ፍቅር የሕግ ፍጻሜ

ለሰው ልጅ ለአብሮ መኖር መሠረት ከሆኑና አስቀድመው ከተነገሩ እውነቶች ውስጥ አንዱ ፍቅር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለፍቅር እና ስለዋጋው ብዙ መልዕክቶች ተጠቅሰዋል። ከዚህ ውስጥ አንዱ በሮሜ፣ በገላትያ፣ በኤፌሶን፣ እንዲሁም በሌሎች ምዕራፎች ላይ የምናገኘው ‹ፍቅር የሕግ ፍጻሜ› የሚለው ሃይለ ቃል ይጠቀሳል።

ፍቅር ከሌሎች ጋር አብሮ የሚያኖረን ተፈጥሮአዊ ሥርዓት ነው። ይሄ ሥርዓት በጥላቻ ካልሆነ በምንም እንዳይላላ ሆኖ የጸና የሕግ ፍጻሜ ነው። የሰው ልጅ ወደዚች ምድር ሲመጣ ከፍቅር ጋር ነው። ፍቅር ተፈጥሮአዊ የሰው ልጅ ማንነት ነው። ፍቅር የሕህግ ፍጻሜ ከተባለ ድህረ ዓለምም ሆነ ቅድመ ዓለም ሁሉም ኩነት በፍቅር ስርዐት ውስጥ እንደሆኑ መረዳት እንችላለን።

የሰው ልጅ ከጥላቻ ጋር ወይም ደግሞ ከተቃርኖ ጋር አልተፈጠረም። አፈጣጠራችንን ብናየው እንኳን ፈጣሪ በመልካችንና በአርአያችን የሰውን ልጅ እንፍጠር ብሎ እንደተነሳ የምንደርስበት እውነት አለ። እናም ወደዚች ዓለም በሰውነት ስንመጣ በፈጣሪ ሃሳብና ግብር ታንጸን ነው። የፈጣሪ ሃሳብ እና ግብር ደግሞ ፍቅር እና ፍቅር ብቻ ነው።

ሰውነት የፈጣሪ ሃሳብና ግብር የተዋሃዱበት ረቂቅ ማንነት ነው። በፈጣሪ ህልውና ውስጥ ደግሞ ፍቅር እንጂ፣ እውነት እንጂ ጥላቻና ሀሰት የለም። ይሄን እውነት የሚያረጋግጥ ሌላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ መጥቀስ ቢያስፈልግ 1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 6 ቁጥር 18 ማየት እንችላለን። በዚህ መልዕክት ላይ ‹እናተ የእግዚአብሄር ቤተመቅደሶች ናችሁ› ተብለናል።

ከዚህ እውነት በመነሳት የሰው ልጅ የእግዚአብሄር ቤተመቅደስ እንደሆነ እንደርስበታለን። ቤተመቅደስ በባህሪው ቅዱስና ንጹህ ነው። በጎ ሃሳብና በጎ ምግባር የታጨቁበት ማንነት ነው። የሰው ልጅ ከፍቅር ጋር ብቻ ነው ወደዚች ዓለም የመጣው። ጥላቻና መሰል አላስፈላጊ ማንነቶችን የተማረው ሰው ከሆነ በኋላ ነው። ለዚህ የእውቁን የነጻነት ታጋይ የኒልሰን ማንዴላን ‹ፍቅር ተፈጥሮአዊ ነው ጥላቻ ግን በትምህርት የምናገኘው ነው› የሚለውን ዘመን ተሻጋሪ አባባል ማስታወስ ይቻላል።

የሀገራችን ፖለቲካ ጥላቻ ወለድ ፖለቲካ ስለመሆኑ ምስክር ሚያስፈልገው አይደለም ። ባልጸዳና ባልዘመነ ፖለቲካዊ ምህዳር የሥርዓት ሁሉ በኩር የሆነውን ፍቅርና አንድነታችንን ተነጥቀን ካብ ለካብ የሚተያዩ ባላንጣዎች ሆነናል። ብዙ ጥላቻዎችን እና የዘር እሳቤዎችን ወርሰን እርስ በርስ ስንገዳደልና ስንገፋፋ እንደነበር የአደባባይ ሀቅ ነው። አሁንም በዛ እውነት ውስጥ ነን።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሕዝብ ፖለቲካ አይደለም። የአንድ ቡድንና የአንድ ራስወዳድ ማንነት ሃሳብ እና ርዮት እንጂ። ፖለቲካችን ኢትዮጵያዊ መልክና ወዝ ቢኖረው ኖሮ በዚህ ልክ በጥላቻና በእኔነት ባልጎለመስን ነበር።

እንደኢትዮጵያዊነት እሴቶቻችን ብንኖር ጥላቻን የሚገል፣ መለያየትን የሚሽር እልፍ ሥርዓት ነበርን። እንደ ኢትዮጵያዊነት ብንኖር በጋራ የሚያቆም እልፍ የሥርዓትና የወግ እሴቶች ነበሩን። የፖለቲካው ሥርዓት ግን ያን እንድናደርግ እድል እየሰጠን አይደለም።

ጥላቻ ወለድ ፖለቲካ ሀገር አይሰራም። እንዲህ አይነቱ ለማንም የማይበጅ ሥርዓት ጥንተ በኩር ኢትዮጵያዊ ፍቅራችንን ካደበዘዘብን ሰንበትበት ብሏል። ፍቅር ያልነካው እውቀት፣ እውነት ያልገባበት ፖለቲካ በድህነት እና በኋላ ቀርነት ለሚሰቃይ ሕዝብ ንቃት አይሰጥም። ንቃታችን ያለው በፍቅር ውስጥ ነው። ፍቅር ከሚሉት የሥርዓት አውድ ፊት ቆመን በአንድነት ካልበላን፣ በአንድነት ካልተሰባሰብን የባሰ እንጂ የተሻለ አይመጣም።

ኢትዮጵያ የምትድነው ፖለቲካውም ፖለቲከኞቻችንም የሕዝብ ሲሆኑ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ይህን ማድረግ አንችልም። ኢትዮጵያዊነት ቀለሙ ፍቅርና አንድነት፣ ህብረት እና ወንድማማችነት ነው። ኢትዮጵያዊነት መሠረቱ ርህራሄና ቸርነት፣ ይቅርታና በጎነት ነው። ታዲያ ከኢትዮጵያ ጉያ በቅለው ኢትዮጵያን የማይመስሉት እነዚህ መልከ ልውጥ አእምሮና ልቦች ከየት መጡ?

በሕዝብ ፖለቲካ ውስጥ ጥላቻ የለም። እኔነት እና ወገኝተኝነት የተፈጠሩት ፖለቲካው ከኢትዮጵያዊነት ስለሸሸ ነው። ሀገር ያረቁ፣ ትውልድ ያቀኑ ባህሎቻችን የት ድረስ እንደሆኑ እናውቃለን። የእርቅና የአንድነት ሥርዓቶቻችን ፍትህና ዘመናዊነት ባልነገሡበት በዛ ዘመን ኢትዮጵያዊነትን አጽንተው ያራመዱ እንደነበሩ ለማንም የሚታወቅ ነው። በሸንጎና በጎሜ፣ በሽምግልናና በፈርሀ እግዚአብሄር ብዙ ጥላቻዎችን ወደፍቅር የቀየርን ሕዝቦች ነን።

ዛሬ ላይ መልካችን ተቀይሯል። ብዙ ባህልና ሥርዓት፣ ብዙ ወግና ልማድ ያላት ሀገር በጥላቻ ፖለቲካ ስትናጥ ማየት ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ነው። ከዚህ እና ከመሰለው እውነታ በመነሳት የሚስፈልገን የሕዝብ ፖለቲካ ነው። የሕዝብ ፖለቲካ የአንድነት ፖለቲካ ነው። የሕዝብ ፖለቲካ ማንም የማይበድልበት፣ ማንም የማይበደልበት የፍትህና የሚዛናዊነት ፖለቲካ ነው።

ኢትዮጵያን ካንቀላፋችበት ለማንቃት የፍቅር ፖለቲካ ያስፈልገናል። ኢትዮጵያን አጎሳቁለን፣ ሕዝባችንን ተስፋ ቢስ አድርገን የምናተርፈው የብቻ ትርፍ የለም። በኢትዮጵያ ዝቅታ ውስጥ የሁላችንም ዝቅታ አለ። በከፍታዋም ከፍ የምንለው አብረን ነው።

ወላጆች በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ ፍቅር ያለበትን ታላቅ ማንነትን መትከል ፤ የሀገር ፍቅርን፣ ሠብዓዊነትን፣ እውነትንና ሚዛናዊነትን ማውደስ ይጠበቅባቹኋል። መምህር ከሆናችሁ ለተማሪዎቻችሁ እውነትን፣ ይቅርታን ማስተማር ፤ በዚህም ጥሩ አርዐያ በመሆን ነጋቸውን መሥራት ይጠበቅባቹኋል። ከክፉ ሥራ ወጥተን በሚጠቅመንና በምንባረክበት ቅዱስ ሥፍራ ላይ መቆማችን ከዝቅታ የሚታደገን በኩረ ኃይላችን ነው።

አባቶቻችን ኢትዮጵያን አቆንጅተው ለዓለም ያስተዋወቁት በጥላቻና በመከፋፈል ሳይሆን በአንድነት እና በፍቅር ነበር። በቀና ልብ፣ በጽኑ ሀገር ወዳድነት፣ በፍቅር ብርሃን እንዳጠመቁን እኛም ለሌሎች የሚሆን ብዙ ፍቅርን፣ ብዙ ይቅርታን መላበስ ታሪክ የምንቀይርበት መነሻችን ነው።

በፍቅር ካልተነሳን ሩቅ የሚወስድ ሌላ መነሻ አይኖረንም። ውብ ፍጻሜዎች በፍቅር የሚጀምሩ ናቸው። መነሻችንን ፍቅር ካደረግን ከህልማችን ወደብ የማንደርስበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ኢትዮጵያ ንጹህ ናት። ያጠየማት ፖለቲካው ነው። ከፖለቲከኞች ወደሕዝብ የሚነፍሰው የራስወዳድነት ንፋስ ነው ያኮሰሳት።

ወደቀደመ ከፍታችን እንነሳ ዘንድ ከሕዝብ ወደፖለቲከኞች የሚነፍስ ንፋስ ያስፈልገናል። ያልጸዳ ፖለቲካ የጸዳች ሀገር አይፈጥርም። ዛሬ ላይ በሁሉ ነገራችን ቆሸሽን በዘረኝነት ዜማ የቆምንው ባልጸዳ ፖለቲካ ነው።

ፍቅር ዘር የለውም። ፍቅር እኔን ብቻ ይድላኝ አይልም። ፍቅር በደልን አይቆጥርም። ለዛም ነው ፍቅር ከሆነው ሕዝብ የሚነፍስ የፍቅር ንፋስ ያስፈልገናል የምለው። ብዙ ተጉዘን ከኢትዮጵያዊነት ወደ ብሄርተኝነት፣ ከእኛነት ወደእኔነት መጥተናል። ከአንድነት ወደመለያየት፣ ከፍቅር ወደጥላቻ ዝቅ ብለናል። ፍቅር የሌለው እውቀት ወደሞት ካልሆነ ወዴትም የሚወስድ ስፍራ የለውም።

ፍቅር ብቻውን ሥርዓት ነው። ፍቅር ብቻውን ሕገመንግሥት ነው። ፍቅር ካለ ይቅር ለመባባል እና ተነጋግሮ ለመግባባት መንገድ አናጣም። የተግባቦት መንገዶቻችን የተዘጉት ፍቅር ስላጣን ነው። እናም ወደእርቅና ወደቀደመው ፍቅራችን በሚወስደን ብሄራዊ ምክክር ላይ ያጣናት ኢትዮጵያ ትመለሳለች ብለን እናምናለን።

ብሄራዊ ምክክር ብዙ ስም ቢኖረውም አንዱና ዋነኛው መገለጫው ግን የይቅርታ መድረክ የሚለው ነው። ፍቅር የሚመለሰው፣ አብሮነት የሚመጣው እንዲህ ባለው መነጋገርን ባስቀደመ ትውውቅ ነው። ይቅርታ ፍቅርን የሚያውቁ ሁሉ የሚናገሩት የነፍሶች ቋንቋ ነው። የይቅርታ ልብ ሁሌ ያማረ፣ ሁሌ የፈካ የፀሀይ መውጫ አናት ነው…በብርሃን የተሞላ። ይቅርታ ሳንሞት ህያው ሆነን በትውልድ ልብ ውስጥ የምንኖርበት ጥበባችን ነው።

ይቅርታ ክፉዎችን ማሸነፊያ፣ እብሪተኞችን መርቻ በትረ ሙሴአችን ነው። በዓለም ላይ በበጎ ሥራቸው በትውልድ ልብ ውስጥ ደምቀው የተጻፉ ነፍሶች ይቅርታ አድራጊዎች ነበሩ። በአሁኑ ሰዓትም በዓለም ላይ ደስተኛና ስኬታማ ሆነው የምናያቸው ሰዎች ከሁሉ ነገራቸው በላይ ፍቅርና ይቅርታን ያስቀደሙ ናቸው። ፖለቲካችን ከፍቅር ከጥሎ ይቅርታ የዋጀው የሥርዓት አውድ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ዋጋ እያስከፈሉን ያሉ ነገሮች ሁሉ ባልተፈጠሩ ነበር።

እግዚአብሄርን የሚፈራ ልብ ሁል ጊዜ ይቅርታ ያደርጋል። የፈረሱ ትዳሮች፣ የፈረሱ ጓደኝነቶች፣ ጸጸት የዋጣቸው ትናንቶች ባጠቃላይ ያልተሳኩ ሰዋዊ ትልሞች ሁሉ ይቅርታ የሌለባቸው ናቸው። እንደሀገር ወደህልማችን እንድንጠጋ፣ ወደአንድነት እና ወደ መግባባት እንድንሸጋገር ይቅር የሚል ልብ ያሻናል።

አንዳንድ ነገሮች ቀላል ናቸው.. እውቀት እና ጥበብ ሳይጠይቁ በፍቅርና በይቅርታ ብቻ የሚረቱ ሆነው እናገኛቸዋለን። ህልም በይቅርታ እንደሚፈጠር ፤ ጥላቻ በፍቅር እንደሚሞት ስንቶቻችን ተረድናል? ምንም ይሁኑ የኢትዮጵያ ችግሮች በፍቅር የሚፈርሱ ናቸው። ምንም ይሁን ፖለቲካችን በይቅርታና እውቀት ባለበት ፍቅር የሚነጻ ነው።

ብዙ የሥነአእምሮ እና የሥነልቦና ጠበብቶች ፍቅርን የምንም ነገር መነሻ ያደርጉታል። ሕይወት ከልብ እና ከአእምሮ ነው የሚጀምረው። ልብና አእምሯችን ውስጥ ባለው ሃሳብ፣ ባለው ሥብዕና፣ ባለው ማንነት፣ ባለው አረዳድ፣ ባለው እውቀት እና ማስተዋል ሕይወት ይወለዳል። ፖለቲካ ልብና አእምሯችን ውስጥ ያለው የሃሳብ እና የአረዳድ ነጸብራቅ ነው ። ፖለቲካችን እንዲጸዳ አእምሯችን ከዘረኝነት እና ከራስወዳድነት ሊጸዳ ያስፈልጋል።

የአንድ ሰው የእውቀቱ ጥግ፣ የሥልጣኔው አጽናፍ የሚለካው በልቡ ውስጥ ባለው የፍቅርና የመልካምነት ብዛት ነው። ዓለም በሚሳሳቱና ልክ ባልሆኑ ሰዎች እንደተሞላች መረዳት ፍቅር እና ይቅርታን እንድናውቅ እድል ይሰጠናል። መልካምን የማታውቅ ነፍስ ከአምላክ ዘንድ አይደለችም። ‹በእግዚአብሄር መንፈስ የሚመላለሱ እነሱ የእግዚአብሄር ልጆች ናቸው› የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ አውቃለው። የእግዚአብሄር መንፈስ ምንድነው? ምን አይነት ነው? ብለን ብንጠይቅ የፍቅርና የይቅርታ መንፈስ እንደሆነ እንደርስበታለን። የእግዚአብሄር መንፈስ ከፍቅር ጀምሮ በፍቅር የሚያበቃ ነው።

እዚህ ምድር ላይ በመልካም ሥራችን ለሌሎች ክብርና ሞገስ ከመሆን ውጪ መጠሪያ ስም የለንም። በምድር ቆይታችን በሥራችን ከመደሰትና ሌሎችን ከማስደሰት ባለፈ ታላቅ ጀብድ የለንም። ሥራችን ነው የሚቀረው። ስማችን፣.. ተግባራችን ነው በትውልድ ልብ ውስጥ የሚቀረው። እናም በእውነት እና በታማኝነት በፍቅርም ኢትዮጵያን ማገልገል ስንኖር መከበሪያችን ስንሞት ደግሞ መጠሪያችን ይሆናል።

ሁሉም ነገር በጊዜ የተገደበ ነው። ይሄ ዓለም ትናንት የሌሎች ነበር ዛሬ ደግሞ የእኛ ሆኗል። ነገ የሌሎች ከመሆኑ በፊት በጊዜአችን ላይ ስማችንን የሚያስጠራ፣ ታሪካችንን የሚመልስ የፍቅር ሥርዓት እንገንባ። ኖረን ለመሞት ሳይሆን ሞተን ለመኖር የሚያበቃ በጎ ሥራን እንትከል። በትውልድ ውስጥ ዳግም መፈጠር ለጥቂቶች የተቻለ ለብዙሃኑ ግን ምኞት የሆነ ነገር ነው። በሌሎች መልካምነት እንደተፈጠርን ሁሉ በእኛ መልካምነትም የሚፈጠሩ ስላሉ ልቦቻችንን ለበጎ ሥራ እናሰናዳ።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2015

Recommended For You