦርነት ቀጣና ውስጥ ከነበሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግና ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመን ጆነዲ፣ ቀደም ሲል ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ ለሁለት ዓመታት ያህል ስለመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምንም መረጃ አልነበረውም። የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በኮርፖሬሽኑ የተዋቀረ የባለሙያዎች ቡድን ወደ መቐለ አምርቶ ፓርኩ ስለሚገኝበት ሁኔታ ምልከታ አድርጓል። በዚህም ፓርኩ ምንም አይነት ዘረፋም ሆነ ውድመት እንዳልደረሰበት ታውቋል። ስለሆነም ፓርኩን በፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
ኮርፖሬሽኑ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማግስት ለረጅም ጊዜ ከሥራ ውጭ የነበረውን የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክን ወደ ሥራ ለመመለስ በርካታ ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል። ለአብነት ያህልም ቡድን በማዋቀር በፓርኩ ምልከታ የማድረግ፣ በፓርኩ ውስጥ ከነበሩ ባለሀብቶች ጋር የመወያየት እንዲሁም የአመራር ውሳኔ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ወሳኔ የመስጠት፣ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ሥራ አቁመው የቆዩ ባለሃብቶችን ከሼድ ኪራይ ነጻ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ለማድረግ የሚያስችሉ፣ ተግባራት ተከናውነዋል። በፓርኩ ውስጥ ከነበሩት ስምንት ባለሀብቶች ጋር በስልክና በኢ-ሜይል (e-mail) መነጋገር ተችሏል፤ በቅርቡም የጋራ ውይይቶች ይደረጋሉ።
የኢንዱስትሪ ፓርኩን ችግሮች ለማቃለል ስለተወሰዱትና በሂደት ላይ ስላሉት የመፍትሔ አቅጣጫዎች ሲያብራሩ ደግሞ ‹‹በፓርኩ ውስጥ የነበሩ ባለሃብቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሚመሩት ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ ባለሃብቶችን የማግኘትና ወደ ሥራ እንዲገቡ የማሳመን ሥራ ተሰርቷል። በፓርኩ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ሠራተኞች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅና ባለሃብቶቹ ወደ ሥራ ሲገቡ የሥራተኛ አቅርቦት ችግር እንዳይገጥማቸው ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ጋር ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል። ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ቢሮ ጋር ውይይት በማድረግ የትራንስፖርቱ ችግር የሚፈታበት ሂደትም ተመቻችቷል። የመብራትና የዳታ እንዲሁም የድምጽ መቆራረጦችን ለማስወገድ የሚያስችል ውይይት ተደርጎ ችግሩን በአጭር ጊዜ ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሥራዎች በመሥራት ላይ ይገኛሉ። የውሃ አቅርቦትን በተመለከተ ደግሞ በአካባቢው ያለው ውሃ ከማኅበረሰቡ አልፎ ለፓርኩ በትንሽ መጠን የሚደርስ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ከአስተዳደሩ ጋር በመነጋገርና የጉድጓድ ውሃ ለማውጣት የሚያስችል የፓምፕ ግዥ ለመፈጸም እየተሠራ ነው›› ብለዋል።
ከጦርነት በኋላ የሚኖር የኢኮኖሚ ግንባታ፣ በተለይም የኢንቨስትመንት ዘርፍ አስተዳደርና አመራር፣ የተለየ አሰራር እንደሚፈልግ ብዙ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በአስረጂነት ማቅረብ ይቻላል። የምጣኔ ሀብት ጥናት ባለሙያዎችም በጦርነት ምክንያት የተጎዳ የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲነቃቃና ቀደም ሲል ከነበረው አፈፃፀምም የተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኝ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ የድህረ ጦርነት የኢንቨስትመንት አመራርና አስተዳደር ሥርዓት መተግበር እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት እና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል ከተፈረመው የሰላም ስምምነት በኋላ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ መነቃቃትና ማንሰራራት ዋስትና ሊሆኑ የሚችሉ የድህረ ጦርነት የኢንቨስትመንት ማነቃቂያ ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀትና በብቃት በመተግበር የትግራይ ክልል የኢንቨስትመንት ዘርፍ ልማትንና የሀገራዊ ምጣኔ ሀብቱን ግንባታ ማፋጠን አስፈላጊ ተግባር እንደሆነ ይታወቃል።
የትግራይ ክልልም በድህረ ጦርነት ኢንቨስትመንት አስተዳደር ረገድ የተለየ አሰራር እንደሚከተል አቶ ዳንኤል ይናገራሉ።‹‹የድህረ ጦርነት ኢኮኖሚ ማገገሚያ ሥርዓት ብዙ ዓይነት አተገባበሮች አሉት። ኢንቨስትመንት ሰላም፣ ፋይናንስ፣ መሠረተ ልማት፣ የገበያ ትስስር… ይፈልጋል። የደረሰውን ውድመት ሊጠግን የሚችል የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል። ክልሉ በድህረ ጦርነት ኢንቨስትመንት አስተዳደር ረገድ የተለየ አሰራር ለመከተል ጥረት ያደርጋል። ለዚህም አንዳንድ የክልሉን ሕጎች ለማሻሻል እየተሞከረ ነው። የድህረ ጦርነት የኢኮኖሚ ማገገሚያ ሥርዓት ውጤታማ እንዲሆን የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት›› ይላሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 25/2015