የትምህርት ጥራት ችግር መፍትሔው እንዳይርቅ

በሀገራችን የትምህርት ጥራት ጉዳይ ዘመን አመጣሽ አገላለፅ፣ ወይም ጽንሰ-ሃሳብ ነው። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በቀድሞው ጊዜ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ብዙም አሳሳቢ ሆኖ ይገኝ ስላልነበረ ነው። “አሳሳቢ ሆኖ ይገኝ ስላልነበረ” ሲባል ግን የትምህርት ጥራትን አስመልክቶ ግንዛቤው ስላልነበረ፤ ወይም፣ የትምህርት ጥራት አስፈላጊ ስላልነበረ ማለት አይደለም። ሁሌም ቢሆን የትምህርት ጥራት እጅግ አስፈላጊ ነው። ልዩነቱ ግን በቀደመው ዘመን በትምህርት ጥራት ጉዳይ የሚደራደር አካል አልነበረም። ከተማሪው እስከ አስተማሪው ሁሉም እውቀትን ፍለጋ ይኳትንም ነበር።

ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ኩረጃ ከውርደትም በላይ ሞት ነው። ምንም እንኳን የቤት ሥራ አለመሥራት የሚያስቀጣ ቢሆንም ሰነፍ መባል እራሱ ከቅጣት በላይ ነው። ከፍተኛ የሥነልቦና ጉዳትም በሰነፍ ተማሪ ላይ ያሳድራል። በፈተና መውደቅ እስከ ቤተሰብ ድረስ የዘለቀ ኀዘንን ያስከትላል። “የእከሌ ልጅ ወደቀ፤ የእከሌስ? እሱማ አለፈ እኮ – – -” መባል በራሱ እስከ ጎረቤት ድረስ ለቁጭት ያበቃል፤ ለኀዘንም ይዳርጋል።

በዩኒቨርሲቲዎችም ኩረጃ የባሰ ውርደት ሲሆን፣ መመረቂያን በገንዘብ ለማሰራት ቀርቶ አንዲት የሌላ ሰው ቃል እንኳ ያለ አግባብ ወደ ጥናቱ ውስጥ ጥልቅ እንዳትል ይደረግ የነበረው ጥንቃቄ ደም የመስጠት ያህል ነበር። ያን ጊዜ በትምህርት ቀልድ አልነበረም። ከዚህ አንፃር የትምህርት ጥራት ጉዳይ ብዙም አጀንዳ አልነበረም። በአሁኗ ኢትዮጵያስ?

በአሁኑ ጊዜ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ተረት እየሆነ የመጣ ይመስላል። በሁሉም የትምህርት እርከኖች በሚባል ኩረጃና በትምህርት መውደቅ ባህል እየሆኑ መጥተዋል። የአሠራር ሥርዓት ሁሉ መስለው ፤ በማስታወቂያ ተደግፈው ለአደባባይ ሲበቁ እየታዩ ነው። ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲዎች በር ላይ መመረቂያ ጽሑፍን በተመለከተ “እናማክራለን”፣ “ፕሮፖዛል እናዘጋጃለን”፣ “ስክሪፕት እንፅፋለን”፣ “የአርትኦት ሥራ እንሰራለን …ወዘተ” የሚሉ ማስታወቂያዎችን በገፍ ማየትና ማንበብ የተለመደ ሆኗል። ኮምፒውተር ይዘው ቁጭ ያሉ ጸሐፊዎች “መመረቂያ ጽሑፍ እዚህ አለ” የሚል በትልቁ ጽፈው መመልከትም ብርቅ አይደለም። ጊዜ ያለፈበትን መመረቂያ ጽሁፍ ወቅታዊ አድርገው ጠርዘውና በቀለም ሳይቀር ኩለውና ኳኩለው በ5 ሺ ብር መቸብቸብ ተለምዷል።

በአሁኑ ጊዜ ከትምህርት ፍትሃዊነት፣ ተደራሽነትና ጥራት ጋር በተያያዘ ያለው ችግር በራሱ ትምህርትን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳ ነው የሚመስለው። ከታች እስከ ላይ ችግር አለ። ከጥግ እስከ ጥግ ተተረማምሷል። ችግሩ በተማሪ ሳይወሰን አስተማሪውንም እየሰለቀጠው ነው። ኩረጃ ከታችም አልፎ ላይ ድረስ ዘልቋል። ምንተፋ (plagiarism) የትጉሃን ተግባር እየሆነ ነው። የሀሰት የትምህርት ማስረጃን መሸመት የተማሪው ብቻ መሆኑ ቀርቶ የአስተማሪውም ተግባር ሆኗል።

የትምህርት ጥራት ችግር ለማሽቆልቆሉ አጃቢዎች ተማሪውና አስተማሪው ብቻ አይደሉም። የሲቪክ ተቋማት ሳይቀሩ ባለ ሀሰት ዲግሪዎች መናኸሪያዎች ከሆኑ ሰነበቱ። ማጭበርበራቸው የተነቃባቸው ከሥራቸው ዝቅ ቢደረጉም ያልተደረሰባቸው ጭራሽ ወደ ላይ ሲወጡ ለማየትም ሆነ በትርኢቱ ዘና፣ ፈታ ለማለት ሲኒማ ኢትዮጵያ ወይንም ብሄራዊ ትያትር መሄድ አያስፈልግም። ከላይ የተጠቀሱት የሞራል ጥሰቶችና የሥነ ምግባር ግድፈቶች እንዳሉ ሆነው ለትምህርት ጥራት ችግር መንስኤዎቹ ምንድን ናቸው? የሚለውን መመልከቱ ገቢ ነው።

ከባለሙያዎች፣ ጥናትና ምርምሮች፣ እንዲሁም ከራሳችን የመማር-ማስተማር ተሞክሮ እንደምንረዳው፣ የትምህርት ግብዓቶች አቅርቦት እጥረት ወይም ጭራሽ አለመኖር፤ የመማር-ማስተማር ከባቢ ሁኔታ አለመመቸት፤ የክፍል ውስጥ የተማሪዎች አያያዝ፤ የማስተማር ሥነ ዘዴ፣ የትምህርት መሣሪያ እጥረት ወይም ጭራሽ አለመኖር ፣ የተጓዳኝ ክበባት አለመኖርና የተማሪዎች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን ፣ በእቅድ የአለመመራት ሁኔታ፤ የትምህርት አመራር፣ አሠራርና አደረጃጀት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ተግባራዊ አለመደረግና የመሳሰሉት ለትምህርት ጥራት መጓደል የየራሳቸው አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ያለ መማሪያ-ማስተማሪያ መጻሕፍት የትምህርት ጉዳይ ባዶ ነው። የመምህሩም ሆነ ተማሪዎች ልፋት ከንቱ ነው። ፖሊሲም ሆነ ሥርዓተ ትምህርት ዋጋ የላቸውም። የተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎ አይታሰብም። የትምህርት ተደራሽነት ብሎ ነገር ጉንጭ አልፋ ይሆናል። የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ሹፈት ካልሆነ በስተቀር እውን ማድረግ አይቻልም። የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት ብሎ ነገር ከሃሳብ ያለፈ ገቢር የለውም።

ይህ ማለት የመማሪያ-ማስተማሪያ መጻሕፍት እጥረት ካለ የትምህርት ጥራት ችግር አለ ማለት ነውና ችግሩን ለመቅረፍ ከመማሪያ-ማስተማሪያ መጻሕፍት ፍላጎትና አቅርቦት መጣጣም አኳያ መሥራት ይጠበቃል ማለት ነው። ይህም ከትምህርት ጥራት ችግር መንስኤዎች አንዱ ሆኖ ይወሰዳል።

በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ችግር ስለ መኖሩ አንዱ ማረጋገጫ በ2014 ዓ.ም በአገር አቀፉ ፈተና ላይ በተደጋጋሚ ሲያጋጥሙ የነበሩ ኩረጃዎችንና የፈተና ስርቆቶች ለመከላከል የተወሰደው ርምጃ ነው። ያለፈው ዓመት ተፈታኞች በተለየ ሁኔታ፣ ማለትም በሀገሪቱ ውስጥ ወዳሉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ገብተው በጥብቅ ቁጥጥር ስር እንዲፈተኑ ተደርገዋል። የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈታኞች ዝቅተኛ ውጤት አምጥተዋል። ከ96 በመቶ በላይ የሆኑትም እንዳልተሳካላቸውም ተገልፆ ነበር።

አስደንጋጭ የተባለው ውጤት እንደሚያሳየው ለፈተና ከተቀመጡት ከ980 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል 30 ሺህ ገደማዎቹ ብቻ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያገኙ መሆናቸው ነው። የ2014 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ ዝቅተኛ ውጤት ያመጡበት ምክንያት ምን ይሆን?” ተብሎ በመላው ሀገሪቱ ለተነሳው ጥያቄ አንዱና ዋነኛው መልስ የትምህርት ጥራት ችግር ነው። በተለያዩ ጉባዔዎች ለምሳሌ በ31ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ ፊት መሪው አጀንዳ የነበረውም ይሄው የትምህርት ጥራት ጉዳይ ነው።

በዚሁ ዓመት የዓለም ባንክ ባወጣው መረጃ መሠረት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ሊያጠናቅቁ የተቃረቡ ሕፃናት ማንበብ አይችሉም። ኢትዮጵያ ውስጥ ከ85 በመቶ በላይ ዕድሜያቸው 10 የደረሰ ሕፃናት ቀለል ያለ ጽሑፍ እንኳን አንብበው መረዳት አይችሉም። ይህም መረጃ የኢትዮጵያ የትምህርት ደረጃ ወዴት እየሄደ እንደሆነ ያመላክታል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናት እና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር የሆኑትና በኢትዮጵያ የትምህርት ሁኔታ ላይ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር በርካታ ጥናቶችን ያካሄዱት በላይ ሃጎስ (ዶ/ር) የጥናት ግኝታቸውን አስመልክተው እንደተናገሩት፣ በፈረንጆቹ 2021 በተደረገ ጥናት 68 በመቶ የሚሆኑ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ‘ዜሮ ሪደርስ’ [ምንም ማንበብ የማይችሉ] ናቸው። 51 በመቶ የሚሆኑ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች ደግሞ አንብበው መረዳት አይችሉም።

ተማሪዎች ከክፍል ወደ ክፍል የሚዘዋወሩት ብቃታቸው ተፈትሾ አይደለም። ዘንድሮ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመጣው ውጤት ተጠያቂው የሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ነው። ይህ ውጤት “የትምህርት ሥርዓቱ የወለደው” ነው። የትምህርት ሥርዓቱ ልጆች ብቃት እንደሌላቸው እየታወቀ ከክፍል ወደ ክፍል እንዲዛወሩ ይፈቅዳል። በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ከ8ኛ እና 10ኛ ክፍል በቀር ሁሉም ተማሪዎች ወደሚቀጥለው ክፍል እንዲሸጋገሩ መደረጉ ለትምህርት ጥራት መውደቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።

ከዚህ አኳያ የትምህርት ሥርዓቱ ካልተስተካከለ በቀር ለውጥ ሊመጣ አይችልም። መምህራን የዚህ አይነት ውጤት ባለቤት እንዲሆኑ ያደረጋቸውም የትምህርት ሥርዓቱ ነው። የተማሪዎቹ ውጤት ለኢትዮጵያ “እንደ ማንቂያ ደወል” ነው። የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች የውጤት ማሽቆልቆል “ለዓመታት ሲንከባለል የቆየ የበርካታ ችግሮች መገለጫ እና ተሸፍኖ የቆየውን እውነተኛ የትምህርት ሥርዓት ያለበትን ደረጃ ያመለከተ ነው።” ሲሉም የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናግረዋል።

ምንም እንኳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ቢደረገም፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ዛሬም ድረስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል ሲል (ራይዝ ኢትዮጵያ፣ እ.ኤ.አ 2021) ገልጿል። ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ደረጃዋን ከፍ ለማድረግ የጀመረችውን ጥረት አጠናክራ መሥራት አለባት። አዳጊ በሚባሉ ክልሎች እና ገጠራማ ሥፍራዎች ያሉ ሕፃናት ጥራት ያለው ትምህርት እያገኙ አይደለም። ይህም በውጤታቸው ላይ እየተንፀባረቀ ይገኛል። ትምህርት ጥራት ይጎድልባቸዋል በሚባሉ አካባቢዎች ያሉት ዐበይት ችግሮች የመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት እና የተሟላ ትምህርት ቤት አለመኖር ናቸው ሲል የጣሰው ወደልሃና (ዶ/ር)፣ ፕሮፌሰር ሪካርዶ ሳባቴስ እና ዳዊት ጥበቡ (ዶ/ር) የጋራ ጥናት ጠቁሟል።

የትምህርት ጥራት መጓደል ዘርፉ የሚፈልጋቸውን ባለሙያዎች እንዳያገኝ፤ ጠያቂና ችግር ፈቺ፣ ሃሳብ አፍላቂ ምሁር እንዳይኖር ያደርጋል። የፈጠራ ሰዎች ይጠፋሉ። ከተማረ ሃይል የሚጠበቀው የባህሪ ለውጥ አይመጣም። የትምህርት ተቋማት ከስርቆት የፀዱ እንዲሆኑ የሚደረገው ጥረት እንዳይሳካ ያደርጋል። በራሱ የማይተማመን ትውልድ ይፈጠራል። ከራስ ጥረትና ልፋት ይልቅ በሌሎች ትከሻ ወረቀትን ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ ይበራከታል። እውቀትን ከመሸመት ይልቅ ኩረጃን እንደአቋራጭ መንገድ መጠቀም ባህል ይሆናል። ራስ ወዳድነት እየተስፋፋ አገርና ሕዝብን የማገልገል ሃላፊነት ይጓደላል። ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆንና ለዴሞክራሲ ባህል ማበብ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ትውልድ አይኖርም። ይህንንም ሁሉም በዚሁ የትምህርት ጥራት መጓደል ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል።

ከለውጡ በፊት በነበረው አስተዳደር፣ በአንድ የወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ዓመታዊ ሪፖርት መግቢያ አንቀፅ ላይ “የትምህርት ዘመኑ ቁልፍ ተግባር የትምህርት ልማት ሠራዊት ለትምህርት ጥራት እውን መሆን ከፍተኛ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ በመሆኑ በወረዳችን በየደረጃው በሚገኙ አመራሮች፤ ፈፃሚዎች እና ባለድርሻ አካላት በተሻለ ሁኔታ በመደራጀት በላቀ አፈፃፀም እየተከናወነ ይገኛል።” የሚል ሰፍሮ ይገኛል።

በዚህ የክንውን ሪፖርት ላይ ሰፍሮ እንደምናየው ከሆነ “የትምህርት ልማት ሠራዊት” የትምህርት ጥራትን እውን ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል ማለት ሲሆን፤ “በላቀ አፈፃፀም እየተከናወነ ይገኛል” ከሚለውም “የትምህርት ጥራት እየተጠበቀ ይገኛል” የሚል ፌዝ መሳይ ላይ እናገኛለን። ከሆነ እሰየው መሆኑን እየገለፅን ማብራራቱን ለባለሙያዎች ትተን ሌሎቹን እንመልከት።

“የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በተዘረጋው የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት ቀደም ሲል በክልሎች ሲከናወኑ የቆዩት የስምንተኛ እና የስድስተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዎች በፌዴራል ደረጃ እንዲሰጡ” የትምህርት ሚኒስቴር መወሰኑ (በሀዋሳ ከተማ የተካሄደው 31ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ ያስታውሷል) ሌላኛው የመፍትሄ አካል ተደርጎ የተወሰደ ስር ነቀል ርምጃ ነው በሚል በብዙዎች ተመስግኗል።

የተሻለ ብቃት ያላቸው ተወዳዳሪ መምህራን ወደ ትምህርት ሥርዓቱ ሊሳቡ ይገባል። ለመምህራን የሚሰጣቸው ዝቅተኛ ክፍያ አንዱ ለትምህራት ጥራት ተጠያቂ ምክንያት ነው። በመሆኑም፣ ማበረታቻ እና ተመጣጣኝ ክፍያ ከግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል። የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በመንግሥት የሚወሰዱ ርምጃዎች ታች ድረስ መውረድ አለባቸው። የችግሩም፣ የመፍትሔውም ወሳኝ አካል መንግሥት ነው።

መንግሥት ንቅናቄውን ከላይ ቢያስጀምረው በተዋረድ እስከ ቤተሰብ ድረስ ይሄዳል። ሁሉም ወገን ሊሳተፍበት ይገባል። ካልሆነ ግን የአንድ ሰሞን ወሬ ብቻ እንዳይሆን ስጋት አለኝ።” የሚለው የዶ/ር በላይ ሃጎስ፤ “ሀገር ለማዳን በሚከፍለው መስዋዕትነት ልክ ትምህርቱን ከወደቀበት ማንሳት የዚህ ትውልድ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲል ያስቀምጣል። በእኛ በኩል የለውጥ ሥራዎችን ጀምረናል” የሚሉት ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ናቸው።

‹‹የትምህርት ጥራትን የማስጠበቁ ሥራ የተቀናጀ ተግባርን ይጠይቃል። ለዚህም ነው የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ እየተደረገ የሚገኘው። በሙከራ ደረጃ የተጀመረው ከ 1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ዘንድሮ ወደ ሙሉ ትግበራ ተገብቷል። ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለው ሥርዓተ ትምህርት ደግሞ ዘንድሮ በሙከራ ደረጃ የተጀመረ ሲሆን በቀጣዩ የ2016 ዓ.ም ወደ ሙሉ ትግበራ የሚገባ ይሆናል›› የሚለው የትምህርት ሚኒስቴር የሥራ ሃላፊዎች መግለጫ አንድ ብስራት ይዞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2015

Recommended For You