ከ1936 ዓ.ም ጀምሮ ለሕትመት ብርሃን የበቃው በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመው ዘኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ አማርኛ ለማይችሉ ውጭ ሀገር ሰዎች የኢትዮጵያን ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በማስተዋወቅ ረገድ የማይተካ ሚና ተጫውቷል።
ከአዲስ ዘመን ቀጥሎ በአንጋፋነቱ የሚጠቀሰው ዘኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ የኢትዮጵያን ታሪክ በእንግሊዝኛ እየሰነደ ዛሬ ላይ ደርሷል። ጋዜጣው በየዘመናቱ የነበሩት ውጣ ውረዶች ሳይበግሩት የየዕለቱን ክስተት እየዘገበ እና የኢትዮጵያን ታሪክ እየመዘገበ 80 ዓመታትን ደፍኗል።
ጋዜጣው ሲመሰረት በሀገር ውስጥ በቂ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት የለም በሚል ዕሳቤ በዋና አዘጋጅነት ተመድበው ሲሰሩ የነበሩት የውጭ ሀገር ዜጎች ናቸው። ሆኖም አንድ ኢትዮጵያዊ ይህንን ሂደት ሰብሮ የመጀመሪያው የኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ለመሆን በቅቷል። ይህ ሰው ያዕቆብ ወልደማርያም ይባላል።
አንጋፋው ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም ከእናታቸው ወ/ሮ ወለተሚካኤል ሰንበቶ እና ከአባታቸው አቶ ወልደማርያም ሹባ በቀድሞው ወለጋ ክፍለ ሀገር ነቀምቴ ከተማ ሰኔ 12 ቀን 1921 ዓ.ም ተወለዱ።
እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ፣ በነቀምቴ ከተማ የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ማለትም ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። የስምንተኛ ክፍል ፈተና ውጤታቸው ከፍተኛ በመሆኑ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጥተዋል።
በጊዜው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ይከታተሉባቸው ከነበሩት ተፈሪ መኮንን ትቤት፣ ጄኔራል ዊንጌት ት/ ቤት እና ኮተቤ ት/ቤቶች መካከል ጋዜጠኛ ያዕቆብ በኮተቤ ትምህርት ቤት ተደልድለው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። በጊዜው ከሶስቱም ትምህርት ቤቶች የወቅቱን የለንደን ማትሪኩሌሽን ፈተና በከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ ተማሪዎች የውጭ ሀገር ትምህርት ዕድል ይሰጥ ነበር። ከላይ ከተጠቀሱት ት/ ቤቶች ከእያንዳንዳቸው ለሶስት ተማሪዎች የትምህርት ዕድል ሲሰጥ፣ አቶ ያዕቆብም ከዘጠኙ አንዱ ሆነው ወደ እንግሊዝ ሀገር እኤአ በ1950 ዓ.ም ማም ራት ችለዋል።
በዚያም በKingston upon-Thames Technical College የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን ተማሪ ሆነው የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተከታትለዋል።
እንግሊዝ ሀገር በነበሩበት ጊዜ ወ/ሮ ሲሊቪያ ፓንክረስት ታዘጋጀው በነበረው “ኒው ታይምስ” እና “ኢትዮጵያን ኒውስ” በሚባለ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ላይ ጽሑፎችን በመጻፍ ያሳትሙም ነበር። የጋዜጠኝነት ሙያ ወደ ውስጣቸው ዘልቆ የገባው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ይታመናል። ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረገው ደግሞ የማኦ ማኦ የነፃነት ትግል በኬንያ ሲካሄድ እዚያው ኬንያ ሆነው ሁኔታውን መታዘባቸው ነበር። ነጮቹ በሚጽፏቸው አርቲክሎች አፍሪካውያንን ሰብዕና ላይ ጭራና ቀንድ እየቀጠሉ እንዴት አድረገው ከሰውነት በታች (ዲ-ሂውማናይዝ) እንደሚያደርጉ አንብበዋል። በዚህም የተነሳ በእንግሊዝኛ መጻፍና ትክክለኛውን የአፍሪካውያን ሥዕል መስጠት የግድ መሆኑን አምነው በስፋት፣ ሰርተዋል።
ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወደ ሀገራቸው በመመለስ በእጅጉ የሚወዷትን ኢትዮጵያን በተለያዩ ሙያዎች አገልግለዋል።
በዋናነት የሚጠቀሱትም
1. በወለጋ ክፍለ ሀገር ነቀምቴ ከተማ ለአንድ ዓመት በመምህርነት፤
2. በቀድሞ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ለአንድ ዓመት፤
3. በውሃ ክፍል ለአንድ ዓመት፤
4. በአምሃ ደስታ ት/ቤት ለአንድ ዓመት በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፤ ፤
ከእነዚህ ዓመታት አገልግሎት በኋላ ጓደኞቻቸው ለጋዜጠኝነት የነበራቸውን ዝንባሌና ከፍተኛ የሆነውን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎቶቻቸውን በመገንዘብ በቀድሞው ጽሕፈት ሚኒስቴር ስር በነበረው ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ እንዲቀጠሩ ይመክሯቸዋል።
እሳቸውም በጊዜው ዋና አዘጋጅ ወደነበረው አሜሪካዊው ዴቪድ ታልቦት ጋር ሄደው ይህንኑ ጥያቄ አቀረቡለት። ታልቦትም አንድ ጽሑፍ እንዲጽፉ ይጠይቃቸዋል። እዚያው ተቀምጠው ሃሳባቸውን አደራጅተው ጽፈው ይሰጡታል። ይበልጥ የቋንቋ ችሎታቸውን ለመገንዘብ በፈረንሳይኛ የተጻፈ ሌላ ጽሑፍም እንዲተረጉሙ አዘዛቸው፣ ይህንንም በቅልጥፍናና በብቃት ተገበሩ። በአጻጻፍ ክህሎታቸው የተደነቀው ታልቦት ወዲያውኑ ወደ ሚኒስትሩ ወስዶ በማግባባት እንዲቀጠሩ አድርጓል።
የዘኢትዮጵያን ሔራልድ የቀድሞ ዋና አዘጋጆች ቋንቋውን የሚያውቁ የውጭ ሀገር ዜጎች ነበሩ። ጋዜጠኛ ያዕቆብ ባስመዘገቡት ከፍተኛ የሥራ ውጤትና ድንቅ አጻጻፋቸው የተነሳ በጋዜጣው ላይ ከተቀጠሩ ከሁለት ዓመት በኋላ በ1959 ዓ.ም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የዘኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኑ።
በጋዜጣው ላይ በሰሩባቸው ዓመታት በርካታ የኤዲቶሪያል ውሳኔዎችንና ጽሑፎችን አበርክተዋል። በተለይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤት እንዲቋቋምና ዘመናዊ የሰው ኃይል አደረጃጀት በሀገሪቱ እንዲኖር በርካታ ጽሑፎችን ጽፈዋል። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ንግግሮችም በግሩም እንግሊዝኛ እየተረጎሙ ለውጪው ማኅበረሰብ መልዕክቱ እንዲደርስ ያደርጉ ነበር።
በጊዜው አጼ ኃይለሥላሴ ኢትዮጵያን ለማዘመን ይተጉ እንደነበር ጋዜጠኛ ያዕቆብ በሕይወት እያሉ ከዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ ጋር እኤአ በኦክቶበር 12 ቀን 2021 ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። ሆኖም ግን ጋዜጠኛ ያዕቆብ የመሬት ይዞታው ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለድህነት አጋልጦታል የሚል አቋም ስለነበራቸው ይሄው እንዲስተካከል ግፊት ያደርጉ ነበር።
ሌላው በተለይ የንጉሡ ሹመኞች በሕዝብ ላይ በደል እያደረሱ ነው የሚል ይዘት ያለው የሰላ ትችትም ያቀርቡ ነበር። ከዚህ ውስጥ ተጠቃሽ ጽሑፋቸው “rotten at the root” የሚል ኤዲቶሪያል ነው። በጸረ ኮሎኒያሊዝምና ጸረ ኒዮኮሎኒያሊዝም አቋማቸውም ይታወቃሉ። በአዲስ አበባ ካሉ ኤምባሲዎችም በዚህ ከፍተኛ ነቀፌታ ይደርስባቸው እንደነበር ተናግረዋል። እንዲህ ያሉ ጽሑፎችን እንዲያቆሙ ማሳሰቢያ እንደደረሳቸውና እሳቸውም በምላሻቸው ሊቆም የሚችለው እነሱም እኩይ ተግባራቸውንና አስተሳሰባቸውን ሲተው እንደሆነ በወቅቱ ተናግረዋል።
ጋዜጠኛ ያዕቆብ የጋዜጠኝነት ሙያቸው በሚፈቅደው ልክ ለእውነት ቆመው ተከራክረዋል። ሕዝቡ በሹመኞች እንዳይበዘበዝና ጋዜጣውም የሹመኞች ድምጽ ብቻ እንዳይሆን በብዙ ደክመዋል። ሕዝቡን የሚያማርሩ አሰራሮችን በመገሰጽ እንዲስተካከሉ አድርገዋል። ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ የዘመኑ ሹማምንትን ገስጸዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ዘንድ መልካም ገጽታ እንዲኖራት ያለመታከት ጽፈዋል። ኢትዮጵያ ተስማሚ አየር ንብረትና ለእርሻ ምቹ መልክዓ ምድር እንዳላት በኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ላይ ለዓመታት ጽፈዋል።
በተለይም ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ሉዓላዊነት የማያስደፍሩ፤ በሀገራቸው የመጣባቸውን ጠላት በአንድነት መክተው የሚመልሱ የአፍሪካውያን የነጻነት ተምሳሌት መሆናቸውን የሚያሳዩ ጽሑፎችን ጽፈዋል። የዓድዋን ተጋድሎና ቀጥሎ የመጣውን የጣሊያኑን የአምስት ዓመታት ወረራ ለውጭ አንባቢያን አስገንዘበዋል። በዚሁም የቅኝ ግዛትን አስከፊነት በብዕራቸው ገልጸው ለውጭ አንባቢያን መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጋዜጠኛ ያዕቆብ ምንም እንኳ በርካታ ዓመታት በመንግሥትና የሕዝብ ጋዜጣ ላይ ቢሰሩም፣ ለሃሳብ ብዝሃነት ያላቸው ጽኑ አቋም በሥራዎቻቸው ላይ ይታያል። ሕዝቡና መንግሥት ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝም ይሰሩ እንደነበር ሥራቸው ይገልጣል። ለምሳሌ ያልተሳካውን የነዋይ ወንድማማቾች የመንግሥት ግልበጣን (የታኅሳሱ ግርግር)ን በተመለከተ፣ አንዱ ሌላውን ለመወንጀልና በንጉሡ ፊት ለማሳጣት ይሞክር እንደነበረ ጋዜጠኛ ያዕቆብ ለዘኢትዮጵያን ሔራልድ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አመላክተዋል። ይህንን ተከትሎም lack of information is a fundamental problem of the country’ የሚል ጠንካራ ኤዲቶሪያል ጽፈዋል።
የራሺያን የየካቲትና ጥቅምት አብዮቶች አድንቀውም በስማቸው ጽሑፎችን ያትሙ ነበር። ምናልባትም ይህ ጽሑፍና ሌሎች የኤዲቶሪያል አቋሞቻቸው በዋና አዘጋጅነት ሥራቸው እንዳይቆዩ አድርጓቸዋል።
አንዳንዶች የጋዜጠኛ ያዕቆብ እንግሊዝኛ ጠጠር እንደሚል ይናገራሉ። እርሳቸውም ይህንን ሆነኝ ብለው እንደሚያደርጉትና ተራ ካድሬ በቀላሉ እንዳይገነዘብና እንዳያስቆማቸው እንደሆነ የተናገሩበት አጋጣሚ አለ።
ጋዜጠኛ ያዕቆብ በአጠቃላይ በአሁኑ አጠራር የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በቀድሞ አጠራሩ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስር በነበረው ፕሬስ መምሪያ ለ37 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፤ ከዘኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ በተጨማሪ በቮይስ ኦቭ ኢትዮጵያ፣ በመነን፣ በየካቲት ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ሰርተዋል።
ከመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ውጭም በተለያዩ በእንግሊዝኛ በሚታተሙ የግል ጋዜጦች ላይም ሰርተዋል። ከእነዚህም መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት፤ በእንግሊዝኛ የሚታተመው አዲስ ትሪቢዩን ጋዜጣ ላይ ለስምንት ዓመታት፣ በእንግሊዝኛው ዘ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ለ20 ዓመታት በዋና አዘጋጅነት ጭምር አገልግለዋል።
ጋዜጠኛ ያዕቆብ ከመስከረም 1 ቀን 1986 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመዘዋወር፤ በሚኒስቴሩ ይታይ የነበረውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት በፕሬስና ኢንፎርሜሽን ክፍል ለ7 ዓመታት ሀገራቸውን አገልግለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት 50ኛ የምስረታ በዓሉን ሲያክብር ጋዜጠኛ ያዕቆብ ኒውዮርክ ሄደው ታድመዋል። አርቲክልም ጽፈው አሳትመዋል።
በ2007 ዓ.ም በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት አሸናፊም ነበሩ።
ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም ሹባ በሕይወት ሳሉ 10 ልጆች ሲያፈሩ፣ በሕይወት ካሉት 4 ወንድና 3 ሴቶች ልጆቻቸው ስምንት የልጅ ልጅ እንዲሁም አንድ የልጅ ልጅ ልጅ አይተዋል።
ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም ባደረባቸው ህመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ94 ዓመታቸው ነሐሴ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ነሐሴ 17 ቀን 2015 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2015