ማን እንደ ሀገር

ወጣት ሱመያ ካሚል የአስረኛ ክፍል አጠቃላይ ፈተናን ተፈትና ያመጣችው ውጤት ለቴክኒክና ሙያ የሚያስገባት ቢሆንም የእርሷንም ሆነ የቤተሰቦቿን ሕይወት መለወጥ የምትችለው አረብ ሀገር ሄዳ በመሥራት እንደሆነ እምነት አደረባት፡፡ ወደ ሳውዲ አረቢያ ሄዳ በመሥራት እራሷንም ቤተሰቧን የመለወጥ ህልም ያዘች።

ወጣት ሱመያ ህልሟን እውን አድርጋ በደላላ አማካይነት የለውጥ ሀገሬ ባለቻት ሳውዲ አረቢያ የሰው ቤት ሥራዋን ጀመረች። ወዲያው እንደሄደች ቀጣሪዎቿ የተቀበሏት ሱመያ በፍጥነትም የማያልቀውን ሥራ ጀመረችው።

ምንም እንኳን የምትበላው ባይስማማትም ሥራው ከመጠን በላይ ከባድና ሌት ተቀን የሚያፈጋ ቢሆንም የምታገኛትን አዲስ አበባ ላይ በችግር ለሚሰቃዩት ቤተሰቦቿ እየላከች ሁለት አመታትን ቆየች። ‹‹ያለሁበት ቤት ባይደላም፤ አይከፋም ነበር›› የምትለው ሱመያ ሰዎቹም ደግ የሚባሉ ባይሆኑም እንደሚሰማው ደግሞ የተጋነነ ክፋትም አልነበራቸውም። እንደውም አንዳንድ መዝናኛ ቦታዎች ሁሉ ይዘዋት ይወጡ እንደነበር ታስታውሳለች።

ሱመያ ያሰበችውን ያህል ሕይወት የሚለውጥ ነገርን አላገኘችም። ችግረኛ የሆኑትና በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩት ቤተሰቦቿም የእሷን ከሀገር መውጣት በመመልከት እጇን ጠባቂ ነበሩና ያገኘችውን እየላከች የእለት ጉርሳቸውን ከመሙላት የዘለለ ትርፍን ማግኘት አለመቻሏን ትናገራለች።

ወጣት ሱመያ የሰራችው ባያረካትም ኑሮ ብላ ግን የአረብ ሀገሩን ዓለም ተያይዛው ነበር፤ ነገር ግን በአንድ ክፉ አጋጣሚ ከምትሰራበት ቤት ወጥታ ስትንቀሳቀስ በፖሊስ ተያዘች፡፡ የገባችበት ቦታ እስር ቤት መሆኑን ያወቀችው በርካታ ኢትዮጵያውያንን ካገኘች በኋላ ነው፡፡ በርካቶቹ በአሰሪዎቻቸው በደል ደርሶባቸው አምልጠው ሲጠፉ የተያዙ፤ አንዳንዶቹም በሀገሪቱ የተከለከሉ መጠጦችን ሲሸጡ እጅ ከፍንጅ በመያዛቸው ለእስር የተዳረጉ መሆናቸውን ተረዳች፡፡

አንዳንዶቹ ከ20 ዓመታት በላይ በሳኡዲ አረቢያ የኖሩ፤ ትዳር የመሰረቱና ልጆችን ያፈሩ ናቸው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ግን በቂ ጥሪት ያልቋጠሩና በሳኡዲ አረቢያ መንግሥት ትዕዛዝ ታፍሰው ከሀገር እንዲወጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ከወራት እስከ ዓመታት የቀን ሥራ ሲሰሩ የቆዩ፤ በማዳም ቤቶች ተቀጥረው በቤት ሠራተኝነት ሲያገለግሉ የኖሩ ናቸው፡፡

ሁሉንም ግን የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ፡፡ ወራትም ሆነ ዓመታት የሠሩት አንዲትም ጥሪት አላፈሩም፡፡ ወደ ሀገራቸው ለመግባት ፍላጎት ቢኖራቸውም ብዙዎቹ እጃቸው ላይ ምንም ነገር ስለሌለ ምን ይዤ ልመለስ በሚል ፍራቻ እስር ቤት መቆየቱን ይመርጡታል፡፡

ሆኖም እስር ቤቱ በየጊዜው እየመጣ በሚታጎረው ስደተኛ ተጨናንቋል፡፡ የእስረኞች አያያዝም ሰብዓዊነት የጎደለውና አዋራጅም ነው፡፡ ሕጻናት ልጆች ይዘው የገቡ ሰደተኞችና እርጉዝ ሴቶችም ሳይቀሩ ምቾት በጎደለው አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ውለው ለማድር ተገደዋል፡፡

“የእስር ቤት ቆይታዬ በጣም አሰቃቂ ከመሆኑ የተነሳ አሁን እንኳን ደግሜ ላስበው አልፈልግም። በርካታ ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ ከመታጎራችን የተነሳ ቦታው አይበቃም ነበር፤ የምንለብሰው፣ የምንበላውም ያን ያህል አልነበረንም ብቻ በጣም ዘግናኝ ነበር” በማለት ሁኔታውን ታስታውሳለች።

የኢትዮጵያ መንግሥት በእስር ላይ ያሉ ዜጎቹን ወደሀገራቸው ለመመለስ ሲነሳም ሱመያ የእድሉ ተጠቃሚ በመሆን ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም ለሀገሯ መሬት መብቃቷን ትናገራለች።

ሰርቼ እለወጣለሁ ከእኔ አልፎ ለቤተሰቤም እተርፋለሁ ያለችው ሱመያ እቅድ ሃሳቧ በአጭሩ ከመቀጨቱም በላይ የሰራችበትን ገንዘብ ልብሷን ብቻ ያላትን ነገር ሁሉ ጥላ መምጣቷንም ትገልጻለች።

“አሁን ላይ ሁኔታው ቢያሳዝነኝም አልቆጭም፤ በሕይወት ተርፌ ሀገሬ መግባቴም ለእኔ ትልቅ ነገር ነው። በእርግጥ የለፋሁበትን እንኳን መያዝ አልቻልኩም፤ ነገር ግን በሕይወት መኖር ከሁሉም ነገር በላጭ በመሆኑ ሕይወቴን ላተረፈልኝ አምላኬና ወደ ሀገሬ እንድገባ ከቤተሰቤ እንድቀላቀል ላስቻለኝ መንግሥት ላቅ ያለ ምስጋናን አቀርባለሁ፡፡” ትላለች።

አሁን ሱመያ ወደ ሀገሯ ከመግባቷም ባሻገር የምትኖርበት ክፍለ ከተማ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ ተደራጅታ ሥራ የምትሰራበት እድል ስላመቻቸላት ዛሬ ላይ ከመሰሎቿ ጋር በመሆን እንጀራ ጋግሮ የመሸጥ ሥራ ውስጥ ገብታለች።

“ማን እንደ አገር” የምትለው ሱመያ የምታገኘው ገንዘብ ያን ያህል ዘና አድርጎ የሚያኖራት ባይሆንም በሀገሯ ላይ ተከብራ ሰርታ የመለወጥ ህልም እንድትሰንቅ ግን እንዳደረጋት ትናገራለች።

እንደ ሱመያ ሁሉ ወጣቶች የተሻለ ኑሮን በማሰብና በመመኘት ሀገራቸውን ጥለው ወደባዕዳን ምድር ይሰደደዳሉ። ይህ የስደት ጉዞ በለስ ለቀናቸው እንዳሰቡት ትርፋማ ሆኖላቸው ሕይወታቸውን፣ ኑሯቸውን፣ አልፎ ተርፎም ሀገርና ቤተሰባቸውን የሚቀይሩበት መልካም አጋጣሚ ይሆንላቸዋል። ነገር ግን እድል ከእነሱ ጋር ያልሆኑቱ ያሰቡት ቀርቶ ያላሰቡት ችግር ገጥሟቸው ለራሳቸውም ለሰውም መሆን አቅቷቸው የባዕዳኑ መጫወቻ የሚሆኑበት አጋጣሚ ብዙ ነው።

በተለይም ሴት እህቶቻችን ኑሮ ባሰቡት መንገድ አልሄድ ሲላቸው ስደትን እንደ ራስ መለወጫና አማራጭ መንገድ አድርገው በመቁጠር ከሀገር ይወጣሉ፤ ጥቂቶቹ ይህ መንገድ ቢሳካላቸውም አብዛኞቹ ግን ያላሰቡት ገጥሟቸው ብዙ ስቃይና መከራን ለማለፍ ይገደዳሉ።

ሴቶች በአሰሪዎቻቸው ተደፍረው በችግር ላይ ሌላ ችግር ጨምረው ይገኛሉ፤ ሀገራቸው አንዳይገቡም የማንን ዓይን አያለሁ በሚል ፍራቻ እዛው እየተሰቃዩ ይቀራሉ። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ያለ ፍቃድ በመንቀሳቀሳቸው ምክንያት በፖሊስ ተይዘው እስር ቤት የሚገቡት ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍተኛ የነበረ መሆኑን በተለያየ ሁኔታ የምናውቀው ሃቅ ነው።

ይህንን የሴት እህቶቻችንን በጠቅላላው ደግሞ የዜጎቻችንን እንግልትና ስቃይ ለማስቆም፤ በስቃዩ ውስጥ ያሉትንም ለሀገራቸው መሬት ለማብቃት በመንግሥት በኩል ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተው ዜጎችም ለሀገራቸው በቅተዋል።

ይህንን ኃላፊነት ወስደው እየሰሩ ካሉ ተቋማት መካከል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አንዱ ሲሆን የሥራ ክህሎት ሚኒስቴር የስደተኞች ኮሚሽንና ሌሎችም በአጋርነት እየተሳተፉ ዜጎችን ካሉበት አገር ከማምጣት ከመጡም በኋላ ጊዜያዊ ማረፊያን እንዲያገኙ በማድረግ፤ በኋላም ከቤተሰቦቻቸው የሚቀላቀሉበትንና በአገራቸው ላይ ሰርተው ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበትን መንገድ በማመቻቸት በኩል ትልቅ ሥራን እየሰሩ ያሉም ናቸው።

አቶ መሳይ ወልደማርያም በሴቶች ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ክትትልና ድጋፍ ዴስክ ኃላፊ ሲሆኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የእነዚህን ዜጎች መረጃ ከማጠናቀር ጀምሮ እስከ መቀበልና ቤተሰቦቻቸው ጋር እስከማድረስ ድረስ ያለውን ሥራ እየሰራ ስለመሆኑ ይናገራሉ።

እነዚህን ዜጎች መቀበል ሲባል እንግዲህ ዜጎቹ እንዳሉበት ሁኔታ በማየት ሴቶችን፤ ሕጻናትን፤ ወንዶችን በመለየት ከዛም ጉዳት የደረሰባቸውና ሌሎች ችግሮቻቸውን እያየ ተቀብሎ ጊዜያዊ መጠለያ ላይ እንዲቆዩ በማድረግም ሁኔታዎችን አመቻችቶና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ወደሚኖሩበት አካባቢ እንዲጓጓዙ የማድረግ ሥራን ይሰራል ይላሉ።

እንደ አቶ መሳይ ገለጻ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህንን ተግባር ከመፈጸም ጎን ለጎን ከስደት ተመላሽ የነበሩበትን ሁኔታ የሚገልጹ መረጃዎችን በማደራጀት በትውልድ አካባቢያቸው ላሉ የክልልና ከተማ መስተዳደሮች የማስተላለፍ ሥራው ይሰራል በማለት ገልጸዋል።

የሁለቱም ዙር የተመለሱ ዜጎች ከመጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ መጋቢት25 ቀን 2015 ዓ.ም በችግር ውስጥ የነበሩና በመንግሥት ድጋፍ የተመለሱ ሴቶች 115 ሺ 799 ሲሆኑ ወንዶች 110 ሺ 587 እንዲሁም ከ18 ዓመት በታች 6 ሺ 717 እንደሆኑም አቶ መሳይ ያብራራሉ።

አቶ መሳይ እንደሚሉት እነዚህ ዜጎች ወደ ሀገራቸው ሲገቡ አቀባበል ይደረግላቸዋል፤ በዚህም መጀመሪያ በአየር ማረፊያ ከተቀበልናቸው በኋላ ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ቦታዎች እንዲሄዱ ይሆናል፤ በመቀጠልም ከሆስፒታሎች ጋር በመተባበር ሙሉ የጤና ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡ በእዛም በጎ ፍቃደኞች ተመድበው ስለሚጠብቋቸው ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ወደ ሆስፒታሎች እንዲሄዱ ይሆናል። በዚህም የሥነ ልቦና ድጋፍ የምክር አገልግሎት ሌሎችንም እንዲያገኙ ከሆነ በኋላ የመጓጓዣቸው ተችሎና የኪስ ገንዘብ ተሰጥቷቸው ወደየቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ እየተደረገም ስለመሆኑ አብራርተዋል።

ይህ ሥራ የሚሰራው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በቅንጅት ነው የሚሉት አቶ መሳይ በዚህ ሂደት አሁን ላይ ከሳውዲ የሚመለሱ ዜጎችን የማምጣት ሥራው ተጠናቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተሰራ ያለው ከሱዳን የሚመጡ ዜችን ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ሥራ መሆኑን አብራርተዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህን ያህል ጥረት ሲያደርግ ክልሎችም በራሳቸው መንገድ ሥራዎችን አደራጅተው ይሰራሉ የሚሉት አቶ መሳይ ከዚህ በሚሄድላቸው መረጃ መሠረትም ምን ላይ ደረሱ የሚለውን ክትትል ያደርጋሉ።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ከማድረግ ባለፈ እነዚህ ዜጎች ወደሚመለከተው አካል እንዲዘዋወሩ ያደርጋል፤ ለምሳሌ የጤና ችግር ያለባቸውን ወደ ሕክምና ሥራ የሚፈልጉ ሲኖሩ ወደሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ይላካሉ፡፡ በተመሳሳይ ትምህርት መማር አለብኝ ለሚሉቱ ደግሞ የትምህርት አገልግሎት ወደሚያገኙበት እንዲሄዱ ሁኔታዎችን እናመቻቻለን በማለት ይናገራሉ።

ቅንጅታዊ አሰራሩ ጥሩ ጅማሮ ላይ ነው ማለት ይቻላል የሚሉት አቶ መሳይ ነገር ግን ጉዳዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ብሎም የሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም የየራሱን ድርሻ ወስዶ ሊሰራ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ተመላሾች ሀገራቸው ገብተው እንዲደረግላቸው የሚፈልጉት ነገር ግዙፍ መሆን፤ ቋሚ አድራሻ አለማስቀመጥ፤ ከአንድ በላይ መጠሪያ ስምን መጠቀም በሥራው ላይ ችግር ሆኗል። ይህንን ማስተካከል ቢቻል ችግሩን መቅረፍ እንኳን ባይቻል በመጠኑም ቢሆን መቀነስ እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት።

“የፌዴራል መንግሥት ከክልሎችና ከዛም በታች ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን መዋቅር ቢስተካከልና በትክክልም ቅንጅታዊ አሰራርን መከተል ቢቻል ጥሩ ነው። በሌላ በኩልም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከስደት ተመላሾችን ማገዝና በትብብር በጋራ ለመሥራት ቢችል መልካም ነው” ብለዋል።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 23/2015

Recommended For You